Economy, ኢኮኖሚ

ገና በኮረና ዋዜማ ላይ የእምቧይ ካብ የመሰለው የድሃ አበዳሪና የሀብታም ተበዳሪ ግንኙነት የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር (፪)- ጌታቸው አስፋው

መንደርደሪያ ሐሳብ

በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ኀይሌን የመሳሰሉ ሊቅ የሒሳብ ባለሙያዎች የሒሳብ ቃላትን ከእንግሊዝኛው ወደ አማርኛ በመተርጎም ሕዝብ እንዲለማመደው ብርቱ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡ አሁን ድረስ ሒሳብ በእንግሊዘኛ ካልሆነ በቀር በአማርኛ ሊገባን አልቻለም፡፡ የኢኮኖሚ በተለይም የገንዘብ ኢኮኖሚም እንደዚያው ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ካልሆነ አይገባንም፡፡

ብሔራዊ ባንክ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚያዘጋጀው ዓመታዊ ሪፖርት የምንዛሪዎችን እና የጥሬ ገንዘብን የትርጉም ልዩነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ቢሆንም ወደ አማርኛው ሲተረጎም ግን ባለሙያዎች እንደፈለግን አንዱን በሌላው እያወራረስን ስለምንናገር ፖሊሲዎችን እና መመሪያዎችን መረዳት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ስለሆነም የሙያ ቃላትን መወራረስ ለማስቀረት የእንግሊዘኛ ትርጉማቸውን በሚመጥን የአማርኛ ቃላት ተርጉሜ ለመጠቀም እንደሞክርኩ አንባቢእንዲረዳልኝ እሻለሁ፡፡ ሐሳቡን በትክክል ለመረዳት የፈለገ ሰው የብሔራዊ ባንኩን ዓመታዊ ሪፖርቶች ቢያነብ በቀላሉ ይረዳል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ለገባው ሰው የአህያ ጭነትን ያህል ከሚከብድ ጆንያ ሙሉ ወሬ አንድ ገጽ በመረጃ ላይ የተንተራሰ ትንታኔ ብዙ ይናገራል፡፡

ከኹለተኛው የዓለም ጦርት ታላቁ ዝቅጠት በኋላ የተከሰተ ከፍተኛው ነው ከተባለው የ2007-2008 የገንዘብ ቀውስ (Financial Crisis) ለመውጣትና የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ምዕራባውያን የተለምዶ እና ያልተለመዱ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲዎችን ነድፈው ነበር፡፡ ከተለምዶ ፖሊሲዎች ውስጥ የብሔራዊ ባንኩ ሰነዶችን በመግዛትና በመሸጥ የገበያ ተሳትፎ በማድረግ፣ የንግድ ባንኮች መጠባበቂያ ተቀማጭ መጣኝን በመቀያየር፣ የብሔራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች ብድር የሚሰጥበትን የአጭር ጊዜ ወለድ መጣኝን (Discount Rate) ዝቅ በማድረግ እና ካልተለመዱ ፖሊሲዎች ውስጥ ለከሠሩ ባንኮች የመድን ዋስትና መስጠት እና የብድር ግኝትን ቀላል የማድረግ መንገዶችን ተከትለዋል፡፡

ከኮሮና ዋዜማ አንስቶ እየተንገዳገደ ያለውን የንግድ ባንኮች የብድር አቅርቦት ሂደት ለማገዝ ብሔራዊ ባንኩ ድጋፍ አደረገላቸው ይባላል ይህ ድጋፍ ከላይ ከተዘረዘሩት ፖሊሲዎች የትኛው እንደሆነ አንኳ ተለይቶ አልተነገረም፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለእያንዳንዷ ለሚያሳትማት ብር ለሕዝብ ባለዕዳ ስለሆነ ይህንን ዕዳውን በነጻ አንስቶ ለንግድ ባንኮች ሊሰጣቸው አይችልም፡፡ ድጋፉ ምን እንደሆነ ሕዝብ መስማት ይፈልጋል፡፡ ባንኩ ይናገር፡፡ በኢትዮጵያ በድኅረ-ኮሮና ከመንግሥት የሚጠበቅ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲና የገንዘብ ገበያ ስትራቴጂ ለውጥ ሥራ ቀላል አይሆንም፡፡ ቁጠባን በማሳደግ ረገድ ከድሃ አበዳሪ እና ከሀብታም ተበዳሪ አዙሪት ውስጥ መውጣት አለባት፡፡ ከሁሉም ከሁሉም የሚቀድመው ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎችም ጭምር የተምታታ ትርጉም የሚሰጠውን የባለሙያዎች በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) የገንዘብና የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶችን ለይተው በመረጃ የተደገፈ ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ ሕዝብንም እንዲያስተምሩ ማድረግ ነው፡፡

የጥሬ ገንዘብ እና የገንዘብ ትርጉሞች ሙያዊ ቃላት ትክክለኛ መልዕክት ማስተላለፍ ስላለባቸው ባለሙያዎች ትንታኔ ሲሰጡ ከወትሮ የቃላት አጠቃቀም ወጣ ብለው ስላጠቃቀማቸው መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡ በአማርኛ ቋንቋ የገንዘብ ትርጉም ይህ ጥንቃቄ ተደርጎ ስለማይታወቅ የቃላት አጠቃቀም የኢኮኖሚ ትንታኔዎችን እና የመንግሥት ፖሊሲዎችን ለመረዳት በሚያስቸግር ደረጃ እየተምታቱ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ስለ ቃላቶቹ በሌላ ቋንቋ እና በዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ሥርዓት (International Financial System) አረዳድና አጠቃቀም ስሜቱን ተረድቶ ወደ አማርኛችን ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ አረዳድ ኹለት ዓይነት የገንዘብ ትርጉሞች አሉ፡፡

አንደኛው ጥሬ ገንዘብ ለማሰራጨት በአዋጅ ሥልጣን የተሰጣቸው ብሔራዊ ባንክ እና ከሕዝብ ተቀማጭ ለመሰብሰብ ፈቃድ ያላቸው ንግድ ባንኮች (Deposit Money Banks) ብቻ ናቸው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለሕዝብ የዕምነት ባለዕዳ ሆኖ የብርና የሳንቲም ምንዛሪዎች (Currencies) ጥሬ ገንዘብን ያሰራጫል ምንዛሪዎች በመቶ፣ በሐምሳ፣ በዐሥር፣ በአምስት እና በአንድ ብርም ይዘረዘራሉ (are cashed)፡፡ አንድ ብር ቆጥበው በኪሶ ቢይዙ የሸቀጥ መግዣ መተማመኛዎ ስለሆነች ብሔራዊ ባንኩ ወይም የኢትዮጵያ መንግሥት በአንድ ብሯ ለእርሶ የእምነት ባለዕዳ ነው፡፡ አንድ ዶላር በኪሶ ቢይዙ ደግሞ ከአሜሪካ ሸቀጥ መግዣ መተማመኛዎ ስለሆነች በአንድ ዶላሯ የአሜሪካ መንግሥት ለእርሶ የእምነት ባለዕዳ ነው፡፡ በሒሳብ መዝገብ አያያዝ እኩልነት (Equality of Debit and Credit side of the Balance sheet) ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት እርሶ ጋር ያለችው አንድ ዶላር ባለቤትም ነው፡፡ የአሜሪካ ሀብታምነት የመነጨውም ከዚህ የዓለም ሕዝብ የሚይዘው ዶላር የእምነት ባለዕዳነት ሥርዓት ሲሆን የዓለም ባንክ እና የዓለም የጥሬ ገንዘብ ጥሪት (IMF) የተቋቋሙትም ይህን ሥርዓት ለማስከበርና ለመጠበቅ ነው፡፡

እንግሊዛዊው የተቋማቱ ዋና መሥራች የነበረው ሎርድ ኬንስ የፈለገው አንድ የዓለም መገበያያ ምንዛሪ እንዲኖር ነበር እንጂ የአገሮች ምንዛሪዎች የአንዱ እንደ ብርና ሽልንግ ወዘተ… የመሳሰሉት የድሃ አገር ምንዛሪዎች ስስ ምንዛሪ (Soft Currency) የሌላው እንደ ዶላር ፓውንድና ማርክ የመሳሰሉት የሀብታም አገሮች ጠንካራ ምንዛሪ (Hard Currency) ተባብለው እንዲከፋፈሉ ባይፈልግም የአሜሪካው ተወካይ ተጽዕኖ አድርጎ ነው፡፡ አሁን እኛ ለሌሎች አገሮች ተፈላጊ የሆኑ ብዙ ሸቀጦች የሌለን አገሮች ሕዝቦች በሌሎች አገሮች እንደልብ የማይመነዘሩ ስስ ምንዛሪዎችን ይዘን የውጭ ምንዛሪ እጥረት እያልን መከራችንን የምናየው፡፡

ንግድ ባንኮች ለአስቀማጮች ባለ ዕዳ ሆነው የሚያሰራጩት የተቀማጭ ጥሬ ገንዘብን (Deposit Money) ወይም የብድር ጥሬ ገንዘብን (Credit Money) ነው፡፡ ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ (Demand Deposit) ከሒሳብ ወደ ሒሳብ በማዛወር ወይም በቼክ ለግብይይት ክፍያ ወይም ለዕዳ ማወራረጃ ሲያገለግል በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) ከምንዛሪ ቀጥሎ በጣም ጥሬው የጥሬገንዘብ ዓይነት ነው፡፡ የቁጠባ ተቀማጭ (Saving Deposit) ባለቤቱ ለባንኩ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ በፈለገው ጊዜ የሚያወጣው የተቀማጭ ዓይነት ሲሆን በጥሬነት ደረጃ ከተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ቀጥሎ ያለ ነው፡፡ የጊዜ ተቀማጭ (Time Deposit) በመርህ ደረጃ ለባንኩ በቅድሚያ አስታውቆና የዝግጅት ጊዜ ሰጥቶ ማውጣት የሚቻል ተቀማጭ ሲሆን ከሁሉም የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶች በጥሬነት ደረጃ በኢትዮጵያ የመጨረሻው ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ከኢትዮጵያ የተለየ የጥሬ ገንዘብ ትርጉም እና የጥሬነት ደረጃ ሊኖር ሲችል አገሮች ይህንኑ ለሕዝባቸው ያሳውቃሉ፡፡

ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት በ2010 ዓ.ም. በአገሪቱ ውስጥ የተዘዋወረው ጠቅላላው ጥሬ ገንዘብ መጠን ስምንት መቶ ሰማንያ ሰባት ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም ገበያ ውስጥ በተሰራጨ ምንዛሪ መልክ እና በንግድ ባንኮች ተቀማጭ መልኩ የብሔራዊ ባንኩ እና የንግድ ባንኮች የጋራ ዕዳ ሲሆን ለመንግሥትና ለግል ባለሀብቶች በተሰጠ ብድር መልኩ ደግሞ የብሔራዊ ባንኩ እና የንግድ ባንኮች የጋራ ሀብት ነው፡፡ በሒሳብ መዝገብ (Balance sheet) አያያዝ ሕግ መሠረት ዕዳ እና ሀብት እኩል መሆን ስላለባቸው አንዱ ሲጨምር ሌላውም ይጨምራል፤ አንዱ ሲቀንስም ሌላውም ይቀንሳል፡፡

ብሔራዊ ባንኩ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በሚያዘጋጀው ሪፖርቶች የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶችን ለኹለት በመክፈል ምንዛሪዎችን እና ተንቀሳቃሽ ተቀማጭን ቀዳማይ ደረጃ ጥሬ ገንዘብ (M1)፣ የቁጠባ ተቀማጭን እና የጊዜ ተቀማጭን ካዕላይ ደረጃ ጥሬ ገንዘብ (M2) ወይንም ጥሬ ገንዘብ አከሎች (Quasi Money) ብሎ ይከፋፍላቸዋል፡፡ ሌሎች አገሮች ሳልሳይና ረዕባይ ደረጃ ጥሬ ገንዘቦች ሊኖሩም ይችላሉ፡፡

ከንግድ ባንክ ተቀማጮች መካከል ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ከምንዛሪ ዕኩል ጥሬ ገንዘብ ተደርጎ የሚወሰድበት ምክንያት ለሦስተኛ ወገን ክፈለው በሚል የቼክ ትዕዛዝ አስቀማጩ ወደ ንግድ ባንኩ ሳይሄድም የግብይይት መሣሪያ ሆኖ ስለሚያገለግል ነው፡፡ መጠኑ ገና አነስተኛ ቢሆንም በኤሌክትሮኒክ ግብይይት ከቁጠባ ተቀማጭም በክፈለው ትዕዛዝ ብቻ ግብይይት ስለሚካሄድ ወደፊት የጥሬ ገንዘቦች የጥሬነት ደረጃ ሊቀየር ይችላል፡፡ ይህ ክፍል ምንዛሪ፣ ጥሬ ገንዘብ፣ ገንዘብ እና የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ በሚል ርእስ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ካሳተምኩት መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡

ዓላማዬ ምንም እንኳ ኢኮኖሚስቶች፣ የባንክና የሌሎች ገንዘብ ተቋማት ሠተኞች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለ ገንዘብ ቃላት ሙያዊ አጠቃቀም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ብጽፍም በመገናኛ ብዙሃን አስነግሬ መጽሐፉን በአገር ፍቅር አዳራሽ ባስመረቅሁበት ጊዜ ከሃያ የማይበልጡ ሰዎች ብቻ እንደተገኙ አሳዝኖኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ባሳተምኩት አንድ ሺሕ ቅጂ ብቻ ገድቤ በመገናኛ ብዙሃን አቅርቤ ላነቃቸው እችላለሁ ብዬም ነው፡፡

ለልብወለድ ተረት ተረት የሚንጋጋ ሁሉ ዘወትር ሰለሚያለቅስበት የዋጋ ንረት እና የጥሬ ገንዘባቸው የመግዛት አቅም መዳከምም ሆነ ለባንኮች በተቀማጭ መልክ ላበደሩት ትክክለኛውን የወለድ መጣኝ አለማግኘት የኑሮ ጉዳይ መስማትና ማንበብ አይፈልግም፡፡ እኔ ግን ከሁሉም በላይ በዋጋ ንረት ምክንያት አልቃሽ የሆነው የከተሜው ምሁር እንዳለቀሰ ይቅር ብዬ አልተውኩም፡፡ የማውቀውን እየጻፍኩና እያነቃሁ እገኛለሁ፡፡

በቅርቡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ከኹለትና ሦስት መቶ ሺሕ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት አይቻልም በማለታቸው በዓላማው ላይ በድጋፍም በነቀፌታም ሐሳብ የሰጡ ሰዎች አሉ፡፡ እኔ በሙያዊ ቃላት አጠቃቀም ቴክኒካዊ ጉዳይ ላይ ብቻ ነው የማተኩረው፡፡

ብዙ ሕዝብ በተለምዶ በሚያውቀው የንግግር ቋንቋ አረዳድ ገንዘብ ወይም ጥሬ ገንዘብ ብሎ ቢጠቀም ችግር ባይኖርበትም፣ በሙያ ትንታኔና በፖሊሲ ማስገንዘቢያ አጠቃቀም ደረጃ ግን ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት ትክክለኛውን ሙያዊ ቃል መጠቀም ይገባቸዋል፡፡ ለምሳሌ የገንዘብ ሚኒስቴር ስንል ገንዘብ የሚለውን ቃል የተጠቀምነው “Finance” ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ነው፡፡ “Foreign Currency” የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል በአማርኛ ስንተረጉመው የውጭ ምንዛሪ እንላለን፡፡ ዶላርን፣ ዩሮን፣ ማርክን፣ የውጭ ምንዛሪ ካልን ብርን ለሙያዊ ትንታኔና ለፖሊሲ ማስገንዘቢያ የአገር ውስጥ ምንዛሪ ልንል የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

በእንግሊዘኛው “Money” በመባል የሚታወቀው በአማርኛ ትክክለኛ ትርጉሙ ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ ጥሬ ገንዘብ ሊያሟላቸው የሚገባ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የክፍያ መሣሪያ፣ ሀብት ማከማቻ፣ ዋጋ መተመኛ፣ ሆኖ ማገልገል፣ ቋሚ ዋጋ ያለው፣ ወዲያው ለመጠቀም የሚቻል ወይም ጥሬ መሆን፣ እና የሕግ አስገዳጅነት መኖር፡፡ ከጥሬ ገንዘብ ውስጥ አንደኛው ምንዛሪዎች በእጅ ቢጨበጡም በአጠቃላይ ትርጉሙ ግን ጥሬ ገንዘብ በቁጥር የሚገለጽ እንጂ በእጅ የሚጨበጥ አይደለም፡፡ በንግድ ባንኮች ቁጥሮችን ከሒሳብ ወደ ሒሳብ በማዛወር ክፍያ መፈፀምም ወይም ኤሌክትሮኒክ ክፍያዎችም ዘመናዊ ጥሬ ገንዘቦች ናቸው፡፡

በ2010 ዓ.ም. የንግዱ ማኅበረሰብ በተንቀሳቃሽ ሒሳብ (Demand Deposit-Current Account) ካስቀመጠው ኹለት መቶ ዐሥራ ሰባት ቢሊዮን ብር ላይ በቼክ መክፈል ይችላል፡፡ ትልቁ ተቀማጭ አራት መቶ ሰማንያ ሰባት ቢሊዮን ብር የቁጠባ ተቀማጭ (Saving Deposit) የቤተሰቦች ቁጠባ ላይ ግን በቼክ መክፈል አይቻልም፡፡ በእኔ ግምት ገዥው በሰጡት መግለጫ የብሔራዊ ባንኩ መመሪያ ያነጣጠረው የቁጠባ ተቀማጭ ባለቤቶች የሆኑ ቤተሰቦች ቁጠባቸውን እንዳያወጡ ነው፡፡

በመመሪያው የተንጫጩት ግን ቤተሰቦች ሳይሆኑ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ናቸው፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ሺፈራው እና አትሌት ኀይሌ ገብረ ሥላሴ በናሁ ቴሌቪዥን ቀርበው መመሪያውን ሲተቹ የንግዱ ማኅበረሰብ ከእንግዲህ ጥሪቱን በንግድ ባንክ አያስቀምጥም፣ የቤት ውስጥ ካዝና ገበያውም እየደራ ይገኛል ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ሆኖም የንግዱ ማኅበረሰብ ይጠበቅበት የነበረው የቁጠባ ተቀማጩን ወደ ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ አዙሮ በቼክ መጠቀም ብቻ ነበር፡፡ ፖሊሲን ለመግለጽ ትክክለኛ ቃላት ባለመጠቀም መልዕክትን በትክክል አለማስተላለፍ ይህን ያህል ሕዝቡ እና የንግዱ ማኅበረሰብ በባንክ ላይ ያለው እምነት እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡

በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ በኤሌክተሮኒክ ግብይይት ከቁጠባ ሒሳብ ላይም ክፍያ መፈጸም የሚቻል ቢሆንም መጠኑ ከዐሥር ሺሕ ያልበለጠ ስለሆነ የቁጠባ ተቀማጭ ለክፍያ ቢያገለግልም አሁንም በትርጉም ካዕላይ ደረጃ የጥሬ ገንዘብ ዓይነት እንጂ እንደ ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ ቀዳማይ ደረጃ የጥሬ ገንዘብ ዓይነት አልሆነም፡፡

በቅርቡ የባንክ ለባንክ ጥሬ ገንዘብ ዝውውር ተፈቀደ ቢባልም ባለቤቱ ባንክ ድረስ ሄዶ የሚያንቀሳቅሰው እንጂ በቼክ ለሦስተኛ ወገን ክፈለው የሚባልበት ካልሆነ በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) እንደ ቀዳማይ ደረጃ የጥሬ ገንዘብ ዓይነት አይቆጠርም፡፡ ሦስተኛው የተቀማጭ ዓይነት የጊዜ ተቀማጭ (Time Deposit) በመርህ ደረጃ ባለቤቱ ተቀማጩን ለማውጣት ለንግድ ባንኩ በቅድሚያ የማስታወቂያ ጊዜ የሚሰጥበት የተቀማጭ ዓይነት ሲሆን የሚያስገኘው ወለድ ከሌሎቹ ይበልጣል፡፡

ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በታተመ የሲራራ ጋዜጣ የብር ኖቶች መቀየር በሚል ርዕስ የባንኮች ማኅበር ከፍተኛ አመራሮች ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀሰውን አንድ መቶ ዐሥራ ሦስት ቢሊዮን ብር መንግሥት ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲያስገባውና የብር ኖት እንዲቀየርም መግለጫ አውጥተዋል የሚል ጽሑፍ አንበቤ ነበር፡፡

የባንኮች ማኅበር አመራሮች ከባንክ ውጪ የሚዘዋወር አንድ መቶ ዐሥራ ሦስት ቢሊዮን ብር ግራ አጋቢ ነው፡፡ ተገበያዮች ፎርጅድ ብር መሆኑን እየተነጋገሩ ካልተገበያዩ በቀር ብሩ በገበያ ውስጥ ተዘዋውሮ ወደ ባንክ ሥርዓት የማይገባበት ምንም ዓይነት ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ጥሬ ገንዘብ እንዴት እንደሚዘዋወር በመረጃ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ራሱ የሚያመለክተው የንግድ ባንክ ኀላፊዎች ስለ ምንዛሪ ዝውውር እና አገልግሎት ያላቸው መረጃ ውሱን መሆኑን ነው፡፡

እኔ በተመለከትኩት የብሔራዊ ባንክ የ2010 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት በእርሾ/መነሻ ጥሬ ገንዘብ (Reserve Money) ሰንጠረዥ ላይ በገበያ ውስጥ በዝውውር ላይ ያለ ምንዛሪ 121.8 ቢሊዮን ብር እና በባንኮች ካዝና ውስጥ ያለ ተቀማጭ 78.9 ቢሊዮን ብር በድምሩ 200.7 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም ከጠቅላላው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ስምንት መቶ ሰማንያ ሰባት ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር ንግድ ባንኮች በብድር ጥሬ ገንዘብ (Credit Money) እርሾ ጥሬ ገንዘቡን 4.42 ጊዜ አርብተውታል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ከጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ውስጥ ብሔራዊ ባንኩ ያለው ድርሻ አንድ አምስተኛ ብቻ ሲሆን አራት አምስተኛውን ድርሻ የሚይዙት ንግድ ባንኮች ናቸው፡፡

በወረርሽኙ ምክንያት በየአንዳንዷ የቁጠባ አስቀማጮች ከንግድ ባንኮች የሚያወጡት አንድ ብር ተቀማጭ ምንዛሪ ምክንያት ንግድ ባንኮቹ ከብድር ጥሬ ገንዘብ የሚያገኙት ገቢ በአራት እጥፍ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ጥሬ ገንዘብ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የፍላጎት አስተዳደር (Demand Management) የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመንደፍ እነዚህን የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶች በዓይነት በዓይነታቸው ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በኹለት የሚከፈሉ ሲሆን አንደኛው የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ በአብዛኛው አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ዋጋ ነው በሚል የነጻ ገበያ እምነት መሠረት ውድድርን መፍጠር ነው፡፡

ለዚህም ነው ምዕራባውያን ከ1980ዎቹ ጀምሮ ወደ ጥንቱ የሊበራል ኢኮኖሚ ፍልስፍና ተመልሰው በአቅርቦት ጎን ፖሊሲያቸው ኒዮ-ሊበራሊስት ተብለው የሚጠሩት፡፡ ሌሎቹ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲዎች ቴክኖሎጂን ማሳደግ ለአገሪቱ ጥቅል ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ ለተባሉ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ልዩ ድጋፍ መስጠት ናቸው፡፡

የፍላጎት ጎን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በኹለት የፖሊሲ መሣሪያዎች ይከፋፈላሉ፡፡ አንደኛው መንግሥት በበጀቱ እና በበጀት ጉድለት (Fiscal Deficit) ቀጥታ ተሳትፎ ኢኮኖሚውን ማነቃቃት ሲሆን፣ ኹለተኛው በጥሬ ገንዘብ (Monetary Policy) ፖሊሲ የግል ክፍለ ኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ በማድረግ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢኮኖሚውን ማነቃቃት ነው፡፡

መንግሥት በጥሬ ገንዘብ የፍላጎት አስተዳደር ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃበት መሣሪያዎችም የተለያዩ ናቸው፡፡ ቤተሰቦች ፍጆታን እንዲጨምሩ በገቢ ፖሊሲው ይጠቀማል፣ ድርጅቶች መዋዕለንዋይን እንዲጨምሩ በወለድ መጣኝ ፖሊሲው ይጠቀማል፡፡ የወለድ መጣኝ ፖሊሲው ሲባል ግን መንግሥት የንግድ ባንኮችን የወለድ መጣኝ ይወስናል ማለተ ሳይሆን ብሔራዊ ባንኩ በሚቆጣጠረው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን እና ራሱ ለንግድ ባንኮች በሚያቀርበው ብድር ወለድ መጣኝ (Discount Rate) አማካኝነት ይገራቸዋል ማለት ነው፡፡

በዚህ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ምሁራንን ጨምሮ ከፍተኛ የግልና የመንግሥት የጥሬ ገንዘብና የገንዘብ ባለሥልጣናት ትክክለኛውን ቃል ተጠቅመው መልዕክታቸውን በማያስተላልፉበት ሁኔታ ትክክለኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፍ ይቻላል ማለት ጉምን ለመጨበጥ እንደመሞከር ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት በዩኒቨርሲቲዎች ከሚሰጡት የገንዘብ ኢኮኖሚክስ ሙያ (Financial Economics) አንስቶ እስከ አገልግሎት ሰጪው በአማርኛ ቋንቋ የቃላት አጠቃቀማቸው ላይ ሊያስብብት የሚገባ ነው፡፡

ኹለተኛው የገንዘብ ትርጉም ብሔራዊ ባንኩን እና ንግድ ባንኮችንም ጨምሮ ሌሎችንም በጠቅላላው ሰነዶችን እንደ ገንዘብነት የሚጠቀሙ የገንዘብ ተቋማት ናቸው፡፡ የመንግሥት በጀትን እና የመንግሥት ሰነዶችን የሚያስተዳድረው የገንዘብ ሚኒስቴር (Ministry of Finance)፣ የግል አክስዮኖችን እና የግል ቦንዶችን የሚስተዳድረው የመዋዕለንዋይ ባንኮች (Investment Banks)፣ የመድን ዋስትናን እና አረቦችን የሚያስተዳድረው የመድን ድርጅት (Insurance Companies)፣ የጡረታ ዋስትና ጥሪቶችን (Funds) የሚያስተዳድረው የጡረታ ዋስትና ተቋም (Pension Agency) ከባንክ ውጪ ከሆኑ የገንዘብ ተቋማት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ይህን ከኢትዮጵያና ሌሎች መሰል አገሮች በቀር በመላው ዓለም በስፋት የሚሠራበትና ቆጣቢዎች በንግድ ባንክ አማካኝነት ለሌላ ከማበደር ውጪም ራሳቸው በቀጥታ አክሲዮን እና ቦንዶችን እንዲሁም ሌሎች ሰነዶችን በመግዛት መዋዕለንዋይ የሚያፈሱባቸውን የገንዘብ ተቋማት ዓይነቶች እና የገንዘብ ገበያዎችን በሚቀጥለው ክፍል ሦስት እንመለከታለን፡፡

(Visited 40 times, 1 visits today)
June 24, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo