Articles, Featured articles, News, ሐተታ, ዜና, ፖለቲካ

ከስካሩ ቀነስ፤ ከመረጋጋቱ ጨመር!

በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ በሚባል ደረጃ ስክነት ጠፍቷል፤ ጩኸት በርክቷል፤ መሳከር ነግሧል፡፡ በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም፣ በማኅበራዊውም መስክ የሰከነ እና በዕውቀት ላይ ተመሠረተ ውይይት እየተደረገ አይደለም፡፡ ሁሉም ጉዳይ ጊዜያዊ እና የዘመቻ ነገር እየሆነ፣ ሁሉም ነገር ስርና መሠረት ያልያዘ እየሆነ ያሉብንን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት አልተቻለም፡፡ ውይይት ተደረገ፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀረበ፣ ችግር ተለይቶ የመፍትሔ ሐሳብ ቀረበ ይባላል፡፡ ሆኖም ሳምንት ሳይቆይ ሁሉም ነገር ተመልሶ እዚያው ሲሆን ይስተዋላል፡፡ የዛሬ ዓመት የቀረበው ጥናት እና ተለዩ የተባሉት ችግሮች እንደገና ሲቀርቡ ይታያል፡፡ ትርምስ እና መልክ-አልባነት መገለጫችን ሆኗል፡፡ ዛሬ የተሾመው አመራር ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ሌላ ቦታ ሲቀየር፣ ዛሬ በአፈጻጸም ድክመት የተገመገመውና ሕዝብ ያማረረው አካል ሌላ የሹመት ቦታ አግኝቶ ሲሸጋሸግ፣ ተጠያቂነት አደጋ ላይ ሲወድ እና ሌብነት ሲበረታታ እየታዘብን እንገኛለን፡፡

[ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ] መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች እንዴት እንደሚመሩ፣ ምን ዓይነት የትምህርት ዝግጅት እና የአመራር ብቃት ያለው አካል እንደሚመራቸው፣ ማን ለምን እና ለስንት ጊዜ በኀላፊነት እንደሚቆይ መገመት ተስኖናል፡፡ የመንግሥትን የሥራ ኀላፊዎች የምደባ ዘይቤ መገመት አልተቻለም፡፡ አንድ አመራር ዓመት ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስት ቦታ ሲረግጥ በአግራሞት እየታዘብን ነው፡፡ የሥራ መሪዎች የተመደቡትን መሥሪያ ቤት አሠራር በሚለምዱበት እና ከሠራተኛው ጋር በሚናበቡበት ጊዜ ተነስተው በምትኩ አዲስ ሰው ይሾማል፡፡ እሱም እንዲሁ ገና በመለማመድ ላይ እንዳለ በሌላ ይተካል፡፡ መክነፍ ባህል ሆኗል፤ መረጋጋት ከአገር ርቋል፡፡

መንግሥታዊ ተቋማትም ራሳቸው በየጊዜው ሲፈርሱና ሲሠሩ ነው የሚታየው፡፡ ዛሬ አንድ የነበረው ተቋም ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሁለት እና አራት ተከፋፍሎ ይደራጃል፤ እንደገና ተመልሶ አንድ ተቋም ይሆናል፡፡ ተቋማዊ ባህል (organizational culture) መገንባት አልተቻለም፡፡ የትኛው ተቋም ምን ዓይነት ሥልጣንና ኀላፊነት እንዳለው መገንዘብ አልተቻለም፡፡ ባለጉዳዮች ከአንድ መሥሪያ ቤት ወደሌላ መሥሪያ ቤት እየተንከራተቱ ጊዜና ጉልበታቸውን እየጨረሱ ነው፡፡ የአገር ሀብት እየባከነ ነው፡፡

መንግሥት የሚያወጣቸው አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችም በተመሳሳይ መልኩ በፍጥነት እየተቀያየሩ ሕዝብ እየተቸገረ ነው፡፡ ዛሬ የወጣው መመሪያ ነገ ሲሻር ይታያል፡፡ በዛሬው መመሪያ መሠረት የተቀጠረ፣ ቤትና መሬት ያገኘ፣ ጉዳዩ ያለቀለት ሰው ነገ ጉዳዩን እንደገና ለመጀመር ይገደዳል፡፡ አዋጁ፣ ድንቡ ወይም መመሪያው ተቀይሯል ይባላል፡፡ የተወሰኑ አካላትን ለመጥቀም የሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችም እንዳሉ በስፋት ይነገራል፡፡ የተወሰኑ ቡድኖችን የመሬት ባለቤትነት ለማረጋገጥ አንድ ዓይነት ደንብና መመሪያ ይወጣል፡፡ እነዚያ አካላት የሚያገኙትን ካገኙ በኋላ ደንቡና መመሪያው ይቀየራል፡፡

ለመሆኑ በእንዲህ ዓይነት የተሳከረ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ነው አመርቂ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው? እንዴት ዓይነት ብልጽግና ነው እውን የሚሆነው?

ወከባው፣ አለመስከኑ እና መሳከሩ በመንግሥት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚውም በሕዝቡም ዘንድ ያለ ነው፡፡ ዛሬ አንዱን ነገ ሌላውን የመጨበጥ በሽታ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስር ሰድዷል፡፡ ከሐሳብ እና አመለካከት ይልቅ በነጠላና ቅርንጫፍ ጉዳዮች ላይ የመጠመድ በሽታ ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካው፣ በማኅበራዊውም መስክ ከገባችበት አረንቋ እንዴት መውጣት እንደምትችል አሻጋሪ ሐሳብ ከማፍለቅ እና በዚያ ሐሳብ ዙሪያ ሕዝብን ከማንቃትና ከማደራጀት ይልቅ ስሜት ኮርኳሪ አጀንዳዎችን በማራገብ አገር እያጠፉ ያሉ ብዙዎች ናቸው፡፡

“ኢትዮጵያን የመሰሉ ሌሎች አገሮች የኢኮኖሚ ችግሮቻቸውን እንዴት ፈቱ? እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ብሔርና ሃይማኖት ያላቸው አገሮች በምን መልኩ ችግራቸውን ተሻግረው የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊገነቡ ቻሉ? በሌሎች ማኅበራዊ መስኮች ላይ ምን ዓይነት ግስጋሴ አደረጉ?” ወዘተ… ብሎ ጠይቆ እና የሌሎች አገሮችን ልምድ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አዋሕዶ ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት እምብዛም ነው፡፡ ሕዝብ እስካደራጀ ድረስ አገርን የሚጎዳ፣ ሕዝብን የሚያተራምስም ቢሆን የትኛውም ዓይነት ቅስቀሳ ጥምቅ ላይ ሲውል እየታዘብን ነው፡፡ ስሜት ቀስቃሽ ብሔር እና ሃይማት ተኮር ጉዳዮችን በማራገብ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማስነሳት ጥረት የሚያደርጉት ብዙዎች ናቸው፡፡ ሕዝብ ያደራጅ እንጂ፣ ሥልጣን ላይ ለመውጣት መሰላል ይሁን እንጂ ምንም ይሁን የሚል አደገኛ አካሄድ እየነገሠ ነው፡፡  

ኢትዮጵያ በግርግር አደጋ ላይ ስትወድቅ እያየን ነው፡፡ በመንግሥት አካላት መሀከል መደማመጥና መናበብ የለም፡፡ አንዱ የመንግሥት ተቋም የሚሠራውን ሌላው ሲያፈርሰው፣ አንዱ አመራር የሚለውን ሌላው ሲቃወመው ይታያል፡፡ በሕዝበኝነት ጎዳና ተሰልፈው የራሳቸውን የግለሰብ ተክለ-ስብዕና ለመገንባት የሚታትሩትም ብዙዎች ናቸው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥዶ ያልሠራውን ሥራ እንደ ሠራ ለማኅበራዊ ሚዲያ ቲፎዞው ሪፖርት ሲያቀርብ የሚውለውም በጣም ብዙ ነው፡፡

ከተፎካካሪው ጎራ ያለው ሁኔታም ከዚህ የማይሻል ነው፡፡ ከገባንባቸው ችግሮች በዘላቂነት በሚያወጡን የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ አተኩሮ በሰከነ ሁኔታ የሚመረምርው፣ የሚጽፍው፣ የሚወያይው እና የሚሠራው በጣም ጥቂት ነው፡፡

ረዥም የአገረ-መንግሥትነት ታሪክ እና የዳበረ የጽሑፍ ባህል ያላት ኢትዮጵያ እንዴት የውይይት እና የተዋስዖ ምድረ-በዳ ሆነች? የሚያሻግር ሐሳብ የሚያፈልቁ ሰዎች በዚህ ደረጃ የሌሉት ወይም ዝም የተሰኙት ለምንድን ነው? ከዘመቻ ወጥተን ዘላቂ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በዕቅድ የምንሠራው መቼ ነው? ከነጠላ እና ቅርንጫፍ ጉዳዮች ወጥነትን በትልልቅ አጀንዳዎች ላይ የምናተኩረው መቼ ነው? ተዋስዖው የሚዘምነው መቼ ነው?

በአገራችን ባዶ ጩኸት በርክቷል፡፡ አለመደማመጥ እና ትርምስ ስር ሰድዷል፡፡ ለራስ ግሰለባዊ እና ቡድናዊ ጥቅም እስከጠቀመ ድረስ ስሜት ኮርኳሪ ቃላትን እየደረደሩ ሕዝብን ማነሳሳት የዘወትር ግብር እየሆነ ነው፡፡ ብዙ አገሮች እንደዘበት ህልውናቸውን ያጡት በዚህ መንገድ ነው፡፡ እጅግ አሰቃቂና ኢሰብአዊ ድርጊቶች የሚፈፀሙት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ጊዜውና ሁኔታው ተመቸን ብለው በየሚዲያው ስሜት ኮርኳሪ ቃላትን እያሰራጩ በአገር ህልውና ላይ ቁማር እየተጫወቱ ነው፡፡ “ተው ይህ ነገር አይሆንም፤ አደጋ አለው” የሚል አካልም አልተገኘም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ስሜትን እየቀሰቀሰ ወደ እሳት የሚማግድ ቅስቀሳ የብዙ ወገኖቻችንን ሕይወት ሲቀጥፍ እና ለዘመናት የተገነቡ ጥሪቶችን በአንድ ጀንበር ሲያወድም ታዝበናል፡፡ ግን አሁንም አልተማርንም፡፡ አሁንም ከስሜት ጎዳና አልወጣንም፡፡ አሁንም ከስካሩ አላገገምንም፡፡

ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም ልኂቃኑ ከመሳከሩ ቀነስ፤ ከመረጋጋቱ ጨመር እንዲያደርጉ በጥብቅ ይመከራሉ፡፡ 

(Visited 14 times, 1 visits today)
September 4, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo