Articles, News, Opinion

“ከብዙዎቹ አመጾች ጀርባ ሕወሓት አለ”-አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

የዚህ እትም የሲራራ ጋዜጣ እንግዳ አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ናቸው፡፡ ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መሥራች አባላት መሀከል አንዱ የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ ልዩነት ምክንያት ከሕወሓት ተሰናብተው ለበርካታ ዓመታት ኑሯቸውን በአውሮፓ (ኔዘርላንድስ) ገፍተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ የኢትዮጵያ ድርጅቶች ኅብረቶችና ቅንጅቶች ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩት ዶ/ር አረጋዊ፣ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ በተለይም በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥቱ መሀከል ስላለው ልዩነትና ተያያዥ ጉዳዮች አወያይተናቸዋል፡፡ ውይይቱን እነሆ፡-

ሲራራ፡- በሕውሓት እና በብልጽግና ፓርቲ አመራሮች መሀከል ያለው ውጥረት እየተካረረ መጥቷል፡፡ በእርስዎ አስተያየት ውጥረቱ እየተባባሰ ሄዶ ወደ ግጭት እንዳያመራ ምን ቢደረግ ይሻላል?

ዶ/ር አረጋዊ፡- የኹለቱ ድርጅቶች አለመግባባት ዛሬ የጀመረ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ቀደም ብሎ ለውጡ ሲመጣ ጀምሮ በተለይ በሕወሓት እና በሌሎች ኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች መሀከል የተፈጠረ አለመግባባት ነው እየተንከባለለ እዚህ የደረሰው፡፡ ምክንያቱም ግልጽ ነው፡፡ ሕወሓት እንደ ድርጅት፡- “አገሪቱ በመሠረታዊነት በጥሩ መስመር ላይ ናት፣ የተፈጠረው የአመራር መዳከምና መበስበስ ስለሆነ በጥልቅ ተሐድሶ እንወጣዋለን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው መስመራችን ግን እንከን የለሽ ነው፣ በምንከተለው ርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲ መሠረት ዓለም የመሰከረለት ዕድገት እያስመዘገብን ነው፣ የዜጎች ሰብአዊ መብቶችም እየተከበሩ ነው” የሚለውን ነባሩን ሐሳቡን ይዞ መቀጠል ነበር የፈለገው፡፡ አሁንም በዚያው በነበረው የጥፋት መንገዱ ነው እየተንገዳገደ ያለው፡፡

በሌላ በኩል “የለውጥ ኀይሎች” እየተባሉ በሕዝቡ ዘንድ የሚጠሩት አካላት ደግሞ፡- “አገሪቱ የቁልቁለት ጉዞ እየሄደች ነው፣ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተከበሩ አይደለም፣ ግጭቶች በርክተዋል፣ ጥቂቶች ከሥርዓቱ ጋር በመጠጋጋት አድሏዊ በሆነ መልኩ የአገር ሀብት ዘርፈው ሲያብጡ ብዙሃኑ ሕዝብ በድህነት እየማቀቀ ነው” ወዘተ… ብለው ታግለው ከመዋቅር ውጪም፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ አግኝተው ለውጡን አምጥተዋል፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ለውጥ በዋናነት የመጣው በኢትዮጵያ ወጣቶች ትግል እና የሕይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ ይህን የለውጥ ኀይል የሕወሓት አመራሮች በፍጹም አልወደዱትም፡፡ አልወደዱትም ብቻ ሳይሆን ለውጡ እንዲቀለበስ ባለ በሌለ አቅማቸው ታግለዋል፡፡ ግን አልቻሉም፡፡ በሕዝብ ኀይል ተሸንፈዋል፡፡ ዋናው ያለመግባባት ምንጭ ይህ ነው፡፡

የሕወሓት አመራር ጥልቅ ተሐድሶ የሚባል ድራማ አድርጎ እንደለመደው የሕዝቡን ጥያቄ አፍኖ በሥልጣን ላይ እቆያለሁ ብሎ አቅዶ ሰፊ ሥራ ሲሠራ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከሕዝባዊ አመጾች በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በርካቶች በገፍ ታስረው ተደብድበዋል፤ አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ ሆኖም ሥርዓቱ መቀየሩ የግድ ስለነበር ከውስጥም ከውጭም በተደረገ ጥረት ያ አፋኝ ቡድን ከነበረበት የሥልጣን ማማ ተገፍትሯል፡፡ የሕወሓት አመራሮች ለ27 ዓመታት የተቀመጡበትን ስፍራ እና ቢሮ ለቀው መቀሌ ተሸጉጠው ነው ያሉት፡፡

ለውጡ ከመጣ በኋላ በተፈጠሩት ችግሮችና አለመረጋጋቶች ጭንቅላታችን ስለተወጠረ ጊዜ አግኝተን አልተወያየንበትም እንጅ ይህ ለውጥ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ በዚህች አገር ብዙ በግፍ ተሠርቷል፡፡ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁ ኢትዮጵያዊያን ከእስር ወጥተው ከሕዝባቸው ጋር እንዲቀላቀሉና በነጻነት ሕይወታቸውን እንዲመሩ ያደረገ፤ ለበርካታ ዓመታት በሕወሓት አመራር ውሳኔ ወደ አገራችን እንዳንገባ ማዕቀብ ተጥሎብን የነበርን በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራችን ገብተን እና ተደራጅተን መንቀሳቀስ የቻልንበን ዕድል የፈጠረ ለውጥ ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ይህ ለውጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ዕውን በሚያደርግ መልኩ እየጎለበተና እየተሻሻለ እንዲሄድ ማድረግ ነው፡፡

በሚደንቅና በሚያሳዝን ሁኔታ፣ የሕወሓት አመራሮች ግን አሁንም መቀሌ ተቀምጠውም አላረፉም፡፡ ወደ ራሳቸው ተመልሰውና አቋማቸውን ገምግመው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለመታረቅ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ወደ ነበሩበት ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ ነው ያሉት፡፡ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎችም ግጭቶችን እየፈጠሩ ነው ያሉት፡፡ ዛሬ በደቡብ ክልል ላለው የፖለቲካ ውጥረት የነሱ እጅ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች አመጾች እንዲቀጣጠሉ እሳት እያቀበሉ ነው፡፡ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው እንስሳት ሕወሓት አገሪቱን እኔ ካልመራኋት እረፍት ልታገኝ አይገባም ብሎ የቆረጠ ድርጅት ይመስለኛል፡፡ ከብዙዎቹ አመጾች ጀርባ ሕወሓት አለ፡፡ በእኔ እምነት አሁን ያለው የፌዴራል መንግሥት በትዕግስት እያለፋቸው እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡

ዞሮ ዞሮ፣ ለአገርና ለሕዝብ ሲባል ያለው መፍትሔ ድርድርና ውይይት ነው፡፡ ከዚህ መለስ ያለው ሕዝብን የሚያስጨርስ አውዳሚ መንገድ ስለሆነ በተለይ የትግራይ ሕዝብ በስሙ እየማሉ ግን ደግሞ ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ሊያለያዩት የሚሠሩትን የሕወሓት አመራሮች ሃይ ማለት ይገባዋል፡፡

ሲራራ፡- በትግራይ ክልል አመራሮች እና በብልጽግና ፓርቲ አመራሮች መሀከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የአገር ሽማግሌዎች እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ሆኖም መቀሌ የነበረው የመጀመሪያ ዙር መድረክ ተስፋ ሰጪ አይመስልም፡፡ እርስዎ የሽምግልናውን ሒደት እንዴት አገኙት?

ዶ/ር አረጋዊ፡- የሕወሓት አመራር አካሄድ ስላላማራቸው እና እንገነጠላለን የሚልም ሐሳብ ውስጥ ውስጡን እያራመዱ በመሆኑ የአገር ሽማግሌዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ለማሸማገል ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት፡፡ ያም ሆኖ ግን የሕወሓት አመራሮች ለሽማግሌዎቹ ጥሩ ምላሽ አልሰጡም፡፡ ይህም የሕወሓትን መርዘኛ አካሄድ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ የሕወሓት ግትር አቋም እስካለ ድረስ በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥቱ መሀከል ያለው አለመግባባት እየተካረረ ነው የሚሄደው፡፡

ሽምግልናው መሞከሩ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ እኛም በዚህ በሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች ጥረት ትልቅ ደስታ ነው የተሰማን፡፡ ሽምግልና በአገራችን የተለመደና በታሪካችንም ብዙ ግጭቶችንና ደም መፋሰሶችን ያስቀረ ትልቅ እሴት ነው፡፡ ነገር ግን በግልጽ እንደታየው አሁን ያለው የሕወሓት አመራር በሽምግልና የሚያምንና ሽማግሌዎችን የሚያከብር አይደለም፡፡ የአምባገነንነት ባሕርይ የተጠናወተው ስብስብ ስለሆነ ለኢትዮጵያ እሴቶች አምብዛም አይጨነቅም፡፡ ችግሩ በሽምግልና ቢያልቅ ጦር መማዘዞች ባይኖሩ ደም ባይፈስ መልካም ነው፡፡

የሆነ ሆኖ ሕወሓት ራሱን እስካልጠቀመው ድረስ ለኢትዮጵያ እሴት ደንታ የሌለው ድርጅት ቢሆንም የትግራይ ሕዝብ ልክ እንደ ሌላው የአገራችን ሕዝብ ለሽምግልና የሚሰጠው ክብደት ትልቅ በመሆኑ፣ የሕዝቡ ጫና ውሎ አድሮ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ስለሆነም ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በሚሰጣቸው አሉታዊ መልስ ተስፋ ሳይቆርጡ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ ነው አደራ የምለው፡፡

ሲራራ፡- ትግራይ ውስጥ የመገንጠል እንቅስቃሴ እያቆጠቆጠ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እውነት በትግራይ ሕዝብ ዘንድ እንዲህ ዓይነት ስሜት አለ?

ዶ/ር አረጋዊ፡- እንዲህ ዓይነቱን ሐሳብ የሚያራግቡት የሕወሓት ካድሬዎችና የሕወሓት ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ለትግራይ ነጻነት እታገላለሁ የሚል ድርጅትም አለ፡፡ ሆኖም የመገንጠል ሐሳብና እንቅስቃሴ በትግራይ ሕዝብ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ሕወሓት ነው የፌዴራል መንግሥቱንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማስፈራራትና የመደራደሪያ አቅሙን ከፍ ለማድረግ ይህን አጀንዳ እያራገበው ያለው፡፡ የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ መነጠል ፈጽሞ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ መሠረት የሆነ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ልነጠል ሊል አይችልም፡፡

ሲራራ፡- እስኪ ደግሞ ስለምርጫ እንነጋገር፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫውን ለማራዘም የሄደበት መንገድ ትክክል ነው ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር አረጋዊ፡- የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምርጫው እንዳይከናወን የሚያደርግ በቂ ምክንያት ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ አሁን በምንገኝበት ፈታኝ ሁኔታ ምንም ዓይነት ምርጫ ማከናወን አይቻልም፡፡ ብዙ አገሮችም በኮቪድ-19 ምክንያት ምርጫ አራዝመዋል፡፡

እኛ እንዲደረግ የምንፈልገው ተፎካካሪ ኀይሎች የሚሳተፉበት፣ የተለያዩ ሐሳቦች በነጻነት የሚስተናገዱበት ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የሚስችሉ የዴምክራሲ ተቋማት ደግሞ በቦታው መኖር አለባቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ሁሉም ባመነበት ሁኔታ በቅድሚያ መገንባት አለባቸው፡፡ ከሁሉም ነገር ይህ መቅደም እንዳለበት ነው የሚሰማኝ፡፡

ሲራራ፡- አሁን ያሉት የዴምክራሲ ተቋማት ምርጫውን ለማድረግ ብቁ አይደሉም ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር አረጋዊ፡- ፈጽሞ በቂ አይደሉም፡፡ ተቋማቱን ለመገንባት ሙከራዎች እየተደረጉ ቢሆንም በቂ ናቸው ለማለት ግን ያስቸግራል፡፡ በዚህ ረገድ እንደ አገር በጣም ሰፊ ጉድለት አለ፡፡ ስለሆነም የዴሞክራሲ ተቋማት ከየትኛውም አካል ገለልተኛ ሆነው እንዲደራጁና እንዲጎለብቱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እሱን ለማደረግ ደግሞ አሁን ጊዜው አለ፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቁ በሆነ የሰው ኀይልና በቁሳቁስ መደራጀት አለበት፡፡ ገለልተኛነቱና ሙያዊ አቅሙም በሚገባ መጎልበት ይገባዋል፡፡ አሁን ገና ነው፡፡ ምርጫ ቦርድም ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትም ብዙ ይቀራቸዋል፡፡

ለምሳሌ እኔ የምመራው ፓርቲ የሚንቀሳቀሰው በዋናነት በትግራይ ክልል ነው፡፡ እዚያ ያለው ደግሞ የሕወሓት አምባገነናዊ አመራር ነው፡፡ አሁን ላሉት የዴሞክራሲ ተቋማት የማይገዛ እና እንዲኖሩም የማይፈልግ አመራር ነው፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ የዴሞክራሲ ተቋማት ተገንብተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ባልሆነበት ምርጫ ማከናወን አይቻልም ብዬ ነው የማስበው፡፡

ሌላው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህም ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጥሩ የተቋቋሙ ተቋማትን ድክመትና አለመጠናከርን ነው የሚያመለክተው፡፡ አለመረጋጋት ባለበት ምን ዓይነት ምርጫ ለማድረግ እንደታሰብ ግልጽ አይደለም፡፡ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ባሉበት ሁኔታ ሕዝቡ በነጻነት ሊመርጥ አይችልም፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በነጻነት መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ስለሆነም እንደ አገር ሰላምና መረጋጋትን ማስከበር የሚችሉ ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት ይኖርብናል፡፡

ሲራራ፡- የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫውን በክልል ደረጃ ለማካሄድ ያስተላለፈውን ውሳኔ እናንተ እንደ ድርጅት እንዴት ገመገማችሁት?

ዶ/ር አረጋዊ፡- ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጪ የሚደረግ ማንኛውም ምርጫ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ጥያቄ ቀርቦለት ያለው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን  ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ማስፈፀም አልችልም ቢልም እንኳ በራሳችን ምርጫውን እናከናውናለን እያሉ ነው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ በግልጽ ሕገ መንግሥቱን መጣስ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ጥሰው የሚያደርጉት ምርጫ የት እንደሚያደርሳቸው አላውቅም፡፡ ሌላው ራሳቸውን ተመራጫ፣ ራሳቸውን አስመራጭ፣ ራሳቸውን ቆጣሪና ታዛቢ አድርገው የሚሾሙበት የምርጫ ሁኔታ ምን ያህል ፍትሐዊ እና ገለልተኛ ይሆናል? የሚለው ለማንም የሚነገር አይደለም፡፡ ሕወሓትና ምርጫ ምንና ምን እንደሆኑ እነሱም፣ እኛም፣ የትግራይ ሕዝብም፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤትም ቢሆን እንዴት እንደተመረጠ ይታወቃል፡፡ ድሮ በነበረው የምርጫ ሂደት በምደባ ነበር ምርጫ ሲከናወን የነበረው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ኮሮጆ እየተገለበጠ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሸማቀቁና ከክልሉ እንዲወጡ ተደርጎ በተካሄደ ምርጫ ነው ሥልጣን ላይ የወጡት፡፡ ስለዚህ በምንም ዓይነት መለኪያ በትግራይ ክልል ደረጃ የሚደረገው ምርጫ ምርጫ ሊባል አይችልም፡፡

አሁን ያለው የትግራይ ክልል መንግሥት ሕዝቡን የናቀ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም የናቀ አካሄድ ነው እየሄደ ያለው፡፡ ይህ ነገር ደግም ተወደደም ተጠላ ሌላ ቀውስ እየፈጠረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን እንደሚታየውም “ፈንቅል” የተሰኘ የወጣቶች ንቅናቄ ተፈጥሯል፡፡ ሕዝብ በራሱ መንገድ እየዘጋ የአስተዳደር ጉድለት እንዳለ እየጮኸ ነው ያለው፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ እንዲያው ዝም ብለን ስሙን ካልለጠፍንለት በስተቀር ምርጫ የሚባል አይደለም፡፡ እርግጥ እነሱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ምን እንደሆነ ስለማያውቁ በለመዱት መንገድ ለመቀጠል ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ግን አንቅሮ እየተፋቸው ነው፡፡

ሕዝቡ ድሮም ቢሆን ከመሀል አገር በአንዳንድ ኀላፊነት የጎደላቸው ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ምክንያት በሕወሓት ጥፋት የትግራይ ሕዝብ ስለሚወቀስና ስለሚወነጀል በመገፋት መንፈስ አስጠጋቸው እንጅ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች በስሙ እንደነገዱበት ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ከትግራይ ውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ፣ በተለይም ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን የሚሉ አካላት ከዚህ ኢትዮጵያን ከማይጠቅም አደገኛና ከፋፋይ አካሄድ ራሳቸውን ማረም ይገባቸዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከማንኛውም ሕዝብ በላይ በከፍተኛ ጭቆና ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ ነው፡፡ “ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው” እየተባለ የሚራመደው መሠረተ-ቢስ ፕሮፓጋንዳ አውዳሚ ነው፡፡ ለማንም አይጠቅምም፡፡

ሲራራ፡- የትግል መሠረታቸውን ትግራይ ክልል ያደረጉ አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫው እንደሚሳተፉ እየገለጹ ነው፡፡ የእናንተስ ውሳኔ ምንድን ነው? በምርጫው ትሳተፋላችሁ?

ዶ/ር አረጋዊ፡- እኛ እንደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዓይነት በሕገ መንግሥት ተደንግጎ የተቋቋመ ገለልተኛ አካል ከሌለ ምርጫ የሚባለውን ነገር አናስበውም፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ምርጫም መካሄድ የለበትም፡፡ ሕገ-ወጥ ነው፡፡ ሕዝቡንም መናቅ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህልውናም ትልቅ አደጋ የሚያመጣ ኀላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው፡፡ ስለሆነም በእኛ በኩል የማይጠራ ጭቃ ውስጥ ግብተን ስናቦካ አንገኝም፡፡ በሕገ መንገሥቱ መሠረተ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማከናወን የሚቻለው በገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት አማካይነት ብቻ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና በሌላቸው እና በየሰፈሩ በሚቋቋሙ የዴሞክራሲ ተቋማት ተብየዎች በሚደረግ ምርጫ ላይ አንሳተፍም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሲቪክ ማኅበራት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት አብረውን ሊቆሙ ይገባል፡፡

ሲራራ፡- አንዳንድ ፓርቲዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከመስከረም 30 በኋላ ሕጋዊ መንግሥት ስለማይኖር የሽግግር መንግሥት ሊቋቋም ይገባል ይላሉ፡፡ ሌሎች የባለአደራ አስተዳደር መመሥት አለበት ሲሉ፤ ከመስከረም 30 በኋላ አገሪቱ እንዴት ትመራ በሚለው ጥያቄ ላይ መወያየትና መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል የሚሉ ድርጅቶችም አሉ፡፡ የእናንተ አቋም ምንድን ነው?

ዶ/ር አረጋዊ፡- አሁን ያለው መንግሥት በግልጽ እንደምናየው በነጻነት መንቀሳቀስን አላገደም፡፡ ሐሳብን በነጻነት መግለጽን እየከለከለ አይደለም፡፡ መደራጀትን አልከለከለም፡፡ በሩን ክፍት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው ያለው፡፡ እነዚህ ነገሮች በቂ ናቸው ብለን ነው የምንወስደው፡፡ እኛ ሌላ የውዝግብ በር መክፈት አንፈልግም፡፡ ችግር በሌለበት ሁኔታ የውዝግብ አጀንዳ ማንሳቱ ለአገርም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ከትግራይ ውጪ ያለው የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ጥሩ ሊባል የሚችል ነው፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ አሁን ትልቁ ችግር ያለው ከመንግሥት ወይም ከገዥው ፓርቲ አካባቢ ሳይሆን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ከራሳቸው ውስጥ ነው፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ከ130 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ያሉት፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው የሚተራመሱ ናቸው፡፡ የረባ ሥራ መሥራት የማይችሉ መሆናቸውን አይተናል፡፡ እንዳልኩት ያለው ሥርዓት ዴሞክራሲን ወደ ተግባር ለማውረድ የሚከለክል ዓይነት አይደለም፡፡ ከትግራይ ክልል በስተቀር እንደልባችን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ሕዝቡም ፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህን ዕድል በመጠቀም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግበት ዕድል ቢፈጠር የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

በአጠቃላይ ለአገሪቱ ደህንነት እና ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ ሲባል በአርቆ አሳቢነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ተጨማሪ ጠጠር መጣል እንጅ አፍራሽ በሆነ ተግባር ውስጥ መሰማራት ትክክል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የየእያንዳንዳችን ገንቢ ተሳትፎ ትፈልጋለች፡፡ ለበርካታ ዘመናት እርስ በርሳችን እየተጠፋፋን ስናደማት ስለቆየን አሁን ጠባብ የሆነ የግሰለብ ወይም የድርጅት ጥቅምን ሳይሆን አገርንና ወገንን አስበን በጋራ መቆም ይገባናል፡፡

በተለይ ተፎካካሪ ድርጅቶች፤ እያንዳንዳችን የየራሳችን ቤት አፅድተን እና ከሌሎች ከሚመስሉን ወይም በሐሳብና በአመለካከት ከሚቀራረቡን ፓርቲዎች ጋር ኅብረትና ውሕደት እየፈፀምን የተወሰኑ በሐሳብና በድርጅታዊ አቅም የጎለበቱ ድርጅቶችን መፍጠር ይገባናል፡፡ አሁን ያለው በአመዛኙ የግለሰብ ድርጅት ነው፡፡ የሽግግር መንግሥትም ይባል ባለ አደራ መንግሥት ወይም ሌላ ዓይነት አደረጃጀት የአገሪቱን ችግር ያባብሰዋል እንጅ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ መጀመሪያ እያንዳንዳችን ውስጣችን እናጥራ፡፡ ራሳችን እንገምግም፡፡ ኅብረትና ውሕደት መፍጠር ካለብን ኅብረትና ውሕደት እየፈጠርን ጠንከር ጠንከር ያሉ ድርጅቶችን ይዘን እንቅረብ፡፡ መሥራት ያለብን በዚህ ላይ ነው፡፡

ሲራራ፡– በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ መንግሥት ተጽዕኖ እንደማይደረግባቸው ይናገራሉ፡፡ እናንተን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ በክልሉ መንቀሳቀስ እንደተቸገራችሁ ትገልጻላችሁ፡፡ ልዩነቱ ከምን የመነጨ ነው?

ዶ/ር አረጋዊ፡- የልዩነቱ ምንጭ በጣም ግልጽ ነው፡፡ በነጻነት እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ፓርቲዎች ማን እንደፈጠራቸው እናውቃለን፡፡ ብዙዎች የሕወሓት አመራር ተቀጥያዎች እና ጭራዎች ናቸው፡፡ ፓርቲው ግቡ ባላቸው ይገባሉ፤ ውጡ ባላቸው ይወጣሉ፡፡ ግን ለሕዝብ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መስለው ነው የሚታዩት፡፡ የሕወሓት አጀንዳ ማስፈፀሚያዎች እንደሆኑ ግን እኛም እናውቃለን፤ ሕዝቡም በደንብ ያውቃል፡፡

ለምሳሌ የአገር ሽማግሌዎቹ መቀሌ ሲሄዱ እነሱ ተጠርተው ውይይቱ ላይ ገብተው ነበር፡፡ እኛም በትግራይ ክልል የምንቀሳቀስ ፓርቲዎች ነን፡፡ እኛን አልጠሩንም፡፡ ዓረና አልተጠራም፡፡ አሲንባ የተባለው ድርጅትም አልተጠራም ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እነሱን እንደ እውነተኛ ተፎካካሪ ፓርቲ አድርጎ መውሰድ አይቻልም፡፡ ሕወሓት የፌዴራል መንግሥቱን ተቆጣጥሮ በነበረበት ጊዜ በርካታ እሱን የሚያገለግሉ፣ እውነተኛ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ግን የሚቃወሙ ድርጅቶችን ፈጥሮ እንደነበረው ሁሉ አሁንም በትግራይ ክልል ደረጃ እያደረገ ያለው እሱን ነው፡፡

(Visited 36 times, 1 visits today)
June 24, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo