Articles, News, Politics, ሕግ, ፖለቲካ

ወገንተኝነት የተጫነው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጥናት ሪፖርት-በበላይነው አሻግሬ (ጠበቃና የሰብአዊ መብት ባለሙያ)

“አምነስቲ አንተርናሽናል” ዓለም ዐቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንደሆነ  ይታወቃል፡፡ ድርጅቱ በዓለም አገሮች ሁሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እየመረመረ የጥናቱን ውጤት ለአገራቱ፣ ለሚመለከታቸው አህጉራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ተቋማት ያሳውቃል፤ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ አምነስቲ በተለይ የሚታወቀው አምባገነን መንግሥታት የሚፈፅሙትን ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ያጋልጣል፡፡

በጠቅላላው አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደ ዓለም ዐቀፍ ተቋም፣ በተለያዩ አገሮች ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንደሚያቀርብ ተቋም፣ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚጠበቅ ከፍ ያለ የገለልተኝነት መለኪያ አለ፡፡ አምነስቲን በዚህ ደረጃ የምንጠብቀው በሁሉም አገሮች እኩል ዓላማ ያለው ዓለም ዐቀፍ ድርጅት እና ለመንግሥታትም ሆነ ለተወሰኑ ቡድኖች ጥቅም ያደረ አይደለም ተብሎ ስለሚገመት ነው፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች የምንመዝነው በዚህ ሚዛን ነው፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከጥር 2019 እስከ ታኅሣሥ 2019 ድረስ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ አጥንቻለሁ ብሎ ባለ 50 ገጽ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ የአምነስቲ ሪፖርት ትኩረት ያደረገው 1ኛ) በኦሮሚያ ክልል በምዕራብና ምሥራቅ ጉጂ ዞኖች በመከላከያ ኀይል፣ በኦሮሚያ ፖሊስ እና በአካባቢው ሚሊሻ አማካኝነት የተፈፀሙ ግድያዎች፣ ሕገ-ወጥ እስር፣ የሴቶችን መደፈር የተመለከተ ሲሆን 2ኛ) በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በአማራና ቅማንት ማኅበረሰቦች መካከል በተከሰተው ግጭት ሳቢያ በክልሉ ልዩ ኀይል፣ የአካባቢ ሚሊሻ እና ፋኖ አማካኝነት በቅማንት ማኅበረሰቦች ላይ ግድያና መፈናቀል ደርሶባቸዋል የሚል ነው፡፡

ይህን የአምነስቲ ሪፖርት መሠረት በማድረግ መንግሥት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ሌሎችም አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡ ለምሳሌ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት በ2019 እ.ኤ.አ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ በምሉዕነት የሚይዝ አይደለም፤ የተቋሙ ኀላፊዎችም ሆነ ተመራማሪዎች፣ የጥናት ውጤቱም ፍጹም ወገንተኝነት የታየበት ነው በማለት ጠንካራ ተቃውሞ አሰምቷል፡፡ ጌታሁን ሔራሞ ደግሞ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚያወጣው የሰብአዊ መብት ሪፖርት ከመንግሥት ውጭ ባሉ አካላት የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያካትት አይደለም ብለው ተችተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጥናት ውጤት ጉድለት ቢኖርበትም ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ውድቅ ልናደርገው አይገባም የሚል አስተያየት ሲሰጡ ተሰምቷል፡፡ እኔ በበኩሌ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያቀረበውን የጥናት ውጤት በተመለከተ ያለኝን ትችት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

የአምነስቲ የጥናት ውጤት የአንድ ዓመት ሪፖርት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን የጥናት ውጤቱ ኢትዮጵያ ያለችበትን የሰብአዊ መብት አያያዝ ሩብ እንኳ የሚገልጽ አይደለም፡፡ በዚህ በኩል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቅ (አብን) ካወጣው ሪፖርት ጋር እስማማለሁ፡፡ አገራችን ግፍ ሲፈጸምባት የከረመች አገር ናት፤ ምናልባት ከግፉ ብዛት አንጻር ለመዘርዘር ሁሉ ጊዜም መዝግበን እና ሰነድ አደራጅተን ማስቀመጥ ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን ፈጽሞ የማንዘነጋቸው ጉዳዮች አሉ፡፡

ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ ከሐምሳ ሺሕ በላይ የአማራ ተማሪዎች ተፈናቅለው ይገኛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ደረጃ ወርደው ታይተዋል፡፡ ምናልባት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተፈናቀሉበት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ታሪክ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ እ.ኤ.አ በ2019 ከመስከረም ወዲህ የታየ ክስተት በመገናኛ ብዙኃንም ተነግሮ መፍትሔ አጥቶ የከረመ ጉዳይ ነው፡፡ (የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ የተፈናቀሉትንም፣ ሲማሩ የነበሩትንም፣ ዩኒቨርሲቲዎችንም፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርንም፣ ግድ የለሹን መንግሥትም እኩል አደረጋቸው፡፡) ትምህርት የመማር መብት ማጣት ከባድ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ በዚያ መሃል የተገደሉ፣ የተደፈሩ፣ ታፍነው የተሰወሩ፣ በርካታ ተማሪዎች አሉ፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት የኢትዮጵያን ሁኔታ በሙሉ የሚገልጽ አይደለም፡፡

እዚህ ላይ ግን የአገራችን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አጥንቶ ያሳየናል ከሚል ጠባቂነት አይደለም፡፡ ነገር ግን የአንድን አገር ዓመታዊ ሪፖርት አጥንቻለሁ ከሚል ተቋም ግን የሚጠበቅ ከአንስተኛ መጠን በታች ሆኖ ስላየሁት ነው፡፡

ሌላው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት መሠረታዊ ችግር በሰሜን ጎንደር ዞን ያለውን ሁኔታ የገለጸበት መንገድ ነው፡፡ ወገንተኛ ሪፖርት ያልኩትም ከዚሁ በመነሳት ነው፡፡ የአምነስቲ ሪፖርት በሰሜን ጎንደር ያለውን ሁኔታ “Inter-communal violence between the Amhara and Qimant” ወደ አማርኛ ሲተረጎም “በአማራና ቅማንት ማኅበረሰቦች መካከል የተፈጸመ ጥቃት” በሚል ነው በተደጋጋሚ የገለጸው፡፡ ይህ አገላለጽ ፈጽሞ ተገቢነት የሌለው ነው፡፡ ምክንያቱም፣

1ኛ) አማራና ቅማንት እንደ ማኅበረሰብ አልተጣሉም፡፡ ጉዳዩ የኹለቱ ማኅበረሰቦች መጠቃቃት አይደለም፡፡ ታዲያ አምነስቲ ከየት አምጥቶ ነው “በአማራና ቅማንት ማኅበረሰቦች መካከል የተፈጸመ ጥቃት” ለማለት የተነሳው? በኹለቱ ማኅበረሰቦች መካከል በሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች አካባቢ ስለነበረው ጉዳይ በተለይ በአዲስ አበባና በጎንደር ከተሞች ውይይት ተደርጎ በብዙኃን መገናኛ ሲቀርብ አይተናል፡፡ በየትኛውም ሕዝባዊና የምሁራን ውይይት ላይ በአማራና በቅማንት መካከል የተፈጸመ ጥቃት ስለመኖሩ የተገለጸም ሆነ ያሳሰበ ጉዳይ አይደለም፡፡

በሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተፈጠረው ችግር “የቅማንት ኮሚቴ” የሚባለው አካል ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በፈጠረው ግብ ግብ ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ፖለቲካዊ ፍትጊያ አማራም ሆነ ቅማንት ሁሉም በደል ደርሶበታል፤ ነገር ግን አንዱ አንዱን አላጠቃም፡፡ ዋናው ጉዳይ ይህ ሆኖ እያለ ነገር ግን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት “በአማራና በቅማንት መካከል በተፈፀመ ግጭት በቅማንት ላይ ጥቃት ተፈፀመ” በሚል ስሁት መነሻ አማራና ቅማንት ወደ ግጭት እንዲገቡ የሚቀሰቅስ ይዘት ያለው ነው፡፡ ይህ የአምነስቲ ሪፖርት አንዳንድ ጦርነትና ግጭት በይፋ እንደሚቀሰቅሱ ብዙኃን መገናኛዎችና አክቲቪስቶች ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ አምነስቲ ገለልተኛ ቢሆንማ ኖሮ በሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ስንት በደል የደረሰባቸው አማሮች በጥናቱ ላይ ዘርዝሮ ባካተተ ነበር፡፡ ለማንም አልወግንም የሚል ተቋም ማንንም ሳይነጥል የደረሰበትን የሰብአዊ መብት ጥሰት ማሳወቅ ይገባው ነበር፡፡

2ኛ) “በአማራና ቅማንት ማኅበረሰቦች መካከል የተፈፀመ ጥቃት” የሚለው አገላለጽ በጥናቱ ዘዴ፣ በጥናቱ ውጤት እና በመደምደሚያው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮበታል፡፡ የጥናት ዘዴው አንድ ማኅበረሰብ ላይ ደረሰ የሚለውን ችግር ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ የጥናት ዘዴው ትክክል ካልሆነ ደግሞ ውጤቱም በዚያው ልክ የጠበበ እና ስሁት ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ያደርገዋል፡፡

ቅማንትን በተመለከተ የሆነውንም ያልሆነውም እየደረቱ የሚያራግቡት እነማን እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ብዙ ጊዜ የቅማንት ጉዳይ ያገባናል ብለው የጦር መሣሪያ፣ የገንዘብ፣ የሰው ኀይል ድጋፍ እያደረጉ በጎንደር አካባቢ ጸጥታና ሰላም እንዳይሰፍን የሚበጠብጡ አካላት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የነዚያ ቡድኖች ድምጽ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡

የክልል ልዩ ኀይሎችን በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከአሁን በፊት በሱማሌ እና ኦሮሚያ ልዩ ኀይሎች አማካኝነት የተፈጸሙ በደሎችን ማውገዙን ጠቅሷል፡፡ አሁን ደግሞ የአማራ ክልል ልዩ ኀይልን አውግዟል፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ በአማራ ልዩ ኀይሎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመጥቀስ አልደፈረም፡፡ አምነስቲ መንግሥት የሚፈጽመውን እንጅ በመንግሥት አካላት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት አይመለከትኝም ያለ ይመስላል፡፡ የክልል ልዩ ኀይሎችን በተመለከተ መንግሥት በአገር ዐቀፍ ደረጃ ሁሉም ክልሎች በእኩል እንዲያቆሙ ማድረግ ይኖርበታል፤ ይህ ሕጋዊ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በየጊዜው እየነጠለ ልዩ ኀይሎችን ከሚያወግዝና እኛም ይህን ከምንጠባበቅ መንግሥት አንድ ወጥ አገራዊ መዋቅር ቢያዘጋጅ ጥሩ ነው፡፡ ይህ የማንም ኀላፊነት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብና የመንግሥት ጉዳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት የምንቀበለው ውጤት እንዳለ አይካድም፡፡ በተለይ መንግሥት ሕዝብን የመጠበቅ አለበት፣ በመከላከያ እና በፖሊስ አባላት የሚፈጸሙ ግድያዎች መቆም አለባቸው፣ የሕዝቡን ሰላም እና ደኅንነት መጠበቅ አለበት፣ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ላይ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ማንኛውም ዓይነት ጥቃቶች ይቁም፣ የሚሉትን ሐሳቦች ሁሉም የሚጋራቸው ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

ከምንም በላይ ግን የሰብአዊ መብቶችን ጉዳይ ዘብ ሊቆምለት የሚገባው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንደሆነ እና የሰብአዊ መብት ተቋማት ያለ ምንም ፍርሃትና አድርባይነት ከሕዝቡ ጎን ሊቆሙ ይገባል እላለሁ፡፡

(Visited 60 times, 1 visits today)
June 10, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo