Featured articles, Politics, ፖለቲካ

ፖለቲካዊ ሙስና በኢትዮጵያ-(ተስፋዬ መኮንን)

ፋሽስት ኢጣሊያ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተፈጠረው የኀይል አሰላላፍ ለውጥና ምክንያት በእንግሊዞች እርዳታና በኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ ድል ከሆነች በኋላ፣ ቀዳማቂ ኀይል ሥላሴ በሱዳን በኩል አድርገው ኦሜድላ (ጎጃም) እንደደረሱ አንድ አዋጅ አውጥተው ነበር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ኦሜድላ ላይ ሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባስነገሩት አዋጅ በአምስት ዓመቱ የጠላት ወረራ ዘመናት በባንዳነት ተሰልፈው አገራቸውን ለሸጡት ምንደኛ አካላት ምሕረት የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን በጠላት የተሰጣቸውን ማዕረግ የሚያፀና ነበር፡፡ ያ አዋጅ ከጠላት ጋር በመተባበራችሁ ምክንያት የሚደርስባችሁ የተለየ ነገር የለም፤ የፋሽስት ኢጣሊያ መንግሥት የሰጣችሁ መዓርግም እንዳለ ይቀጥላል የሚል ዓይነት ይዘት ያለው፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ አዋጅ ነበር፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ በዚህ አዋጅ ምክንያት የባንዳዎችን፣ ሹምባሾችንና ስደተኞችን ታማኝነት ለማግኘት ችለዋል፡፡ በዱር በገደል እየተንከራተቱ አገራቸውን ከወራሪ ለመከላከል መስዋዕትነት የከፈሉ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ግን ወደ ዳር እንዲገፉ ሆኗል፡፡ ይልቁንም እንደ ብላታ ታከለ ወልደ ሐዋሪያት እና እንደ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ያሉት የኢትዮጵያ ቀንዲሎች በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ተገድለዋል፤ ብዙዎችም እስርና በግዞት እንዲኖሩ ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የፖለቲካዊ ሙስና እርሾ የተተከለው በዚህ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ ለአገርና ለሕዝብ የቆሙትን አርበኞች ገሸሽ አድርገው ታማኝ አገልጋዮቻቸውን (የሚበዙት ስደተኞችና ባንዶች ናቸው) በየመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቱ ሾሙ፤ የእሳቸውን አመራር የሚቃወሙትን ወይም ከእሳቸው የተለየ አመለካከት ያላቸውን አገለሉ፡፡ በዚህ የንጉሠ ነገሥቱ ውሳኔ ምክንያት አገራችንም ሆነች የእሳቸው አስተዳደር ውሎ አድሮ የገጠማቸውን ሁላችንም ስለምናውቀው እዚህ ላይ መዘርዘሩ አስፈላጊ አይደለም፡፡

የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴን መንግሥት ያስወገደው ደርግ ከተራ ወታደር እስከ ሺሕ አለቆች የተሰበሰቡበት፣ እዚህ ግባ የማይባል ሀብትና ንብረት ያልነበረው ስብስብ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ደርግ በአንድ በኩል ወደ ሠራዊቱ እንመለሳለን የሚሉ አካላት ስለነበሩበት፣ በሥልጣን ላይ ለመቀጠል አዝማሚያ በሚሳዩት ወገኖች አካባቢም ቢሆን እምብዛም ስለቢሮክራሲው ዕውቀቱም ፍላጎቱም ባለመኖሩ ከመንግሥት ቢሮክራሲው ርቀው ነበር የቆዩት፡፡ ይህ ሁኔታ የተቀየረው ኢሕአፓ በመለመላቸው አንደ ሲሳይ ሀብቴና ሞገስ ወልደ ሚካኤል አማካይነት ሲሆን፣ “ቋሚ ተጠሪ” የሚል መደብ ተፈጥሮ የድርጅት ሰው በየመሥሪያ ቤቱ እንዲገባ ተደረገ፡፡ በዚህ ምክንያት የድርጅት እና የመንግሥት ሥራ ተቀላቀለ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ሚኒስተሮችን፣ የመምሪያና የቢሮ ኀላፊዎችን የሚቆጣጠረውና የሚያዘው ቋሚ ተጠሪው ሆነ፡፡ ድርጅታዊ ኀላፊነት ከመንግሥታዊ ኀላፊነት የበለጠ የሚያስከብርና ተጽዕኖ ፈጣሪ እየሆነ ሄደ፡፡ ለድርጅት ብቻ ሳይሆን ለድርጅቱ መሪ ማጎብደድ፣ ለድርጅቱና ለድርጅቱ መሪ ሲባል አገር የሚጎዳ እርምጃም ቢሆን መውሰድ የተለመደ አሠራር ሆነ፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖም ታዲያ የደርግ አባላት ሥልጣናቸውን ለማጠናከርና ለማስጠበቅ ሁሉንም የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም፣ በግላቸው ይሄ ነው የሚባል ሀብትና ንብረት ለማፍራት ያደረጉት ሙከራ እምብዛም ነው፡፡

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ሥልጣን ከያዘ በኋላ የታየው ሁሉ ከቀዳማዊ ኀይል ሥላሴም ከደርግም በእጅጉ የተለየ ነበር፤ ነውም፡፡ ሕወሓት መንግሥታዊ ሥልጣኑን እንደተቆጣጠረ በቀጥታ ቢሮክራሲውን መመንጠርና ለእሱ ታማኝ በሆኑ አካላት መሙላት ነው የጀመረው፡፡ በዚህ እርምጃ በርካታ በሥራ ትጋታቸውና በሥነ-ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ኢትዮጵያዊያን ሕወሓትን ሊቃወሙ ይችላሉ በሚል ምክንያት በገፍ እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ሜዳ ላይ በትኖ በራሱ ሽምቅ ተዋጊ ኀይል የቀየረው ሕወሓት፣ ቢሮክራሲውንም በራሱ አባላትና ደጋፊዎች ሞላው፡፡ በዚህ ምክንያት በመንግሥታዊ ቢሮክራሲው ውስጥ ፓርቲና መንግሥት ተቀላቀለ፡፡ ሹመት፣ ሽልማት፣ የደረጃ ዕድገት፣ የትምህርት ዕድልና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቀሞችን የሚያገኙት የሕወሓት/ኢሕአዴግ አባላት ሆኑ፡፡ ትልቁ መሥፈርት ዕውቀትና ክህሎት ሳይሆን የድርጅት አባልነት እንዲሆን ተደረገ፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ተንኮታኮተ፡፡

የሕወሓት መሪዎች መንግሥታዊ ሥልጣንን ለሀብት ማጋበሻነት በማዋላቸው ሁለት ዐሥርት በማይሞሉ ዓመታት ምንም ዓይነት ሀብት ያልነበራቸው ሽምቅ ታጋዮች ሚሊየነር ቢለየነር ሆኑ፡፡ ሥልጣንን መከታ በማድረግ የአገርና የወገን አንጡራ ሀብት ዘርፎ ፎቅ መገንባት፣ የተንደላቀቀ ኑሮ መኖር የሚያሳፍር መሆኑ ቀረ፡፡ የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው በዚህ መረን የለቀቀና ዓይን ያወጣ የአገር ሀብት ምዝበራ በመጠመዳቸው ምክንያት ነው ሳያስቡት የሀብታቸው ምንጭ የሆነው ሥልጣን ከእጃቸው የወጣው፡፡ የውድቀታቸው ዋና ምክንያት አልጠግብ ባይነታቸው ነው፡፡

የሚያሳዝነው አሁንም ሌላ በላተኛ ራሱን በከፍተኛ ፍጥነት እያደራጀ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በረራ ጋዜጣ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርሁት፣ አሁን የሚታየው የሕወሓት የበላይነት ነግሦበት የቆየውን ሥርዓት በኦሕዴድ/ኦዴፓ የበላይነት ለመቀየር የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡ በኦሮሞ ብሔርተኞች በኩል የሚታየው ኀላፊነት የጎደለው ስግብግነት ብዙ ኢትዮጵያዊያንን እያሳነ ይገኛል፡፡ ሕወሓት በ27 ዓመታት ውስጥ ያልደፈረውን እነሱ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እያሳዩን ነው፡፡ በዚህች አጭር ጊዜ የፍትሕ ሥርዓቱን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርንና ሌሎችን መሥሪያ ቤቶች ከላይ እስከታች ተቆጣጥረዋል፡፡

በዚህች የፖለቲካ ሥልጣን የሀብት ምንጭ በሆነባት አገር እኛም የድርሻችን ይድረሰን በሚል መንፈስ ከፍተኛ ስግብግብነት እየታዘብን እንገኛለን፡፡ ይህ እጅግ አደገኛ አካሄድ ውሎ አድሮ ለአገር ጠንቅ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት በቃል ደረጃ ኢትዮጵያዊነትን እየሰበከ በተግባር የኦሮሞ የበላይነት የነገሠበት ሥርዓት ሲገነባ ዝም ብሎ እያየ ወይም ተባባሪ እየሆነ ነው፡፡ ለማንም አይጠቅምም፤ በጊዜ ካልታረመ አገርና ሕዝብን ወደ መቀመቅ የሚከት የጥፋት ጎዳና ነው፡፡

መፍትሔው ምንድነው?

መፍትሔው ትግል ነው፡፡ መፍትሔው ሁሉም ዜጋ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል ብሎ በቁርጠኝነት መነሳትና እያንዳንዷን ኢፍትሐዊ እርምጃ መታገል ብቻ ነው፡፡ ግለሰቦች በሚያማልሉ ቃላት ስለኢትዮጵያዊነት ስለዘመሩ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስጠብቃሉ ማለት አለመሆኑን ማወቅና በሥራቸው መመዘን ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ ግን ለዚህ ሁሉ አዙሪት ዘላቂ መፍትሔው ሁሉም መክሮ ዘክሮ ያፀደቀው ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማበጀት ነው፡፡ ጠንካራና ገለልተኛ ፍርድ ቤት እስከሌለ ድረስ ኢፍትሐዊነቱ ይቀጥላል፡፡ በመንግሥት አካላት መካከል ጠንካራ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱም ፓርላማውም አሁን እንደሚታየው በሥራ አስፈፃሚው ቁጥጥር ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው፡፡ የሥርዓቱን ኢፍትሐዊ ተግባራት እየተከታተለ የሚያጋልጥ ጠንካራ ሚዲያ ከሌለ ሁሉም የግለሰብ አምባገነኖች አጨብጫቢ ሆኖ እንዲቀጥል ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡

ስለዚህ ከሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች የሚጠበቀው ዜግነታችንን ከምር ይዘን፣ ዜጋ መሆናችን ዋጋ እንዳለው አውቀን ከዜጎች የሚጠበቀውን ኀላፊነት መወጣት ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው በአንዳችን ላይ የሚደርስ ኢሰብአዊና ኢፍትሐዊ ድርጊት በሌላችን ላይ እንደደረሰ አውቀን በጋራ መታገል፣ የነገድ የበላይነት የነገሠበት ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩል ዐይን የሚያይ ሥርዓት እንዲገነባ መታገል ነው፡፡ አምባገነኖች ስሜት ኮርኳሪ በሆኑ ቃላት እየሸነገሉ አገርና ሕዝብን ወደ ገደል ሲወሰዱ በዘምታ ልናያቸው አይገባም፡፡ ተግባራቸውን፣ ለሁሉም የሚሆን ሥርዓት ለማቆም የሚያደርጉትን እርምጃ ማየትና መከታተል ይገባናል፡፡ ማመን የሚገባን ከግለሰብና ድርጅት ይልቅ በሐሳብንና በጠንካራ ሐሳብ ላይ የቆመ ሥርዓትን እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ሁላችንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትኖረን መታገል ይገባናል፡፡ ለመብታችን ዘብ እንቁም!

(Visited 84 times, 1 visits today)
March 15, 2019

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo