Economy, ኢኮኖሚ

ገና በኮቪድ-19 ዋዜማ ላይ የእምቧይ ካብ የመሰለው የድሃ አበዳሪና የሀብታም ተበዳሪ ግንኙነት የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር (፩) -በጌታቸው አስፋው

በኢሕአዴግ የተበላሸው የጥሬ ገንዘብና የቁጠባ አስተዳደር ያለፈውን መነካካት፣ መውቀስ፣ ማውገዝ፣ ወዘተ… ለዛሬና ለነገ ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም ሆኖም ግን መፍትሔ ከችግር ዳሰሳ ስለሚነሳ ለዛሬና ለነገ መፍትሔ ለመፈለግ የትናንትን ችግር መፈተሽ ይጠቅማል፡፡

ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ከፉውን የወረርሽኝ ጊዜ ያላቸውን ከወገኖቻቸው ጋር ተካፍለው ለማሳለፍ የሚያደርጉት ጥረትም ያለፈውን የሚያስረሳ ነው፡፡ ያለፈውን ጉዳይ ለትምህርታችን እና የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ብቻ ከተጠቀምንበት ለውጤት እንበቃለን፡፡ ስለሆነም በኢሕአዴግ ዘመን ስለነበረው የድሃ አበዳሪና የሀብታም ተበዳሪ ግንኙነት የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት ጉድለቶች ማውሳት የወደፊቱን ለማስተካከል እንደ መነሻ አድርጎ ማየት ይቻላል፡፡

ከዚህ ጭብጥ በመነሳት፣ በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ችግሮችን እንዲሁም በሚቀጥሉት ክፍል ኹለት እና ሦስት ጽሑፎች መፍትሔዎችን እንመለከታለን፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ከ1983 ጀምሮ በንግድ ባንክ ቁጠባ የሀብት ማዛወር ስልቱ የድሃ አበዳሪና የሀብታም ተበዳሪ የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥርዓት ፈጥሯል፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ኩራዝ እያበሩ፣ በሳር ክዳን ጣሪያ ቤት ውስጥ እየኖሩ፣ ጥፈው እየለበሱ፣ በባዶ እግር እየሄዱ፣ መደብ ላይ እየተኙ፣ በእንጨትና በፍግ እያበሰሉ፣ መሬት ተቀምጠው እየተመገቡ፣ ውሃ በቆርቆሮ ጣሳ እየጠጡ፣ የገጠር ድሆች ቆጥበው በኪሳራ የቁጠባ ወለድ ለሀብታም ያበድራሉ፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት ለቤት ሥራ ተብሎ በውዴታ ግዴታ እንዲቆጥቡ የተደረጉት የከተማ ጫማ አሳማሪዎች፣ ሳልቫጅ ነጋዴዎች፣ የቤት ውስጥ አገልጋዮች፣ የቀን ሙያተኞች በአክሳሪ የወለድ መጣኝ በንግድ ባንኮች አስተላላፊነት ለተበዳሪ ሀብታም አበድረዋል፡፡

ጠላ ጠምቀው ካቲካላ ቀቅለው፣ ሽንኩርት ቸርችረው፣ ኩበት ለቅመው፣ እንጀራ ጋግረው፣ የማገዶ እንጨት ከዱር ለቅመው፣ ውሃ ከምንጭ ቀድተው፣ ድሆች ቆጥበው ለንግድ ባንኮች አበድረዋል፤ ሀብታሞች ከንግድ ባንኮች ተበድረውታል፡፡

የልማት ባንክ፣ የኢንቬስትመንት ባንክ ወዘተ… የሚባሉት ለረጅም ጊዜ ብድር የሚሰጡ የገንዘብ ተቋማት ጥሪታቸውን (Fund) የሚያገኙት ከአባል ግለሰቦችና ድርጅቶች ሲሆን፣ ንግድ ባንኮች ግን ስማቸው እንደሚያመለክተው ከሕዝብ የቁጠባ ተቀማጭ ተቀብለው ለአጭር ጊዜ ንግድ ሥራ እንዲያበድሩ በአዋጅ ሥልጣን ተሰጥቷቸው የተቋቋሙ የተቀማጭ ጥሬ ገንዘብ ባንኮች (Deposit Money Banks) ናቸው፡፡ የንግድ ባንኮችን ማስታወቂያዎች ልብ ብለን ብናያቸውም እንዲቆጥብ የሚገፋፉት ድሃውን ነው፡፡ የከተማም ሆነ የገጠር ሰው ባንክን እንዲለምድ ይቀሰቅሱታል፤ የሚልሱት የሚቀምሱት አጥተው ውጭ ባሉ ዘመዶቻቸው የሚረዱ ቤተሰቦች እንዲቆጥቡ ያበረታቷቸዋል፡፡

በውጭ ምንዛሪ ቆጥቡ፣ በአገር ውስጥ ምንዛሪ ቆጥቡ የማባበያ መንገዱ ብዙ ነው፣ ባጃጅ እንሸልማለን፣ ቴሌቪዥን እንሸልማለን፣ የሚሉ ማስታወቂያዎች ያስነግራሉ፤ ሀብታም በባጃጅና በቴሌቪዥን ይታለላል ተብሎ አይገመትም፡፡

በመሠረቱ የካፒታሊዝም ሥርዓተ ኢኮኖሚ የተመሠረተው በካፒታሊስታዊ የማምረት ዘዴ (Capitalistic method of Production) ነው ማለት ካፒታሊስት ወይም በቋንቋችን ከበርቴ እንበለው ከፍጆታ አስተርፎ ቆጥቦ ማምረቻ መሣሪያን ወይም ካፒታልን ፈጣሪ ነው ለማለት ነበር እንጂ ካጣ ከነጣ ድሃ ተበድሮ ይከብርበታል ማለት አልነበረም፡፡ ሀብታሙ ከድሃው ይበደራል መንግሥትም ከደሃው ይበደራል፤ ድሃው ማበደር እንጂ መበደር አያውቅም፡፡ እንደ በለጸጉት አገሮች የፍጆታ ብድር (Consumer Credit)፣ የቤት ሥራ ብድር (Mortgage Loan)፣ ወዘተ… የሚባሉት ለሸማቾች የሚቀርቡ የድሃው የብድር ዓይነቶች የሉም፡፡ ደርግ ለቤት ሠሪዎች በአራት በመቶ ወለድ ይሰጥ የነበረውንም ኢሕአዴግ አጠፋው፡፡

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋምንና ደደቢትን የመሳሰሉ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለገበሬው የቁጠባ ተቀማጭ አምስት በመቶ ወለድ ብቻ እየከፈሉ የራሱን ተቀማጭ ለማዳበሪያ መግዣ በዐሥራ ስምንት በመቶ ወለድ እያበደሩ መክፈል ሲያቅተውም በሬዎቹን ይሸጡበት ነበር፡፡ የዛሬ ሃያ ዓመት ለጡረታ ብለው መንግሥት ዘንድ ያስቀመጡት አንድ ብር ሸቀጦችን በመግዛት አቅሙ ተዳክሞ ዛሬ ዐሥር ሳንቲም እንኳ አያወጣም፡፡ ብሩን መንግሥት ዘንድ ሲቆጥቡ እርስዎ ለመንግሥት አበዳሪና መንግሥት ከእርስዎ ተበዳሪ ነበሩ፤ ሸቀጦችን በመግዛት አቅሙ አንድ ብር የነበረን የእርስዎን ቁጠባ ከሃያ ዓመት በኋላ ጡረታ ወጥተው መንግሥት የተበደሮትን መልሶ የሚከፍሎት ሸቀጥን በመግዛት አቅሙ አንድ ብር ሳይሆን ዐሥር ሳንቲም ብቻ ነው መንግሥት አተረፈ፤ እርስዎ ከሰሩ፡፡

ሰዎች ጥሬ ገንዘብ የሚቆጥቡት ለኹለት ጉዳይ ነው፡፡ ለችግር ጊዜ (Security) ይሆነኛል በማለት አለበለዚያም ወለድ አግኝቶ ለማትረፍ (Speculation) ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቆጣቢው ኪሳራ እንጂ ትርፍ ስለማያገኝ የቁጠባው ምክንያት በድሆች ለችግር ጊዜ ተብሎ ነው፡፡

በ2010 ዓ.ም. ከሦስቱ የንግድ ባንኮች ቁጠባዎች በቼክ ለመገበያየት በነጋዴው ከሚቆጠበው ኹለት መቶ ዐሥራ ሰባት ቢልዮን ብር ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ (Demand Deposit) እና ተርፎት ወለድ ለማግኘት በሀብታም ከሚቆጠበው ዘጠና አንድ ቢልዮን ብር የጊዜ ተቀማጭ (Time Deposit) ከእጥፍ በላይ ለችግር ጊዜ ተብሎ በድሃው የተቆጠበው አራት መቶ ሰማንያ ሰባት ቢልዮን ብር የቁጠባ ተቀማጭ (Saving Deposit) ይበልጣል፡፡

ቆጥበው የያዙት ብርና ሳንቲሞች ምንዛሪዎ ከእጅዎ ከወጣ ኹለት ነገር ሊያጡ ይችላሉ፡፡ አንዱ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብዎን የወሰደው ሰው አገር ለቆ ሊሄድ ወይም በአገር ውስጥም ሆኖ ሊከዳዎት ወይም ቸግሮት አጥፍቶ ላይከፍሎት ይችላል ባንክም ቢሆን ከስሮ የሚመልስልዎት ሊያጣና ሊያጉላላዎት ይችላል፡፡ የመቅለጥና የመጉላላት አደጋ አለው፡፡ ሌላው ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብዎ በእጅዎ ወይም በኪስዎ ካልሆነ የሚገዛ ነገር ቢያጋጥምዎ ላይገዙ ነው፡፡ ስለዚህም ሰዎች ምንዛሪ ጥሬ ገንዘባቸው ከእጃቸው ወጥቶ በሌላ ሰው እጅ ከገባ ለሚያጡት ከላይ የተገለጹ ሁኔታዎች ስጋት መካሻ ምንዛሪያቸው አድጎ መመለስ አለበት፡፡

ይህን ያደገ መጠን ነው ኢኮኖሚስቶች ለሠራተኛው ደሞዝ ለመሬት ኪራይ ለድርጅት ትርፍ እንደሚሉት የካፒታል አገልግሎት ዋጋ ወይም ወለድ ብለው የሚጠሩት፡፡ የቁጠባ ተቀማጭም ሆነ የባንክ ብድር መጣኝ ቢቻል መንግሥት በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲው ተጽዕኖ እያደረገ በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር በገበያ ኀይላት ቢወሰን ይመረጣል፡፡ የወለድ መጣኝ ቁሳዊ ሀብትንም በፍጆታና በመዋዕለንዋይ አማራጮች በመደልደል የኢኮኖሚውን ዕድገት ይወስናል፡፡

መረጃዎች ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን በነበሩት 29 ዓመታት ውስጥ በከፍተኛው 35 በመቶ እና በዝቅተኛው 15 በመቶ መካከል ይዋዥቅ የነበረውን የዋጋ ንረት አማካይ 20 በመቶ አድርገን ብንወስድ እና በዚሁ ጊዜ በ3 በመቶ ዝቅተኛውና በ7 በመቶ ከፍተኛው መካከል የነበረውን የቁጠባ ተቀማጭ ወለድ መጣኝ አማካይ 5 አድርገን ብንወስድ በ25 ዓመት ውስጥ በዓመት በአማካይ 15 በመቶ ቆጣቢው በኪሳራ ወለድ በተበዳሪው ተበዝብዟል፡፡

የ2010ን 487 ቢልዮን የቁጠባ ተቀማጭ የባንክ ሒሳብ በ15 በመቶው ብናበዛ በአንድ ዓመት ውስጥ 73 ቢልዮን ብር ገደማ ድሃ ቆጣቢው በተበዳሪው ሀብታም ተመዝብሯል፡፡ የሃያ ዘጠኝ ዓመቱን በተመሳሳይ መልክ በናሰላ ስንት ዓባዮችን እንገድብ ነበር፤ ስንት የጎጆ ፋብሪካዎችን እንከፍት ነበር፤ ከድህነት የሚያወጡን ብዙ ሥራዎች እንሠራበት ነበር! ተበዳሪ ሀብታም ከአበዳሪው ድሃ በኪሳራ ወለድ ተበድሮ ፎቅ ሠራበት፡፡ የአንድ መለስተኛ ፋብሪካ ወጪን በመቶ ሚልዮን ብር ብንገምት በ2010 ኪሳራ ወለድ ቆጣቢዎች ባጡት ጥሬ ገንዘብ በ73 ቢልዮን ብር ሰባት መቶ ሠላሳ ፋብሪካዎች መሥራት ይችሉ ነበር፡፡ የሃያ ዘጠኝ ዓመታት ኪሳራ ስንት ሺሕ ፋብሪካ እንደሚሠራም ማስላት ይቻላል፡፡

ከንግድ ባንክ ተበድረው ሕንፃ የገነቡትም እንዴት እንደከበሩ በተመሳሳይ ሁኔታ መመልከት እንችላለን፡፡ በአማካይ በሃያ በመቶ የዋጋ ንረት መጣኝ ዐሥራ አምስት በመቶ ወለድ እየከፈለ ከባንክ ገንዘብ የተበደረ መዋዕለንዋይ አፍሳሽ ለንግድ ባንኩ ዐሥራ አምስት በመቶ ወለድ የከፈለ ይምሰል እንጂ፣ በዓመቱ መጨረሻ ለባንኩ የመለሰው ገንዘብ ሸቀጦችን በመግዛት አቅሙ በሃያ በመቶ ስለሚቀንስ፣ ሒሳቡ ተቀናንስ ተበዳሪው በመበደሩ ብቻ አምስት በመቶ ተከፈለው እንጂ አልከፈለም፡፡ ተበዳሪው በኹለት መንገድ ያተርፋል ከዋጋ ንረት በታች በሆነ የወለድ መጣኝ በመበደሩም ያተርፋል፤ የሠራው ሕንፃ በዋጋ ንረቱ ምክንያት ዋጋው ስለሚጨምርም ያተርፋል፡፡

የኦሮሚያን ድሃ ገበሬ፣ የአማራን ድሃ ገበሬ፣ የትግሬን ድሃ ገበሬ፣ የሱማሌን ድሃ ገበሬ፣ የደቡቡን ድሃ ገበሬ፣ የጋምቤላውን ድሃ ገበሬ ወዘተ… አደህይተው በድህነቱ ምክንያት አንዱ ድሃ ሌላውን ድሃ እንዲጠላ መሬቱን እንዲሻማ “ከእኔ የዘር-ማንዘር ርስት ና ውጣልኝ” እንዲባባል ያደረጉት የድሃ ድሃ ያደረጉት በአክሳሪ የተቀማጭ ወለድ መጣኝ ከድሃው ተበዳሪው የኢሕአዴግ መንግሥት እና በአክሳሪ የተቀማጭ ወለድ መጣኝ ከድሃው ተበዳሪዎች አጋሮቹ የከተማ ሀብታሞች ናቸው፡፡

መንግሥትና ሀብታም ድሃውን በዋጋ ንረት የገቢውን የመግዛት አቅም አዳክመው ከሚበዘብዙት በተጨማሪ በተቀማጭ ወለድ መጣኝ በአበዳሪ-ተበዳሪ ግንኙነትም ይበዘብዙታል፡፡ ፖለቲከኞቻችን ችግሮቻችንን ዘራችን ውስጥ ይፈልጉታል እንጂ ኢኮኖሚው ውስጥ ቢፈልጉት ለሁሉም የሚበጅ ቀላል መፍትሔ ያገኙልን ነበር፡፡

የቀድሞው ብሔራዊ ባንክ ገዥ ቃለ ምልልስ ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለኢኮኖሚው ዕድገት የፋይናንሱ አስተዋጽዖ ምንድን ነው? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ የሰጡት መልስ፡- “ቀዳሚ ተግባር አድርገን የወሰድነው የአገር ውስጥ ቁጠባን ማስፋት ነው፡፡ ይህንንም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆነ ብለን ከፍለነዋል፡፡ የግሉን ቁጠባ ለማሳደግ በገጠሩ ገበሬው ቢቆጠብም እንኳ የሚያውለው በሬ ለመግዛት ነው፡፡ ስለዚህም የባንክ ተደራሽነትን አስፍተን ቁጠባው በባንክ እንዲሆን ለማድረግ ተንቀሳቀስን፡፡ የባንክ ቅርንጫፎችን ከ25 እስከ 30 በመቶ ለማሳደግ ተንቀሳቀስን፡፡ ከጠበቅነው በላይም ተሳክቶልናል” የሚል ነበር፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥው እንዳሉት የገጠሩ ቁጠባ ከግብርናው አምራች ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ከተማው ሕንፃ ግንባታና አገልግሎት ኢኮኖሚ የተዛወረበት አንዱ የመንግሥት ሀብትን ከድሃው ወደ ሀብታሙ ማስተላለፊያ ስልት ነው፡፡ ይህ ቁጠባ አደገ ሳይሆን ቁጠባ ከገጠር ወደ ከተማ ተሻገረ ነው፡፡ ገበሬው በበሬ ቁሳዊ ካፒታል መልክ ይቆጥብ የነበረው ወደ ጥሬ ገንዘብ ቁጠባ ተቀየረ፤ የገበሬው ቁጠባ ግብርናን ከማስፋፋት ይልቅ ወደ ሕንፃ ግንባታና ወደ አገልግሎት ኢኮኖሚ ተዛወረ፤ የግብርናው ካፒታል ወደ ከተማ በመሸሹ ገበሬው በበሬና በጎተራ እህል ቋሚ ካፒታል በመቆጠብ ፋንታ በጥሬ ገንዘብ መልክ ቆጥቦ ለከተሜው በማበደሩ በ2008 ዐሥራ ኹለት ሚልዮን ሕዝብ ተራበ፡፡ በከተሞች ሕንፃ ግንባታና የአገልግሎት ዘርፍ የተጨናነቀው ካፒታል ከገጠር ሙልጭ ብሎ በመሸሹ ወጣቶች ከግብርና ውጪ ሥራ በማጣታቸው ወደ ከተማ ፈለሱ፡፡

ደርግ እንኳ በገጠር የተቆጠበችውን እዚያው በገጠሩ ለአምራቾችና ለአገልግሎት ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንድትውል በማድረግ ኢንቨስትመንት ገጠሩ ላይ እንዲበረታታ አድርጎ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን የገጠሬው ቁጠባ የውጭ አገር ሰዎች ወደሚገቡበትና ወደሚያርፉበት ወደ ቦሌ እና ወደ ሼራተን ጠጋ እንዲል ተደረገ፡፡ ይህ ደግሞ የገጠሩ ሕዝብ በመንግሥት ፖሊሲ ደስተኛ አለመሆኑ በ2008 እና በ2009 የኅብረተሰብ አመጹ የተቀሰቀሰው በገጠሩ ሕዝብና በገጠሩ ወጣቶች መሆን ማስረጃነት በግልጽ ታይቷል፡፡

ኹለተኛው የሪፖርተር ለቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ጥያቄ ‹በቁጠባው ላይ ምን ለውጥ መጣ?› የሚል ሲሆን፣ የብሔራዊ ባንኩ ገዥ መልስ፡- “በ2003 ዓ.ም. 680 አካባቢ ብቻ የነበረው የባንክ ቅርንጫፎች ቁጥር በዕቅዱ ዘመን መጨረሻ ላይ 2800 ደርሷል፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ 3900 ደርሷል፡፡ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም 1600 ቅርንጫፎች ደርሰዋል፡፡ ያቀድነውን ተግባራዊ በማድረጋችን የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ጨመረ፡፡ በ2003 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከነበረው ወደ ስድስት እጥፍ አደገ በቁጠባው መጨመር የተሰጠው የብድር መጠን ወደ አምስት እጥፍ ጨመረ፡፡” የሚል ነበር፡፡

ሦስተኛው የሪፖርተር ጋዜጠኛ ጥያቄ ከእያንዳንዱ ከሚሰጥ ብድር 27 በመቶ ለቦንድ ግዢ ማዋሉን የተመለከተ ሲሆን፣ የባንኩ ገዥ፡- “አዎ ኢንቨስትምንት እንዲስፋፋና ድህነት እንዲወገድ ሥራ እንዲፈጠርና ገቢም እንዲጨምር ለማድረግ ንግድ ባንኮች የብሔራዊ ባንክ ቦንድ እንዲገዙ አደረግን ብሔራዊ ባንኩም ለልማት ባንክ በመስጠት ባንኩ ለማኑፋክቸሪንግና ለመሳሰሉት እንዲያበድር በማድረጋችን በዚህ ረገድ የነበረውን ማነቆ ፈትተናል” ነበር ያሉት፡፡ አክለውም፡-

“እንዲያውም የአገራችን ባንኮች የትርፍ ምጣኔ ከዓለም አንደኛ ነው 100 ብር አክስዮን ያለው ሰው 40 ብር ትርፍ ያገኛል፡፡ ይህ በዓለም የሌለ ነው፡፡ ከፍተኛ ተብሎ የሚጠቀስ የትርፍ ድርሻ ነው፡፡ ገና በሚያድጉ አገሮች እንኳ ትልቁ የትርፍ ክፍፍል ድርሻ 20 በመቶ ነው ወደ ትልልቆቹ አገሮች ብትሄድ የትርፍ ድርሻው አምስትና ስድስት በመቶ ነው” ብለው ነበር፡፡

ገዥው እንዳሉት ባንኮች ለቆጣቢዎች አምስት በመቶ ወለድ ከፍለው በ17 በመቶ ወለድ ያበድሩታል፡፡ በዚህ መሀል ወደ ዐሥራ አንድ ብር ያህሉ ትርፍ ነው፡፡ ወጪያቸው ሦስት በመቶ አይሞላም፡፡ ለቁጠባ በሚከፍሉትና ለብድር በሚጠይቁት ወለድ መካከል ያለውን ሕዳግ ብሔራዊ ባንክ መቆጣጠር አልፈለገም፡፡ 27 በመቶው ተቀንሶ በቀሪው ተቀማጭ የሚያገኙት ትርፍ በጣም ብዙ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የግል ባንኮች በአብዛኛው ብድር የሚሰጡት ለአገልግሎት በመሆኑም ካሉ በኋላም ስለ ባንኮቹ አቅም ሲያብራሩ፡-

“የአገሪቱ ባንኮች ከሌላው ዓለም በተለየ ከፍተኛ አትራፊ የመሆናቸውን ያህል የአገልግሎት ተደራሽነታቸው ሲታይ ግን፣ ኋላቀር እንደሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አጠቃላይ የካፒታል አቅማቸው ከ50 ቢሊዮን ብር አይበልጥም፡፡ ይህም በኬንያ ወይም በደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ አንድ ባንክ ያነሰ አቅም እንዳላቸው አመላካች መሆኑ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ በተለይ 18ቱም ባንኮች የተናጠል አቅማቸው ሲታይ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ የኢንዱስትሪው ዕድገት ከሚመዘንባቸው ነጥቦች አንዱ በሆነው በተደራሽነት ሲሰፈሩም፣ በአፍሪካ ያላቸው ደረጃ ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ብድር የመስጠት አቅማቸው፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው፣ ቁጠባ የማሰባሰብ ብቃታቸውና ሌሎች በዘርፉ የሚጠቀሱ አገልግሎቶች ሲነሱ፣ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ከሰሐራ በታች ካሉ አገሮች አኳያ የሚገኙበት አቋም ይህ ነው አይባልም፡፡”

የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዥውን ቃለ ምልልስ በአንድ ዓረፍተ ነገር አጠቃሎ መናገር ቢያስፈልግ ያሉት እኛ መንግሥት እና አጋሮቻችን ባለሀብቶች ባንኮቻችንን ተጠቅመን በአበዳሪ-ተበዳሪ ግንኙነት ድሃውን ሕዝብ ለመበዝበዝ የሚቻለንን ሁሉ አድርገናል ነው፡፡

ሰሞነኛ ጉዳይ ሰሞኑን ከመንግሥት መግለጫዎች እንደምንሰማው ደግሞ ተበዳሪዎች በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም መስክ የተሰማሩ የባንክ ብድራቸውን መክፈል ስለማይችሉ የብድር መክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘምላቸው የሚጠይቅ ነው፡፡ አንዳንድ ባለሀብቶችም (ኀይለ ገብረ ሥላሴ በናሁ ቴሌቪዥን) በሚዲያ ቀርበው ሲናገሩ “ባለሀብት ከምትሉን ባለዕዳ ብትሉን ይሻላል” እያሉ ነው፡፡

በድኅረ-ኮሮና ተበዳሪዎቻቸው ያልከፈሏቸውና ቆጣቢዎቻቸው ተቀማጮቻቸውን ያወጡባቸው ንግድ ባንኮች ሥራቸው ተቃውሷል፡፡ ይህን ለማርገብም ይመስላል የብሔራዊ ባንክ ገዢው ከኹለትና ሦስት መቶ ሺሕ በላይ በምንዛሪ (Currency) ከባንክ ማውጣት አይቻልም አሉ፡፡ መልዕክቱ በምንዛሪ ብቻ ማውጣት ለሚችሉት ለቁጠባ አስቀማጮች እንጂ በቼክ ክፍያ ሌላ ሦስተኛ ሰው ማውጣት ለሚችልበት የንግድ ተንቀሳቃሽ አስቀማጮች አይደለም፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥው በጥሬ ገንዘብ ከኹለት መቶ ሺሕ በላይ አይቻልም ያሉት የሙያ ቃላት ቴክኒካዊ ስህተት መሆኑን እና የንግድ ባንክ ተቀማጮችም ጥሬ ገንዘብ እንደሆኑ ወደፊት እንመለከታለን፡፡

መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ የቆጣቢዎችን ቁጥር ሃያ አምስት ሚልዮን እንዳደረሰ ይናገራል፡፡ በሁሉም ንግድ ባንኮች እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ2010 ዓ.ም. በቁጠባ ሒሳብ (Saving Account) አራት መቶ ሰማንያ ሰባት ቢልዮን ብር ተቆጥቧል፡፡ ሆኖም የድሃ አበዳሪና የሀብታም ተበዳሪ ግንኙነት በኮቪድ-19 ኹለት ወር እንኳ ሊዘልቅ ባለመቻሉ ብሔራዊ ባንኩ ልዩ ልዩ ጊዜያዊ መመሪያዎችን ማውጣት አስፈልጎታል፡፡ በነ ‹የቶሎ ቶሎ ቤት ዳር ዳሩ ሰንበሌጥ› የወጡት መመሪያዎች ጊዜያዊ መፍትሔዎች ሊሆኑም ወይም ችግር አባባሾች ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ እውነቱ የሚረጋገጠው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዘግየት ብሎ በሚገኙ መረጃዎች ትንታኔ በማድረግ ብቻ ነው ትንታኔው በድኅረ-ኮሮና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቁ ፈተና የሆነው የጥሬ ገንዘብ እና የቁጠባ አስተዳደርን ለማሻሻልም ይጠቅማል፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ስለ ጥሬ ገንዘብ ሽፋን ሥርጭትና ውጤት ላይ ላዩን ብቻ የሚመለከቱ ኢኮኖሚስቶች የንግድ ባንኮችን አቅም ከኬንያ ከናይጄሪያና ከደቡብ አፍሪካ ጋር በማወዳደር በፍጥነት ማደግ እንደሚገባቸው ምክረ ሐሳብ ሲሰነዝሩ ከርመዋል፡፡ የብሔራዊ ባንኩና የንግድ ባንኮች ጥምረት የባንክ ሥርዓቱም (Banking System) ሆነ የባንኮቹ ለየብቻ ሀብትና ዕዳ አሁን ካለው በላይ ቢሆን በዋጋ ንረት ላይ ስለሚከሰተው ቀውስ አላጤኑም፡፡

በሀብትና ዕዳ መዝገብ ሒሳብ (Balance sheet) እኩልነት ሕግ መሠረት ባንኮች ለመንግሥትና ለባለሀብቶች በማበደር ተጨማሪ የብድር ሀብት በፈጠሩ ቁጥር በብሔራዊ ባንክ ወደ ገበያ በሚገባ ተጨማሪ ምንዛሪ ልክ ለሕዝብ የእምነት ባለዕዳ በመሆን እና በአስቀማጮች ወደ ንግድ ባንኮች በሚገባ ቁጠባ ልክ ንግድ ባንኮች ካስቀማጮች የአምነት ባለዕዳ ይሆናሉ፡፡ ይህ ተጨማሪ ዕዳቸው ደግሞ ወደ ገበያ ውስጥ የሚገባ ተጨማሪ ጥሬ ገንዘብ ሆኖ የዋጋ ንረትን እየፈጠረ የብር ሸቀጥንም ሆነ የውጭ ምንዛሪን የመግዛት አቅም የሚያዳክም ይሆናል፡፡

የሰሞኑ የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች በተለያየ መልኩ ሊተረጎሙ ይችላሉ፡፡ ተበዳሪዎች የንግድ ባንኮች ዕዳዎቻቸውን እንዳይመልሱ ማድረግ በአንድ በኩል በሕዝቡ እጅ ገበያ ውስጥ የሚዘዋወረውን ምንዛሪ ስለሚያበዛው የዕለት ተለት በምንዛሪ (በካሽ) የእጅ በእጅ ሽያጭ ገበያዎች ይደራሉ፤ አትክልትን የመሳሰሉ ምግቦችና የመሠረታዊ ቁሳዊ ሸቀጦች ዋጋዎች ይወደዳሉ፡፡ የሰሞኑ የአትክልት ዋጋ መጨመር ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው እንጂ በሳምንታት ውስጥ አቅርቦት ጨምሮ ነው ወይም ቀነሶ ነው ልንል አንችልም፡፡

መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው አቅርቦት ላይ ብቻ ሳይሆን ፍላጎት ላይም ይሥራ ብዬ ለዓመታት ስወተውት የነበረው ለዚህ ነበር፡፡ ፍላጎትን ማስተዳደር ማለት ወደ ሸማቾች የሚገባው የጥሬ ገንዘብ ገቢ ላይ ተጽዕኖ በማድረግ ለፍጆታና ለቁጠባ በሚደለድሉት ገቢያቸው ላይ የፖሊሲ ተጽዕኖ በማሳደር ይግራ ማለት ነው፡፡

የሕዝባችን ገቢ እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሆቴሎቻችንን የአልጋና የመስተንግዶ አገልግሎት ይሸምቱ የነበሩት የውጭ ዜጎች ብቻ በመሆናቸው በወረርሽኙ ምክንያት ገበያ አጥተው ለመዘጋት መብቃታቸው እኛ ለመኖር ሳይሆን ሌሎችን ለማኖር የተፈጠርን ነው የመሰለብን፡፡

በሌላ በኩል ወደ ንግድ ባንኮች የሚመለስ ብድር ከቀነሰ ባንኮች አርብተው (Money Multiplier) ለሌላ ተበዳሪ የሚያበድሩት ምንዛሪ ስለሚያጥራቸው በጊዜ ብዛት ንግድ ባንኮች የሚፈጥሩት የብድር ጥሬ ገንዘብ (Credit Money) ስለሚቀንስ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትም አብሮ ይቀንሳል፡፡ በዚያው ልክም ኢኮኖሚው ይኮማተርና ሥራ አጥነት ይፈጠራል፡፡ ይህን በመፍራት ይመስላል ብሔራዊ ባንኩ አስቀማጮች በምንዛሪ መልክ ከባንክ የሚያወጡትን መጠን ለመገደብ የተገደደው፡፡

በብሔራዊ ባንኩ ስለ ካፒታል ገበያ መቋቋምም በድንገት መነገሩንም ባለፈው ሳምንት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ከሲራራ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ካሉት ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡ የካፒታል ገበያ (Capital Market) እና ተጓዳኙ የጥሬ ገንዘብ ገበያ (Money Market) በአንድነት ስማቸው የገንዘብ ገበያ (Financial Market) ከመቋቋማቸው በፊት የትኞቹ ድርጅቶች ወደገበያው ገብተው ይመዘገባሉ (Being Listed)፣ የድርጅት ዋጋ ተማኝ (Enterprise vahator) አለ ወይ? ገበያውን የሚያሳልጡና በባለሙያ የተደራጁ ተቋማት አሉ ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ፡፡

ምንም እንኳ የገንዘብ ገበያ መቋቋም ደጋፊና ተሟጋች ብሆንም ጥቂት ባለሀብቶች ከአንድ ኪስ ወደ ሌላ ኪስ ሊያዟዙሩ ካልሆነ በቀር አሁን ባለው የጥሬ ገንዘብ እና የገንዘብ አስተዳደር አቋም፣ የተቆጣጣሪ አካላት ስለ ገንዘብ ገበያ በቂ ዕውቀት አለመኖር የካፒታል ገበያው ለሕዝብና ለኢኮኖሚው በሚጠቅም መልኩ ይደራጃል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ ምናልባት ብሔራዊ ባንኩ በጭንቀት ከሃያ ዓመት በፊት በውጭ ኮንሰልታንቶች አስጠንቶ ያስቀመጠውን እንደ መፍትሔ ይሆናል ብሎ ያመነበት የቀውስ ወቅት ስትራቴጂ ነው፡፡ የካፒታል ገበያ የቀውስ ማስታገሻ የጭንቅ ጊዜ ባይሆንም ብሔራዊ ባንኩ ግን የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ሊያደርገው ነው የፈለገው፡፡

በድኅረ-ኮሮናስ ብሔራዊ ባንኩ እና መንግሥት የድሃ አበዳሪና የሀብታም ተበዳሪ ግንኙነቱን ብሎም የጥሬ ገንዘብ እና የገንዘብ አስተዳደሩን ችግር ለመፍታት ምን ዓይነት የወለድ መጣኝም ሆነ የብድር ግኝት የጥሬ ገንዘብና የገንዘብ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ይነድፉ ይሆን? ባለሀብቶች እንደጀመሩት በመረዳዳት ወረርሽኙን እንድናልፈው እየለምኩ፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት በመፍትሔ ሐሳብ እና የባንኮች ማኅበር ከባንክ ውጪ የሚዘዋወር አንድ መቶ ዐሥራ ሦስት ቢሊዮን ብር (ሕገ-ወጥ ይሁን ሕጋዊ የተገለጸ ነገር የለም) በዚሁ ርዕስ ክፍል ኹለትና ሦስት እመለሳለሁ፡

(Visited 34 times, 1 visits today)
June 15, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo