Articles, Economy, ኢኮኖሚ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወቅታዊ ሁኔታ (አንዳንድ ነገሮች) -በኀይሉ ደሬሳ

የተበላሸ ብድር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በነበራቸው የምክር ቤት ቆይታ ለረጅም ዓመታት ሲንከባለል የነበረውን የተበላሸ የብድር መጠን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለማስተካከል እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ በተለይም የንግድ ባንክ ላይ ተጠራቅሞ የነበረው የተበላሸ የብድር መጠን ከፍተኛ ነበር፡፡ ባንኩ የመንግሥት እንደ መሆኑ መጠን  85 በመቶ ገደማ  ብድሩ ለመንግሥት ተቋማት የተሰጠ ነው፡፡ የንግድ ባንክን የተበላሸ የብድር መጠን ለማስተካከል የተበዳሪዎቹን ተቋማት ጤናማነት መመዘኑ እና አቅማቸውን ማሳደጉ  አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ባለው ስሌትም አብዛኛዎቹ ተቋማት ጥሩ ይዞታ ላይ እንዳሉ ነው የሚታሰበው፤ ከዚህ ቀደም የወሰዷቸውን ብድሮች ይመልሳሉ የሚል ግምት በመንግሥት በኩል አለ፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ ሊያሳስብ የሚችለው የተቋማቱ ቀጣይነት እና ብድሩን እንዴት አድርገው ይከፍላሉ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

በልማት ባንክ ላይ ያለውን የተበላሸ ብድር መጠን ለማሻሻል በጥናት ላይ የተመሠረተ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ እነዚህ ማሻሻያዎች ያለውን ችግር ይፈቱታል የሚል ተስፋ ተጥሏል፡፡ አንዳንዴም ብድሩ አይመለስም ተብሎ ተስፋ ከተቆረጠ ብድሩ እንደ ኪሳራ ተቆጥሮ  ከተበላሸ ብድር ውስጥ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት ሪፖርቶች ውስጥ የተሰረዘው የተበላሸ ብድር ላይታይ ይችላል፡፡ ልማት ባንክ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ እነዚህን ነገሮች አብሮ እንዳደረገ ነው የሚሰማኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በግልጽ የትኛውን መንገድ  እንደተከተሉ  አላስቀመጡም፡፡  

በቀጣይ በልማት ባንክ በኩል የሚያሳስበው፤ ባንኩ እንዴት ያልተቋረጠ የገንዘብ ምንጭ ያገኛል የሚለው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የሚያበድረገውን ገንዘብ ከግል ባንኮች በሚገኝ የብሔራዊ ባንክ ሰነድ (N-Bill) ነበር የሚሸፍነው፡፡ እሱ የባለፈው ዓመት ላይ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ የልማት ባንክን የገንዘብ ምንጭ ለመወሰን የተለያዩ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው የሚገኘው፡፡ ከምክረ ሐሳቦች መሀከል ቦንድ አዘጋጅቶ በመሸጥ የፋይናስ ወጪውን መሸፈን፣ የብሔራዊ ባንክ ሰነድን በተወሰነ መልኩ ማሻሻያ ተደርጎበት እንዲመለስ ማድረግ፣ የውጭ ፈንድ ማፈላለግ የሚሉ ይገኛበታል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ውሳኔ ላይ የተደረሰበት ነገር የለም፡፡ የሆነ ሆኖ አዳዲስ ምክረ ሐሳቦችም ተካተውበት በቀጣይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ይኖራሉ፡፡

የ2013 ዓ.ም. በጀት

በ2012 ዓ.ም. የተያዘው በጀት ባለመብቃቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጨማሪ 28 ቢሊዮን ብር በጀት እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡ በጀቱ በዚህ ደረጃ ሊያብጥ የቻለው የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ከዕቅድ ውጪ የሆኑ ሥራዎች በመኖራቸው ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ የመንግሥት ግብረ መልስ የሚያስፈልጋቸው ሥራዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሥራዎች በጀቱ ከታሰበው በላይ እንዲለጠጥ አድርገዋል፡፡ ቀድሞም በጀቱ ሲያዝ የበጀት ጉድለት ነበረበት፤ ነገር ግን በተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ እና በተገኙ ብድሮች በጀቱን ለማሟላት ተሞክሯል፡፡

ለ2013 ዓ.ም. የበጀት ዓመት 476 ቢሊዮን ብር (ለግማሽ ትሪሊዮን ተጠጋ ገንዘብ) ለመበጀት ረቂቅ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ ይህኛም ከአምናው ሰፋ ያለ የበጀት ጉድለት ሊገጥመው እንደሚችል ተገማች ተደርጓ መፍትሔ ሐሳቦች አብረው ተቀምጠዋል፡፡ አንደኛው በዘንድሮ ዓመት ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ሊገኙ የሚችሉ ድጋፎች መጠቀም መቻል ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ላይ በርካታ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት የገንዘብ አሰባሰብና አወጣጥ (ፊስካል) ፖሊሲያቸውን ለቀቅ አድረገው ድጋፎችን እየሰጡ ነው፡፡ ሌላው የገንዘብ-ነክ (ሞኒተሪ) ፖሊሲውን በማያናጋ መልኩ መንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ከብሔራዊ ባንክ በመግዛት በጅቱን መሙላት ነው፡፡ መንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ከብሔራዊ ባንክ ሲገዛ ገንዘብ በኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ያለ በመሆኑ የከፋ የዋጋ ንረት ላያመጣ ይችላል የሚሉ ግምቶች ተወስደዋል፡፡ ነገር ግን ረቂቁ ገና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው የፀደቀው፡፡  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊሻሻሉ የሚችሉ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡

የጥሬ ገንዘብ ኖት ለውጥ

የባንኮች ማኅበር ከሳምንታት በፊት ከባንክ ሥርዓት ውጪ የሆነ 113 ቢሊዮን ብር መኖሩን ጠቅሶ የገንዘብ/ብር ኖት ለውጥ ቢደረግ  የሚል ምክረ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ማኅበሩ እንደ ሐሳብ ቢሆን የሚለውን ምክር መስጠት ይችላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን  ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ኖትን ለማቀየር ሐሳብ የለውም፡፡ የጥሬ ገንዘብ ኖት ረጅም ጊዜ ያገለግላል ተብሎ የሚገመት ነው፡፡ አዲስ ኖት ማሳተሙም እጅግ በጣው ውድ ነው፡፡ አንድ ነገር ለማስተካከል ተብሎ ሁሉንም ነገር መቀየር ያለበት አይመስለኝም፡፡ በጊዜ ሂደት መሠራት ያለበት የጥሬ ገንዘብ አስፈላጊነትን መቀነስ ነው፡፡

እዚህ ላይ፣ የጥሬ ገንዘብ ኖት መቀየር የሚሰጠው ጥቅም ምንድን ነው የሚለው ጉዳይ በአግባቡ መታየት ያለበት፡፡ ማኅበሩ የጥሬ ገንዘብ ኖት ቢቀየር ሰው ገንዘብን ወደ ባንክ ያመጣል የሚል እሳቤ ነው ያለቸው፡፡ ነገር ግን ለውጥ ቢደረግም ገንዘብ የራሳቸው እስከሆነ ድረስ ዳግም ከባንክ ለውጠው ማውጣት ይችላሉ፡፡ አሁን ገንዘብ አስቀመጡ የሚባሉትም አካላት ቢሆኑ ገንዘቡን ያስቀመጡት ሊጠቀሙበት ነው የሆነ ቀን ወደ ባንክ ማምጣታቸው አይቀርም፡፡  ያኔ ባንኮችን የገጠማቸው የገንዘብ እጥረት ይፈታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን ብሔራዊ ባንክ እየሠራ ያለው የኤሌክትሮኒክሱን ገንዘብ ዝውውር በማሳደግ ጥሬ ገንዘብ መያዝ የሰዎች ምርጫ እንዳይሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ አሁን ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ ዝውውር እንዲፈፀም ተደርጓል፡፡ በቀጣይ የግል ባንኮችም ሁሉንም ማስተናገድ የሚችሉ የፖስ ማሽን እንዲጠቀሙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች በአግባቡ ከተሠሩ ጥሬ ገንዘብ (ካሽ) መያዙ ያን ያህል አንገብጋቢ ላይሆን ይችላል፡፡ ሰው በራሱ ጊዜ ገንዘብን ወደ ባንክ ያመጣዋል፡፡

(Visited 63 times, 1 visits today)
June 15, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo