Articles, News, ሐተታ

ወደፊት እንራመድ!-በዳንኤል ክንዴ (ዶ/ር)

እ.ኤ.አ. ኅዳር 7 ቀን 1987 “የሕይወት ዘመን ፕሬዚዳንት” ሲባሉ የነበሩት የቱኒዚያው የቀድሞ መሪ ሀቢብ ቡርጊባ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤን አሊ የተገለበጡበት ቀን ነው። ቤን አሊ “ሕገ መንግሥታዊ መፈንቅለ መንግሥት” የሚል ስያሜ ባተረፈው ደም ያላፋሰሰ ሒደት፣ የርዕሰ መንግሥትነቱን ሥልጣን በጨበጡ ማግስት በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታታቸውም በላይ፣ ቱኒዚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ኀይሎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ከባቢ እንደሚፈጠርና አገራቸው አዲስ የፖለቲካ ጎዳና እንደምትጀምር አብስረው ነበር።

ይህንን የፕሬዚዳንት ቤን አሊን እርምጃ ተከትሎ ከእስር የተፈቱት ዝነኛው ምሁርና ፖለቲከኛ ረሽድ ጋኑሺም እሳቸውና የትግል ጓዶቻቸው ቤን አሊ የጀመሩትን የፖለቲካ ሒደት እንደሚደግፉ፣ ይልቁንም ቀደም ሲል እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ተከልክሎ የነበረው ‹አል ናህዳ› የተሰኘው ፓርቲያቸው የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ ተጠቅሞ እንደሚንቀሳቀስና የሒደቱ አካል እንደሚሆን ገለጸው ነበር።

ወቅቱ ሁሉም በወደቁት ፕሬዚዳንት ላይ የሚረባረብበት፣ በአገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ስለመከፈቱ የሚገልጽበት፣ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ባልተለመደ ሁኔታ የሚከባበሩበት፣ የሚደናነቁበትና ሁሉም በተስፋ የተሞላበት ወቅት ነበር። ችግሩ፣ ይህ ሁሉ የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ ብሩኅ ተስፋ ብዙም አልቆየም። የ‹አል ናህዳ› የፖለቲካ እንቅስቃሴና ድርጅቱ በሕዝቡ ዘንድ ማግኘት የጀመረው ድጋፍ ያሰጋቸው ቤን አሊ፣ ብዙም ሳይቆዩ በንቅናቄው ላይ የተለያዩ የእመቃ እርምጃዎችን መውሰድና የድርጅቱን አባሎች ማሰርና ማሳደድ ጀመሩ። ከዚህም በላይ እ.ኤ.አ. ሚያዚያ 1989 በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ የድርጅቱ አባላት በግላቸው ካልሆነ በስተቀር፣ ድርጅታቸውን ወክለው መወዳደር እንደማይችሉ ተገለጸ፤ ድርጅቱም በምርጫው እንዳይሳተፍ ዕቀባ ተደረገበት። ሆኖም የንቅናቄው አባላት ተስፋ ሳይቆርጡ በግለሰብ ደረጃ ተወዳድረው ራሱ የቤን አሊ መንግሥት ባመነው መሠረት 14 በመቶ ድምጽ ማግኘት ቻሉ።

ውጤቱና የንቅናቄው አካሔድ ለቤን አሊ መንግሥት የሚዋጥ አልሆነም። ስለሆነም ይህ የ‹አል ናህዳ› ግስጋሴና የሕዝብ ድጋፍ ያሰጋው መንግሥት፣ ንቅናቄውንና የንቅናቄውን አባላት አንዴ እስላማዊ መንግሥት ሊመሠርቱ ይንቀሳቀሳሉ እያለ እየወነጀለ፣ ሌላ ጊዜ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየከሰሰ ብዙዎችን ወደ እስር ቤት ወረወራቸው። በክስ ላይ ክስ እየተደራረበባቸው በጽናት ሲታገሉ የቆዩት ጋኑሺም የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው ከሰኔ 1989 በኋላ ወደ ለንደን ለመሰደድ ተገደዱ። በሌሉበት የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ረሽድ ጋኑሺ፣ በስደት ሆነው የንቅናቄው መሪና አገር ውስጥ የሚደረገው ትግል ዋና አንቀሳቃሽ (የመንፈስ መሪ) ነበሩ። አገር ቤት ካለው ሕዝብና ከድርጅታቸው አባላት ጋር ያላቸው ግንኙነትም ጠንካራ ነበር።

እ.ኤ.አ ከ1990 ጀምሮ በየጊዜው እየተቀሰቀሰና በመንግሥት እየተመታ የቀጠለው የቱኒዚያ ወጣቶች ተቃውሞ ለኹለት ዐሥርት ዓመታት ውጤት ማምጣት ባይችልም፣ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2010 መገባደጃ ላይ ዓለምን ባስደመመና ለሌሎች የዐረብ አብዮቶች በር ከፋች በሆነ ሰላማዊ ተቃውሞ የቤን አሊን አገዛዝ ለማስወገድ በቅቷል። የቤን አሊን አገዛዝ መወገድ ተከትሎ ወደ አገራቸው የተመለሱት ጋኑሺ፣ በቱኒዚያ የፖለቲካ ሽግግር ላይ ትልቅ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። ስደተኛው ጋኑሺ ወደ አገራቸው ሲመለሱ፣ አሳዳጁ ቤን አሊ ከአገር ተባረሩ። አሳዳጁ ተሳዳጅ የሚሆንበት እና ተሳዳጁ መልሶ አሳዳጅ የሚሆንበት የጥፋት አዙሪት – አስቀያሚው የአፈና አገዛዝ ትሩፋት!

ቤን አሊ መፈንቅለ መንግሥት ባደረጉ ማግስት አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ እንዳሉት ሁሉ፣ በአገራችንም የደርግ አገዛዝ ወድቆ የሽግግር መንግሥት በተመሠረተበት ወቅት ብዙ ብዙ ተብሎ ነበር። ስለ አዲሲቱ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ምሥረታ፣ ስለ መድበለ ፓርቲና መድበለ ሐሳብ ሥርዓት ግንባታ፣ ስለ ሕግ የበላይነት፣ ስለ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ወዘተ… ያልተባለ በጎ ነገር አልነበረም።

በወቅቱ ልክ እንደቱኒዚያ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች የተፈቱ ሲሆን፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ ብዙ ወገኖችም በታላቅ ተስፋ ወደ አገራቸው ተመልሰው ከመንግሥት ጋር መሥራት ጀምረው ነበር። ሆኖም በእኛም አገር ተስፋው ለብዙ ጊዜ አልቆየም። ሁኔታዎች በሒደት እየተፈተሹ ሲመጡና አሸናፊው ኀይል እንደሚለው ልዩነትን እንደማያከብርና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ያለው ቁርጠኝነት በጣም ደካማ መሆኑ ግልጽ ሲሆን፣ በሽግግር መንግሥቱ ተሳታፊ የነበሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ራሳቸውን ከሒደቱ ማግለል ጀመሩ። አንዳንዶችም ከሒደቱ በግፊት እንዲወጡ ተደረገ። በ1992 የመጀመሪያው ብሔራዊ ምርጫ ተቃዋሚዎች ያልተጠበቀ የምክር ቤት ወንበር ማግኘታቸው፣ በተለይ ደግሞ በምርጫ 97 መንግሥትን ያስደነገጠ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘታቸው ያልተዋጠለት አገዛዙ፣ የዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚፈጠርበትን ዕድል ዘጋው። በሒደቱ ተሳታፊ የነበሩ ፖለቲከኞችን ማሰርና ማሳደደ የተለመደ ሆነ። በዚህ ምክንያት በሰላማዊ ትግሉ ተሳታፊ የነበሩት ወገኖች፣ ሌላ መንገድ መቀየስ ጀመሩ። ከውጭም ከውስጥም በተደረገ ጥረት ለውጥ መጣ፡፡ ግን አሁንም ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡

አሁንም ሌላ ዙር አመጽ?

በየካቲት 66ቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ላይ የጻፉ ምሁራን እንደሚገልጹት የዐፄ ኀይለ ሥላሴ መንግሥት በሐሳብ የተበለጠውና ውድቀቱ የተፋጠነው የኢትዮጵያ ተማሪዎች “መሬት ላራሹ!” የሚለውን ዝነኛ መፈክር ካነገቡ በኋላ ነው። መሬት ላራሹና ሌሎች ጥያቄዎች፣ በተለይም  የሕዝቦች እኩልነትና የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄዎች ከተነሱ እነሆ ግማሽ ክፈለ ዘመን ተቆጠረ። ሆኖም ከእነዚህ ግንባር ቀደም ጥያቄዎች ውስጥ ብዙዎቹ አሁንም በቂ ምላሽ አላገኙም። ይልቁንም እነዚህ በውዝፍነት ያደሩ የሕዝብ ጥያቄዎች ሌሎች ተጨማሪ ጥያቄዎችን እየወለዱ በመቀጠላቸው ምክንያት አገራችን አሁንም ወደ ሌላ ግጭት ልትገባ ብቻ ሳይሆን ህልውናዋም ፈተና ላይ ሊወድቅ የሚችልበት ዕድል እየታየ ነው። 

አብዮት ለምን፣ መቼና እንዴት ይከሰታል? የአብዮት መሠረታዊ ባህርያትስ ምንድን ናቸው? ወዘተ… የሚሉት ጥያቄዎች በአብዮት ጉዳይ ላይ የሚጽፉ ምሁራንን በሰፊው ሲያከራክሩ የቆዩ ትላልቅ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው። በምሁራኑ መካከል የሚደረጉት ክርክሮች አሁንም መቋጫ አላገኙም፤ ወይም የሚያገኙ አይመስሉም።

ክሬን ብሪተን (Crane Briton) የተባለው በዚህ ዘርፍ ጥልቅ ምርምር ያደረገ ምሁር፣ The Anatomy Of Revolution በሚለው መጽሐፉ የሩሲያውን የጥቅምት አብዮት ጨምሮ ሌሎች ትላልቅ (ክላሲካል) አብዮቶች በሰባት ጉዳዮች ላይ ተመሳስሎሽ እንዳላቸው ገልጿል። እነኝህ አብዮቶች በተከሰቱባቸው አገራት (ሀ) ኅብረተሰቦች ከቀደመው ጊዜ ይልቅ መሻሻሎች (ለውጦች) በማሳየት ላይ ነበሩ፤ (ለ) በኅብረተሰቡ መሀከል ግልጽ የሆነ የመደብ መቃቃር ነበር፤ (ሐ) ገዥ ኀይሎች ወይም መንግሥታት ደካማ (አቅመ ቢስ) ሆነው ነበር፤ (መ) ገዥ ሕሩያን (elites) በራስ መተማመን የጎደላቸው ሆነው ነበር፣ (ሠ) መንግሥታቱ የፋይናንስ ችግሮች ነበሩባቸው፤ (ረ) የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ሥርዓቱን ከድቷል ወይም መደገፉን አቁሟል፤ (ሰ) የተከሰቱትን አመፆች ለመቀልበስ የተወሰዱት የኀይል እርምጃዎች ደካማ (ውጤት አልባ) ነበሩ።

በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸውና በኢትዮጵያ አብዮት ላይ የጻፉ ምሁራን ሆኑ በሒደቱ ያለፉ ፖለቲከኞች ከላይ ብሪተን የጠቀሳቸው ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተከሰቱና አገሪቱም በወቅቱ ለአብዮት ዝግጁ እንደነበረች ይናገራሉ። የየካቲት 66ቱ ኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ከሌሎች ሶሻል አብዮቶች ጋር የሚጋራቸው ነጥቦች ግን እነኝህ ብቻ አይደሉም። ብዙዎች እንደሚስማሙበት የየካቲቱ አብዮት እንደ ታላቁ የፈረንሳይ አብዮትና እንደ ሩሲያው አብዮት በተስፋ ጀምሮ በሰቆቃና ፀፀት የተደመደመ አብዮትም ነበር። ከዚህም በላይ፣ ጽንፈኝነት የክላሲካል አብዮቶች አካል ነውና የየካቲት 66ቱ አብዮት በጽንፈኝነት የታጀበና ሽብር የነገሠበት፤ እንደሌሎች አብዮቶች ሁሉ አገሪቱን ወደ መልካም ነገር ያሸጋግራታል ሲባል ፈላጭ ቆራጭነትን በመትከል የተጠናቀቀ አብዮትም ነበር።

የየካቲት 66ቱ አብዮት ፍጻሜ አሳዛኝ ከመሆን አልፎ ያልመለሳቸው ብዙ የሕዝብ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ አብዮቱን ተከትሎ የወጣው የመሬት አዋጅ የባለመሬት-ጭሰኛ ግንኙነትን በማጥፋቱ ፍትሐዊ እንደነበር ግን የሚካድ አይመስለኝም። እንደሚታወቀው ከአብዮቱ በፊት ብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭሰኛ እንጂ ዜጋ አልነበረም። ከአብዮቱ በኋላ ነው እውነተኛ ዜጋ ለመሆን የበቃው። ስለሆነም በዚህም ረገድ ቢሆን ያ አብዮትና አብዮታዊው ትውልድ ሊመሰገኑ ይገባል።

ሆኖም በአብዮቱ ወቅት የተነሱና ምላሽ ያልተሰጣቸው ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ስለነበሩ፣ በተለይ በወቅቱ የዜጎች የነጻነት ጥያቄ ምላሽ ያላገኘ ስለነበረ፣ ይህን ጥያቄ ያነገቡ ድርጅቶች ከየአቅጣጫው ተፈልፍለው ለወታደራዊው አገዛዝ መውደቅ ምክንያት ሆነዋል። ስለሆነም አብዮት ልክ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ በአንድ ፍንዳታ የሚቆም ክስተት ባለመሆኑ የ1983 ለውጥ ከየካቲቱ አብዮት ቀጥሎ የተከሰተ የመጀመሪያው ንዝረት (aftershock) ወይም ኹለተኛው ምዕራፍ ነው ሊባል ይችላል። በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ቃል ገብቶ ሲያበቃ፣ ያልመለሳቸው በርካታ መሠረታዊ ጥያቄዎች ስላሉ፣ በእነዚህ የሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ተመሥርቶ የተደረገው ምርጫ 1997 እንደ ሦስተኛ፣ እንዲሁም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች መጠኑንና አድማሱን እያሰፋ የመጣው ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደ አራተኛ ምዕራፎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ናቸው። ጥያቄዎች እስካልተፈቱ ድረስ ንዝረቱ አሁንም ይቀጥላል፡፡

የሕዝቦች እኩልነት ጥያቄ በአብዮቱ ወቅት ከተነሱት ዐበይት ጥያቄዎች አንዱ እንደነበር አይዘነጋም። እንዲያውም ጥያቄው አብዛኛውን ሕዝብ የሚያስማማ አጀንዳ ሳይሆን አይቀርም። ልዩነት የሚመጣው፣ የሕዝቦች መብት በምን መልኩ ይከበር? በሚለው አጀንዳ ላይ ነው። አሁን በሀገራችን የተያዘው መንገድ ምግቡን ሰጥቶ እጅን የማሰር ያህል ነው። ከመነሻው ተቀባይነት ለማግኘት በሚል መነሻ የተፈጠሩት ክልሎች ካርታው ከተሰጣቸው በኋላ የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ጉዳይ ላይ እንደፈለገ ለመወሰን የሚያደርገው ጥረት የራስ አስተዳደር ከሚለው አሠራር ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ነው፤ እንደሚታየው። የእኩልነትና የነጻነት ጥያቄው የፍትሐዊ ልማት ጥያቄንም ያጣመረ ነው።

እንደሚታወቀው በአገራችን ጥቂቶች እጅግ የተጋነነ ሕይወት በመምራት ላይ ሲሆኑ፣ ብዙኃኑ ሕዝብ አሁንም እንደ ድሮው በከፍተኛ ድህነት ላይ የሚገኝ ነው። በየካቲት 66ቱ የአብዮት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ሲነገርለት የነበረውና መቀስቀሻ የነበረው የጥቂቶች ምቾትና የሰፊው ሕዝብ አስከፊ ድህነት በዘመናችን በኢንዱስትሪ ደረጃ አድጎ፣ በሀብታሙና በድሃው መካከል ያለው ልዩነት ለመናገርም የሚከብድ ሆኗል። ትልቅ የማኅበራዊ ፍትሕ ጥያቄ አለ፡፡

ሌላው በየካቲት 66ትም ሆነ በዘመነ ኢሕአዴግ ምላሽ ያላገኘው ጥያቄ፣ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ነው። በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩት ሕገ መንግሥታትና ሌሎች ሕጎች ንጉሠ ነገሥቱን የሚያገለግሉ የመግዣ መሣሪያዎች እንደነበሩ በስፋት ተጽፏል፤ ተዘግቧል። ይኽን አስተሳሰብ በመቃወም የተጀመረው “ሕዝባዊ መንግሥት ይመሥረት!” የሚለው የአብዮት ዘመን መፈክር ሕዝቡ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት መሆን እንደሚገባውና ማንም ኀይል ከሕግ በላይ ሆኖ የሕዝቡን መብት እንዳይደፈጥጥ የሚያስገነዝብ ነበር። ሁሉም በሕግ ፊት እኩል የሚሆንበትን ሥርዓት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ከተጀመረ ከ50 ዓመታት በኋላም ግን የሕግ የበላይነት ጥያቄ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። 

ነባር ጥያቄዎቻችን

የአገራችን ነባር ችግር ፍትሕ ነው፡፡ ስለ ፍትሕ ስናወራ በርካታና ውስብስብ የሆኑ ቁም ነገሮችን እያነሳን መሆኑ ግልጽ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ስለ ፍትሕ እና ስለ ፍትሐዊ የፖለቲካ ሥርዓት በማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራን በኩል ተጻራሪ ንድፈ ሐሳቦችና አከራካሪ አስተያየቶች እንደሚሰነዘሩ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ በኩል “ሰብአዊ መብቶችና መሠረታዊ ነጻነቶች የሰው ልጅ በተፈጥሮው ያገኛቸው ወይም ተፈጥሮ ያጎናጸፈችው ጸጋዎች ናቸው፣ ስለዚህም ማንም እነዚህን ነጻነቶችና መብቶች ሊቀማው ወይም ሊነጥቀው አይችልም” የሚል ንድፈ ሐሳብ አለ፡፡ ከእነዚህ የሰብአዊ መብት መሠረት የሰው ተፈጥሮ ነው ከሚሉት ምሁራን በተቃራኒው፣ “ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች ሰው በተፈጥሮው ያገኛቸው ሳይሆኑ በማኅበራዊ ህልውናው የተጎናጸፋቸው መብቶችና ነጻነቶች ናቸው” የሚሉ ምሁራን አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄውን ከታሪክ አንጻር በመመርመር ከዕድገትና ከሥልጣኔ ጋር ሲያዛምዱት፣ ሌሎች ደግሞ ከአስፈላጊነት (utility) ጋር በማያያዝ መሠረቱንና ምንጩን ከቅርብ ታሪክ ጋር ያጣምሩታል፡፡ ሌሎችም በርካታ ንድፈ ሐሳቦችና አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡

የሆነ ሆኖ፣ በምሁራኑ ዘንድ የሚካሄደው ክርክር አሁንም እንደቀጠለ ቢሆንም፣ ሰብአዊ መብቶችና መሠረታዊ ነጻነቶች ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የተጎናጸፏቸው ጸጋዎች መሆናቸው ከሞላ ጎደል በሁሉም ምሁራን ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል ማለት ይቻላል፡፡ በትርጉሙና በአተገባበሩ ላይ ዛሬም ልዩነቶች የሉም ባይባልም፣ ፍትሐዊ የፖለቲካ ሥርዓት የሚባለው መሠረታዊ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል መብቶች በሕግ ደረጃ የተረጋገጡበትና ተግባራዊ የሚደረጉበት ሥርዓት ነው በሚለው አስተያየት ላይ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ነገሩን ዘርዘር አድርጎ ለመግለጽ ያህል፣ ፍትሐዊ የፖለቲካ ሥርዓት የሚባለው ሁሉም ዜጋ የሕይወት ነጻነቱና የሰውነት ደኅንነት መጠበቅ መብቱ የተከበረበት፣ ሁሉም ዜጋ በማናቸውም ቦታ በሕግ ፊት እንደሰው ተቀባይነት የማግኘት መብቱ የተረጋገጠበት፣ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የሆኑበትና ያለምንም ዓይነት አድልዎ እኩል የሕግ ጥበቃ የሚያገኙበት፣ ሁሉም ዜጋ በሕገ መንግሥት ወይም በሕግ የተሰጡ መሠረታዊ መብቶችን የመድፈር ድርጊቶች ሥልጣን ላላቸው ፍርድ ቤቶች አቅርቦ ትክክለኛ ብይን የማግኘት መብቱ የተረጋገጠበት፣ ማንም ዜጋ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ እንዲያዝ፣ እንዲታሰር ወይም እንዲሰደድ የማይደረግበት፣ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት መብቶቹ፣ ግዴታዎቹና ማናቸውም የቀረበበት የወንጀል ክስ በሚወሰንበት ጊዜ በነጻና በማያዳላ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ግልጽ በሆነ ችሎት የማቅረብና የማሰማት መብቱ የተረጋገጠበት፣ የወንጀል ክስ የቀረበበት ማናቸውም ሰው አስፈላጊዎቹ የመከላከል ዋስትናዎቹ ሁሉ በተሟሉበት በግልጽ ችሎት ጥፋተኝነቱ በሕግ መሠረት እስካልተረጋገጠበት ድርስ እንደ ንጹሕ የመቆጠር መብቱ የተረጋገጠበት፣ ማንም ሰው ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት በብሔራዊ ወይም በዓለም ዐቀፍ ሕግ በማድረግ ወይም ባለማድረግ ጥፋት ባልሆነ ነገር እንደ ጥፋተኛ ሊቆጠር የማይችልበትና ወንጀሉ በተፈፀመበት ጊዜ ከተደነገገው ቅጣት የበለጠ ቅጣት ሊጣልበት የማይችልበት፣ ሁሉም ዜጋ በግል ወይም ከሌሎች ጋር ሆኖ በማኅበር የንብረት ባለቤት የመሆን መብቱ የተከበረበትና ንብረቱን ያለሕግ ሊያጣ የማይችልበት፣ ሁሉም ዜጋ በሰላም የመሰብሰብና በማኅበር የመደራጀት ነጻነቱ የተከበረበት፣ ማንም ሰው ያለ ፈቃዱ የየትኛውም ማኅበር (ስብስብ) አባል እንዲሆን የማይገደድበት፣ ሁሉም ዜጋ በቀጥታ ወይም በነጻ ምርጫ በተመረጡ እንደራሴዎች አማካይነት በሀገሩ መንግሥት ውስጥ የመሳተፍ መብቱ የተከበረበት፣ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ የሕዝብ አገልግሎት ውስጥ በእኩልነት የመሳተፍ መብቱ የተረጋገጠበት፣ የመንግሥት ሥልጣን መሠረት የሕዝብ ፈቃድ የሆነበት – ይህም ፈቃድ በተወሰነ ጊዜ በሚከናወኑ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫዎች በምስጢር የድምጽ አሰጣጥ ወይም ተመጣጣኝ በሆነ ነጻ የድምጽ መስጠት ሥነ ሥርዓት ሁለንተናዊና እኩል በሆነ የመምረጥ መብት የሚገለጽበት እና ሌሎች ተያያዥ መብቶችና መሠረታዊ ነጻነቶች የተከበሩበት ሥርዓት ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ ነጥቦች በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ እነዚህንና ሌሎች በርካታ ጠቃሚ ድንጋጌዎችን ያቀፈ ሰነድ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ጠቃሚ ድንጋጌዎች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ቢሰፍሩም፣ የሀገራችን የፍትሕ ሥርዓት አሁንም በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኝ ደግሞ የሚያከራክር ነገር አይደለም፡፡ ያለ  ጥርጥር ሕዝባችን በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው መተማመን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ የፍትሕ ተቋሞቻችን ከፍተኛ የሆነ የገለልተኛነት ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው፡፡ ድንጋጌዎቹ በሕገ መንግሥት ደረጃ መቀመጣቸው እጅግ የሚያስመሰግንና የሚደገፍ ቢሆንም እነዚህን ድንጋጌዎች ነጻና ገለልተኛ ሆኖ በሥራ ላይ የሚያውላቸው የፍትሕ ሥርዓት እስካልተገነባ ድረስ፣ ድንጋጌዎቹ የወረቀት ላይ ጌጥ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡

ያለ ነጻና ገለልተኛ የፍትሕ ሥርዓት የዜጎች ነጻነትና ሰብአዊ መብት ሊከበር እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስ ጠንካራና ከየትኛውም የፖለቲካ ኀይል ጋር ያልወገነ ወይም ገለልተኛ የሆነ የፍትሕ ሥርዓት፣ ማለትም ገለልተኛ የሆነ የዳኝነት አካል፣ ነጻና ገለልተኛ የሆነ ዐቃቤ ሕግ፣ ነጻና ገለልተኛ የሆነ ፖሊስና የማረሚያ ቤት ተቋም እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 79 (6)፡- “በፌደራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፤” ይላል፡፡ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 7፡- “በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካል፣ ከማንኛውም ባለሥልጣንም ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተጽዕኖ ነጻ ነው፤” ሲል፣ ንዑስ አንቀጽ 8፡- “ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነጻነት ያከናውናሉ፡፡ ከሕግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም፤” በማለት ይደነግጋል፡፡

ሆኖም እነዚህ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች በሥራ ስለማይውሉ እና በሥራ ላይ መዋል አለመዋላቸውን የሚቆጣጠር ነጻና ከየትኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር ወገንተኛ ያልሆነ ተቆጣጣሪ ተቋም ባለመኖሩ ምክንያት፣ የሀገራችን የዳኝነት ተግባር ወይም በአጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱ ያለበት ሁኔታ (ደረጃ) እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ ዳኞች በአስፈጻሚው አካል ቁጥጥር ሥር ናቸው ወይም አስፈጻሚው አካል ያዘዛቸውን ነው የሚፈፅሙት? የሚለው አስተያየት ከተማውን የሞላው አስተያየት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ለመሆኑ ሕዝባችን ለዳኞች፣ ለአቃብያነ ሕጎችና ለፖሊሶች ያለው አመለካከት ምን ይመስላል? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ሕዝባችን በፍትሕ ሥርዓቱና በፍትሕ ተቋማቱ ላይ ያለው እምነት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ የአገዛዙ መሣሪያ እንደሆነ ነው የሚቆጠረው፡፡ ይኼ ትልቅ አደጋ ነው፡፡

በአገራችን በየአካባቢው እጅግ በሚዘገንን መልኩ የሚታየው የዜጎች ሞትና የንብረት መውደም መንስኤ ከሕግ አለመከበር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በማያከራክር ምክንያት በአገራችን ሥርዓት አልበኝነት የነገሠው ሕግ ማስከበርና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ባለመቻሉ ምክንያት ነው፡፡ ሕግ ማስከበር ሲባልም እንደ ቀድሞው ዘመን ሕግን የፖለቲካ መሣሪያ ማድረግ ሳይሆን ሕግን የዜጎች ደኅንነት መጠበቂያ ማድረግ ማለት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ሕግ ካልተከረና የዜጎች ደኅንነት ካልተከበረ ተመልሰን ወደለየለት አመጽና ትርምስ ውስጥ መግባታችን የማይቀር ነው፡፡ አገራችን ደግሞ ሌላ ዙር አመጽ የመሸከም ተከሻ የላትም፡፡

(Visited 12 times, 1 visits today)
June 15, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo