Articles, Politics, ሐተታ, ፖለቲካ

እንደገና የአፈና አገዛዝ?-(ብርሃኑ አበጋዝ (ዶ/ር)

“ግፉ በዛ!” ታኅሣሥ 24 ቀን 2004 ዓ.ም. የአወሊያ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የጠየቁት ጥያቄ ነው፡፡ በዕለቱ አወሊያ ትምህርት ቤት ውስጥ በመስዋዕትነት የተመሠረተው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የሙስሊሙ ብቸኛ ወኪል ለሆዳቸው ባደሩና የሙስሊሙን ጥቅም አሳልፈው በሰጡ ሰዎች ተሞልቷል፤ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ጥሶ ይህን ምረጡ ያንን አትምረጡ እያለ በውስጥ ጉዳያችን መግባቱን ያቁም፤ የተባረሩት መምህሮቻችን ይመለሱ፤ መንግሥት የአሕባሽ አስተምህሮን መደገፉን ያቁም ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎች ተስተጋቡ፡፡ የተማሪዎች ጥያቄ የብዙሃኑ ሕዝበ ሙስሊም ጥያቄ ስለሆነ፣ በርካታ ሕዝብ ተማሪዎችን ተቀላቀላቸው፡፡ የሕዝበ ሙስሊሙን መብት ለማስከበርም ተወካዮች ተመርጠው ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መወያየት ጀመሩ፡፡

አገዛዙ የሕዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ አንድ ጊዜ በበጎ ሌላ ጊዜ በጥርጣሬ ዐይን እያየ፣ ውይይቶችም አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያሉ ቀጠሉ፡፡ ሐምሌ 2004 ዓ.ም. ግን አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፡፡ በአቡበክር አሕመድ የሚመራውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በከፊል፣ ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር ግንኙነት አላችሁ ከተባሉ ግለሰቦች ጋር ተይዘው በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ታሰሩ፡፡

መንግሥት የኮሚቴው አባላት በውጭ አገራት ከሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች ጋር ግንኙነት ፈጥረው ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመናድ እስላማዊ መንግሥት የመመሥረት ተልዕኮ አንግበዋል ሲል ወነጀላቸው፡፡ ይህን ለማስረዳትም ጥር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ማታ ከኹለት ሰዓት ዜና በኋላ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹ጅሐዳዊ ሃረካት› የተባለ ዘጋቢ ፊልም ቀረበ፡፡ በዘጋቢ ፊልሙ ላይም መንግሥት አቡበከር አሕመድን ጨምሮ አምስት የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው አባላት በድብቅ ካሜራ የተቀረፁ ምስሎቻቸውን በማሳየት “ጥፋተኝነታቸውን ለሕዝብ ያሳይልኛል” ያለውን ጉዳይ በሚፈልገው መንገድ አቀረበ፡፡

“ድምፃችን ይሰማ!” በሚል መሪ ቃል የታጀበው የሕዝበ ሙስሊሙ እንቅስቃሴ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥልቀትና የሕዝብ ተሳትፎ እያገኘ ቀጠለ፡፡ አገዛዙ ፀብ አጫሪ እርምጃዎች እየወሰደ፣ የራሱን ሰዎች አስርጎ እያሰገባ ብጥብጥ ለማስነሳትና የሕዝበ ሙስሊሙን ተቃውሞ በቀላሉ ለማንበርከክ ጥረት ቢያደርግም እንቅስቃሴው በእጅጉ ሰላማዊ ነበር፡፡ ለሥርዓቱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ከማሳየት ጀምሮ ከሙስሊሞች እንቅስቃሴ በኋላ ሌሎች ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በስፋት ጥቅም ላይ ያዋሉት እጅን በማጣመር ወይም የ“ታስሬያለሁ/ታስረናል” የሚለውን ምልክት በማሳየት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡

አገዛዙ የሕዝቡ ሙስሊሙን እንቅስቃሴ መሪዎች አስሮ ግፍ ከመፈፀም እስከ ማሳደድ የደረሰ ከባድ ጫና ምክንያት ንቅናቄው ቀስ በቀስ የተዳፈነ ቢመስልም፣ የተቃውሞ ስልቱ ግን ለሌሎች ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች አርአያነት ያለው ነበር፡፡ አገራዊ ለውጡ ቅርጽ እንዲይዝና አሁን ከደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ ያደረገው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡

ከኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም በኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰ፡፡ በሕዝባዊ እንቅስቃሴው ላይም የኦሮሞ ወጣቶች ማስተር ፕላኑን አንቀበልም የሚለውን ተቃውሞ ለማስተጋባት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሲያደርጉት እንደነበረው፣ ኹለት እጆቻቸውን አጣምረው የ‹X› ምልክት በማሳየት በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመለጠፍ ተቃውሟቸውን ማሰማት ቀጠሉ፡፡ ሕዝባዊ ተቃውሞው አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ የቀጠለ ሲሆን፣ በሒደቱ ከፍተኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ጨምሮ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲታሰሩ፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ በጣም ብዙ ንብረትም ወድሟል፡፡

አገዛዙ ያሰረውን አስሮ የገደለውን ገድሎ ማስተር ፕላኑን እንደሚሰርዝ ገለጸ፡፡ በዚህም ምክንያት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ የተቀዛቀዘና የተዳከመ መሰለ፡፡

አገሪቱ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ባለችበት ጊዜ ነው ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ሌላ ታሪክ ቀያሪ ክስተት የተፈጠረው፡፡ በጎንደር ከተማና አካባቢው ካሉ አካላት ጋር በመቀናጀት፣ ከወልቃይት አማራ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት መሀከል የተወሰኑትን አፍነው ለመውሰድ፣ ከስድስት ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ ሲያሴሩ የከረሙት የትግራይ ልዩ ኀይል አባላት፣ ከፌደራል ፖሊሲ ጋር በመተባበር ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ለመያዝ ያደረጉት ጥረት የከሸፈው በዚኸው ዕለት ነበር፡፡ ኮ/ል ደመቀ የጸጥታ ኀይሉ አባላት ሕጋዊ ከሆኑ ማታ ሳይሆን ጠዋት ሊያናግሩት እንደሚገባ ቢገልጽላቸውም፣ አሻፈረኝ ብለው በኀይል ለማፈን ሲሞከሩ ኮ/ል ደመቀ ራሱን ለመከላከል በወሰደው እርምጃ ከልዩ ኀይሉ አባላት መሀከል ስምንቱ ተገደሉ፡፡

ይህ በኮ/ል ደመቀና በሌሎች የወልቃይት አማራ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ላይ የተቃጣው የእስርና የግድያ ሙከራ መላው የጎንደርን ሕዝብ በቁጣ ያነቃነቀ ክስተት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ እጅግ ብዙ ሕዝብ የተሳተፈበትና ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ፡፡ በዚህ ሰልፍ ላይ የወጣው ሕዝብ ከአማራ ክልልም አልፎ “የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የእኛም ደም ነው፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይፈቱ፤” ወዘተ. የሚሉ መፈክሮችን አሰማ፡፡

ይህ ብዙዎችን ያስደሰተና በሕወሓት በኩል “እሳትና ጭድ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች የኅብረት መንፈስ ያለመለመ አካሄድ በባሕርዳርና በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞችም በስፋት ተንጸባርቋል፡፡ የ‹X› ምልክቱም አድማሱን እያሰፋ በሁሉም የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

በዚህ ምክንያት ቀድም ሲል በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ታጥሮ የነበረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደጊዜ አድማሱ እየሰፋና ሥርዓቱን እየተገዳደረ ሲመጣ፣ መንግሥት ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ አገሪቱ ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ፡፡

አዋጁን መሠረት አድርጎም በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በተለይም የአማራና ኦሮሚያ ክልል ወጣቶች በገፍ ይታሰራሉ፡፡ ብዙዎች በየወታደራዊ ማሰልጠኛ ጠቢያው ከተወሰዱ በኋላ “አይደገምም” የሚል ቲሸርት ለብሰው እንዲታዩ ተደረገ፡፡

ኢሕአዴግም “የምታገልለትን ዓላማና መስመር የሳተ የአስተሳሰብ መዛባት ችግር ገጥሞኛል፤ እንደ ዴሞክራሲያዊ፣ ልማታዊ፣ የለውጥ አራማጅ ታግሎ የሚያታግል ድርጅታዊ አመራር፣ ቀደምት የድርጅቱ መሪዎች የነበራቸውን አቅጣጫና መስመር ለቅቆ ሕዝብን ተጠቃሚ የማያደርግ፣ የሌሎችን [የኒዮ-ሊብራል ኀይሎችን] ዓላማ ሙሉ ለሙሉና በከፊል በመውሰድ በግል ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ መስመሮችን የማራመድ፣ የጋራ ርዕዮተ ዓለም ብለን ካሰመርነው መስመር የማፈንገጥ ሁኔታ በድርጅቱ ውስጥ ታይቷል፤ በውስጣችን በተለይ ደግሞ በአመራር ደረጃ በመንግሥታዊ ሥልጣን የነበረው አተያይና አጠቃቀም ፈር እየለቀቀ መሄዱን ተከትሎ፣ ለሕዝብና ለአባላት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ መስጠት አልተቻለም፤” በማለት “ጥልቅ ተሐድሶ” ያለውን መርሐ-ግብር ነድፎ በስብሰባና ግምገማ ላይ ተጠምዶ ከረመ፡፡

መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም. የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለስድስት ቀናት ባካሄደው ግምገማ ሊቀመንበሩን አቶ ሙክታር ከድርንና ምክትላቸውን ወ/ር አስቴር ማሞን ከኀላፊነታቸው አነሳ፡፡ በምትካቸው የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ የነበሩትን አቶ ለማ መገርሳን ሊቀመንበር፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩን ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ጥቅምት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው አምስተኛ የሥራ ዘመን ኹለተኛ ዓመት ኹለተኛ አስቸኳይ ጉባኤ አቶ ለማ መገርሳን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አድርጎ መርጧል፡፡ በክልል ምክር ቤቱ ከተሾሙት የክልል ካቢኔ አባላት ውስጥ፣ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፣ ቀጥለውም የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሆነዋል፡፡

በወቅቱ ሕወሓት፣ ብአዴንና ደኢሕዴን የጎላ የአመራር ሽግሽግ ባያደርጉም ቆየት ብሎ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እስከ ረቡዕ፣ ኅዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. 35 ቀናት የፈጀ ስብሰባ አካሂዶ ዘጠኝ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል፡፡

ይኹን እንጂ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆኑ በግንባር ደረጃ የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች፣ ግምገማዎች፣ “ጥልቅ ተሐድሶ” የተሰኘው የድርጅቱ መርሐ-ግብር እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለ ማርያም ደሳለኝ ያዋቀሩት “በምሁራን የተደራጀ ነው” የተባለው አዲስ ካቢኔ መፍትሔ ሊያስገኙ አልቻሉም፡፡ አገዛዙ ዜጎችን በገፍ በማሰር፣ የኢንተርኔት አገልግሎትን በመዝጋት፣ በውጭ አገራት የሚንቀሳቀሱ የሚዲያ ተቋማትን በአሸባሪነት ፈርጆ ጣቢያዎችን የሚከታተሉ ዜጎችን በማሰር ወዘተ. ሕዝባዊ ተቃውሞውን ሊገታው አልቻለም፡፡ ይልቁንም የሕዝቡ ተቃውሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ መሄዱ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መሀከል የልዩነት በር ከፈተ፡፡

በግንባሩ አባል ድርጅቶች መሀከል የተከሰተው ልዩነት እየተባባሰ ሲሄድና ሥርዓቱ የሕዝቡን ጥያቄ የመመለስ አቅሙ እየተዳከመ ሲመጣም፣ ለኹለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገደደ፡፡ ለስደስት ወራት ይቆያል የተባለው ይኸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዐርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀ ሲሆን፣ አዋጁ ዐርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ395 የድጋፍ ደምፅ፣ በ88 የኦሕዴድ አባላት የተቃውሞ ድምፅ እና በ7 ድምፀ ተዓቅቦ ፀደቀ፡፡ አዋጁ የፀደቀበት ሒደትና በድምጽ ቆጠራ ላይ የታየው አለመግባባትም ሌላ የልዩነትና የክርክር አጀንዳ ሆኖ ሰነበተ፡፡

ሐሙስ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. “በአገሪቱ ለሚታዩ ችግሮች እኔም የመፍትሔው አካል ለመሆን በፈቃዴ ከሥልጣን ለመልቀቅ ወስኛለሁ፤” በማለት ሥልጣን መልቀቃቸውን ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገለጹ፡፡

በአቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ ምትክ የግንባሩን ሊቀመንበር ለመምረጥ ከመጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ስብሰባ (ግምገማ) ላይ ተቀምጦ የሰነበተው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ማክሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ባወጣው መግለጫ የ42 ዓመቱን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን አስታወቀ፡፡ በኢሕአዴግ ምክር ቤት በተሰጠው ድምጽ መሠረት ዶ/ር ዐቢይ 108፣ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ 59፣ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል 2 ድምጾች ማግኘታቸው ታውቋል፡፡

በድርጅቱ የተለመደ አሠራር መሠረት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አቶ ኀይለማርያም ደሳለኝን በመተካት መቶ በመቶ በግንባሩ አባላት በተሞላው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሰየሙ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ በገቡት ቃልና በጀማመሯቸው መልካም ሥራዎች ምክንያት በምርጫ ከተመረጠ መሪ በላይ የሆነ ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡

ቃል እና ተግባር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዝብ ሳይመረጡ በአጭር ጊዜ እጅግ ከፍ ያለ ተቀባይነት ያገኙትን ያህል፣ ከቤተ መንግሥት ጥበቃ፣ እስከ ንግድ ባንክ ኀላፊና ሠራተኞች፣ ከአዲስ አበባ አስተዳደር እስከ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ እስከ ኢትዮ-ቴሌኮም በሁሉም መሥሪያ ቤቶች ዐይን ባወጣ መልኩ ኦሮሞዎችን በመሾም በአጭር ጊዜ ሕወሓትን የሚያስከነዳ አካሄድ መጀመራቸው አመራራቸውን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ ብዙዎች ተስፋ ያደረጉት የዴሞክራሲ ሽግግርም በሚያሳዝን ሁኔታ አደጋ ውስጥ እየገባ ይገኛል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞች ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ከመገንባት ይልቅ “ተራው የእኛ ነው፤” በሚል መንፈስ ሁሉም ነገር አይቅረኝ ሲሉ እየታዘብን ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይም በቃል ደረጃ ስለ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ እና ስለ ኢትዮጵያ እኩልነት እየሰበኩ በተግባር ግን በአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች እጅ እየወደቁ ይገኛሉ፡፡

ይህ ሁሉ የሚያሳየው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በትክክል እንደገለጸው መከራችን ገና ያላለቀ እና ከፊት ለፊታችን ከፍተኛ ትግል የሚጠብቀን መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም በሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ትግልና መስዋዕትነት የመጣው ለውጥ ተራው የእኛ ነው በሚሉ አክራሪ ኀይሎች እንዳይኮላሽ የመጠበቅ ኀላፊነት ወድቆብናል፡፡ ለውጡ እንዲቀለበስ ያለ እንቀልፍ የሚሠራው ግፈኛው የሕወሓት ቡድን መልሶ እንዳያንሰራራ ብቻ ሳይሆን ጊዜው የእኛ ነው የሚሉ ኀይሎች ለውጡን እንዳይበሉት በአንክሮ ልንከታተላቸው ይገባል፡፡ ያለን ምርጫ ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እስክትገነባ ድረስ በጽናት መታገል ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ ያለው ሁሉ የባርነትና የጥፋት መንገድ ስለሆነ ከቶውንም አንመርጠውም፡፡

(Visited 66 times, 1 visits today)
March 15, 2019

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo