Articles, Featured articles, Politics, ሐተታ, ፖለቲካ

የዘር ፍጅት፤የኢትዮጵያ ፈተና?

ፈር መያዣ

ዶናልድ ዱቶን የተባለ ጸሐፊ “የዘር ማጥፋት፣ የጭፍጨፋና ቅጥ ያጣ አመጽ ሥነ-ልቦና” (2007) የተሰኘውን መጽሐፉን ሲጀምር፡- “አሁን ሰብአዊውን ገመና ስላወቅሁት፣ የመጽሐፌን መታሰቢያነት ለውሻዬ አድርጌዋለሁ፤” ይላል፡፡ ምናልባትም ያሳለፍነው ክፍለ ዘመን ገድል በታሪክ ድርሳናት ሲዘከር ከሁሉ ጎልቶ የሚታይ ጉዳይ ቢኖር የሰው ልጅ በገዛ ራሱ ላይ የፈጸመው ሰቆቃና ጭካኔ መሆኑ አይቀርም፡፡

ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ባለፉት መቶ ዓመታት ፍጅቶችና መቅሰፍቶች በማይታመን ፍጥነት ጨምረዋል፡፡ አገሮች ከመላው ክፍለ ዓለማት ተቧድነው ኹለት ታላላቅ ጦርነቶችን ተዋግተዋል፡፡ በዚህም ከ100 ሚሊዮን ሰዎች በላይ አልቀዋል፡፡ መንግሥታት በየክፍለ ዓለማቱ፣ በየቀጠናውና በየጎረቤቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጦርነቶች አድርገዋል፣ ብዙ ሚሊዮኖችም አልቀዋል፡፡ ሠላሳ ኹለት አገሮች በተካፈሉበት በአንደኛው የዓለም ጦርነት (1906-10 ዓ.ም.) በሠላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰው አደጋ 14 በመቶ ሲሆን፣ ስድሳ አንድ አገሮችን ባሳተፈው በኹለተኛው የዓለም ጦርነት (1931-37 ዓ.ም.) 67 በመቶ፣ በክፍለ ዘመኑ መገባደጃ ደግሞ ወደ 90 በመቶ አሻቅቧል፡፡ አፍሪካውያን ነጻነታቸውን ለማግኘት የከፈሉት መስዋዕትነት ድኅረ-ነጻነት ከተፋሰሱት ደም ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

በተለይም ከሶሻሊሰቱ ካምፕ መፈራረስ በኋላ በዘውጌና ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦች መካከል የሚደረጉ ቀጥተኛ ግጭቶች በመጠንም፣ በአውዳሚነትና ዘግናኝነትም ከፍተኛ እመርታ አሳይተዋል፡፡ በዚህም ዓለማችን ከርዕዮተ ዓለማዊ ግጭቶች ወደ ማንነት ግጭቶች ስለመሸጋገሯ ብዙ ተጽፏል፤ ተተንትኗል፡፡

ይህ የኋልዮሽ ሽግግር በዘር፣ በደም፣ በቋንቋ ላይ ወደተመሠረተ ደመነፍሳዊ ማኀበር መሆኑ ያስከተለው የጥላቻ ፖለቲካ ደግሞ አጠቃላይ ሰው በሰውነቱ አብሮ በሠላም የመኖርን ብቻ ሳይሆን ጭራሹን የማኅበረሰቦችን በምድር ገጽ የመቆየት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፡፡ ብሔረሰቦች በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ቀዳሚ ስፍራ እየያዙ በመጡ መጠን ደግሞ ብሔረሰቦችን ከምድረ-ገጽ የማጥፋት ሙከራዎች እዚህም እዚያም እየጎሉ መጥተዋል፡፡

በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በተለይም በቦስኒያና በኮሶቮ፣ እንዲሁም በአፍሪካውያኑ በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲና ኮንጎ የማይታመኑ እልቂቶችን አይተናል፤ታዝበናል፡፡ በጎረቤታችን ሱዳን በዳርፉር መቶ ሺሕዎች በገዛ መንግሥታቸው ጋሻ ጃግሬነት ሲጨፈጨፉ ታዝበናል፡፡ ደቡብ ሱዳን እንኳን ነጻ በወጣች ማግስት እንደገና ወደ እርስ በርስ ግጭት በመግባቷ እጅግ ብዙዎች በብሔረሰባዊ ማንነታቸው ምክንያት አልቀዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ድንበር ተሻጋሪ አደጋዎች ማገርሸታቸውን እየታዘብን ነው፡፡ የአዲሲቱ አገር ሦስተኛ ዓመታዊ የልደት ክብረ በዓል ሐምሌ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ባከበረች ማግስት በዴንካና ኑዌር ጎሳዎች መካከል የተነሳው የእርስ በርስ ጦርነት በዓለም ዐቀፍ ሸምጋዮችም የሚፈታ አልሆነም፡፡ እንዲያውም አገሪቱ ከመወለዷ ወደመምከኑ እያዘገመች ይመስላል፡፡

አካባቢያችን የዓለም የጦርነትና የደም መፋሰስ ቀጠና ከመሆኑም በላይ፣ በአገራችንም ቢሆን ላለፉት ሃያ ዓመታት የተጫነብን ብሔረሰባዊ ማንነትን አልፋና ኦሜጋ ያደረገ ፖለቲካ በማኅበረሰቦች መካከል ያሉ ድልድዮችን በመስበር፣ ጥላቻንና መካረርን የማፋፋሚያ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

ማኅበራዊ ግጭቶች ከድንገተኛና ውሱንነት አልፈው ወደ ሰፊና ስልታዊ የዘር ጥቃት ድርጊቶች እየተሸጋገሩ መምጣታቸውን፣ የዘር ጥላቻ በስሙ ሐውልት ማስቀረጹን እየታዘብን ነው፡፡ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች እያሰለሱ የሚከሰቱት ዜጎችን የማፈናቀል ወንጀሎች በምን ዓይነት ሁኔታ ወደ ዘር ማጥፋት ዘመቻዎች እንደሚለወጡ በትክክል መተንበይ አይቻልም፡፡ ቀጥለን በዘር ላይ ተመርኩዘው ከሚፈፀሙ ጥቃቶች ዋነኛው የሆነውን ‹ጄኖሳይድ› ወይም የዘር ማጥፋት ወንጀልን ዓለም ዐቀፋዊ መልክ፣ መንስኤዎቹንና ሒደቱን እንዲሁም የዘር ጥቃቶች እንዴት ደረጃ በደረጃ እንደሚያድጉና ምንስ መፍትሔ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ ባጭሩ እንመለከታለን፡፡

‹ጄኖሳይድ›

በብሔረሰብና በእምነት ላይ ተመርኩዘው ከሚደረጉ ጥቃቶች መካከል እጅግ አሰቃቂ የሆነውና የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ተብሎ የሚታወቀው ‹ጄኖሳይድ› ነው፡፡ ‹ጄኖሳይድ› የሚለውን ቃል የጅምላ ዘር ማጥፋት ተግባርን እንዲገልጽ በ1936 ዓ.ም. የፈጠረውና በዓለም ዐቀፍ ሕግጋት ውስጥ እንዲካተት ከፍተኛ ጥረት ያደረገው ራፋኤል ለምኪን የተባለ አይሁዳዊ ምሁር ነበር፡፡ ወቅቱም ናዚ ጀርመን ለአይሁዳውያን “የማያዳግም መፍትሔ” ያለችውንና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወደር ያልተገኘለትን ጭፍጨፋ የምትፈፅምበት ነበር፡፡ ይህንን ድርጊት ከሰብአዊ ጥቃቶች በልዩ ወንጀልነት ለመፈረጅ በመጀመሪያ የዘር ማጥፋትን ትርጉም መወሰን አስፈላጊ ነበር፡፡

ስለሆነም የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ  በታኅሣሥ 1939 ዓ.ም ያሳለፈው ውሳኔ ቁጥር A/Res/96(I) የ‹ጄኖሳይድ› ጥቃት ክልል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቡድኖችን እንዲያካትት ተስማማ፡፡ ነገር ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ በታኅሣሥ 1941 የፀደቀው A/RES/260A (III) ደንብ ጠባቡን በዘርና በእምነት ማንነት ላይ ያተኮረውን ትርጉም እንዲይዝ በመደረጉ፣ “የዘር ማጥፋት ወንጀልን ስለመከላከልና መቅጣት ስምምነት” (አንቀጽ 2) መሠረት፣ ‹ጄኖሳይድ› የሚባለው አንድን ብሔረሰብ፣ ዘውግ፣ ጎሳ ወይም ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ በጠቅላላው ወይም በከፊል ለማውደም በማሰብ የሚከተሉት አምስት ተግባራት ሲፈፀሙ ነው፡-

(1) የቡድኑን አባላት መግደል፤ (2) በቡድኑ አባላት ላይ ጽኑ አካላዊ ወይም አእምሯዊ ጉዳት ማድረስ፤ (3) በማኅበረሰቡ አኗኗር ላይ በሙሉ ወይም በከፊል አካላዊ ጥፋት ለማስከተል የተሰላ እርምጃ መውሰድ፤ (4) በማኅበረሰቡ ውስጥ ወሊድ እንዳይደረግ ወይም እንዳይኖር የታለመ እርምጃ መውሰድ፤ (5) የማኅበረሰቡን ሕፃናት በግድ ወደሌላ ማኅበረሰብ ማዛወር፡፡

ከዘር ማጥፋት ጋር ተቀራራቢ ትርጓሜ ያለውና ብዙ ጊዜም በተለዋጭነት የሚውለው “ዘር ማጽዳት” (ethnic cleansing) የተባለው ሲሆን፣ ይህ ድርጊት ደግሞ አንድን ማኅበረሰብ ከኖረበት አካባቢ በኀይል ማፈናቀልን ይወክላል፡፡ ምንም እንኳን ስቃይን፣ ስደትንና ግድያን ቢያካትትም የዘር ማጽዳት ዓላማው ተጠቂውን ማኅበረሰብ በሙሉ ወይም በከፊል ማጥፋት አይደለም ይባላል፡፡

ይሁን እንጂ የዘር ማጽዳት እርምጃ በጊዜ ካልተገታ ወደ ዘር ማጥፋት መሸጋገሪያ መሆኑን በመገንዘብ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤው በ1984 ዓ.ም. ዘር ማጽዳት የዘር ማጥፋት ዓይነት እንደሆነ ወስኗል፡፡ ሌላውና ሰብአዊ ወንጀሎች የሚለው እሳቤም በሠላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ መጠነ ሰፊና የተቀናጁ ጥቃቶችን የሚመለከተው ሲሆን፣ በተመሳሳይ በአንድ ዘር፣  ብሔረሰባዊ ወይም ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ ላይ ብቻ የተነጣጠረ አይደለም፡፡ ዘር ማጥፋት ከሰብአዊ መብቶች ጥሰት እጅግ የላቀ ተግባር ነው፡፡ ዘር ማጥፋት  ሌላ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ሌላ የጎሳ ግጭት ወይም የከሸፈ ወይም የመከነ መንግሥት ተምሳሌት ብቻም አይደለም፡፡  በሰው ለጆች ላይ ከሚያደርሰው እኩይ መቅሰፍት የተነሳ፣ ዘር ማጥፋት በራሱ በሥልጣኔ ላይ የተቃጣ አረመኔያዊ ጥቃት ተደርጎም ይቆጠራል፡፡

በዚህም መሠረት በሶማሊያ መንግሥት ውድቀት የተነሳ የተፈጠረው ነውጥና ፍጅት በቦስኒያ፣ በሩዋንዳ፣ በኮሶቮና በዳርፉር ከታዩት ድርጊቶች የተለየ ነው፡፡ ‹ጄኖሳይድ› እንደፊተኛው ግብታዊ ወንጀል ሳይሆን፣ በአደገኛና መሰሪ የፖለቲካ ኤሊቶች ታስቦና ታቅዶ በስልት የሚፈጸም አረመኔያዊ የጅምላ ጭፍጨፋ ዘመቻ ነው፡፡ እነዚህ ልዩነቶች የጸጉር ስንጠቃ ጉዳይ አይደሉም፡፡ የዘር ማጥፋትን በተመለከተ በርካታ የተራራቁ ምሁራዊ አስተያየቶች ቢኖሩም፣ አጠቃላይ ተቀባይነት ያገኘውና ወንጀሉን ለመከላከል፣ ለማስቆምም ሆነ ለመቅጣት አመቺው ብቸኛው ሕጋዊ ትርጓሜ ከላይ የተቀመጠው ነው፡፡ እንደ ዊሊያም ሻባስ ያሉ የሕግ ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት የዘር ማጥፋትን ለመዳኘት የሚያገለግል የሕግ ማዕቀፍ ሰባት አንቀጾችን ካካተተው ከኑረምበርግ መርሆችና ከጄኖሳይድ ስምምነት ጀምሮ ለግማሽ ምዕተ ዓመት የኖረ በመሆኑ አዲስ መቅረጽ አስፈላጊ አይሆንም፡፡

የዘር ጥቃት ተዋናዮች

ጭካኔና አረመኔያዊነት ቀለም፣ ብሔረሰብ፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ መደብ፣ ርዕዮተ ዓለም ወዘተ. አይለይም፡፡ በሁሉም ክፍለ ዓለማት፣ በሁሉም ዘመናት፣ በሁሉም ሥርዓታት ተከስቷል፡፡ ኮሚኒስቶቹ እነ ስታሊን፣ ማኦ ሴቱንግ፣ ቺያንግ ካይሼክና ፖልፖት በጨፍጫፊነታቸው ሂትለርን የሚያስከነዱ ነበሩ፡፡ የሰው ልጆች በጃፓን፣ በካምቦዲያ፣ በኮንጎ፣ በቡሩንዲ፣ እንዲሁም በቅርቡ በመካከለኛው አፍሪካና በሶሪያ ተቃዋሚዎች መካከል እንደተከሰተው የጠላትን ሥጋ እስከመብላት ድረስ ወደ አውሬነት እንደሚወርዱ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡

ሥልጣኔ የሰው ልጅን ባሕርይ ያሻሽለዋል የሚለው አስተያየት እጅግ አከራካሪ ነው፡፡ ራሱ የሰው ልጅ የመጠፋፋት አቅም በኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ብቻ የሚወሰን አለመሆኑ ገሃድ ሆኗል፡፡ የሩዋንዳው “የሜንጫ ጭፍጨፋ” ከናዚዎች ሳይንሳዊ የጥፋት ዘዴዎች በአምስት እጥፍ ስሉጥና አውዳሚ ነበር፡፡ በ100 ቀናት ብቻ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉትን የቀጠፈ ሲሆን፣ ሰማንያ በመቶውን ቱትሲዎች የጥቃቱ ሰለባ አድርጓል፡፡ ስመጥሩ የፖለቲካ ሳይንቲስትና በፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ሥር የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበሩት ዝቢግኒው ብርዚንስኪ እንዳሉት “ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድ ሚሊዮን ሕዝብን ከመግደል ይልቅ መቆጣጠር የቀለለ ነበር፡፡ ዛሬ ግን አንድ ሚሊዮኖችን መግደል ከመቆጣጠር በአጅጉ የቀለለ ሆኗል፤” (ሀጋን 2009)፡፡

የዘር ማጥፋት በዘፈቀደና በድንገት የሚቀሰቀስ ሳይሆን ታስቦና ታቅዶ የሚከወንና የራሱ  ተዋናዮችና ውስጣዊ ሒደቶች ያሉት ብቻ ሳይሆን በቡድን የሚከወን ድርጊትም ነው፡፡  የዘር ማጥፋት ወንጀል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሥነ ልቦናዊ መልኮችን ያካተተ ሰፊ ሒደት ውጤት ነው፡፡ እስከዛሬ እንደታየው የዘር ማጥፋት በዋነኝነት የሚቀነባበረውና የሚፈጸመው መንግሥታዊ ሥልጣን በጨበጡ የፖለቲካ ኤሊቶችና ደጋፊዎቻቸው በመሆኑ ወንጀሉን ለመከላከል፣ ለማስቆምም ሆነ ጥፋተኞችን ለፍርድ ለማቅረብ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሥልጣን የጨበጡ ቡድኖች በዘር ጥቃት ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ ሊሆን ይችላል፡፡

በጀርመን የናዚ ፓርቲው ግልጽ የሆነ ፀረ ሴማዊ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ገና ሂትለር ሥልጣን ከመያዙ በፊት ጀምሮ ለ15 ዓመታት የተካሄደ ነበር፡፡ ሂትለር መንግሥት እንደመሠረተ በቀጥታ ሕልሙን ተግባራዊ ማደረግ ጀመረ፡፡ በአይሁዳውያን ላይ የተከተለው ፖሊሲ በጦርነቱ ዋዜማ በ1931 ዓ.ም.  ሙሉ በሙሉ ከጀርመን ሕይወት ውስጥ አገለላቸው፡፡ ለውድመት ተመቻቹ፡፡ በኮሶቮና በቀሪው ዩጎዝላቪያ የተፈጸመው የዘር ማጽዳት ዕቅድ የተነደፈውና መስከረም 1979 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው በሰርቢያ የሳይንስና ሥነ ጥበብ አካዳሚ አማካኝነት ነበር፡፡ ይህም ሰነድ ሚሎሶቪች ሥልጣን እንዲቆናጠጥና ዓላማውን በተግባር እንዲያውል ረድቶታል፡፡

በሩዋንዳም ከጥላቻ ዘመቻው እስከ ግድያ ትዕዛዙ ድረስ ሂደቱ የተመራው በመንግሥት ፖለቲከኞች አማካይነት ነበር፡፡ ሁቱ መራሹ አገዛዝ የጥላቻ ፖለቲካ ሲያካሂድ የነበረው ቢያንስ ለአርባ ዓመታት ገደማ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ቱትሲዎች በጦር ኀይሉ ውስጥ ያላቸውን ቦታ እንዲያጡ መደረግ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ግልጽ መድልዎና በደል ይደርስባቸው ነበር፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ ፀረ ቱትሲ ፕሮፓጋንዳዎችን ያሰራጩ ነበር፡፡ በ1995 ዓ.ም. የፈነዳው የዳርፉር ጭፍጨፋም የሱዳን መንግሥት የሃያ ዓመታት ፀረ ጥቁር/አፍሪካውያን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻና ፖሊሲ ፍሬ ነበር፡፡  ከደቡብ ሱዳን ነጻነት በኋላ ደግሞ ፕሬዚዳንት አልበሽር በንቀት ‹ዙርጋ› እያለ የሚጠራቸውን ሦስት የዳርፉር ብሔረሰቦች ማለትም ዳር፣ ማሳሊትና ዛግዋን መሬት የጃንጃዊድ ዐረብ ሚሊሻዎች ከመደበኛው የመንግሥት ሠራዊት በማበር እንዲነጥቁ፣ ነዋሪዎቹን እንዲያሰቃዩ፣ እንዲገድሉና እንዲደፍሩ፣ መንደሮችን በጠቅላላ እንዲያወድሙና ከብቶችንም እንዲወርሱ አድርጓል፡፡

ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው በሥልጣን ያለው አገዛዝ ዋና ተዋናይ ይሁን እንጂ፣ የዘር ጥላቻን በማራገብና ሕዝቦችን ለመጠፋፋት በማዘጋጀት በኩል መንግሥትን የሚቃወሙ ብሔረሰባዊ ወይም ፖለቲካዊ ቡድኖችም ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖች አቅማቸው እስከፈቀደ ድረሰ በጠመንጃም ሆነ ያለጠመንጃ የሚፋለሙትን መንግሥት ከአንድ ወይም ከሌላ ብሔረሰብ ጋር በማዛመድ የዘር ጥላቻና ተቃውሞ ይቀሰቅሱበታል፡፡ አገዛዙ ለፖለቲካቸው የሚመች ከሆነም ደግሞ በዴሞክራሲ፣ በፍትሕና በእኩልነት ስም በሕዝቦች ውስጥ የሚነፈርቅ ጠላትነት ይዘራሉ፡፡ ነገር ግን በሠላምም ይሁን በአመጽ ሥልጣን ካልያዙ፣ ወይም ከፍተኛ ማኅበራዊ ነውጥ ካልተፈጠረላቸው በስተቀር እኩይ ዓላማቸውን  በተግባር የማዋል ዕድል የላቸውም፡፡

ከሥነ ልቦና አንጻር ስናየው ደግሞ ሰፊ የዘር ጥቃቶች አመንጪዎችና አንቀሳቃሶች በበታችነት ስሜት የሚሰቃዩ የፖለቲካ ኤሊቶች ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ምሁራን በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ላይ ርዕዮተ ዓለሙን በመንደፍና በማስፋፋት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የጥላቻው ደረጃ ወደ እብደት ደረጃ ሲሻገር ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የዘረፋ ቡድን ካፖዎች፣ የለየላቸው ንኮችም ሳይቀር በብሔረሰብ ወይም በሃይማኖት ተቆርቋሪነት ስም ብቅ ብቅ ይላሉ፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ዶብሪካ ኮሲክ (ሰርቢያ)፣ ፈርዲናንድ ኒህማና (ሩዋንዳ)፣ ዶ/ር ጎብልስና (ጀርመን) ዶ/ር ሊዎን ሙገሴራ (ሩዋንዳ)፣ አረመኔው ሳይካትሪስት ራዶቫን ካራዲችን የመሳሰሉ ምሁራንን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የዘር ጥቃት በሰፊው ሲተገበር ቢያንስ በተርታው ሕዝብ ውስጥ የተወሰነ ተቀባይነትና ተባባሪነት ማግኘት የግድ ነው፡፡ በጥላቻ የተዋጠና የማያመነታ የካድሬ ቡድን እስካለ ድረስ ደግሞ ሰፊውን ሕዝብ በውድም በግድም ወደ ጥፋቱ ማኅበር ማስገባት ይቻላል፡፡ ማባበል፣ መደለል፣ ማስፈራራት፣ ማግለል፣ መቅጣት፣ መሳቂያ ማድረግ፣ ቀስ በቀስ ተግባር ላይ የሚውሉና በአረመኔያዊ ተግባሮች ላይ ለመሳተፍ የሚያመነቱን ለመቀላቀል የሚውሉ ስልቶች ናቸው፡፡ በጀርመንና በሩዋንዳ ታይተዋል፡፡

ተመራማሪዎች እንደሚሉት አመጽ አንድ ጊዜ ከተጫረ በተዋናዮቹ ውስጥ እመርታዊ ለውጥ ያስከትላል፡፡ በግለሰቦች ማንነት፣ በማኅበራዊ ደንቦች፣ በተቋማት፣ እንዲሁም በወግ ልማዶች ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ድርጊቱ የተለመደና ተራ እንዲመስል ያደርገዋል፡፡ ክፉ አትዋል የሚለው ብሂል “ከፍ ባሉ” የቡድኑን ንጽሕና፣ መልካምነትና ደህንነት በመጠበቅና ጠላቶችና አጥፍቶ የተሻለ ማኅበረሰብ መፍጠር በሚሉ የሞራል መርሆዎች ይተካል፡፡

ለመሆኑ የዘር ማጥፋትን የመሰሉ ዘግናኝ ድርጊቶች መሠረታዊ መንሥኤዎች ምንድናቸው? የባህል፣ ቋንቋና እምነት ልዩነቶች፣ የሀብት ክፍፍል ችግሮች፣ የፖለቲካ ሥልጣንና ውክልና፣ የዘመናዊነት ተጽዕኖዎች፣ የሰው ልጅ እኩይ ተፈጥሮ ወይስ ውስብስብ የሥነ ልቦና ችግሮች? የሚገርመው ነገር የዘር ጥቃቶች በዓላማም ሆነ በግብ በዘርና በእምነት ማንነት ላይ የተመሠረቱ ይሁን እንጂ፣ ለምሳሌ እንደ ሩዋንዳ ባሉት አገሮች የብሔረሰብ ድንበሮች፣ ቋንቋ፣ ባህል ወይም እምነት ቀዳሚ የግጭት ምክንያቶች አልነበሩም፡፡ የዘር ጥቃትን በተለያየ ደረጃ የሚፈጽሙና የሚያስፈፅሙ ቡድኖች ቢያንስ ኹለት ዋና ዋና ምክንያቶች ይኖራቸዋል፡፡ አንደኛው ፖለቲካዊ ምክንያት ሲሆን የጥቃቱ ዒላማ የሥልጣን ተቀናቃኝ ሊሆን፣ አገዛዙን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ተብሎ የሚገመትን ብሔረሰባዊና ሃይማኖታዊ ቡድን በተቻለ መጠን ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ከምድረ ገጽ ጠራርጎ ለማጥፋት የሚፈጸም ድርጊት ነው፡፡

ኹለተኛው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሲሆን በተለይም በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ ተሰባጥረው የሚኖሩና በኢኮኖሚው የተለያየ ዘርፍ እጅግ በተሳካላቸው ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በእነዚህ ስኬታማ ማኅበረሰቦች የቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ አሉባልታዎች ከመንዛት፣ ከማሻጠርና አድማ ከማድረግ ጀምሮ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣልና በመውረስም ጭምር እስከማክሰር ይሄዳል፡፡ በገጠርማ አካባቢዎችም ከመሬታቸው የማፈናቀልና የመቀማት እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ በተለይ በአገራችን በበርካታ ቦታዎች በጉራፈርዳ፣ በአሶሳ፣ ወዘተ. የተደረጉ “በመጤነት” የተፈረጁ ማኅበረሰቦችን በማስፈራራትና በማስገደድ ማባረር እነዚህን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መልኮች ያቀላቀለ ከመሆንም አልፎ፣ የጥቃቱ አበጋዞች ወደፊት ለሚመኙት “ንጹሕ” ክልልና አገር መንገድ የሚያዘጋጅ ሒደት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው ማኅበረሰቦችን በኃይል በማስገደድ ከመኖሪያቸው የማፈናቀል ዓለም ዐቀፍ ወንጀል “ዘር ማጽዳት” ተብሎ ይታወቃል፡፡

በዘር ጥቃት መንስኤነት የሚታወቀውና ረቀቅ ያለው ምክንያት ሥነ ልቡናዊ ሲሆን በተለይም ደግሞ ዋነኞቹን አሉታዊ ስሜቶች በቀል፣ ቅናትና ስጋትን ይጨምራል፡፡ የዚህ አጠቃላይ መንፈስ መንስኤዎች ታሪካዊም ነባራዊም፣ እውነታም ምናባዊም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በቀል ጥቂትም ቢሆን ታሪካዊ ይዘት ያለውና ላለፉ ጉዳቶች መካሻ የሚፈልግ ስሜት ሲሆን፣ አቀራረቡም በፍትሕና ርትዕ ስም ይሆናል፡፡ ቅናት ደግሞ በተቃራኒው ቡድን ነባራዊም ሆነ ምናባዊ ሀብት፣ ተሰጥኦ ወይም ዕሴት ላይ የተመሠረተ፣ ነገር ግን ማኅበራዊ ተቀባይነት የሌለው መንፈስ በመሆኑ ራሱን እንደ እኩልነት፣ አገር ወዳድነት፣ ተቆርቋሪነት፣ ወዘተ ባሉ መልኮች የሚገልጥ ነው፡፡ ስጋት ታሪካዊውንም፣ ነባራዊውንም፣ መጻኢውንም አቅጣጫዎች የሚዳስስ በራስ ያለመተማመን ስሜት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ስሜቶች የተቀላቀሉበት የበታችነት መንፈስ ደግሞ የፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ የበላይነት የማያጠፋው መሆኑ አንዱ አወሳሳቢ ችግር ነው፡፡

ኒኮላስ ሮቢንስና አዳም ጆንስ ‹‹የተጨቋኞች ዘር ማጥፋት›› (2009) በሚል ርእስ በሳተሙት መጽሐፍ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ኀይሎች (በሕዳጣን?) የሚካሄዱ ጭፍጨፋዎችን በማጥናት ረገድ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ግንባር ቀደሙ በነባራዊው እውነታና በኅሊናዊ ግንዛቤ መካከል የሚስተዋለው ተገላቢጦሽ/ተቃርኖ ነው፡፡ ሩዋንዳን ለአብነት ብንወስድ የሁቱዎች ብሔራዊ የበላይነት ከ1952 ዓ.ም. ጀምሮ በይፋ ቢመሠረትም፣ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ግን የተዋረድ ግንዛቤው ሊለወጥ አልቻለም ነበር፡፡ የቱትሲዎች ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ቁሳዊና አካላዊ የበላይነት ላይ የተመረኮዙ ፍረጃዎች በሰፊው የሁቱ ማኅበረሰብ ውስጥ የቅናት፣ የበቀልና የስጋት ምንጮች ነበሩ፡፡ ሁቱዎች ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ እነዚህን ስሜቶች ከማጥፋት ይልቅ ቅኝ ገዥዎች በፈጠሯቸው የሐሰት እምነቶች ራሳቸውን ኮድኩደው ቀጠሉ፡፡

ከላይ እንደጠቀስነውም ሁቱ መራሹ መንግሥት ቱትሲዎች ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል የበቀል ጭቆና ሲያደርግባቸው ቆይቷል፡፡ በርካታ ቱትሲዎች ተገድለዋል፤ አገራቸውንም ጥለው ተሰድደዋል፡፡ በኋላም በ1950ዎቹ  የተሰደዱት ቱትሲዎች ልጆች በ1980ዎቹ መጀመሪያ ወደ አገራቸው በኀይል ለመመለስ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር የተሰኘ ጦር በኡጋንዳ መሥርተው ትግል ሲቀጥሉ በርካታ ቱትሲዎች ይህን ወታደራዊ ዘመቻ የሚደግፉ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን ይህ እንቅስቃሴ የሁቱዎችን የማይሞት ስጋት እንዲያንሰራራ አደረገው፡፡ ቱትሲዎች አሁንም ሥልጣናችንን ቀምተው የጥንቱን አገዛዝ ሊጭኑብን እያሴሩ ነው የሚል ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ ተቀሰቀሰ፡፡ አንዳንድ ወቅታዊ አቀጣጣይ ጉዳዮች ሲጨመሩበትማ ሁኔታው ወደ ዘር ማጥፋት ሥነ ልቦና አደገ፡፡ ለምሳሌ ሁቱዎች በነሐሴ ወር 1985 ዓ.ም. የተደረገው የአሩሻ ስምምነት ለቱትሲዎች ያደላ ነው የሚል ቁጭት አድሮባቸው ነበር፡፡

በዚህ ላይ ደግሞ ለሁቱ ጽንፈኞች ተአማኒነት መጨመር የቡሩንዲው ሁቱ ፕሬዚዳንት ሜልኮር ንዳዳየ በቱትሲ ጄኔራሎች ጥቅምት 1986 ዓ.ም. መገደሉ ዋነኛው ነበር፡፡ ይህን የስጋት ጡዘት ለመደምደም ሀቢሪማናም በሚያዝያ 1986 ዓ.ም. በአውሮፕላን አደጋ ሕይወቱ አለፈች፡፡ ይህም አገሪቱን ወደ ደም ምድርነት ቀየራት፡፡ በዘመናችን ከፍተኛ የዘር እልቂት በተፈፀመባቸው አገራት በጀርመን፣ በሰርቢያና ኮሶቮ፣ በዳርፉርና በሌሎችም አካባቢዎች የታዩት ተመሳሳይ ሒደቶች ናቸው፡፡

እዚህ ላይ ትኩረታችንን የዘር ጥቃት ርዕዮተ ዓለም ምንድነው? ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ዘግናኝ ወንጀል ለመከላከልም ሆነ ለማስቆም ያልቻለው በምን የተነሳ ነው? የዘር ጥቃትን አስቀድሞ ለማወቅና ለመጠንቀቅ ምን መደረግ አለበት? ወደሚሉት ጉዳዮች እንመልስ፡፡ የዘር ጥቃት የሚገለጥባቸውን መልኮችና ደረጃዎች፣ ችግሩን ለመቅረፍ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ያጋጠመውን ፈተና፣ እንዲሁም በየፈርጁ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የመከላከል እርምጃዎች እንዳስሳለን፡፡

ምድራችን ሰብአዊ ፍጡራን ለመጠፋፋት የተፋጠጡባት አውድማ የመሆኗ ነገር በእጅጉ የሚያሳስብ ነው፡፡ ችግሩን የበለጠ አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ የሰው ልጅ ዘር ማንዘሩን ከናካቴው ለማውደም የሚያስችል አቅም ማበጀቱ ነው፡፡ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ከባተ በኋላም አመክንዮና መርህ በጠቋሮቹ የስሜትና ጥላቻ መናፍስት እንደተዋጡ የቀሩ ይመስላል፡፡ በየአቅጣጫው ሕይወት እየረገፈ ደም እየጎረፈ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ፍዳ ደራሲ የሆነው የማንነት ፖለቲካ አሁንም ከመንበሩ አልወረደም፡፡ ታዲያስ ምን ይበጃል?

የጥላቻ ፖለቲካ የማንነት አስተሳሰብን ተጣብቶ የሚኖርና በሂደትም ጭራሽ ፖለቲካ የተባለን ነገር የሚያጠፋ መንፈስ ነው፡፡ አደገኛነቱም በከፊል የመደብ፣ የርዕዮተ ዓለምና የእምነት ድንበሮችን ተሻግሮ ከማስተባበር ባሕርይው ይመነጫል፡፡  የዘር ጥቃት አቅጣጫውን የሳተ ጽንፈኛ ብሔረተኝነት ወይም ጎሰኝነት ውጤት ሲሆን፣ ብሔረተኝነት ደግሞ ድሩም ማጉም ታሪክ ነው፡፡ ለዘረኞች “ሌላው” ማኅበረሰብ ብሔራዊ ባላንጣም ታሪካዊ ጠላትም ነው፡፡ ይህን ጠላት ለማጥቃት በሚነድፉት መርሐ ግብር ውስጥም ታሪክ ነክ ፖለቲካ ዋነኛ የብሶት አስታዋሽና አንቀሳቃሽ ኀይል ሆኖ ያገለግላል፡፡ ታሪክ ለጠባብ፣ አጭርና አፍራሽ ግብ እንዲውል እንዳመችነቱ ይፈበረካል፣ ይቃናል፣ ይወላገዳል፣ ይበረዛል ወዘተ.

ዘውጌ ብሔረተኞች የታሪክ እስረኞች እንደመሆናቸው መጠን ለአብሮነትና አዎንታዊ መስተጋብሮች የከረረ ጥላቻ አላቸው፡፡ ካሰመሩት ጠባብ ቅጥር ውጭ ያሉትን ታሪኮች በሙሉ የጭቆናና የጨቋኝ ብሔረሰብ ገድሎች በማለት ያጣጥላሉ፡፡ ቆምንለት የሚሉትን ማኅበረሰብ ራስ በቅ፣ ፍጹምና ያልተነካካ አድርገው ይስላሉ፡፡ ዶ/ር የራስወርቅ (1998፣78) እንዳስገነዘቡት “አክራሪ ጎሰኞች የማንነት መጋራትን፤ እንደድልድይ የሚያገለግሉ የብዝሃ-ማንነት ባለቤት የሆኑ ሰዎች መኖር ለሚያራምዱት አጀንዳ አመች አለመሆን በሚገባ ስለሚረዱት ይክዱታል፤ ያጥላሉታል፤ ያወግዙታል፡፡ ጎሳቸውን ወይም ብሔረሰባቸውን በጠባቡ የሚያጥር ትርጉም ያስቀምጡታል፡፡ ንጹሕነቱን መጠበቅንም ዋነኛ ጉዳይ ያደርጉታል፤”  እነዚህ ኀይሎች ታሪካዊ ቁስሎችን በመሞዠቅ፣ የግጭት ገድሎችን ነጥሎ በማጋነን የቁጭት መንፈስን ለማፍላት አበክረው ይሠራሉ፡፡ “የትናንቱ ግፍ ሳይበቃን፣ ዛሬም ለጥቃት ተጋልጠናል፤” የሚል ፍርሃት ይዘራሉ፡፡ በነጻነት፣ በፍትሕና ርትዕ ስም ለታሪካዊ በቀል ያነሳሳሉ፡፡

የጥላቻ ፖለቲካ “መሰሪ ጠላታችን ሳይቀድመን እንቅደመው” በሚል የአልሞት ባይ ተጋዳይነት አቋም ለማስፈን የሚታለም/የሚታቀድ ሲሆን፣ ቁልፍ አስተሳሰቡም “አከርካሪን መስበር፣ አፈር ማስጋጥ፣ አንገት ማስደፋት፣ ቅስም መስበር” ወዘተ. በሚሉ ሐረጎች ይገለጣል፡፡ በባሕርይው ይህ የደመኝነት አስተምህሮ በነተበ የታሪክ እውነታ ወይም በለየለት ፈጠራ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለምሳሌ የሰርቦች ቁጭት ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት በ1381 ዓ.ም. በተደረገው የኮሶቮ ጦርነት ከደረሰባቸው ሽንፈት ይነሳና በኹለተኛው የዓለም ጦርነት በፋሽስታዊው የክሮሽያ ኡስታሻ አገዛዝ እስከተፈጸመባቸው ግፍ ድረስ በቀጭን ክር ያስተሳስራል፡፡ ይባስ ብሎም ቱርኮች በ14ኛው ክፍለ ዘመን፣ ክሮአቶች ደግሞ በ1940ዎቹ ለፈጸሙት በደል በ1990ዎቹ የቦስኒያ ሙስሊሞችን ጭዳ አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ ዘውጌ ብሔረተኞችና ጎሰኞች ከዛሬውና ከመጭው ተስፋ ይልቅ ባለፉ ታሪኮች በመኮድኮዳቸው፣ ጠላቶቻቸው አያቶችና ቅድመ አያቶች ናቸው፡፡ በአገራችን አንዳንዶች ደማቸው የሚሞቀው እነሚኒልክ ሲነሱ ሲሆን፣ የሚያባንናቸው “የነፍጠኞች ሴራ ከትናንት እስከዛሬ” ነው፡፡ ይኸው የተወላገደ የተጠቂነት ቅርስ የዛሬን እውነታም በቅጡ እንዳይገነዘቡ ይከልላቸዋል፡፡ ዓለምን ቢጨብጡም ኅሊናቸው ዓይተኛም፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚጠቁሙት “ተጨቆንኩ” የሚለው ቡድን ሥነ-ልቦና ጨቋኝ የተባለውን በተመለከተ ካሳደረው ያለመተማመንና የቅናት ስሜት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ እሮሮውም በውኑም ሆነ በሕልሙ ባለጋራውን እያሰበ እንጂ በተጨባጭ ባለበት ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ አይደለም፡፡ ስለዚህም ናዚዎች፣ ሰርቦችና ሁቱዎች ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊው ሥልጣን በእጃቸው ተጠቅልሎ እያለ “ጠላቶቻችን ሊያጠፉን ወይም ሊውጡን ነው፤” የሚለው ደመነፍሳዊ ቅዠት ይረብሻቸው ነበር፡፡

ልብ ሊባል የሚገባው የጥላቻ ታሪክ አበጋዞች የአገም-ጠቀም ደራሲያን ሳይሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑና በየትምህርት ተቋማቱ ውስጥ የተሰገሰጉ “ምሁራን” ናቸው፡፡ እነዚህም ለ‹ጄኖሳይድ› ከሚደረጉ የሥነ ልቦና ዝግጅቶች መካከል ዋነኞቹ በሆኑት ብሔረተኛና ጎሰኛ ስሜቶችን የሚያጠናክሩ አስተሳሰቦችና ተቋማትን በማስፋፋት፣ እንዲሁም የጀግንነት ወኔን በመቀስቀስ ረገድ በቀደምትነት ይሳተፋሉ፡፡ “ያልተበረዘ ያልተከለሰ” ታሪካችንን ለመጻፍ ከኛ በላይ ላሳር ይላሉ፡፡ ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ እስከሆነ ድረስ በጥናትና ምርምር የተለወሰ ውሸትና ክህደት ለማራመድ ቅንጣት አያመነቱም፡፡ አቅማቸው በፈቀደ መጠን የሚወጥኑት የአስተሳሰብ ጽዳት ከታሪክ አሻራዎች ጽዳት ይጀምራል፡፡ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ መዛግብት፣ የታሪክና ቅርስ መዘክሮች ዋነኛዎቹ ዒላማዎች ይሆናሉ፡፡

 የትምህርት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎችም ማኅበራዊ መድረኮች በጽንፈኛ አስተምህሮዎች ይቃኛሉ፡፡ የቦታዎች፣ መንገዶች፣ ተቋማት፣ አልፎም የግለሰብ ስሞች ሳይቀሩ ይለወጣሉ፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎች የኢትዮጵያ ታሪክና ኢትዮጵያን የሚመለከቱ መልካም ነገሮች እነሱ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እንደጀመሩ ሊያስገነዝቡን የሚታትሩት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ የቀደሙት የኢትዮጵያ መሪዎች የሠሩት ሥራ ወይ ከነጭራሹ አይነሳም፤ ከተነሳም በአሉታዊ ጎኑ ብቻ ነው፡፡

የሁቱ “የታሪክ ምሁራን” ልክ በአገራችን እንደተደረገው ቱትሲዎች በሩዋንዳ የሠፈሩበትን ሒደት “የውስጥ ቅኝ አገዛዝ” (internal colonialism) በማለት ፕሮፓጋንዳ ሲሠሩበት ኖረዋል፡፡ የሰርብና የሁቱ ጽንፈኞች በ1980ዎቹ ባካሄዱት የኅሊና ብዝበዛ፣ በሕዝባቸው መካከል ጥላቻና ፍርሃትን በማንገስ ለዓላማቸው አመቻችተውታል፡፡ ኒል ክረሰል (2002፣ 97) እንደጠቆመው የዘር ጥቃት አስከፊነት የጋራ ማንነት መገለጫዎች በተንሰራሩበት፣ በተጋነኑበትና ለፖለቲካ ጥቅም በተበጃጁበት መጠን የተወሰነ ይሆናል፡፡ በአጭሩ ታሪክ የዘር ማጥፋት ርዕዮት ምሰሶ ነው፡፡

(Visited 176 times, 1 visits today)
March 15, 2019

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo