Articles, Politics, World News, ሐተታ, ኢኮኖሚ

የሶማሌ ክልል ልኂቃን ወደ ማዕከል መምጣት-በፋሲል ኑርልኝ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምርምር ያደረጉት ግሪካዊ ፕሮፌሰር ጆን ማርካኪስ “Ethiopia: The Last two Frontiers” በሚለው መጽሐፋቸው የሶማሌንና የአፋርን ክልሎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ጽፈዋል፡፡ ፐሮፌሰር ማርካኪስ እንደሚሉት እነዚህ ኹለት ክልሎች በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት እና/ወይም በአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ያላቸው ተሳትፎ አናሳ መሆኑ ለአገረ መንግሥቱ ህልውና ጠንቅ በመሆኑ በፍጥነት መስተካከል ያለበት ነው፡፡

እውነትም በእነዚህ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች የአገሪቱን ህልውና ጠብቆ በማቆየት ረገድ ከማንም ያላነሰ ሚና እያላቸው ፍትሐዊ የሆነ የፖለቲካ ተሳትፎ ኖሯቸው አያውቅም፡፡ ለአብነት ያህል የሶማሌ ብሔር በአገሪቱ በሕዝብ ብዛት በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም የሚገባውን ያህል የፖለቲካ ውክልና ኖሮት አያውቅም፡፡ በዚህ ምክንያት በሶማሌ ልኂቃን ዘንድ ከፍ ያለ የመገፋት ስሜት ስለነበር ሁልጊዜም ከማዕከላዊ መንግሥቱ አንጻር ተቃራኒ የሆነ አቋም የሚያራምድና ማዕከላዊ መንግሥቱን የሚታገል የታጠቀ ኀይል በአካባቢው ጠፍቶ አያውቀም፡፡ በነበረው የሰላም እጦት ምክንያትም አካባቢው ከልማት ተገልሎ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጅ ይህ የኹለቱ ክልሎች ሕዝቦች የፖለቲካ ተሳትፎ ማነስ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሻሻለ የመጣ ይመስላል፡፡ የሶማሌ ክልልን ሁኔታ ብቻ ነጥለን ብናይ ክልሉ በተነጻጻሪ የተሻለ አመራር አግኝቷል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት በክልሉ ከወትሮው የተሻለ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኗል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ከተመሠረተ ወዲህ ደግሞ የሶማሌ ክልል ተወካዮች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ ከብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ውስጥ 40 ያህሉ የሶማሌ ክልል ተወካዮች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በፌደራል መንግሥት ደረጃም ቢሆን፣ አቶ አሕመድ ሽዴ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር፣ ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሒ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር፣ ዶ/ር አብዲዋሳ መሐመድ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ የዘርፍ ኀላፊ (?)፣ ከሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አደም ፋራህ የኢፌዴሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ተሰይመዋል፡፡ ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች አሉ፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ፍትሐዊ የፖለቲካ ውክልና የሚያረጋግጥ ጎዳና ይበል የሚያሰኝ እና ለኢትዮጵያን አገረ መንግሥት ከማዘመንና ከማጠናከር አንጻር ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት በግድም ተመሠረተ በፈቃደኝነት ለበርካታ ዘመናት ህልውናውን ጠብቆ እንደቀጠለ ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ድንበሯ የታወቀ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለረዥም ዘመናት ዕውቅና ያላት ብቻ ሳይሆን የበርካታ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች መሥራች ከሆኑ ጥቂት አገሮች አንዷ የሆነች አገር አለችን፡፡ የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ትልቅ ነው፡፡ የሕዝቧ ብዛትም ከአፍሪካ በኹለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ትልቅ ሀብትና ፀጋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጎደላት ሁሉንም ዜጎቿንና ሕዝቦቿን በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ አገራችን የጎደላት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሽግግር ነው፡፡

ፍትሐዊ የፖለቲካ ውክልና ካለ፤ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚኒት ከነገሠ፤ ሁሉም ዜጎችና ሕዝቦች በእኩልነት የሚኖሩበት ሥርዓት ከተመሠረተ ኢትዮጵያ ለሌሎች አብነት የምትሆን አገር ትሆናለች፡፡ ይህ ደግሞ የሚቻልና መሆን ያለበት ነገር ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኀይሎች ከአግላይ የቡድንና ዘውግ-ተኮር አጀንዳ ወጥተው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነጻ በሚያወጡና ተጠቃሚ በሚያደርጉ አጀንዳዎች ላይ ቢረባረቡ ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡ አገሪቱ ከዘመኑ ጋር የዘመነ የፖለቲካ ሥርዓት ካላት እና የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ሽግግር ከመጣ እንኳንስ ለራሷ ዜጎች ለሌሎችም የምትተርፍ አገር ናት፡፡

(Visited 18 times, 1 visits today)
June 15, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo