Articles, News, Opinion

የዐቢይ መንግሥት ጠንካራ ነው- ፋሲል ኑርልኝ

“በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ደካማ ነው፤ አገሪቱ በየቦታው በታጠቁ ኀይሎች እየታመሰች ነው፤ በመንግሥት ላይ መንግሥት የሆኑ አካላት እንደፈለጋቸው አመጽ እየጠሩና ሕዝብ እያስገደሉ ሳይጠየቁ በነጻነት እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ሕወሓትም ከክልሉ አልፎ አገር እንዲያተራምስ ዕድል ተሰጥቶታል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ሕወሓት በማናለብኝነት መንፈስ ምርጫ ለማካሄድ ወስኗል፤ ሃይማኖት ተኮር ፓርቲዎችና ባንኮች ብቅ ብቅ እያሉ በአገሪቱ ህልውና ላይ አደጋ እየተደቀነ ነው” ወዘተ… ሲባል እንሰማለን፡፡ ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው የሕዝብ ቅሬታዎችና ብዥታዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ፡፡

በእኔ አስተያየት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግሥት ጠንካራ ብቻ ሳይሆን በጣም ጠንካራ መንግሥት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን መሪ እየተሰደበና እየተተቸ፣ ከዚያም አልፎ አንዳንድ አካባቢዎች ከማዕከላዊ መንግሥት ውጭ የሆኑ ወይም የተቃረኑ ውሳኔዎችን እየወሰኑ መንግሥት ይረጋጋል የሚል እምነት የለንም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን ለውጥ በመጣ ቁጥር ያለፈው ሥርዓት መሪዎች ካልተንበረከኩ ማዕከላዊ መንግሥቱ የሚጸና አይመስለንም፡፡ ለዚህ ነው በ66ቱ አብዮት ወቅት ብዙ ሰው ወደ ደርግ መሪዎች እየቀረበ የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ መንግሥትን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ ራሳቸውን ንጉሠ ነገሥቱንም እንዲገድላቸው ሲወተውት የነበረው፡፡ “እነሱ እያሉ ምን ለውጥ አለ?” ሲባል ነበር በወቅቱ፡፡ ደም የጠማቸው እነ መንግሥቱ ኀይለ ማርያምም “እንኳንም ዘንቦብሽ…” እንደሚባለው፣ እንኳንም የሕዝቡን አስተያየት አግኝተው ከመግደል አይመለሱም ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም. እና ከዚያ በኋላ የደርግ መሪዎች እንዲገደሉ ሲቀሰቅሱ የነበሩ በርካታ ሰዎች እንደነበሩም አይዘነጋም፡፡

በአጠቃላይ ያለፈው ወይም የተሸነፈው ሥርዓት መሪዎች ካልተወገዱ ወይም ካልተንበረከኩ ለውጥ የመጣ የማመስለው የአገራችን ሰው ብዙ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥት በደካማነት የሚከሱት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ለምን እነ ጌታቸው አሰፋ አልታሰሩም? ለምን እነ ስበሐት ነጋ አልተወገዱም? ለምን ሕወሓት በሕይወት ኖረ? ነው እየተባለ ያለው፡፡

የሕወሓትም ይሁን የድርጅቱ ከፍተኛ መሪዎች መኖር የዐቢይ አሕመድን መንግሥት ደካማ ሊያሰኘው ከቶም አይችልም፤ አይገባምም፡፡ አገሪቱን እየመራት ያለው ስብስብ ለብዙዎች አይነኬ ይመስል የነበረውን፣ ታንኩም ባንኩም በእጁ የነበረውን ቡድን ነው ያለ ደም መፋሰስ ያሸነፈው፡፡ ብዙዎች አይነቀነቅም ሲሉት የነበረውን ያን ግፈኛ ቡድን በእንዲህ ዓይነት ጥበብ ማሸነፍ መቻል ጥንካሬን ይጠይቃል፡፡ ያ ቡድን አሁንም መቀሌ ውስጥ መሽጎ አገሪቱ እንዳትረጋጋ ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ በየቦታው የአመጽ እሳት ለመለኮስ ሌት ተቀን እየሠራ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ እንጂ እየተጠናከረ ሊመጣ የሚችልበት ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡

ብዙ ሰዎች ሕወሓት ተሞክሮ ስላለው ተመልሶ ሊያንሰራራና ፌዴራል መንግሥቱን ሊቆጣጠረው ይችላል ይላሉ፡፡ በእኔ አስተያየት ይህ መቼም ሊሆን የማይችል ነገር ነው፡፡ እርግጥ ሕወሓት በእንዲህ ዓይነቱ ቀቢጸ-ተስፋ ውስጥ አይኖርም አይባልም፡፡ የፌደሬራሊስት ኀይሎች ብሎ ቀለብተኛ ግለሰቦችን ሰብስቦ ሲያደራጅ የከረመው፣ ከዚያም አልፎ ከአንዳንድ ጽንፈኞች ጋር እያበረ አገር ለማተራመስ የሚሞክረው በዚህ መንፈስ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በእጅጉ ተቀይሯል፡፡ እንደ ሕወሓት ዓይነት አናሳ ቡድኖች እንደፈለጉ አድራጊ ፈጣሪ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ የለም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡ እነ አቶ ስበሐት ነጋ አዲስ አበባ እየናፈቀቻቸው በመጨረሻው የሕይወት ዘመናቸው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እያሳለፉ ነው፡፡ ያን ያህል የቅንጦትና የምቾት ሕይወት ለለመደ ሰው ከትግራይ ውጪ (ለዚያውም ከመቀሌና አካባቢዋ) መንቀሳቀስ አለመቻል ትልቅ የቁም እስርና ሽንፈት ነው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት ጠንካራ መንግሥት ነው የሚባልባቸው ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ “የለውጡን ካልኩሌተር የሠራሁት እኔ ነኝ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኹለት መንግሥት ነው – አንዱ በዐቢይ የሚመራው፤ ሌላው በቄሮ የሚመራው፤ አመጽ መጥራቱን እናውቅበታለን” ወዘተ… እያሉ በየጊዜው ሲዝቱ የነበሩትን እነጃዋር መሐመድን ልካቸውና አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ ያሳየ መንግሥት ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት፡፡

ከነጃዋርን ጋርም ይሁን የሕወሓት አመራር ጋር በቀጥታ ከመላተም ግፈኝነታቸውን እና ምን ያህል ለሕዝብ ሳይሆን በሕዝብ ላይ ቆሙ መሆናቸውን በትዕግስት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳየት ተችሏል፡፡ ጃዋር መሐመድ ያጣው የተመኘውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ሕልሙን ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብ መሪነቱንም ጭምር ነው፡፡

ይህን ማድረግ ትልቅ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ ይህን መፈጸም ጥንካሬን ይጠይቃል፡፡ ጽንፈኛ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች አጀንዳ አጥተው በሰፈር አጀንዳ ሲራኮቱ እንዲውሉ ያደረገው የዐቢይ መንግሥት ጥንካሬ ነው፡፡ ምላሰ ረዣዥሞች በዚህች አገር ሰላምና መረጋጋት እንደሌለ ሊሰብኩ ቢሞክሩም የዐቢይ መንግሥት ደምጹን አጥፍቶ በትዕግስት ሥራ እየሠራና መሠረቱን እያሰፋ ነው፡፡ ያለ ጥርጥር ዝም የተሰኘው ብዙሃን (silent majority) ከመንግሥት ጎን ነው፡፡ አንድም ሌሎች ኀይሎች ሁሉንም አቅፈው መሄድ የማይችሉ ደካሞች በመሆናቸው፤ ኹለትም የዐቢይ መንግሥት ከነውስንነቱም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት፣ ዕድገትና ብልጽግና በተመለከተ በፈጠረው ተስፋ፡፡

ታንኩንም ባንኩንም ተቆጣጥሮ የነበረን ኀይል ያለ ደም መፋሰስ ማሸነፍ ትልቅ ጥበብና አቅም ይጠይቃል፡፡ ባላንጣ ከነበረ ከጎረቤት ጋር ሰላም ማውረድ፤ በዚህም የሰላም ኖቪል ተሸልሞ የአገርን ክብር ከፍ ማድረግ … ትልቅ እምርታ ነው፡፡ ጠላትም ወዳጅም ሊክደው የማይችለው እምርታ!

(Visited 42 times, 1 visits today)
June 24, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo