Articles, History, World News, ሕግ

የክልሎችን አወቃቀር የመከለስ አስፈላጊነት

በሥራ ላይ የሚገኘው የክልሎች አደረጃጀት በሽግግር ወቅት የተሠራ፣ በሚመለከታቸው የመስኩ ምሁራን ጥልቀት ያለው ጥናት ያልተደረገበትና የሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦችና ፖለቲከኞች ፍላጎት በአግባቡ ያላስተናገደ፣ ይልቁንም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በወቅቱ ተደራጅተው ይንቀሳቀሱ የነበሩት የተቃዋሚ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች አመራሮችና አባላት ጭምር በንቃት፣ በብስለት እና የእኩልነት ስሜትን በሚያስተናግድ መልኩ ተሳትፈው ሐሳባቸውን በነጻነት ያራመዱበትና ድምጻቸውንም የሰጡበት እንዳልነበር የተለያዩ ወገኖች አሁንም ድረስ በአንክሮ ሐሳባቸውን ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡

በወቅቱ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የበላይነቱን በያዘበትና ገና በቅጡ ሥራ ላይ ባልዋለበት ሁኔታ፣ የገዥው ፓርቲ ፖለቲከኞች በተለይም የሕወሓት መሪዎችና ግንባር ቀደም ካድሬዎች ፍላጎትና ውሳኔ ይበልጥ ተቀባይነት የሚያገኝበትና ተግባራዊም እየሆነ የነበረበት አጋጣሚ ስለነበር፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልን የፈጠሩት አምስቱ ክልሎች ሳይቀሩ ወደ አንድነት የመጡት፣ በወቅቱ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ቢተው በላይ (ከድርጅታቸው የበላይ አመራር የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል) ባቀረቡላቸው የማግባቢያ ሐሳብ መሠረት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎች በሰጡት ውሳኔ አማካኝነት ነው፡፡

በሌላ አነጋገር በአሁኑ ወቅት በአንድ ላይ ተካተው የሚገኙት 56ቱም የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ የፖለቲካ መሪዎቹም ጭምር በአግባቡ መክረውና ዘክረው፣ በአስፈላጊነቱም ላይ በሚገባ አምነውበትና ፍላጎታቸውንም በሥርዓቱ ገልጸው የተፈጸመ ውሕደት አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት የተቃውሞ ሐሳባቸውን በግልጽ የሚያቀርቡ አንዳንድ የክልሉ ምሁራንን ጨምሮ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡

ለዚህም ነው ከዓመታት በፊት ብዙም የመልካም አስተዳደር ችግር ያልገጠማቸውና የክልሉን የፖለቲካ መዘውር እያሽከረከሩ ባሉበት ሁኔታ ጭምር የርዕሰ መስተዳድርነቱን ቦታ የወላይታው ተወላጅና የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለ ማሪያም ደሳለኝ በመያዛቸው ብቻ የሲዳማ ምሁራንና ፖለቲከኞች “ሲዳማ ራሱን የቻለ ክልል መሆን አለበት” ብለው በብሔረሰቡ ምክር ቤት ሳይቀር ወስነውና አስወስነው አቋማቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጽሑፍ ለማሳወቅ ረዥም ጊዜ ያልወሰደባቸው፡፡ በክልሉ ምዕራባዊ አካባቢ የሚገኙት የብሔረሰብ አስተዳደሮችም ቢሆኑ የፖለቲካ ጫናው በርትቶባቸውና በድርጅታዊ ዲስፕሊን ማለትም በኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አስተሳሰብ ተጠፍረው እውነተኛ እምነታቸውን እንደ ሲዳማ ፖለቲከኞች በድፍረት ተነሳስተው በግልጽ ወደ መድረክ የመወያያ አጀንዳ እንዲሆን አያድርጉት እንጂ የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀምና ውስጥ ለውስጥ ሳይቀር የክልሉ ማዕከል ወደ ሆነው ሐዋሳ ከተማ ለመድረስ በጅማ በኩል ዞረን አዲስ አበባን አቋርጠን ሺሕ ኪሎ ሜትሮችን ለምን እንድንጓዝና የምዕራብ ኢትዮጵያን ሰበርባራ ቦታዎችና በረሃዎች እንድናቆራርጥ ተፈረደብን? የሚል ቅሬታ በመያዝ ጥያቄ ማንሳታቸው አልቀረም፡፡ ይህ ጥያቄ ወደ ሕዝበ-ውሳኔ ሄዶ ሲዳማ በክልልነት እንዲደራጅ እየተደረገ ነው፡፡

ከዚህም አልፎ ቀደም ሲል ጀምሮ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በአማራና በትግራይ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በትግራይና በአፋር ክልሎች መካከል በሚገኙ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ እየተነሳ ያለው የድንበር ጥያቄ ችግሩን እያባባሰው መምጣቱን መገንዘብ እንችላለን፡፡ በመሆኑም ያለፈውን ስህተት ከመሠረቱ ለማረምና የክልሎች አደረጃጀትም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ጥያቄ በትክክል የሚመልስ፣ የሕዝቦችን ቅሬታ በተሟላ መልኩ ሊያስወግድ የሚችል እንዲሁም የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችልና ብሔራዊ መግባባትን ያለ ብዙ ውጣ ውረድና ከፍተኛ መስዋዕትነት ማምጣት የሚችል እንዲሆን ከተፈለገ፣ ክልሎች እንደ አዲስ ቢደራጁ ጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት በብዙ የመስኩ ምሁራን ዘንድ ይንጸባረቃል፡፡

ይህም ሆኖ ቀጥሎ የቀረበው የአደረጃጀት አማራጭ በመነሻ ሐሳብነት የሚታይ ስለሆነ፣ በቀጣይ በሚሰነዘሩ አስተያየቶች አማካኝነት ይበልጥ እየዳበረ ወይም እየተስተካከለ የሚሄድና የገዥውን ፓርቲ ፖለቲከኞች ጨምሮ የሌሎችንም አመለካከት ለማግኘት ሊረዳ ስለሚችል ጉዳዩ ይበልጥ አከራካሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ በሌላ አነጋገር በአንድ በኩል ሐሳቡን በሚደግፉ ምሁራንና የኅብረተሰብ ክፍሎች አማካኝነት በሚሰነዘሩ ገንቢ አስተያቶች በሌላ በኩል ይህ ጉዳይ ምን ሲደረግስ ታሰበ የሚል አቋም ይዘው በሚቀርቡ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች የመሟገቻ ሐሳቦች አማካኝነት የውይይት ርዕስ ሊሆን ስለሚችል፣ ከኹለቱም ወገን በሚመጡ ሐሳቦች ይበልጥ ሊዳብር ይችላል፡፡   

አንደኛ፤ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥር የሚገኙት በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቢያንስ በአራት ክልሎች ተደራጅተው በአዲስ መልክ እንዲዋቀሩ ቢደረግ፣ በዚህም መሠረት የሲዳማና የጌዴኦ ብሔረሰብ አስተዳደሮች በአንድ ላይ ሆነው ራሱን የቻለ ብሔራዊ ክልል ቢፈጥሩና ማዕከላቸውንም ራሳቸው ተስማምተው እንዲመርጡ ዕድል ቢሰጣቸው አሊያም ሐዋሳን ማዕከላቸው አድርገው ሊቀጥሉ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ የከምባታ፣ የሃዲያ፣ የወላይታ፣ የጋሞ ጎፋ፣ የዳውሮና በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች የብሔረሰብ አስተዳደሮች በአንድ ላይ ተደራጅተው አንድ ክልል ቢመሠርቱና በራሳቸው ምርጫ ወላይታ ሶዶን ወይም አርባምንጭን ማዕከላቸው ቢያደርጉ፣ በምዕራብ የደቡብ ክልል አካባቢ የሚገኙት ከፋ ሸካና ቤንቺ ማጂ አስተዳደር ዞኖች ደግሞ በአንድ ላይ ተደራጅተው አንድ ክልል ቢፈጥሩና ማዕከላቸውንም ራሳቸው በነጻነት መርጠው እንዲንቀሳቀሱ ቢደረግ፣ እንዲሁም ጉራጌና ስልጤ ቀደም ሲል ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኹለቱ ብሔረሰብ ልኂቃን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በማሰወገድ የሚስማሙበትን ሁኔታ አመቻችተው በአንድ ላይ ሆነው ራሱን የቻለ ክልል ቢያደራጁ ለመልካም አስተዳደር መስፈንም ሆነ ለፈጣን ልማት መመዝገብ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረክታል ተብሎ ይታመናል፡፡ እንዲሁም በክልሉ ውስጥ የሚገኙት የልዩ ወረዳዎች ወደሚቀርባቸው ክልል በራሳቸው ፈቃድ እንዲካተቱ ቢደረግ ሒደቱን ይበልጥ አሳታፊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ያደርገዋል የሚል እምነት አለ፡፡

ኹለተኛ፤ የኦሮሚያ ክልል በቆዳ ስፋቱም ሆነ በሕዝብ ብዛቱ አሁን ካሉት ብሔራዊ ክልሎች እጅግ ትልቁ በመሆኑ ምክንያት ከ30 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ የሚኖርበት ከመሆኑም በላይ የቆዳ ስፋቱም በተለይም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ እጅግ የተለጠጠና ከ350 በላይ ወረዳዎችን ያቀፈ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ይህን ትልቅ ክልልና ሕዝብ በአንድ የአስተዳደር አካባቢ አጭቆ ማቆየቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ማመዘኑ አይቀርም፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ እንደሌሎች የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ ቋንቋውን እየተጠቀመና ባሕልና ወጉን እያሳደገ በሦስት ክልሎች ማለትም ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኦሮሚያና ምዕራብ ኦሮሚያ በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ማዕከሉን በየክልሉ አማካይ ቦታ ላይ ወስኖ እንዲተዳደር ቢያደርግ የኦሮሞን ሕዝብ በቀላሉ አንቀሳቅሶ ልማትን ለማፋጠንም ሆነ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት እየፈቱና ጥያቄዎችንም በቅርብ እየመለሱ ማኅበራዊ ችግሮችንም ጭምር በየጊዜው እየፈቱ መሄድ ስለሚችሉ ዘላቂ ጥቅም ያስገኝ እንደሆነ እንጅ አንዳንድ የዋህና አላዋቂ ፖለቲከኞች አሊያም መሰሪ አስተሳሰብ ያላቸው ወግ አጥባቂ የኦሮሞ ምሁራን እንደሚያስቡት የኦሮሞን ሕዝብ ከፋፍሎ ለማዳከም ታስቦ የሚፈጸም እንደማይሆን ታሳቢ ከተደረገ ጥቅም እንጂ ጉዳት ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም፡፡

ሦስተኛ፤ የአማራ ብሔራዊ ክልልም ቢሆን ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ በሕዝብ ብዛቱም ሆነ በቆዳ ስፋቱ በትልቅነቱ የሚታወቅ በመሆኑ ቢያንስ በኹለት ተከፍሎ ማለትም ምሥራቅ አማራና ምዕራብ አማራ ተብሎ እንደ አዲስ ቢደራጅ የክልሉ ነዋሪ ሕዝብ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆን ካልሆነ በስተቀር በዚህ ምክንያት አንዳችም ጉዳት እንደማይደርስበት አስቀድሞ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን እኮ የክልሉን ስፋትና የሕዝቡን ብዛት ታሳቢ በማድረግ ለሥራ እንዲያመችና የምሥራቅ አማራን ነዋሪ ሕዝብ በቅርብ ለማገልገል ሲባል ደሴና ደብረ ብርሃን ላይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እየተከፈቱ መሆናቸው ይታወቃል፣ በዚህ ረገድ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡

አራተኛ፤ የሶማሌ ብሔራዊ ክልል በሕዝብ ብዛቱ ከሌሎቹ ክልሎች በተለይም ከትግራይ ክልል አንጻር ሲታይ ያን ያህል የተጋነነ ልዩነት የሚያመጣ ባይሆንም በቆዳ ስፋቱ ግን ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ቀጥሎና ከአማራ ክልልም ጭምር ልቆ የሚታይ ስለሆነ በአንድ ክልል ብቻ አጨናንቆ ማቆየቱ የአስተዳደር አመቺነትን የማይፈጥር በመሆኑ ቢያንስ የኦጋዴን አካባቢ ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን በማድረግ ለኹለት ተከፍሎ ቢደራጅ የክልሉ ነዋሪ ሕዝብ በማኅበራዊ ልማትም ሆነ በመልካም አስተዳዳር የተሻለ ተጠቃሚ ይሆን ካልሆነ በስተቀር አንዳችም ጉዳት እንደማይደርስበት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡  

በመጨረሻም አሁን ያሉት ክልሎችም ሆኑ በአዲስ መልኩ የሚደራጁት የክልል መስተዳድሮች ቀደም ሲል በተወሰኑ ቡድኖች የተሳሳተ ስሌት ላይ ተመሥርተው የተፈጠሩት የድንበር ችግሮችና በዚህም ሳቢያ የተከሰቱትን የሕዝብ ቅሬታዎች በጥናት ላይ ተመሥርቶ በዘላቂነት የሚፈታ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ ከወዲሁ መገንዘቡ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ረገድ በትግራይና በአማራ፣ በአፋርና በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ፣ በደቡብና በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በኦሮሚያ እንዲሁም በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል የሚስተዋሉት በድንበር ይገባኛል ላይ ተመሥርተው የተከሰቱት ግጭቶችና በየጊዜው እየቀረቡ ያሉት እውነተኛ የሕዝብ የማንነት ጥያቄዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ እነዚህም ሁኔታዎች ከአድልዎ በጸዳ አኳኋን በሰለጠነና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ በዘላቂነት ሊፈቱ ይገባቸዋል፡፡

የዚህ ዓይነት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ቢደረግ የአገሪቱን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ዕድል የሚፈጥርና የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያበረታታ የሚያስችል አደረጃጀት ስለሚሆን እንደተሻለ አማራጭ መታየት ይኖርበታል፡፡ እንደተለመደው የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦችን ለመከፋፈል ከመፈለግ የሚመጣ የጠባቦች ወይም የትምክህተኞች ሴራ ነው የሚለውንና ላለፉት በርካታ ዓመታት ጉንጭ አልፋ ሆኖ የቀጠለውን የተለመደ አድካሚ ክርክር ወደ ጎን ትተው ሁኔታውን እንደገና ቢያጤኑት እጅግ ጠቃሚ መሆኑ የሚቀር አይመስለኝም፡፡

በመሆኑም ከነባሮቹ ዘጠኝ (አሁን ዐሥር) ክልሎች ላይ አምስት ወይም ስድስት አዳዲስ ክልሎችን በመጨመር አገሪቱ ከዐሥራ አምስት በማይበልጡ ክልሎች እንደገና እንድትደራጅ ቢደረግ፣ ቀደም ሲል በአገሪቱ ከነበሩት አደረጃጀቶች አንጻር ሲታይ ያን ያህል የተጋነነ ለውጥ የሚያመጣ ካለመሆኑም በላይ፣ አስተዳደራዊ ወጪውም ቢሆን ከሚያስገኘው ማኅበራዊ ፍትሕና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ሲታይ ያን ያህል የሚከብድ አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነቱ አደረጃጀት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የቆየ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በተሟላ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ ከመሆኑ አንጻርም ሲታይ የሚያስከትለው ተጨማሪ አስተዳደራዊ ወጪ ከዚህ ግባ የማይባል ነው የሚሆነው፡፡

አደረጃጀቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት የሚቀርፍና ለሕዝቦቹም ማኅበራዊ ፍትሕን የሚያስገኝ በመሆኑ፣ የገዥው ፓርቲ መሪዎች ትልቅ ቦታ ሰጥተው እንደገና ቢያጤኑትና ለተግባራዊነቱም አበክረው ቢንቀሳቀሱ ለራሳቸው ህልውናም ሆነ ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዘላቂ ጥቅም ፋይዳው እጅግ የጎላ መሆኑንን በቅጡ በመገንዘብ ጭምር አንዳንድ አድርባይና አስመሳይ የብሔር ፖለቲከኞች እንደሚሉት የአገሪቱ አንድነትም ሆነ የሕዝቦች ህልውና ይበልጥ አደጋ ላይ የሚወድቅበትም ሆነ ከአሁኑ የባሰና አላስፈላጊ የሚባል አስተዳደራዊ ወጪ የሚያስከትልበት ሁኔታ አይፈጠርም፡፡

ይልቁንም አሁን ላይ ይበልጥ እየተስፋፋ የመጣውን ሙስና በጽናት ታግሎ በማስቆምና የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ መልሶ በሁሉም መስኩ የሕዝብን ተሳትፎ በአግባቡ ማሳደግ የሚቻልበትን አሠራር ቀይሶ መንቀሳቀስ ከተቻለ፣ በአንድ በኩል የተወሰኑ ክልሎች በመጨመራቸው ምክንያት በተወሰነም ቢሆን የሚያድገውን አስተዳደራዊ ወጪ ማካካስ የሚቻልበትን ሁኔታ በመፍጠር፣ በሌላ በኩል ደግሞ መልካም አስተዳደርን በማስፈንና ማኅበራዊ ፍትሕን በማንገስ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የያገባኛል ስሜትን እንዲፈጥር በማድረግ አላስፈላጊ ወጪዎችንና አሁን ላይ በግልጽ እየታየ ያለውን የቅንጦት መኪኖችንና የቢሮ ዕቃዎችን በየዓመቱ የመቀያየሩን ሒደት በማስቆም እንዲሁም እንደ ወረርሽኝ አገሪቱን እያጥለቀለቀና እንደ ሰደድ እሳት ሀብቷን እየለበለበ የሚገኘውን ልቅ የሙስና ድርጊት ጠንክሮ በመዋጋት የበጀት ጫናውን በዘላቂነት እያቃለሉ መሄድ እንደሚቻል የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በጽናት ያምናል፡፡        

(Visited 71 times, 1 visits today)
June 10, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo