Politics, World News, ሐተታ, ፖለቲካ

ፈርሶም የማይረጋጋው ደቡብ ክልል-በዳዊት ዋበላ

ፈር መያዣ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ስብሰባ የደቡብ ክልል የዞን እና የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው ተዘግቧል፡፡ በስብሰባው በሕዝበ ውሳኔ ክልል መሆኑ የተረጋገጠው የሲዳማ ዞንን ጨምሮ የደቡብ ክልልን በአራት የሚከፍለው አዲስ አወቃቀር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፍ ከስምምነት ላይ መደረሱም ተመልክቷል፡፡ “የሰላም አምባሳደሮች” በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሰው ስብስብ ያዘጋጀው አዲስ የክልል አደረጃጀት ጥናት ለስብሰባው ታዳሚዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በጥናቱ መሠረት የደቡብ ክልል በሕዝበ ውሳኔ ክልል መሆኑን ያረጋገጠውን የሲዳማ ክልልን ጨምሮ በአራት ክልሎች እንዲከፈል ያደርገዋል፡፡

ጥናቱ ከቀረበ በኋላ በተደረገ ውይይት የወላይታ ዞን እና የጌዲኦ ዞኖች ሁኔታ በተለይ መነሳቱ ተገልጿል፡፡ የኹለቱ ዞኖች እጣ-ፈንታ ወደፊት በሚደረጉ ውይይቶች እንደሚወሰን ተመልክቷል፡፡ የወላይታ እና ጌዲኦ ጉዳይ መፍትሔ እንዳገኘ፤ ደቡብ ክልልን መልሶ ለማወቀር የተላለፈው ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ ከስምምነት ላይ መደረሱን የስብሰባው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

‹ኢትዮጵያ ኢንሳይደር› እንደገለጸው ሰማንያ አባላትን የያዘው ይህ ቡድን ያዘጋጀው ምክረ ሐሳብ በግንቦት ወር መጀመሪያ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለውይይት በቀረበ ወቅት በተወሰኑ ብሔሮች ተወካዮች ቅሬታ በማስነሳቱ በክልሉ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተጨማሪ ውይይቶች እንዲደረጉ ምክንያት ሆኖ ነበር።

ከውይይቶቹ የተገኙ ግብዓቶች ተካተውበታል የተባለው እና በዛሬው ስብሰባ የቀረበው ምክረ ሐሳብ የደቡብ ክልልን ለሦስት የሚከፍል እንደሆነ የስብሰባው ተሳታፊ ለ‹ኢትዮጵያ ኢንሳይደር› ማስረዳታቸው ተገልጿል። በዛሬው ስብሰባ ወደፊት የሚቋቋሙት ክልሎች ስያሜም ሆነ ሌሎች ዝርዝር ነገሮች አለመነሳታቸውን የሚናገሩት የስብሰባው ተሳታፊ ሆኖም የትኛው ዞን እና ልዩ ወረዳ፣ በየትኛው ክልል እንደተካተተ ይፋ መደረጉን ገልጸዋል።

በተለምዶ “ምዕራብ ዞን” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያሉ ሸካ፣ ቤንች፣ ማጂ፣ ከፋ እና ዳውሮ ዞኖች በአንድ ክልል ስር እንዲሆኑ በምክረ ሐሳቡ ላይ ቀርቧል ተብሏል። “ማዕከላዊ ዞን” በመባል በሚታወቀው አካባቢ ያሉት የጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሀድያ፣ ከምባታ፣ ሀላባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ በጋራ ሆነው ኹለተኛ ክልል እንዲመሠርቱ በምክረ ሐሳቡ መቀመጡ ታውቋል።

አዲስ ከሚቋቋሙት ክልሎች “ሰፋ ያለ ቦታ የሚያካልል ነው” የተባለለት “ኦሞቲክ” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው አካባቢ ነው። በዚህ አካባቢ የሚገኙት የጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮ እና ኮንሶ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንዲጠቃለሉ በዛሬው ስብሰባ ከውሳኔ ላይ መደረሱ ተነግሯል።

የወላይታ ዞን በዚህኛው ክልል ስር እንዲካተት በሐሳብ ደረጃ ቢቀርብም በስብሰባው ተሳታፊዎች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን በስፍራው የነበሩት የ‹ኢትዮጵያ ኢንሳይደር› ምንጭ ተናግረዋል። የስብሰባው ተሳታፊዎች ወላይታ ዞን ለብቻው ተነጥሎ የራሱን ክልል እንዲመሠረት ሐሳብ ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል።

እንደ ‹ኢትዮጵያ ኢንሳይደር› ዘገባ ከሆነ የወላይታ ዞን ላይ ጠንከር ያለ ቅሬታ በተለይ ሲያቀርቡ የነበሩት ከዞኑ ጋር የአስተዳደር ወሰን የሚጋሩት የጋሞ እና ዳውሮ ተወካዮች ነበሩ ተብሏል። ጉዳዩን በአንክሮ የተከታተሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “በጉዳዩ ላይ ከየብሔሩ ሽማግሌዎች ጋር ለመምከር አቅጣጫ አስቀምጠዋል” ብለዋል የስብሰባው ተሳታፊ። በዚህ ምክንያትም የወላይታ ጉዳይ ወደፊት ውሳኔ ይሰጥበታል በሚል በይደር መቆየቱን እኚሁ የስብሰባው ተሳታፊ ገልጸዋል።

በዛሬው ስብሰባ እንደ ወላይታ ሁሉ እልባት ያላገኘው ጉዳይ የጌዲኦ ዞን ጉዳይ እንደነበር ተገልጿል፡፡ የ“ሰላም አምባሳደሮች” የተሰኘው ቡድን ያዘጋጀው የቀደመ ምክረ ሐሳብ ላይ የጌዲኦ ዞን፣ ከቡርጂ እና አማሮ ወረዳዎች ጋር በመሆን አንድ ክልል እንዲመሠርት ሐሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ከአካባቢው ሕዝቦች ተቃውሞ በመነሳቱ አማራጩ ውድቅ መደረጉን ምንጮች አስረድተዋል። በዛሬው ስብሰባ ላይ ጌዲኦ በልዩ ዞን እንዲደራጅ ከስምምነት ላይ ቢደረስም “በየትኛው ክልል ይካተት?” የሚለው ግን ወደፊት ይወሰናል መባሉንም አክለዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበረው የደቡብ ክልል አመራሮች ስብሰባ የተጠናቀቀው የደቡብ ክልልን አዲስ አወቃቀር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተላለፍ ውሳኔ በማሳለፍ እንደነበር በስፍራው የነበሩ ተሳታፊ ለ‹ኢትዮጵያ ኢንሳይደር› መናገራቸው ተዘግቧል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ከሕገ መንግሥቱ አንጻር ለሚመረምረው ቋሚ ኮሚቴው ይመራዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የማይረጋጋው ክልል

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከ56 ያላነሱ ብሔረሰቦችን ያቀፈ ክልል ሲሆን፣ ከብሔረሰባዊ ስብጥሩ አንጻር ሲታይ ሰላማዊና ለሌሎች ክልሎችም አብነት ሊሆን የሚችል የመቻቻል ተምሳሌት የሆነ የሆነ ክልል ነበር፡፡ የሐዋሳ ከተማ ዕድገትና የሕዝብ ስብጥር ለሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች ትልቅ ተስፋና የአብሮነት ስሜት የሚፈጥር ነበር፡፡ ሐዋሳ ለደቡብ ክልል ኅብረትና አብሮነት ሁሉም ነገሩ ናት ማለት ይቻላል፡፡ የደቡብ ሕዝቦች አብሮነት የተቋጠረባት ከተማ ናት፤ ሐዋሳ፡፡ ለዚህ ነው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሲነሳ ሁልጊዜም “የደቡብ ኅብረታችን ይበተናል” ሐሳብ ይነሳ የነበረው፡፡ እውነትም የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ አይሎ መጥቶ የሲዳማ ብሔር በሕዝበ ውሳኔ በክልል ለመደራጀት መወሰኑን ተከትሎ የደቡብ ክልል ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡

ሲዳማ ክልል መሆኑን በሕዝበ ውሳኔ ከማረጋገጡ በፊትም ቢሆን ሌሎች ብሔረሰቦች፣ በተለይም ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ከፋ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ሐድያ፣ ከምባታ ተንባሮ ወዘተ… ክልል ለመሆን በየብሔረሰብ ምክር ቤቱ አስወስነው ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም አጥኝው ቡድን እያንዳንዱ ብሔረሰብ ክልል ይሁን ቢባል ለአስተዳደር የማይመች በመሆኑ በአራት ክልሎች ስር ቢዋቀር የተሻለ መሆኑን ገልጿል፡፡ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ይሰፍናል፤ ሕዝቡም በአንድ ልብ ወደ ልማት ይመለሳል በሚል የተዘጋጀው አዲሱ አወቃቀር ግን ሰላምና መረጋጋት የመፍጠር አቅም ሊኖረው መቻሉ አጠራጣሪ ነው፡፡ የሥነ ሰብዕ (አንትሮፖሎጂ) ምሁሩ ፕሮፌሰር ተሮንቮል እንደሚሉት አዲሱ አወቃቀር በአዲሶቹ ክልሎች ውስጥ በሚካተቱ ብሔረሰቦች ዝንድ ይበልጥ ውድድርና ሽኩቻ የሚፈጥር፤ አሁንም አዳዲስ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል እንጅ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋትን አያመጣም፡፡ “በሚያሳዝን ሁኔታ የደቡብ ክልለ የሰላምና መረጋጋት ተምሳሌትነት አክትሟል፡፡ ክልሉ በኢትዮጵያ ደረጃ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል እና ልዩ እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ ክልል ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ተፍረክርኮ አገሪቱ ችግር ውስጥ ስትገባ ከክልሉ ውጭ በሆኑ አካላት ተሳትፎ ጭምር ክልሉ እንዲፈርስ ተደርጓል” ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡

ደቡብ ክልል ኅብረ ብሔራዊ ክልል ነበር፡፡ አሁን የሚዋቀሩት ክልሎችም ከዚህ ኅብረ ብሔራዊነት አያመልጡም፡፡ እያንዳንዱ ክልል በውስጡ በርካታ ብሔረሰቦችን ያቀፈ ክልል ነው የሚሆነው፡፡ “ቀደም ሲል በደቡብ ክልል ደረጃ የብሔረሰቦች ቁጥር መብዛት በየብሔረሰቦቹ ልኂቃን መሀከል አላስፈላጊ ሽኩቻ እንዳይኖር አስተዋጽዖ ነበረው፡፡ ክልሉም ትልቅ ነው፡፡ በክልል ቢሮዎች ደረጃ በተለያየ ደረጃ ለመሳተፍና ለመቀጠርም ዕድል ነበር፡፡ አሁን የሚመሠረቱት ክልሎች በአንጻሩ በቆዳ ስፋት ትናንሽ ከመሆናቸውም በላይ የሚኖራቸው ሀብትም በዚያው መጠን ውስን ነው፡፡ ስለሆነም ያለችውን አነስተኛ ነገር ለመከፋፈል በየብሔረሰቡ ልኂቃን ዘንድ ከፍ ያለ ሽሚያ ሊኖር እንደሚችል መገመት አይከብድም” የሚሉት ደግሞ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዳዊት ስዩም ናቸው፡፡

“የደቡብ ክልል የመቻቻልና የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተምሳሌትነት ከሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ በኋላ ፀሐዩ ጠልቃበታለች፡፡ በዚህ ሒደት ትልቅ ዕድል ያጡት የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦችና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ የደቡብ ሕዝቦች የአብሮነት ፕሮጀክት ደጋፍ ተደርጎለት ቢጎለብት ኖሮ ኢትዮጵያ በእጅጉ ትጠቀም ነበር፡፡ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ከድሮ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም እነ ጃዋር መሐመድ ለራሳቸው ፖለቲካዊ ጥቅም ሲሉ ሁኔታውን አግለብልበው በዚህ ደረጃ በማድረሳቸው የክልሉ ሕዝብም ኢትዮጵያም ትልቅ ዕድል አምልጧቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚፈጠሩት ክልሎች የሰላም ደሴት ይሆናሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጉራጌና ስልጤ፣ ጋሞ፣ ጎፋና ወላይታ፣ ሐድያና ከምባታ ጠምባሮ … እንዴት ነው በቁራሽ ክልል ላይ ተግባብተው የሚኖሩት? የትኛው ከተማ ነው የየክልሉ ዋና ከተማ የሚሆነው? በምን መስፈርት? እነዚህ ብሔረሰቦች (በተለይም ልኂቃኑ) አልስማማ ስላሉ እኮ ነው ሁሉም በብሔረሰብ ዞንና በወረዳ ደረጃ የተደራጀው፡፡” ይላሉ አቶ ዳዊት፡፡

(Visited 60 times, 1 visits today)
June 15, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo