Articles, News, Politics, ሕግ

አገር ግንባታ በኢትዮጵያ፤ ከትናንት እስከ ነገ -በቴዎድሮስ ኀይሌ

1.ንድፈሐሳባዊና ታሪካዊ መግቢያ

1.1. አገር ግንባታ ምንድን ነው?

በመጀመሪያ ‹አገር ግንባታ› (na­tion-building) የሚለው እሳቤ በአማርኛው አጠቃቀሙ የብሔርተኝነት ሦስት አዕማዶች ከሆኑት አገር፣ ሕዝብና መንግሥት በአንዱ ላይ ብቻ የቆመ ይመስላል:: ስለዚህም ለእንግሊዝኛው የተሻለው አገላለጥ ‹ብሔር ግንባታ› ነበር:: ይሁን እንጂ አገር ያለ ሕዝብና መንግሥት፤ ሕዝብ ቢያንስ በምኞት ደረጃ ያለ አገርና መንግሥት፤ መንግሥት ደግሞ ያለ አገርና ሕዝብ የተሟላ ትርጉም አይሰጡም:: የአገር ግንባታም ሊኖር አይችልም:: ስለዚህም አገር ግንባታ ስንል ግዛታዊ ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊና መንግሥታዊ መልኮችንም ያካተተ የአገራዊ ብሔር ግንባታ ሂደት መሆኑን እንረዳለን::

ሁለተኛ ‹ግንባታ› የሚለው የምህንድስና እሳቤ በተለምዶ ታቅዶና ታልሞ ብሔራዊ ማንነት፣ አንድነትና ዘላቂነት የመፍጠርና የማደራጀት ተግባር የሚል አንድምታ ስላለው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል:: ምክንያቱም በግንባታው ተግባር ላይ ያልታሰበባቸው ክስተቶችና የጋራ ተሞክሮዎችም የበኩላቸውን ሚና ስለሚጫወቱ:: ስለዚህም አገር ግንባታ ከዜሮ የሚጀምር ወይም ከሌላ ማኅበራዊ ቅርፅ አዲስ አገር የመፍጠር ጉዳይ ብቻ አይደለም:: እንዲያውም በአብዛኛው በነባር ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችና ማንነት ላይ የሚመሠረት የጥራትና ይዘት ማሻሻል ሂደት ሲሆን ይታያል::

ሦስተኛ አገራዊ ብሔር ወይም ብሔራዊ መንግሥት ግንባታ ፖለቲካዊ ርዕዮትን ከባህላዊ ንቅናቄ ያጣመረ ሂደት ነው:: የብሔር አመሠራረት አንድ ሕዝብ ከጋራ ታሪክ፣ ነባራዊ ሁኔታና በተለይም ከመጻኢ እጣ ፈንታው ጋር በሚኖረው ኅሊናዊ ቁርኝት ይወሰናል:: ማለትም ብሔር ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ልሣናዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ የመሳሰሉት ነባራዊ ግንኙነቶችና እነዚህ በጋራ ንቃተ ኅሊና ውስጥ በሚፈጥሩት ሐሳባዊ ነጸብራቅ ጥምረት የተዋሐደ ማኅበረሰብ ነው:: ብሔራዊ መንግሥታት በኀይል ቢመሠረቱም በአስተማማኝና ዘላቂ መሠረት ላይ የሚቆሙት በቂ ሕዝባዊ ተቀባይነት ሲያገኙ ነው::

1.2.መንግሥት ግንባታና ብሔር ግንባታ

የአገር ግንባታ ፖለቲካዊና ባህላዊ ሂደቶች በተግባር የተወሳሰቡና የማይነጣጠሉ ናቸው:: ሆኖም ከትንታኔ አኳያ በሁለት ከፍለን በመንግሥት ግንባታና በብሔር ግንባታ ዘርፎች ልናያቸው እንችላለን:: መንግሥት ግንባታ ለአገር አስተዳደር የሚያገለግሉ ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊና ሥርዓታዊ መዋቅሮች ላይ ያተኩራል:: በተለይም ወታደራዊና ኤኮኖሚያዊ ሀብቶችን የማማከል፤ የመሬት ስሪትና የግብር ሥርዓት የመዘርጋትና የመቆጣጠር፤ የፍትሕና ሕግ ሥርዓት የማቆምና የማስከበር ተግባራትን ያጠቃልላል:: በሌላ በኩል ብሔር ግንባታ አገራዊ ማንነትና ሥነ ልቦናዊ አንድነት ላይ የሚያተኩር ሂደት ነው:: ለዚህም ሲባል የጋራ ርዕዮተ ዓለም መንደፍ፣ የጋራ ሥርዓተ ትምህርት፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችንና ትዕምርቶችን ማደራጀት፣ ማበልፀግና መጠበቅን ያካትታል:: የተሟላ የአገር ግንባታ የሁለቱም የመንግሥትና የብሔር ግንባታ ድምር ውጤት ነው::

በየዘመኑ የመንግሥት አቋም መጠናከርና ተግባራዊ መስፋፋት ለብሔርተኝነት መፈጠርና መጎልበት ወሳኝ ነው:: መንግሥት በጦርነትም ሆነ በሰላም የአገር ግንባታ መሪ ተዋናይ ይሆናል:: ለብሔራዊ ጉዳዮች አጠቃላይ ማዕቀፉን በማመቻቸትና ዘውጋዊ ወይም ብሔረሰባዊ ድንበሮችን በመወሰን ረገድ ብርቱ ሚና ይጫወታል:: ስለዚህም ማናቸውም ጥናት በመንግሥታዊ ርዕዮቶች፣ ሥርዓቶች፣ ተቋማትና ሕግጋት ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት:: ሆኖም እይታችን የሚሟላው እነዚህ ላዕላይ ኀይሎች በማኅበረሰቦች አቋም ላይ የሚያስከትሉትን ታኅታይ ውጤቶችና ተጽዕኖዎች በሚዛናዊነት ሲያዋሐድ ነው::

በአጠቃላይ አገር ግንባታ ነባራዊና ኅሊና፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ፣ መንግሥታዊና ሕዝባዊ መልኮችን ያቀናጀ ሂደት ነው:: ይህንን ሰፊና ውስብስብ ሂደት ለመመርመር ታሪካዊ ሥነ-ዘዴ ምቹ አቀራረብ ነው:: የዚህ አንዱ ምክንያት እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ብሔራዊ መንግሥታት ታሪካዊ ማኅበረሰቦች መሆናቸውና ታሪክ በህልውናቸው ላይ ማዕከላዊ ሚና ስለሚጫወት ነው:: ሌላው ምክንያት ታሪካዊ እይታ በመንግሥትና ብሔር ግንባታ መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት፣ እንዲሁም የሁለቱን ሂደቶች መስተጋብር በረዥሙ በመመርመር የአገር ግንባታውን ለውጥና ቀጣይነት አሟልቶ ለመገንዘብ ስለሚያስችል ነው::

በዚህ ጥናት የኢትዮጵያን ረዥም የአገር ግንባታ ሂደት ለመመርመር የመንግሥታዊና ብሔራዊ ግንባታ ዘርፎችን ያቀናጀ የትንታኔ ማዕቀፍ እንጠቀማለን:: ለዚህም ሲባል ከላይ በቀረበው አጭር የብሔርተኝነት ንድፈ ሐሳባዊ ግንዛቤ መሠረት አራት የግንባታው አዕማዶችን ለይቶ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል:: እነዚህም 1) የጋራ ርዕዮተ ዓለም፤ 2) ሕዝባዊ ባህል፤ 3) የጋራ ተቋማትና መዋቅሮች፤ 4) የጋራ ሕግጋት፣ ወግና ልማዶች ናቸው:: በቅድሚያ እነዚህ በታሪክ ውስጥ ያለፉበትን ውጣ ውረድ በመከለስ አጠቃላዩን አገራዊ ምስል ለማግኘት እንሞክራለን::

ከታሪክ አንጻር ብዙውን ጊዜ መንግሥት ግንባታ ከብሔር ግንባታ ሲቀድም ይታያል:: በአገር ግንባታው ሂደት መንግሥትና ሕዝብ የሚጫወቱት ሚናም እንደየዘመኑ ተጨባጭ ሁኔታ ሊለያይ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ይዘቱ ሊዋዥቅ ይችላል:: በመንግሥት ግንባታ ረገድ የሚከሰቱ ውጣውረዶች በብሔር ግንባታውም ላይ አዎንታዊም አሉታዊም ተጽዕኖ ያሳድራሉ:: ለምሳሌ መንግሥቱ በውስጣዊ ሽኩቻዎች ሊዳከምና ሊከስም፣ አልፎም በቅኝ አገዛዝ ሥር ሊወድቅና ሊጠፋም ይችላል:: በተጓዳኝ የብሔሩ ባህላዊና ኅሊናዊ ህልውና እነዚህን ተግዳሮቶች በመቋቋም ፀንቶ ሊዘልቅ፣ አለያም ሊበረዝና መልኩን ሊቀይር ወይም ከናካቴው ሊጠፋም ይችላል::

የጥናታችን ዓላማ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን ከመፈተሽ በላይ ከተመክሯችን ለነገውም የአገር ግንባታ ጥረት የሚበጀንን ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ አገር ግንባታ አራቱ አዕማዶች የነበራቸውን ድምር ፋይዳ ወይም የግንባታውን ሂደት ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ ስኬትና ውድቀት የምንገመግምበት አጠቃላይ መስፈርት ያስፈልገናል:: የማንኛውም አገራዊ ብሔርተኝነት ግብ የመንግሥቱን ሕጋዊና ፖለቲካዊ ድንበር ከብሔሩ ባህላዊና ሥነ ልቦናዊ ድንበር ለማጣጣምና የጋራ አቅጣጫ ለማስያዝ ነው:: ይህንን ግብ ታሳቢ በማድረግ የብሔርተኝነት ጥናት ምሁራን የአገር ግንባታን ባሕርይ ከሚመዝኑባቸው ዐበይት መስፈርቶች መካከል ሂደቱ በተለይ 1) ማንነት፤ 2) አንድነት፤ 3) ዘላቂነት ከመፍጠሩ ላይ እናተኩራለን::

1.3. የኢትዮጵያ አገር ግንባታ ታሪካዊ እርከኖች

የኢትዮጵያን የአገር ግንባታ ሂደት ከታሪክ አንጻር ለመረዳት የየራሳቸው ልዩ ባሕርያት ባላቸው በሁለት ዐበይት እርከኖች መክፈል ያስፈልጋል:: የመጀመሪያው የታሪካዊት ኢትዮጵያ (historic Ethiopia) ወይም ብሔረ ኢትዮጵያ የታሪክ አንጓ በቅጡ ከማይታወቀው ጥንታዊ መነሻው ጀምሮ የዘመነ መሳፍንት እስካከተመበት እስከ 19ኛው ምዕት መንፈቅ ድረስ ይዘረጋል:: የዚህ ቅድመ ዘመናዊና ልማዳዊ አገር ግንባታ የጀርባ አጥንት ሃይማኖታዊነት ነው:: ሃይማኖት የማኅበረሰቡ ሕይወት አስኳል የሆነበትና የኢትዮጵያዊነትን ተፈጥሮ፣ ህልውናና ርዕይ በመለኮታዊ ፍልስፍና የሚረዳና የሚተረጉም ነው::

ሁለተኛው ከአፄ ቴዎድሮስ ንግሥ የሚነሳው የዘመናዊት ኢትዮጵያ የታሪክ አንጓ የአውሮፓ የቅኝ ተስፋፊነት ስጋት ካስከተለው የዘመናዊነት ምኞት ጋር የተከሰተ ሲሆን፣ የ“አዲሲቱ ኢትዮጵያ” (ተሃደስቲ ኢትዮጵያ) እሳቤ ብለን ልንሰይመው እንችላለን:: በሃይማኖታዊነት ፋንታ ዓለማዊነትን የብሔራዊ ሕይወት ማዕከል ያደረገው ይህ የአገር ግንባታ ሂደት ኢትዮጵያዊነትን ከፖለቲካዊ ርዕዮት አኳያ የሚረዳና የሚተረጉም ነው:: በመጤና እንግዳ ፍልስፍና፣ በአዲስ አስኳላ አፈራሽ ልሂቃዊ መደብ፣ ለአዲስ ቁሳዊ ሥልጣኔ የተሰለፈ ነው::

በታሪካዊትና በዘመናዊት ኢትዮጵያ መካከል ያለውን ዝምድና አስመልክቶ በታሪክ ምሁራን መካከል የተራራቁ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ:: ለአንዳንዶች እነዚህ ፍፁም አንድ ሲሆኑ፣ በሌላኛው ጥግ ደግሞ ሁለቱ ኢትዮጵያዎች በጭራሽ አይገናኙም:: በዚህ ጥናት ውስጥ ለማሳየት እንደሚሞከረው እነዚህ ሁለት የአገር ግንባታ እርከኖች ከመንግሥት ግንባታም ሆነ ከብሔር ግንባታ አኳያ መሠረታዊ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም በበርካታና ውስብስብ ድሮች የተቆራኙ፣ የቀጣይነትና ለውጥ ነፀብራቆች ናቸው:: ስለዚህ “ለወደፊቱስ ምን ይበጀናል?” የሚለውን ጥያቄ በታሪክ ተመክሮ ለመመለስ ሁለቱን ሂደቶች በንፅፅር መመርመር የግድ ይሆናል::

2.የኢትዮጵያ ዘመናዊ የአገር ግንባታ ሂደት

የጥናታችን ዐቢይ ትኩረት የሆነው የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ ከዜሮ አልተነሳም:: ከቀድሞው ብሔረ ኢትዮጵያ የሚለዩትን መሠረታዊ ባሕርያት ያገኘው ነባሩን በማሻሻል፣ ከባዕድ በማዳቀል፣ ከናካቴው አስወግዶ በመተካት ነው:: ከዚህ አልፎም አዳዲስ ርዕዮቶች፣ ባህሎችና እሴቶ፣ ተቋማትና ሥርዓታት በመፍጠር ጭምር ነው:: ይህንን ሰፊ የለውጥና ቀጣይነት ሂደት ከአራቱ የአገር ግንባታ አዕማዶች አኳያ በየተራ እንመርምር::

2.1. ከጋራ ርዕዮተ ዓለም አንጻር

የብሔሮችን ማንነትና ታሪክ ለመረዳት ዋናው ቁልፍ ርዕዮተ ዓለማቸው ነው:: ምክንያቱም ርዕዮታቸው አጠቃላይ ፍጥረተ ዓለሙን የሚተረጉሙበት፤ ማኅበራዊና ኅሊናዊ ድንበሮቻቸውን የሚደነቡበት፤ የገዛ ውልደታቸውን፣ ዕድገታቸውንና ተስፋቸውን የሚከትቡበት ፍኖተ ካርታ በመሆኑ ነው:: ደረጃውና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም ብሔሮች ማንነታቸውን የሚረዱበትና የሚያስረዱበት፤ እንዲሁም ሕዝባቸውን ማኅበራዊ አቅጣጫ የሚያስይዙበት ርዕዮት ይፈጥራሉ፣ ያበለፅጋሉ፣ ይጠብቃሉ:: በዘመናዊት ኢትዮጵያ አፈጣጠርና ግንባታ ከሁሉ የላቀውና መሠረታዊው ለውጥ ርዕዮተ ዓለማዊ ነው::

የታሪካዊት ኢትዮጵያ ማንነት መሠረት ሃይማኖትና ፖለቲካ፣ መንፈሳዊና ሥጋዊ በግልጽ የማይለዩበት አሐዳዊ ርዕዮተ ዓለም ነው:: በይሁዶ- ክርስትና እምነትና አስተምህሮ የተቃኘውና በተለምዶ “ሰሎሞናዊ ትውፊት” የሚባለው ይህ ብሔራዊ ርዕዮት የአገሪቱን ታሪካዊ ለውጦችና ተመክሮዎች እያጣጣመ በዘመናት የተሸመነ የትውስታዎች፣ ትዕምርቶችና እሴቶች ድር ነው:: በማኅበረሰቡ አንኳር ሥጋዊና መንፈሳዊ ትኩረቶችና ክስተቶች ላይ የሚያጠነጥን፣ እውነታና ፈጠራ የተቀላቀሉበት የብሔራዊው ስብዕና አፅመ ታሪክ ነው:: የኢትዮጵያን ማንነት፣ ሉዓላዊነትና ዘላለማዊ እጣ ፈንታ ይነድፋል:: የመንግሥቱ አፈጣጠር፣ አወቃቀርና ተልዕኮ፤ የሕዝቡ የደምና የታሪክ ዝምድናና ልዩ ባሕርይ ሁሉ መሠረት ነው:: የኢትዮጵያ አቋም፣ መንፈስና ርዕይ የሚገለፁባቸው ቁልፍ ባህላት፣ እሴቶችና ትዕምርቶች ምንጭ ነው::

በአንጻሩ የዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባታ መሠረት ሃይማኖትና ፖለቲካ፣ ምድራዊና ሰማያዊ የተነጣጠሉበት ብዝሃዊ ርዕዮተ ዓለም ነው:: በምዕራብ-ምሥራቅ ዓለማዊ ፍልስፍናና አስተምህሮ የተመራውና ቁሳዊ ብልፅግናና ግብ ያደረገው ይህ ታሪካዊ ሂደት በአጭር ጊዜ ሁለገብና ሥር ነቀል ለውጦችን በማስከተል የአገሪቱን ብሔራዊ መልክ በማያዳግም የቀየረ ነው:: ከአፄ ቴዎድሮስ አንስቶ የአዘማኞቹ ነገሥታትም ሆነ የሪፑብሊካውያኑ መሪዎች ዋነኛ ምኞት የምዕራቡንና የምሥራቁን ቁሳዊ ሥልጣኔ ቀድቶ ለመትከልና ለማስፋፋት፣ ሕዝቡንም በዚህ ፀጉረ ልውጥ ሥርዓት አስልጦ ለማስገባት የታለመ ነበር::

የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ መሪ ቃል “አዲሲቱ ኢትዮጵያ” ልንለው እንችላለን:: በአመዛኙ ወደፊት አቅጣጫ የተቃኘ፣ ባዕዳን ርዕዮቶች የተፈራረቁበት፣ እንግዳ ተቋማትና ሥርዓታት የቆሙበት፣ አዳዲስ ማኅበራዊ መደቦች የተፈጠሩበት ነበር:: የመንግሥት ግንባታውም ሆነ የብሔሩ እሳቤና መገለጫዎች ለውጣ ውረድና ለውዥቀት የተጋለጡበት ነበር:: ከለዘብተኛ ጥገናዊ እስከ ሥር ነቀል አብዮታዊ ጥጎች የተራመደው አገራዊ ብሔርተኝነት የኢትዮጵያዊነትን መደባዊና እምነታዊ ቅጥሮች አፍርሶ በሰፊና አካታች ሕዝባዊ ሉዓላዊነት ተክቶታል:: ከብሔርተኝነት መርሆች አኳያ የአገር ግንባታው ያለፈበትን ታሪካዊ ሂደት በሦስት ምዕራፎች ልንከፍለው እንችላለን::

የመጀመሪያው በሥርወ-መንግሥታዊ መርህ (dynastic principle) የቀጠለ ጥገናዊ ምዕራፍ ከዘመነ መሳፍንት ማክተም አንስቶ እስከ 1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ድረስ ያለው አንድ ምዕተ ዓመት ገደማ ነው:: ይህ ከብሔረ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊት ኢትዮጵያ መሸጋገሪያ እርከን የአገር ግንባታው ታሪካዊና ባህላዊ መሠረቱን በጅምላ ሳይለቅቅ በዝግታና በጥንቃቄ (በጃፓን አርአያነት) እየመረጠና እያዋዛ ለማዳቀልና ለማሻሻል የሚሻ ነበር:: እያደር ኢትዮጵያዊነት ከባህላዊና እምነታዊ ወደ ሕጋዊና ፖለቲካዊ የዜግነት እሳቤ ያዘነበለበት ነበር:: የ1923 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በተለይ ከአድዋ ጦርነት (1888 ዓ.ም.) በኋላ ስልታዊና ሥርዓታዊ ፈር የያዘው የዘመናዊነት ሂደት ከፍተኛ ነጥብ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል::

ሆኖም የፋሽስት ጣልያን ጣልቃ ገብነት (1928-1933 ዓ.ም.) ይህን ታዳጊ ሂደት በማደናቀፍ በአገር ግንባታው ይዘትና አቅጣጫ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል:: ጣልያን በአምስቱ የወረራ ዓመታት ያስከተለችው ጉዳት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ህልውና እስካሁንም የሚፈታተን ነው:: የፋሽስት አስተዳደር የኢትዮጵያዊነትን መሠረቶች ማኅበረሰቦች፣ እምነቶች፣ ተቋማትና ሥርዓቶች፣ ታሪክ፣ ባህል፣ እሴቶች፣ ትዕምርቶችን (ስሟንም ጭምር) ጠራርጎ ለማጥፋት የታለመ ነበር:: የኢትዮጵያን ብሔራዊ ድር ለመበጣጠስ በዘውግ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ አውራጃ፣ መደብ፣ ትውልድና ሞያ በመከፋፈል ማኅበራዊ ጥላቻ፣ ግጭትና ቀውስ በማባባስ ስልት ላይ ያተኮረ ነበር::

ይህ የተሳካ የቅኝ ወረራ በ1933 ዓ.ም. ወደ አልጋው የተመለሰውን አፄያዊ ሥርዓት ምዕራባዊ ሥልጣኔን በፍጥነት መቅዳትን ብቸኛው የብሔራዊ ህልውና ዋስትና አድርጎ እንዲቆጥር አስገድዶታል:: እያደርም ፈሩን የለቀቀ የዘመናዊነት ጉጉትና የባዕድ አምልኮ ነግሦ፣ ምዕራባዊነት በተራማጅነት ተወድሷል:: ታሪካዊውና አገር በቀሉ ደግሞ በወግ አጥባቂነት፣ ዘልማዳዊነትና ኋላ ቀርነት ተፈርጇል:: በውጤቱም ግንባታው አገራዊ ወዝ እያጣ፣ ነባሩ የኢትዮጵያዊነት እሳቤ በአዲስ ብሔራዊ ርዕዮት እንዲተካ ግፊት አስነስቷል:: በተለይም ከ1950ዎቹ አጋማሽ አንስቶ የዘመናዊው ሥርዓት ተስፈኛው የአስኳላ ትምህርት ቀመስ መደብ በአገዛዙ ላይ በማመጽ፣ ተጻራሪ መልክና መንፈስ ያላቸው አገራዊና ዘውጋዊ ርዕዮቶች ሊፈጠሩ ችለዋል::

ሁለተኛው በአብዮታዊ መርህ (revo­lutionary principle) የተመራው ምዕራፍ በ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት የፖለቲካ ሥልጣን በተቆናጠጠው በወታደራዊው አገዛዝ (ከ1966- 1983 ዓ.ም.) ዘመን የተከናወነው ሥር ነቀል የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ነበር:: አጠቃላይ ሥርዓተ ማኅበራዊ አብዮት የተካሄደበትና የኢትዮጵያን ብሔራዊ አቋምና መንፈስ እንዲሁም የመንግሥቱን መዋቅር፣ ባሕሪና ተልዕኮ በእንግዳ ሶሻሊስታዊ ርዕዮት አፍርሶ የሠራ ሂደት ነበር:: በተለይም በመንግሥት ግንባታው ረገድ የተከናወኑት ሥር ነቀልና ዘላቂ ለውጦች ኢትዮጵያን በሪፐብሊካዊ ቅርፅና በሕዝባዊ ሉዓላዊነት መርህ ላይ ለማቆም አስችለዋል::

በአንጻሩ ደርግ ከአነሳሱ ጀምሮ በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት አቋሙና በብሔር ግንባታ ጥረቱ ጽንፍ አልረገጠም ነበር:: በተማሪው ንቅናቄ የተቀነቀኑት ማርክሳዊ- ሌኒናዊ ርዕዮቶች ለኢትዮጵያ ባዕድና የማይበጁ ናቸው የሚል እምነት ነበረው:: ይኹን እንጂ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የተባለው አገር በቀል ብሔርተኛ አቋሙ በሲቪሉ የግራ ኀይል የሰላ ትችት ስለተሰነዘረበት የሶሻሊስቱን መስመር ለመከተል ተገድዷል:: ስለዚህም በታኅሣሥ 11 ቀን 1967 ዓ.ም. ባወጣው “ኅብረተሰባዊነት” በተባለው የፖለቲካና ኢኮኖሚ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያዊነትን ከሶሻሊዝም ለማዳቀል ሞክሮ ነበር::

በደርግ ትንታኔ መሠረት ኅብረተሰባዊነት ከኢትዮጵያ አፈር፣ ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖቶች የመነጨ ፍልስፍና ነው:: ከታላላቅ ሃይማኖቶቻችን የሰብአዊ እኩልነት አስተምህሮ፣ ከአብሮና ተካፍሎ መኖር ባህላችን፣ እንዲሁም በብሔራዊ መስዋዕትነት ካሸበረቀው ታሪካችን የሚመነጭ የፖለቲካ ፍልስፍና ነው:: የኅብረተሰባዊነት አምስት ቁልፍ መርሆች ብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ አንድነት፣ ብሔራዊ በራስ መተማመን፣ የሥራ ክቡርነት እና የሕዝብ ጥቅም ቀዳሚነት ናቸው::

ወታደራዊው አገዛዝ ከሲቪሉ ግራ ክንፍ የወረሰው ሶሻሊዝምን ብቻ ሳይሆን የንቅናቄው መቂናጥ የነበረውን የብሔረሰቦች ጥያቄን ጭምር ነበር:: ይህን በተመለከተ በሚያዝያ 12 ቀን 1968 ዓ.ም. የታወጀው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም” (ኢብዲአፕ) አገዛዙ ከተቀናቃኞቹ ጋር ያለውን መሠረታዊ ልዩነቶች በግልጽ ያስቀምጣል:: ኢብዲአፕ የመደብ ተቃርኖን ከብሔረሰባዊ፣ ሃይማኖታዊና ጾታዊ ተቃርኖዎች በሚያስቀድመው ማርክሳዊ መርህ መሠረት የብሔረሰቦችን ባህላዊ ነጻነት ያረጋግጣል:: ነገር ግን ፖለቲካዊ ነጻነትን በአካባቢያዊ ራስ-ገዝነት ይወስናል:: የሲቪሉ ሃይል በተለይም በውስጡ የተቀፈቀፉት ዘውጋዊ ድርጅቶች የመደብ ተቃርኖን የበላይነት ለይስሙላ ቢያቀነቅኑም፣ በተግባር ብሔረሰባዊ ጥያቄን ከሁሉም ተቀዳሚ አድርገው ተሰልፈው ነበር::

ሦስተኛው በዘውጋዊ መርህ (ethnic prin­ciple) የተመራው የአገር ግንባታ ምዕራፍ የአማጺ ኀይሎች ጥምር የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ደርግን በትጥቅ ትግል ገርስሶ መንበረ ሥልጣኑን በግንቦት 1983 ዓ.ም. ከተቆናጠጠበት ይነሳል:: ዘውጋዊ ርዕዮት የበላይነቱን የተቀዳጀበትና አገዛዙ ወታደራዊ ድሉን ወደ ሥር ነቀል የአገር ግንባታ ሂደት የተረጎመበት ምዕራፍ ነው:: ለዚህ የዋለው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ርዕዮተ ዓለም በ1975 ዓ.ም. ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) ሲመሠረት አንስቶ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) መሪ የፖለቲካ አስተምህሮ የነበረው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ነው::

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ ተግባራዊ ሕግ የተቀየረባቸው ገዥ ሰነዶች የሽግግር ቻርተሩ (ከሐምሌ 15 ቀን 1983 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም.) እና በነሐሴ 1987 ዓ.ም. የታወጀው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የአገዛዙን ዘውግ ተኮር ርዕዮት መሠረታውያን ያሳያሉ:: ኢትዮጵያ አሐዳዊ ብሔር ሳትሆን ብዝሃዊ ወይም የብሔሮች ብሔር ናት:: ብሔራዊ መሠረቷም ሕዝባዊ ሉዓላዊነት ሳይሆን ዘውጋዊ ሉዓላዊነት ነው:: ስለሆነም ዜግነታዊ ብሔርተኝነት በዘውጋዊ ብሔርተኝነት ተተክቷል:: “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ፖለቲካዊ ነጻነት በማጎናፀፍ የመንግሥቱ አስተዳደራዊ መዋቅር መሠረት ተደርገዋል::

ምንም እንኳን ቻርተሩም ሆነ ሕገ መንግሥቱ የአገራዊው መንግሥት አሐዳዊ፣ ፌዴራላዊ ወይም ኮንፌዴራላዊ ስለመሆኑ በግልፅ ባይወስኑም በተግባር የተሠራው መዋቅር ዘውጌ ፌዴራላዊ ነበር:: በታኅሣሥ 2 ቀን 1984 ዓ.ም. የታወጀው የብሔራዊ ክልላዊ ራስ-ገዝ አዋጅ ቁ.7/1984 “ብሔር ወይም ብሔረሰብ ማለት በአንድ ኩታ ገጠም መልክዓ ምድር የሚኖር፣ አንድ የሚያግባባ ቋንቋና የአንድነት ሥነ ልቦና ያለው ሕዝብ ነው፤” ሲል ቢያብራራም፣ ኢሕአዴግ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አስተዳደራዊ እርከኖችን ለመወሰን የተጠቀመው ዋነኛ መስፈርት ቋንቋ ነበር:: የሕገ መንግሥቱ አወዛጋቢ አንቀፅ 39 ንዑስ አንቀፅ 5 በዚህ ላይ የጨመረው ማሻሻያ የጋራ ባህልን ብቻ ነው::

በአጠቃላይ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የተመራው የኢሕአዴግ አገር ግንባታ በብዙ ረገድ ከቀደሙት አገዛዞች ይቃረናል:: ወታደራዊውና ዘውዳዊው አገዛዞች የዘውግ ፖለቲካን እንደ ብሔራዊ አንድነት ስጋት ሲቆጥሩት፣ ኢሕአዴግ ሕጋዊና ተቋማዊ ቁመና በማላበስ የብሔራዊ አንድነት ዋስትና አድርጎታል:: አሐዳዊና የተማከለ ብሔራዊ መንግሥትን አፍርሶ ብዝሃዊና ያልተማከለ ዘውጋዊ መንግሥት ገንብቷል:: ከግል መብቶች ይልቅ ለቡድን መብቶችና ነጻነቶች አፅንኦትና ቅድሚያ ሰጥቷል:: ኢሕአዴግ አገራዊ ብሔርተኝነትን ችላ ከማለት አልፎ በጠላትነት በመፈረጅም ይወቀሳል::

2.2. ከሕዝባዊ ባህል አንፃር

ብሔሮች በፖለቲካዊው መንግሥት ቢመሠርቱም ቅሉ፣ ማንነታቸው ዘላቂ ዋስትና የሚያገኘው በባህል አንድነት አማካኝነት ነው:: የኢትዮጵያዊነት ልዩ ባሕሪ ወይም ብሔራዊ አቋም የተፈጠረው የትውልዶች ማኅበራዊ ዝንባሌዎችና ተሞክሮዎች በጋራ ታሪክ ላይ ባከማቹት የባህል አሻራ ነው:: የዚህ የባህል አሻራ አንዱ ዘርፍ የሆነውና ማኅበረ ሥነ ልቡናዊ ባሕሪ ያለው ባህል በአጠቃላይ የማኅበረሰቡን እምነት፣ ዕውቀት፣ ግብረገባዊነትና ሌሎች እሴቶችን ይመለከታል::

ከላይ የገለፅነው የዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ርዕዮተ ዓለም ረቂቅና ሐሳባዊ ነው:: ከየአገዛዙ ዕድሜና ከንዑስ መደቦች ወይም ጠባብ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅፅር አይዘልም:: በአንጻሩ ባህል ረቂቁና ውስብስቡ በሰፊው ሕዝብ ውስጥ የሚገዝፍበትና ህያው የሚሆንበት ዋነኛው መንገድ ነው:: በሌላ አነጋገር ባህል ለኢትዮጵያ አገር ግንባታ ወሳኝ ኀይል የሚሆነው ገዥውን ርዕዮተ ዓለም ሕዝባዊ መሠረት በማስያዝ የዕለት ተዕለት ሕይወት አካል ሲያደርግ ነው::

የብሔረ ኢትዮጵያ ባህል እምብርት ሃይማኖት ነው ብለናል:: ከ4ኛው መቶ አጋማሽ ወዲህ ታቦት ክርስትና የይሁዲነትና ክርስትና ቁልፍ ትዕምርቶች የሆኑት ፅላተ ሙሴውና ግማደ መስቀሉ የሚሰናሰሉበት፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊነትና በኩረ መንግሥትነት ማረጋገጫና የብሔራዊ እምነቱ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ዋነኛ መለያ ሆኖ አገልግሏል:: ኢትዮጵያዊነት በየደብሩና ጎጡ የሚሰበክበት መድረክ፤ ኢትዮጵያውያን በየእለቱ፣ በየሳምንቱ፣ በየወሩና አውደ ዓመቱ ማንነታቸውን በጋራ የሚያድሱበት ትዕምርታዊ ቁርባንም ነበር::

ከዚህም በላይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና የኢትዮጵያዊነት አስኳልና የዜግነት ቀንደኛ ቅድመ ሁኔታ በመሆን፣ ገዥና ተገዥን ሳይለይ የብሔሩን አባላት በእኩልነት የሚያሰናስል ርዕዮታዊ ባህል ነው:: በአጠቃላይ በአገሪቱ የተገነባው ሰፊ ሕዝባዊ ባህል መሠረት ነው:: ብሔራዊ ፊደል፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ ቀን መቁጠሪያ፣ ፍልስፍና፣ ቅኔ፣ ሕግጋት፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ አልባሳትና ቁሳቁስ፣ ኪነ ጥበብና ኪነ ሕንጻ፣ ሙዚቃ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ የመጻሕፍት ድጎሳ፣ ሕዝባዊ በዓላትና አውዳመቶች፣ የትምህርት ሥርዓቱና መላው ብሔራዊ የሕይወት ዘይቤ በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖት ላይ የቆመ ነበር::

የዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ሂደት ኢትዮጵያዊነት ከአሐዳዊ የባህል ግንዛቤ ይልቅ እንደ ብዝሃዊ ባህላትና ማኅበረሰቦች ድምር የተቆጠረበት ነው:: ከጠባቡ የብሔረ ኢትዮጵያ ባህላዊ ወሰን በመውጣት ወደዳር የተገፉ እምነቶችንና ማኅበረሰቦችን ለማካተትና መላውን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የሚያስተሳስር የጋራ ብሔራዊ ባህል ለመገንባት ያለመ ነው:: ሆኖም በነባሩና በአዲሱ መካከል የሚኖረውን መስተጋብር በመወሰን ረገድ የብሔር ግንባታው አስኳል የሆነው ባህላዊ ለውጥ ከፍተኛ ተግዳሮቶች ገጥመውታል:: ትልቁ ተግዳሮትም ከዚህ ሰፊ ባህላዊ ቅርስ ውስጥ የቱን መውሰድ፣ የቱን መተው፣ የቱንስ ማሻሻል ይቻላል፤ ሌሎች ማኅበረሰቦችስ አስተዋጿቸው ምንድን ነው? የሚለው ነበር::

በአጠቃላይ የዘመኑ አቅጣጫ ዓለማዊነት እየጠነከረ፣ ሃይማኖት ከብሔራዊ ባህል ጋር ያለው ግንኙነት እየላላና ባህል እንደ ግለሰባዊ ምርጫነት የተቆጠረበት ነው:: ሆኖም በዘውዳዊው ሥርዓት የብሔረ ኢትዮጵያን ባህላዊ ቅርስ ለአዲሱ ባህል ግንባታ ለማዋል ጥረቶች ተደርገዋል:: የዚህ ኹነኛ ምሳሌ ዕድሜ ጠገቡ የቤተ ክህነት ትምህርት በዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ አስተዋጽዖ የሚያበረክትበትን መንገድ የመፈለግ ጥረት ነው:: የግዕዝን ሥነ ጽሑፋዊ ሚና በአማርኛ የመተካት ዓይነት አንዳንድ ሂደቶች የመንግሥቱ ተፈጥሮአዊ ዕድገት ውጤቶች ነበሩ::

በተለይ እስከ ወታደራዊው አገዛዝ ማብቂያ ድረስ የትምህርት አጠቃላይ ግብ የጋራ ብሔራዊ ተስፋና እሴቶችን የሰነቁ፣ በአገሪቱ ባህልና ታሪክ መሠረት የያዙ፣ በዘልማዳዊና ደመነፍሳዊ ወገንተኝነት ያልተሰናከሉና ኀላፊነት የሚሰማቸው ዜጎችን መቅረፅ ነበር:: ስለዚህም በመላ አገሪቱ ሁሉን አካታች እሴቶችንና ትዕምርቶችን ለማበልፀግ ንቁ ሙከራዎች ይደረጉ ነበር:: ለምሳሌ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በሚያዚያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም. ከተከፈተ ጀምሮ አማርኛ የሥርዓተ ትምህርቱ አካል ሆኖ በወታደራዊውም መንግሥት ከግዴታ ትምህርት ዓይነቶች አንዱ ሆኖ ዘለቋል:: የኢትዮጵያ ታሪክም ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት የጋራ ኮርስ ይሰጥ ነበር:: ከ1940 አንስቶ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ትምህርት ቤቶች በወጥነት የብሔራዊ መዝሙር ወይም ሰንደቅ ዓላማ ሥርዓትን ያከናውኑ ነበር::

ዘመናዊ ብሔሮች ትምህርት ቀመስ በመሆናቸው የትምህርት መሠረቱ እየሰፋ ቢያንስ ማንበብና መጻፍ የሚችል ኅብረተሰብ ሲፈጠር ሌሎችም ኢመደበኛ የትምህርት መንገዶች ጠቀሜታቸው እየጎላ መጥቷል:: በዚህ ረገድ ዘመናዊ የመገናኛ ብዙሃን በአገር ግንባታው ፖለቲካዊም ባህላዊም ዘርፎች ውስጥ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው አዳዲስ ተቋማት መካከል ናቸው:: በመስከረም 1914 ዓ.ም. የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ በ1916 ዓ.ም. ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ምሥረታ ተነስተው እያደር የየወቅቱን ቴክኖሎጂ በመከተል የተስፋፉት ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ የሬዲዮንና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የመንግሥትን ዓላማ ለማስረፅ፣ የሕዝብን ድምፅ ለማሰማትም ይሁን የጋራ አገራዊ አስተሳሰብ ለመቅረፅ በጣም ጠቃሚ መድረኮች ነበሩ::

ሌላው ከትምህርት መስፋፋት ጋር ሕዝባዊ መልክ እየያዘ የመጣው ባህላዊ ተቋም ኪነ ጥበብ ሲሆን፣ በተለይ በቅድመ አብዮት ጀምሮ የዘርፉ ዐቢይ ትኩረት ታሪካዊ ጭብጦች፣ ብሔራዊ ጀግኖች፣ የዘመናዊነትንና የኢትዮጵያዊነትን ብሔራዊ አጀንዳዎችና እሳቤዎች የሚያንፀባርቁ ነበሩ:: በ1950ዎቹ መጨረሻ በዚህ ረገድ የታየው አጠቃላይ ኪነታዊ እመርታ አንኳር መገለጫዎች የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ ሙዚቃና ሥነ ጥበብ ልምላሜ ጊዜ የማይሽራቸው ድርሰቶችን፣ ተውኔቶችን፣ ጥዑመ ዜማዎችን አፍርቷል:: አጠቃላዩ ሂደት በዋነኝነት በአማርኛ ቋንቋ አማካይነት የሚገለጽ አዲስና ዘመናዊ ባህልና አስተሳሰብ በአስተማማኝ መመስረቱን አብስሯል::

በሌላ በኩል የአብዮተኝነት መንፈስ በአዲሱ ምሁራዊ መደብ ውስጥ እየጎላ ሲመጣ፣ ብሔራዊው ባህል ወርደ ጠባብና መላው ኢትዮጵያን የማይወክል ስለመሆኑ ተገቢ ጥያቄ ተነስቶበታል:: የኮሚኒስታዊ ርዕዮት የበላይነቱን ሲይዝ በባህል ላይ በተለይ በሃይማኖታዊ ባህል ላይ ቀጥተኛና እጅ አዙር ጥቃት ተከፍቶበታል:: ኢአማኒነት በወታደራዊው አገዛዝ የመንግሥት ይፋዊ “ሃይማኖት” ሆኗል:: የአገር ባህል ከዕለት ተዕለት ሕይወት እየራቀ እንደ ብርቅ ትርኢት የታየበት፣ ሰፊ የምዕራባዊና ምሥራቃዊ ባህል ወረራ የተፈጠረውን ክፍተት የሞላበት ሂደት ተከስቷል::

አግድምም በመላ አገሪቱ የተለያዩ ባህላዊ ማኅበረሰቦች መካከል መስተጋብራዊ እመርታ በመፈጠሩ፣ ፈጣን ባህላዊ ልውውጥና ለውጥ ከማዕከልና ከከተሞች አልፎ ገጠሩንና ዳር አገሩን ጭምር ያዳረሰበት ነው:: የዚህ ድርብ አገራዊና የባዕድ ባህል አስተላላፊ ደግሞ በተለያዩ ሲቪልና ወታደራዊ አገልግሎቶች በመላ አገሪቱ የተሰማራ አማርኛ ተናጋሪ ልሂቅ ነበር:: ሆኖም ዋነኛው የዘውጋዊ ቡድኖች ተቃውሞ የተመሠረተው ከባዕዳዊው የምዕራብ ምሥራቅ ባህል ይልቅ በአገራዊው የባህል ተጽዕኖ ላይ ነበር:: ይህም እያደር ከእርስ በርስ መረዳጃና ባህላዊ ድርጅቶች ወደ ዘውጋዊ የፖለቲካና ወታደራዊ ድርጅቶች ከባህል ነጻነት ጥያቄ ወደ ፖለቲካ ነጻነት ትግል ተሸጋግሮ ለመንግሥቱ ከፍተኛ ተግዳሮት ደቅኗል::

በዚህ ረገድ ዘውዳዊውና ወታደራዊው አገዛዞች የተከተሉት ብሔራዊ ፖሊሲ ባህላዊ ይዘት የሌለው ፖለቲካዊ አንድነት ፋይዳ ቢስ ነው የሚል ነበር:: የሁለቱ የባህል ግንባታ አቅጣጫና ይዘት እንደ ርዕዮተ ዓለማቸው የተራራቀ ቢሆንም ቅሉ፣ የባህል ውሕደት ስልታቸው ግን ኢትዮጵያን በአንድ ቡድን ባህል ሥር የሚጨፈልቅ (assim­ilationist) አልነበረም:: የባህላዊ ማኅበረሰቦች መሠረታዊ ልዩነቶች እንደተጠበቁ በቁልፍ ብሔራዊ ምልክቶች የተዋሃደና ከዘውጎች የላቀ አገራዊ ባህል የመገንባት (integrationist) እንጂ:: የግንባታው ቀንደኛ መሣሪያዎችም አማርኛ ቋንቋና ብሔራዊ የትምህርት ሥርዓት ነበሩ:: ስለዚህም ዘውጋዊ ባህሎችና ማንነቶች ባይደፈጠጡም ጠንካራ ዘውጋዊነት በሁለቱም አገዛዞች ይከለከልና ብሔራዊነት በውስጠ ታዋቂነት ይበረታታ ነበር::

ከዚህ አኳያ የኢሕአዴግ የባህል ፖሊሲ የተገላቢጦሽ ነው:: ዘውጋዊ ማንነቶችንና ባህሎችን በየራሳቸው ክበብ የሚገድብና የሚያጋንን፤ አገራዊ ባህሎችንና ትስስሮችን የሚያዳክም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል:: ኢሕአዴግ የሚያራምደው ብዝሃዊነት ‹በኅብረ- ባህላዊነት› (multiculturalism) ይገለጻል:: ነገር ግን በተግባር የዋለው የባህል ፖሊሲው የኅብረ- ባህላዊነት ቁልፍ እሳቤ የሆነውን በማኅበረሰቦች መካከል መስተጋብርን የመፍጠር፣ ብዝሃነትን በአንድነት ውስጥ የማስተናገድ ሚዛናዊ ቀመር የለውም:: ስለሆነም በመቀራረብና መተዋወቅ ፈንታ መራራቅንና ባይተዋርነትን የሚያባብስ፣ ሰፊ የተራክቦ መንገዶችንና ዕድሎችን ከመዘርጋት ይልቅ በጠባብ ፖለቲካዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ አፍራሽ (disintegrationist) ነው::

2.3. ከጋራ ተቋማትና መዋቅሮች አንጻር

የኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሌላው ፈርጅ በዘመናት የተፈጠሩና የዳበሩ የአገሪቱን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀት መልኮች፣ ተቋማትና መዋቅሮችን ይመለከታል:: ከጥገናዊነት እስከ ሥር ነቀል ለውጦች የዘለቀው የዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ሂደት፣ በአዲስ ርዕይ አዳዲስ ተቋማትና መዋቅሮች የተዘረጉበት፣ አዳዲስ ማኅበራዊ መደቦችም የተፈጠሩበት ነበር:: ከሁሉም ግንባር ቀደሙ አጠቃላይ ሥርዓተ ማኅበራዊ ለውጥ ነው::

የብሔረ ኢትዮጵያ ማኅበራዊ መዋቅር በግብርና መሠረት ላይ የቆመ፣ ከአጥቢያ እስከ ዙፋን በተዘረጋ የመሬት ሥሪትና የግብር ሥርዓት የተሳሰሩ ባላባታዊ፣ ካህናዊ፣ ወታደራዊና አርሶ አደር መደቦችን ያቀፈ ተዋረዳዊ እርከን ነው:: በአንጻሩ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ግንባታ በሂደት ይህንን በዝባዥ ሥርዓተ ማኅበር አፍርሶ አገሪቱን በብሔራዊ እኩልነት መርህ ላይ መሥርቷል:: ከ1966ቱ አብዮት በኋላ የባላባቱ መደብ ሲከስምና የኤኮኖሚ መሠረቱ መሬት ወደ ሕዝብ እጅ ሲዛወር፣ አዳዲስ የሠርቶ አደርና ንዑስ ከበርቴ መደቦች፣ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ሥርዓቶች ተስፋፍተዋል::

የብሔረ ኢትዮጵያ አገር ግንባታ ተቋማዊ ምሶሶዎች ቤተመንግሥትና ቤተክህነት መሰረት ከጥንታዊት አክሱም ይነሳል:: በጋራ ሃይማኖታዊ ርዕዮትና ባህል የተቆራኙ የአገር ግንባታው ፖለቲካዊና መንፈሳዊው ክንፎች ናቸው:: ይሁን እንጂ በዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ እነዚህ ተቋማት በዓላማና ተግባር ለመነጣጠልና አቋማቸውንና ሚናቸውን ለመቀየር ተገድደዋል:: በተለይ ቤተመንግሥት በ1966ቱ አብዮት ሥር ነቀል ለውጥ ተደርጎበታል:: ሰሎሞናዊ ሀረግ የሚቆጥረው ዘውድ ተገርስሶ በሪፐብሊካዊ መንግሥት ተተክቷል:: የአገዛዙ ቅቡልነት መሰረት ከሥልጣነ መለኮት ወደ ሥልጣነ ሕዝብ ተቀይሯል:: የዘውዱ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ትዕምርትነቱ አብቅቷል:: የርዕሰ ብሔርና ርዕሰ መንግሥት ጣምራ ውክልናውም በአዲሱ ሪፐብሊክ ተለያይተዋል:: በወታደራዊ መዋቅር የተደራጀው ባላባታዊ ገዥ መደብ በሲቪል መዋቅር ወደተደራጀ ወታደራዊ መደብ ተቀይሯል::

አሐዳዊም ቅርፅ ይኑረው ብዝሃዊ፤ ዘውዳዊም ይሁን ሪፐብሊካዊ፣ አብዮታዊም ሆነ ዘውጋዊ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ግንባታ መንግሥት እያደር በአቅሙ፣ በተደራሽነቱና በባሕሪው ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል:: ዘመናዊው መንግሥት ከሠራዊቱና ደህንነት ተቋማቱ አንስቶ ቁልፍ የሃይልና ምጣኔ ሀብታዊ ምንጮችን በመጠቅለል ጉልበት አዳብሯል:: በ1900 ዓ.ም ከተሞከረው የሚኒስትራዊ አደረጃጀት ተነስቶ በመላ አገሪቱ የተንሰራፋ ቢሮክራሲና በሲቪል አገልግሎት ኀይል የሚታገዝ ሰፊና ጥልቅ መዋቅር መፍጠር ችሏል:: በድኅረ ጣልያን በ‹ውስጥ አገዛዝ ደንብ› (ቁጥር 1፣ 1934) የጀመረው የተማከለ አገራዊ አስተዳደር የመዘርጋት እርምጃ በ1940 ዓ.ም ከጠቅላይ ግዛት እስከ ወረዳ አስተዳደር መሥርቶ አጠናቅቋል:: ይህ የጠቅላይ ግዛት አስተዳደር ሥርዓት ከዚህ በኋላ ጉልህ ለውጥ ያደረገው በ1955 ዓ.ም. ሐረርጌ ለሁለት ተከፍሎ ባሌ ሲፈጠርና ኤርትራ ስትደመር ነበር::

ከአብዮቱ ወዲህ የጠቅላይ ግዛት አስተዳደር ወደ ክፍለ ሀገር የተቀየረው በተወሰኑ ማሻሻያዎች ነበር:: ሆኖም መንግሥት ከቀበሌ እስከ ማዕከል በተዘረጋ የአስተዳደር መዋቅር፣ በትይዩ በተደራጁ በርካታ ሕዝባዊና የሞያ ማኅበራት፣ እንዲሁም በጥልቅ የፓርቲ ሰንሰለት አማካኝነት ቁጥጥርና ተደራሽነቱን አረጋግጧል:: በድጋሚ የ1984 ዓ.ም. ድንጋጌ ይህንን ታሪካዊ መሠረት ያለውን የክፍለ ሀገር አስተዳደር ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ቀይሮ አዲስ ዘውጋዊ የክልል መንግሥታት ተክቷል:: በአጠቃላይ መንግሥቱ ከልማዳዊው የሰላም ማስከበር፣ ግብር መሰብሰብና ፍትሕ ሰጪነት ኀላፊነቶቹ ወጥቶ በማኅበረሰቡ ሁለገብ ሕይወት ላይ ዋነኛ ተዋናይ፤ የሥልጣን፣ የክብርና የጥቅም ምንጭ ሆኗል:: እንዲያውም መንግሥቱ ሌሎችን ባህላዊና ልማዳዊ ተቋማትን የማግለል፣ የመጠቅለልና የመዋጥ ባሕሪው እየገነነ መጥቷል::

የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ በጥልቅ የነካት ሁለተኛዋ ተቋም ቤተ ክህነት ናት:: ይህቺ ተቋም የኢትዮጵያዊነት እሳቤ አፍላቂ፣ አስተዋዋቂና አራማጅ በመሆን ለሺሕ ዘመናት ዘልቃለች:: የብሔሩን ባህላዊና ኅሊናዊ ድንበር አስፋፍታለች:: የብሔራዊ ታሪክ ዘጋቢና የቀጣይነት መሃንዲስ፣ መንግሥቱ ሲዳከም ብሔራዊውን መንፈስ የምታተጋ ሆና ቆይታለች:: በዘመናዊት ኢትዮጵያ ቤተ ክህነት ከቤተ መንግሥት ጋር የነበራት አንድነት ላልቷል፣ የኢኮኖሚ ጉልበቷ ሳስቷል፤ ከብሔራዊ ፖለቲካ ተገልላ በመንፈሳዊ ተግባሯ እንድትወሰን ተገድዳለች:: የቤተ ክህነትን የብሔር ግንባታው ርዕዮተ ዓለማዊና ባህላዊ ሚና የተረከቡት አዳዲስ ተቋማት በዋነኝነት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሕዝባዊ ትምህርት (መገናኛ ብዙሃን ጨምሮ) ናቸው::

የዘመናዊነት ተቀጥላ የሆነው የፖለቲካ ሥርዓት በአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ላይ ያልተመሠረተ ፀጉረ ልውጥ ተቋም ነበር:: ከአፄው ዘመን እስከ ኢሕአዴግ የዘለቀው ፓርላማ ሲራራ ጥር 30/2012 1ኛ ዓመት ቁጥር 001

ከአስፈጻሚው መንግሥት ነጻ ወጥቶ እውነተኛ የሕግ አውጪ ተቋም ለመሆን አልቻለም:: የፓርቲ ፖለቲካም ቢሆን ሐቀኛ የብዝሃዊነትና ዲሞክራሲ መሣሪያ ለመሆን አልበቃም:: በተለይም በአገር ግንባታው ውስጥ የመንግሥቱ ዋነኛ ርዕዮተ ዓለማዊ ክንድ ምኑም ኢትዮጵያዊ የማይመስለው ወገንተኛ ፓርቲ ነው::

የፓርቲ ፖለቲካ በባዕድ ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተና ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅድመ ሁኔታዎች የሌሉት ባለ ሰፊ አውድ ተቋም ነው:: ሆኖም ይህ ዓለማዊ ተቋም ከአስገዳጅነት ያለፈ ሥር በሰፊው ሕዝብ ውስጥ አልሰደደም:: ከነባሩ ባህልና ማኅበራዊ እሳቤ በተቃራኒ የቆመና በጥራዝ ነጠቅነት የቀረ ነበር:: ከአገሪቱ ያልተቀዱት ጥቂት መለያ ትዕምርቶቹም እጅግ ጠባብና ከየአገዛዙ ያለፈ ዕድሜ አልነበራቸውም:: ቤተ ክርስቲያን በምዕመኖቿ ላይ ያላትን ያክል ጠንካራ ተጽዕኖ አልነበረውም::

ዘመናዊ ትምህርት በ1901 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ ከ1920ዎቹ ወዲህ ሲስፋፋ፣ ከአገር በቀል ሃይማኖታዊ ትምህርት ሥርዓቶች የተለየ ቅርፅና ይዘት ነበረው:: ተልዕኮውም ዓለማዊውን ዕውቀት፣ ክህሎትና ሞያ በማስጨበጥ አዲሱን ትውልድ በመንግሥቱ የዘመናዊነት ዓላማ መቅረፅ ነበር:: ለዚህ ኀላፊነት የተሰጠው የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስትር በ1923 ዓ.ም ሲመሠረት በአቡኑ መሪነትና በንጉሠ ነገሥቱ የበላይ ጠባቂነት ሥር ነበር::

ያም ሆኖ በድኅረ ጦርነቱ እንደ አዲስ ከሚኒስትር መሥሪያ ቤት እስከ መሠረተ ትምህርት ጣቢያ ተቋማዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ሰብአዊና ቁሳዊ ግብአቶች የሚቆረጡለት ግዙፍና ወጥ የትምህርት ሥርዓት ተዘረጋ:: ከ1941 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት የመሠረተ ትምህርት ቤቶችን በመላ አገሪቱ በማቋቋም ትምህርት ለሁሉም ዜጎች መዳረስ የሚገባው ሕዝባዊ መብት አደረገው:: ሂደቱ በአብነትና መድረሳ አሸጋጋሪነት ተነስቶ በ1943 ዓ.ም. እስከ ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚደርስ የሥልጠና፣ ትምህርትና ምርምር መሠረት ተጣለ:: ዘመናዊ አስተሳሰብ የሚያራምድ፣ በዘመናዊ ዕውቀት፣ ክህሎትና ሞያ የታጠቀ ሰፊ መሠረት ያለው መደብ ተፈጠረ::

2.4. ከጋራ ሕግጋት ወጎችና ልማዶች አንፃር

ብሔራዊ የሕግ መደላድል ማለትም የወል ሕግጋትን፣ ብሔራዊ ወጎችና ልማዶችን መፍጠር፣ ማስፋፋትና ማስከበር ሌላው የኢትዮጵያ አገር ግንባታ አካልና የአንድነት መሣሪያ ነው:: የታሪካዊት ኢትዮጵያ ልማዳዊ ሕገ መንግሥቶች ተደርገው የሚቆጠሩት ክብረ ነገሥት፣ ፍትሐ ነገሥትና ሕገ ወሥርዓተ መንግሥት ከዘመነ አክሱም የሚነሳው ብሔራዊ የሕግ ሥርዓት ግንባታ ጥረት አንኳር ውጤቶች ናቸው:: ሕግጋቱ በመንግሥት፣ አገርና ሕዝብ መካከል የሚኖሩትን ግንኙነቶች የሚወስኑና የሚገዙ በመሆን አገልግለዋል::

እነዚህ ሰነዶች የተዘጋጁት በአገሪቱ ታሪክ የተከሰቱትን ታላላቅ የኀይል አሰላለፍ ለውጦች፣ የመንግሥቱን መስፋፋትና መጠናከር አቅጣጫዎችን ተከትለው ነበር:: ትኩረቶቻቸው የየዘመናቸውን አንገብጋቢ ችግሮች መፍትሔ በመስጠት ላይ ነበር:: በአተገባበራቸውም በአገሪቱ ውስጥ በየአካባቢው የነበሩትን ልማዳዊ የሕግ ሥርዓቶች ከማስወገድ ይልቅ በላያቸው ተደርበው አገልግለዋል:: ከአጥቢያ እስከ ዙፋን፣ ከጭቃ እስከ ምስለኔ በተዘረጋ መዋቅር የሰላም፣ የፍትሕና የግብር ሥርዓት ማስተዳደሪያ ሆነዋል:: ያም ሆኖ ከብሔርተኝነት አኳያ ትልቁ ቁምነገራቸው በተለያዩ ማኅበረሰቦች፣ መደቦችና ክልሎች መካከል የጋራ ሥርዓተ ሕግጋትና ወጎችን በማበረታታትና የትስስር መንፈስን በማስፈናቸው ነው::

ዘመናዊ መንግሥታት ሕጋዊ ተቋማት በመሆናቸው ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ ተብለው በሦስት አበይት ክፍሎች ይዋቀራሉ:: ምንም እንኳን ይህ ዓይነቱ መዋቅራዊ ሙከራ ከ1900 ዓ.ም. ቢጀምርም፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ሰፊና ውስብስብ የሕግ ሥርዓት ግንባታ ኹነኛ መነሻ 1923 ዓ.ም. ነው:: በተለይ በሐምሌ 1923 የታወጀው የተጻፈ ሕገ መንግሥት አገር በቀሉን ከባዕዱ ለማዳቀል የሞከረ የመንግሥቱ ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ነበር:: ይህ ሰነድም ሆነ በዚያው ዓመት የወጣው የዜግነት ሕግ ዘመናዊት ኢትዮጵያን በሕጋዊ ማኅበረሰብነት ለመመሥረት የሚደረገው ጥረት አካል ነበር:: ሌላው በ1923 ዓ.ም. የወጣው የመጀመሪያው የወንጀል ሕግም ለአገሪቱ ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ፈር ቀዳጅ እርምጃ ነበር::

የ1923ቱ ሕገ መንግሥት በአገር ግንባታው መንግሥታዊና ብሔራዊ ፈርጆች ላይ ካደረጋቸው መሠረታዊ ማሻሻያዎች አንዱ በመንግሥቱ ረዥም ታሪክ ተግዳሮት ከሆነው የሥልጣን ሽኩቻና ቀውስ የፀዳ፣ ጠንካራና የተረጋጋ ዘውዳዊ ተቋም መመሥረት ነው:: በአዋጁ አንቀጾች 3 እና 4 አልጋውን ከሰፊ ሥርወ መንግሥታዊ መሠረቱ አላቅቆ በኀይለ ሥላሴ ሀረግ ብቻ መወሰኑ፣ “ለአልጋው ወራሽነት ያለውን ማናቸውንም ብዥታ ለመከላከልና በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ፅኑ ጉዳት ለማስቀረት፤” ነው:: ነገር ግን ይህ የማዘመን እርምጃ የዘውዱን የብሔራዊ አንድነት ምልክትነት አደጋ ውስጥ ጥሎታል::

ሌላው የሕገ መንግሥቱ ፋይዳ ዘመናዊ የዜግነት ድንጋጌ ማስተዋወቁ ነበር:: ከብሔረ ኢትዮጵያ ባለ ሁለት እርከን (ሃይማኖታዊ – ሕጋዊ) የዜግነት ተመክሮ ሃይማኖታዊውን ቅድመ ሁኔታ በማስቀረት በግዛተ መንግሥቱ ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በእኩልነት ሕጋዊ ዜግነትን አጎናፅፏል:: “የኢትዮጵያ ተወላጆች በሙሉ የግዛተ አጼው ዜጎች በአንድነት ብሔረ ኢትዮጵያን ይመሠርታሉ፤” ይላል:: ይህ ሰነድ ገና ያልበሰሉም ቢሆኑ ዘመናዊ የዜግነት መብቶችና ግዴታዎች እሳቤን ለማስተዋወቅም ሞክሯል::

የተሻሻለው የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥትም የመንግሥቱን ብሔራዊ አቋም የሚያጠናክሩ ድንጋጌዎችን አስፍሯል:: በዋነኝነት አማርኛ ለአንድ ሚሊኒየም ገደማ በልሣነ መንግሥትነት ቢያገለግልም፣ በይፋ የመንግሥቱ የሥራ ቋንቋ መሆኑ ተደንግጓል:: ብሔራዊ ሰንደቁን ዓለማዊና አካታች ለማድረግ የአንበሳው (ቤተመንግሥት) እና መስቀሉ (ቤተክህነት) ምልክቶችን አስቀርቶ ሌጣውን በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ወስኖታል:: በሌላ በኩል ብሔሩን ሙሉ በሙሉ ከዘውዱ በመነጠል እውነተኛ የሕዝባዊ ሉዓላዊነት እሳቤ ያንፀባረቀው የ1966ቱ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ነበር:: ይህ ተግባራዊ ለመሆን ያልታደለ ሰነድ በዜግነት ረገድ (አንቀፅ 23) ማንኛውም ከወላጆቹ አንደኛው ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የኢትዮጵያ ዜጋ መሆኑን ደነገጎም ነበር::

መንግሥትና ሃይማኖትን የማለያየት ግፊት የጀመረው በቅድመ ፋሽስት ወረራ ቢሆንም፣ ቤተ መንግሥትና ቤተክህነትን ከርዕዮትና ግብር አንድነት የነጣጠላቸው የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ነበር:: ዘውዳዊው አገዛዝ ሲገረሰስ በመንግሥቱና በብሔሩ መካከል የነበረው አሐዳዊነትም በይፋ እንዲቀርና በርዕሰ ብሔርና በርዕሰ መንግሥት እንዲከፈል ተወሰነ:: ነገር ግን በጥንታዊው ዘውድ እግር የተተካው አዲሱ ፕሬዚዳንታዊ ርዕሰ ብሔር የኢትዮጵያ አንድነትና ታሪክ ተምሳሌት የመሆን ክብርን ለማግኘት አልቻለም::

በአጠቃላይ በዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሂደት ሥርዓተ ሕግጋት፣ ወጎችና ልማዶችን አስመልክቶ የተከናወኑት ለውጦች የየአገዛዙን ርዕዮተ ዓለም የሚያንፀባርቁ ነበሩ:: የዘውዳዊው አገዛዝ ጥገናዊ ማሻሻያ ዓለም ዐቀፋዊ የሥነ ሕግ ተመክሮዎችን እየቀዳ ደረጃ በደረጃ የሚገነባና በሥርዓተ ማኅበሩ ላይ መሠረታዊ ለውጦችን ያላስከተለ ነበር:: ከላይ ከተጠቀሱት ሥርዓተ ሕግጋት ለውጦች በተጓዳኝ የአገር ግንባታ መሠረቶች በሆኑት በአስተዳደር፣ መሬት ስሪት፣ በመዋዕለ ነዋይና በግብር ሥርዓቱ ላይ የተደረጉት ለውጦች ጉልህ ቢሆኑም፣ ለአዲሱ ንዑስ ከበርቴ ምሁራዊ መደብ ግን ለዘብተኛና አድሃሪ ነበሩ::

ስለዚህም እነዚህ ዐበይት ሥርዓተ ማኅበራዊ ለውጦች የተካሄዱበት አብዮትና ወታደራዊው አገዛዝ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ግንኙነቶች በሥር ነቀል ሁኔታ የሚቀይሩ እርምጃዎችን ወስዷል:: በፈራረሰው ሥርዓት ምትክ የሚገነቡ መንግሥታዊና ብሔራዊ መዋቅሮችና ተቋማትን፣ እንዲሁም ለነዚህ የሚስማሙ ሕግጋትን ማውጣትና ተጓዳኝ ወጎችና ልማዶችን ማዳበር ነበረበት:: ይሁን እንጂ ደርግ ሕገ መንግሥቱን በ1980 ዓ.ም. እስካወጣበት ድረስ በአዋጅና ድንጋጌ ሲያስተዳድር ቆይቷል::

ኢሕአዴግ በሰኔ 1983 ዓ.ም. በድል አድራጊነት ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሲገባ የደርግ ሕገ መንግሥት ገና በአግባቡ በሥራ መዋል አልጀመረም ነበር:: ስለዚህም የመጀመሪያው ተግባሩ ይህንን የሚተካ ሥርዓተ ሕግ ለመመሥረት የሚያገለግል የሽግግር ቻርተር ማውጣት ነበር:: የኢሕአዴግ አገዛዝ በዘውጋዊ ርዕዮቱ ላይ ተመሥርቶ ያካሄደው የአገር ግንባታ ተግባር በከፊል ያለፉትን ሥርዓቶች ቅርሶች ለማፈራረስና አዲስ መንግሥታዊና ብሔራዊ ግንባታ ለማድረግ ያለመ ነበር:: የዚህም ሥር ነቀል ተግባር እምብርት በርካታ ክልላዊ መንግሥታት ከነሙሉ ሕገ መንግሥታቸው፣ የሕግና ፍትሕ ሥርዓትና መንግሥታዊ ወጎችና ልማዶቻቸው በአዲስ ትልም መገንባት ነበር:: 3.የአገር ግንባታው ባሕሪያት

የማንኛውም የአገር ግንባታ መድረሻ ግቦችና የብሔርተኝነት ርዕዮተ ዓለምና ንቅናቄ የሚያጠነጥንባቸው ቁልፍ ጉዳዮች ብሔራዊ ማንነት፣ አንድነትና ዘላቂነት ናቸው:: ከላይ ከአራት አምዶች አኳያ የተመለከትነው የኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሂደት ልዩና ግልፅ የብሔራዊ ማንነት ንቃተ ኅሊና ፈጥሯል? ጠንካራ የብሔራዊ አንድነት መሠረት ጥሏል? የአገሪቱን ህልውና ቀጣይነት አረጋግጧል?

በደምሳሳው ሲታይ በጥንታዊትና ታሪካዊት ኢትዮጵያ የተጣለው የብሔራዊ ማንነት መሰረት ለአገሪቱ አንድነትና ህልውና ወሳኝ ኀይል ሆኖ ከማገልገሉም በላይ በትውልዶች ቅብብሎሽ ወደ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ዘልቋል:: ይሁን እንጂ ዘመናዊው መንግሥት የወጠነውን አዲሱን ብሔርተኝነት በመገንባት ረገድ ማንኛውም አዘማኝ መንግሥት የሚያጋጥሙት የማንነት፣ የአንድነትና የዘላቂነት ተግዳሮቶች ተደቅነውበት ነበር::

3.1 ማንነት

ብሔራዊ ማንነት አንድ ብሔር ውስጣዊ አንድነቱንና ከሌሎች አቻዎቹ ልዩነቱን የሚረዳበት ታሪካዊና ማኅበረ ሥነ ልቡናዊ ግንዛቤ ነው:: በኢትዮጵያ ማንነት አመሠራረትም ሆነ ግንባታ ረገድ ራስ-ገለፅነት (self-definition) ወሳኝ ነጥብ ነው:: ‹ራስ-ገለፅነት›፤ ማለት አንድ ሕዝብ የጋራ መጠሪያውን ከመሰየም ጀምሮ እያደር በውስጡ የሚጎለብትና የቡድኑን ማኅበራዊና ኅሊናዊ ድንበሮች የሚያሰምር፤ አባላቱ ስለ ራሳቸው ያላቸውን ግንዛቤ የሚያዳብር አዳጊ የማንነት ስሜት ነው:: ኢትዮጵያዊ ማንነት በታሪክ ሂደት በውስብስብ ድሮች የተገመደና ለብሔሩ አባላትና ለተቀረውም ዓለም ጭምር ‹ማነው ኢትዮጵያዊ?› የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው::

ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያ የምትባል አገር፣ ሕዝብና መንግሥት ብሔራዊ ማንነት ነው:: ስለዚህ እንደማንኛውም ብሔርነት የስሜትም የፖለቲካም ማኅበረሰብነት ድምር ነው:: በአንድ ወገን መተሳሰሪያው የጋራ ርዕዮት፣ ታሪክና ባህል የሆነና ያለፈውን እድልና ፈተና ተመርኩዞ የወደፊቱን እጣ ፈንታ ተስፋ የሚያደርግ የጋራ ስብዕና መንፈስ ነው:: በሌላ ወገን ኢትዮጵያዊነት በግዛተ መንግሥቱ የሚገኙ ዜጎች ሁሉ በፖለቲካዊ ማኅበሩ አባልነት በቀጥታ በትውልድ የሚቀዳጁት ሕጋዊ ሰውነት ወይም ዜግነታዊ ማንነት ነው::

ከዘመነ አክሱም እስከ 1966ቱ አብዮት በበላይነት የዘለቀው የብሔረ ኢትዮጵያ ማንነት በሥጋዊና መንፈሳዊ ወይም ትውልዳዊና ርዕዮታዊ (ሃይማኖታዊ) ዝምድና ላይ የተዋቀረ ግንዛቤ ነው:: ኢትዮጵያዊነት ነገዳዊ፣ አውራጃዊ፣ ባህላዊና መደባዊ ዝንጉርጉርነት በደም፣ በታሪክና በእምነት የሚቃየጡበት አሐዳዊ ማንነት ነው:: የብሔረ ኢትዮጵያ ማቋቋሚያ ሰነድ የሚባለው ክብረ ነገሥት ይፋ እስከወጣበት እስከ መካከለኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጥብቅ መሠረት የያዘው የዚህ ማንነት ጥምር ባህላዊ መልኮች የሃይማኖት ጥራትና የሥልጣኔ የበላይነት ናቸው:: የኢትዮጵያን የእምነት ጥንታዊነት፣ ንጹሕነትና ትክክለኛነት፤ የሥልጣኔዋን ገናናነት፤ የመንግሥቷን ቀጣይነትና የነገሥታቷን ግርማዊነት፤ የሕዝቧን ሃይማኖተኝነት፣ ደግነት፣ ጀግንነትና ነፃነት ወዳድነት ያካትታል::

ኢትዮጵያውያን በረዥም ታሪካዊ መስተጋብር ያዳበሩት የማንነት ሥነ ልቡና ወደኋላ ከታሪካዊ-ትውፊታዊ መነሻቸው፣ ወደፊት ከአገራቸውና መንግሥታቸው እጣ ፈንታ ጋር የተቆራኘ ነው:: ኢትዮጵያ እግዚአብሔር ከመንግሥታት ሁሉ መርጦ በፀጋውና ረድኤቱ የማይለያትና ልዩ መሲሃዊ እጣ ፈንታ የተላበሰች ቅድስት አገር፤ ብሔራዊ ርዕይዋም የፈጣሪዋን ተልዕኮ መፈፀም መሆኑን አጥብቆ ያምናል:: በሦስት ሺሕ ዘመናት በሚሰላ ርዕዮታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሱ ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጠንካራና ዘላቂ የማንነት ስሜት አዳብሯል::

ይሁን እንጂ በተለይ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ በመንግሥቱ የኀይል መዋዥቅ፣ በእስላማዊ ኀይሎች፣ በኦሮሞና ሌሎችም ዳራዊ ሕዝቦች ፍልሰትና ወረራ ምክንያት በመንግሥትና ብሔር ግንባታው ሂደቶች ላይ ተደጋጋሚ መደናቀፍና አለመጣጣም ተከስቷል:: እስልምና ቀስ በቀስ ከጠረፋማው ወደ ማዕከላዊው ግዛት በመስፋፋት አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀለም ሊሆን ችሏል:: የዚህ ሂደት ከፍተኛ ነጥብ የሆነው የግራኝ አሕመድ ጦርነት (1517-1536 ዓ.ም.) እስልምናን በክርስቲያናዊው ደጋማ እምብርት የተከለና የላቀ ተጽዕኖ ላሳደረው የኦሮሞ ሕዝብ መስፋፋት በር የከፈተ ነበር::

ከ16ኛው ምዕት ለጥቆ የነበሩት ሦስት ምዕታት የኢትዮጵያን ባህላዊና ፖለቲካዊ መልክዐ ምድር ለዘለቄታው የቀየሩ፣ ነባሩን ብሔራዊ ርዕዮትና መንግሥት ያዳከሙና ከሞላ ጎደል የዘመናዊውን ኢትዮጵያ ገፅታ የቀረፁ ታላላቅ ክስተቶች አስተናግደዋል:: ማዕከሉን ጎንደር ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት ከ1625 እስከ 1761 ዓ.ም. እነዚህን የእስላም – ኦሮሞ ጥምር ኀይሎች ግስጋሴ መክቶ ሥልጣኑን ለማጥበቅ፣ ቤተክህነትንና ጦር ሠራዊቱን ለማጎልበት አልቻለም:: እንዲያውም ሰፊውን የአገሪቱን ደቡባዊ ግዛት ተቀምቶ ለህልውናው የሞት ሽረት የሚታገል ነበር::

ዘመነ መሣፍንት (1761-1847 ዓ.ም.) ይህ ሂደት በብሔራዊ ማዕከሉ ፍፁም መንኮታኮት የተደመደመበትና እስልምናና ኦሮሞነትን ያጣመሩ የየጁ የጦር አበጋዞች ሥልጣነ መንግሥቱን የተቆጣጠሩበት ዘመን ነበር:: ብሔራዊ መንግሥቱ በአውራጃዊ ኀይሎች የተከፋፈለበት፣ ሰሎሞናዊው ዘውድ ማዕረጉን ተገፍፎ ለታሪካዊ አንድነት ትዕምርትነቱ ሲባል ብቻ የተጠበቀበት ዘመን ነበር:: የየጁ መሳፍንት ባለፉት ሶስት ምዕታት በማዕከላዊውና ዳራዊው ማንነቶች መካከል የተደረገው ሰፊ መስተጋብርና ውሕደት ውጤቶች ናቸው:: ስለዚህም በብሔራዊው ፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉበት አቅም አዳብረዋል:: የብሔረ ኢትዮጵያን ማንነት አስገዳጅ መስፈርት ለማሟላት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትናን ተቀብለዋል:: አማርኛንም ልሣነ መንግሥት አድርገው ቀጥለዋል::

የዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባታ የወረሳቸው ሁለት የብሔራዊ ማንነት እርከኖች ናቸው:: በአንድ ወገን በፖለቲካዊም ባህላዊም (በዋነኝነት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት) ዝምድና የተሳሰሩ፣ የአገሪቱ ጠንካራና ግልፅ የማንነት ስሜት መሠረቶችና የአገር ግንባታው አስኳል ማኅበረሰቦች:: በሌላ ወገን ደግሞ ብሔራዊ ማንነታቸው በመንግሥቱ ፖለቲካዊ ዝምድና የተወሰነ፣ ከማዕከሉ በተለያየ የስሜትና ታማኝነት ርቀት ላይ የሚገኙ ዳራዊ ማኅበረሰቦች ናቸው:: የብሔረ ኢትዮጵያ አሃዳዊ ማንነት በርካታ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦችን ያገለለ ነበር::

ዘመናዊው የአገር ግንባታ የኢትዮጵያዊነትን አገራዊ፣ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ማንነት ግንዛቤ የማሻሻልና የመቀየር ሂደት ነው:: ዓላማውም የአገሪቱን ብዝሃነት በእኩል ማስተናገድና በስሜታዊውና ፖለቲካዊው፣ በአስኳሉና ዳሩ ማንነቶች ድንበር መካከል ያለውን ርቀት ማጥበብ ነበር:: ይህ ኢትዮጵያዊነትን የማዘመን አዎንታዊ እርምጃ ተቀዳሚ ትኩረቱ የኢትዮጵያን መለኮታዊ ስብዕና ወደ ዓለማዊ ስብዕና መለወጥና አሮጌውን ባለሁለት እርከን ማንነት በአንድ ህጋዊ ማንነት ወይም ዜግነት መተካት ነበር::

ይሁን እንጂ ዘመናዊው የማንነት ግንባታ ጉልህ ውሱንነቶችም ነበሩበት:: ዘመናዊት ኢትዮጵያ እንደ ብሔረ ኢትዮጵያ ለአዲሱ የአገር ግንባታ የሚሆን ግልፅ፣ ጠንካራና ዘላቂ ርዕዮተ ዓለም አልገነባችም:: በተለይ ከተማሪው ንቅናቄ አንስቶ በደርግና በኢሕአዴግ አገዛዞች ጭምር በጅምላ ተቀድተው ለአገር ግንባታ የዋሉት ፖለቲካዊ ርዕዮቶች ባዕድ፣ ግልብና ዋዣቂ በመሆናቸው የብሔሩን ማንነትና እጣ ፈንታ በግልፅ አያስቀምጡም::

የዘመነ ደርግ የአገር ግንባታ ከብሔር ግንባታ ይልቅ የመንግሥት ግንባታ ያመዘነበት ነበር:: በሙሉ ልብ ያልተያዘው የሶሻሊስት ኢትዮጵያዊነት ግንባታ ሕዝባዊ መሠረት ስላልነበረው ህልውናው ከአገዛዙ ዕድሜ አልዘለለም:: ዘመነ ኢሕአዴግ ደግሞ አገራዊ ብሔር ግንባታው ፍፁም ችላ ተብሎ በንዑስ ብሔራዊ ማንነቶች ግንባታ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር:: ዘውጋዊ የፌዴራል ሥርዓቱ “ሕገ መንግሥታዊ አርበኝነት” የሚባለውን ሳይቀር የአገራዊ ማንነት ግንባታን ያዳከመ ነበር:: ስለዚህም የጋራ ሕዝባዊ ባህልና እሴቶች እየከሰሙ፣ ከብሔራዊ ማንነት ይልቅ አካባቢያዊና ዘውጋዊ ማንነቶች እየጎሉ መጥተዋል::

በአጠቃላይ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ግንባታ በአገሪቱ ያሉትን ብዝሃዊ ማንነቶች የሚሻገር የጋራ ልዕለ ዘውጋዊ ስብዕና ሊፈጥር አልቻለም:: የአዲሲቱ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ የብሔረ ኢትዮጵያን ቅርስ በአግባቡ ለመጠቀም አልቻለም ወይም አልፈለገም:: ወይም ደግሞ ለታሪካዊው ማንነት የረባ አዲስ አማራጭ አላቀረበም:: ዘመናዊው ትውልድ ለባዕዳን ተጽዕኖ የተጋለጠና የማንነት ቀውስ የሚያራዠው መጢቃ በመሆኑ፣ ለመናፍቃዊና ጨለምተኛ አስተሳሰቦች ሰለባ ሆኗል:: የመንግሥቱ ህልውና የተመሠረተው በሥልጣኔ አራማጅነት ስለሆነ፣ ብሔራዊ ርዕዩ የምጣኔ ሀብታዊ ብልፅግና ነው:: ስለዚህም ለአዲስ ብሔራዊ ማንነት አስተማማኝ መሠረት አልተጣለም::

3.2.አንድነት

ብሔራዊ አንድነት ማለት የተለያዩ ማንነትና ፍላጎት ያላቸውን ማኅበረሰቦችና ቡድኖችን በጋራ ታሪክ፣ ባህልና ርዕይ ማስተሳሰር ነው:: በሕዝብና መንግሥት መካከል፣ በመንግሥት ልዩ ልዩ አካላትም መካከል የሚፈጠር የግብርና የዓላማ አንድነት ነው:: ብሔራዊ አንድነት መሠረታዊ ልዩነቶችን ሳይጨፈልቅ ብዝሃነትን በቁልፍ ላዕላይ ትስስሮች የሚያዛምድና የተቀናጀ መስተጋብራዊ ሥርዓት የሚፈጥር አንድነት ማለት ነው::

ታሪካዊው ኢትዮጵያዊነት በርዕዮታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ሥነ ልቡናዊ አንድነት ላይ የቆመ ብሔርተኝነት ነው:: አገርን፣ ሕዝብና መንግሥትን በአንድ አስተምህሮ፣ በአንድ መንፈስ፣ በአንድ ልሣን፣ ለአንድ ዓላማ የሚያቆራኝ ማኅበረሰብ ነው:: ከንጉሥ እስከ ባላገር ያሉ ማኅበራዊና መደባዊ እርከኖች ሽቅብ በጋራ ርዕዮትና ባህል እየታረቁ የአንድነት መንፈስ የሚጋሩበት ማኅበር ነው:: ብሔር የሚለው የግዕዝ ቃል እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊነት የማይነጣጠል ተፈጥሯዊ አንድነት አላቸው::

የብሔረ ኢትዮጵያ አንድነት ከላይ ለፖለቲካዊው መንግሥትና ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በሚኖር ታማኝነት፣ ከታች ደግሞ በማኅበረሰቦች ታሪካዊና ባህላዊ አብሮነት ሀረጎች የታሰረ ነበር:: ዘውዳዊው መንግሥት የኢትዮጵያ አስኳልና ዳር ማኅበረሰቦች አንድነት ዐቢይ ተቋማዊ ሰንሰለት ነበር:: የፖለቲካ ሥርዓቱ በማዕከላዊና (centripetal) ተስፈንጣሪ (cen­trifugal) ኀይሎች መካከል በሚደረስ ሚዛን ላይ የተመሠረተ ነበር:: የኢትዮጵያ መንግሥት በረዥም ታሪኩ በግዛቱ ያሉትን ዘውጋዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ብዝሃነቶች በአንድነት የማሰለፍ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አቅም አደርጅቷል:: በመላ አገሪቱ የሰላም፣ የፍትሕና የግብር ሥርዓት ዘርግቶ በጋራ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ማዕቀፎች ያስተሳስራል:: በዜግነት መብቶችና ግዴታዎች ያስተሳስራል:: በጋራ መስዋዕትነትና አርበኝነትም ብሔራዊ አንድነት ያጠናክራል::

ከመንግሥቱ በተጓዳኝ የአገሪቱ ብዝሃዊ ማኅበረሰቦች በበርካታ ድንበር ተሻጋሪ ሀረጎች የተሰናሰሉ ነበሩ:: ከጋራ መልከዓ ምድር ጀምሮ የጋራ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ እሴቶች፣ ተመክሮዎች፣ አብሮ መኖርና ሰጥቶ መቀበል ያደረጃቸው ዕድሜ ጠገብ ማኅበራዊ ግዴታዎች፣ ደንቦችና ወግ ልማዶች የአንድነቱ ታኅታይ መሠረቶች ናቸው:: እንደ ክርስትናና እስልምና ያሉ ነባር ሃይማኖቶች ዘውጋዊና አካባቢያዊ ድንበሮችን የሚሻገሩና በጋራ ባህላዊና ፖለቲካዊ አውድ ላይ የበቀሉ ናቸው:: ግዕዝ የብሔራዊ አንድነት አማርኛ ደግሞ የመንግሥታዊና ሕዝባዊ አንድነት መሣሪያዎች ሆነው አገልግለዋል::

የአገር ግንባታው የስሜትና የፖለቲካ ገፅታዎች መሳ ለመሳ የሆኑበትና ፍጹም ብሔራዊ አንድነት ያለው አገር የሚገኘው በተምኔታዊው ዓለም ብቻ ነው:: ኢትዮጵያውያንም ስለ አገራቸው፣ መንግሥታቸውና ብሔራዊ ማንነታቸው የሚኖራቸው ስሜትና ቅንዐት ወይም አገር ወዳድነት፣ አርበኝነትና ሕዝባዊነት መንፈስ በማንኛውም ወቅትና በመላ አገሪቱ ወርድና ቁመት ወጥና ያልተዛነፈ ሊሆን አይችልም:: ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋነኝነት የመንግሥቱ ፖለቲካዊ ቁመና በተለዋወጠበት ፍጥነትና ስፋት ልክ፣ በማዕከሉና ዳርቻው ወይም በነባሩና አዲሱ ማንነቶች መካከል በቂ ባህላዊና ትዕምርታዊ ትስስር አለመደርጀቱ ነው::

የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የዜግነት ሕግ ያቆመው፣ በፖለቲካዊውና ስሜታዊው ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ክፍተት በመድፈን ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ነው:: ዘላቂነት ባይኖራቸውም በሕዝብና መንግሥት መካከል አዲስ ባህላዊና ርዕዮታዊ አንድነት ለመፍጠርም ሙከራዎች ተደርገዋል:: ነገር ግን ከጥረቶቹ ሁሉ በመንግሥቱ ላይ የተደረጉት ሥር ነቀል መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ለውጦች በከፍተኛ ደረጃ የተማከለና ጠንካራ ተቋም መፍጠር ተሳክቶላቸዋል::

በአጠቃላይ ዘመናዊ ኢትዮጵያዊነት ያበበበትና አገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ተዋሐደ ብሔራዊ መንግሥትነት የቀረበችበት ወቅት መቼ ነው ቢባል የ1950ዎቹ ዐሥርት ይመስላል:: በሌላ በኩል አስገራሚነቱ በመጭው ዘመናት ለአገር ግንባታው ጥረት ፅኑ ተግዳሮት የሚደቅኑ ተቀናቃኝ ርዕዮቶችና ኀይሎችም ያቆጠቆጡት በዚሁ ዐሥርት ነበር:: ዞሮ ዞሮ የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ በበርካታ ምክንያቶች የተነሳ የታሰበውን ብሔራዊ አንድነት ለማምጣት አልቻለም::

የዘውዳዊው መንግሥት የማዘመን እርምጃዎች በታሪካዊት ኢትዮጵያ አስኳል ማኅበረሰብ መካከል የፈጠረው ስንጥቅ ቀዳሚው ተግዳሮት ነበር:: ኀይለ ሥላሴ አልጋውን ከታሪካዊው ብሔር ቁርኝት ለመነጠል ያወጁት የገደብ ሕግ መራር ተቃውሞ የገጠመው የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ተጋሪ ከነበሩ ወግ አጥባቂ አውራጃዊ መሣፍንቶች ነበር:: በሌላ ወገን የዘውዱ ዘገምተኛ ተራማጅነት ያላረካቸውና ለበለጠ መሠረታዊና ትርጉም ያላቸው ለውጦች ግፊት የሚያደርጉ ኀይሎችም ከራሱ ከመንግሥቱ ውስጥ በመነሳት በ1953 ዓ.ም. የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እስከማድረግ ደርሰዋል::

ከ1960ዎቹ መባቻ አንስቶ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ዑደት እየተቆጣጠረ የመጣው የአዲሱ ትውልድ ሥር ነቀል አብዮተኝነት በአባቶቹ ላይ ሙሉ ትውልዳዊ ጦርነት በመክፈት፣ ከናካቴው የታሪክና የባህል እትብቱን የበጠሰና የአገር ግንባታውን ሽግግር ያከሸፈ ነበር:: አማጺው ትውልድ በውስጡ የተፈለፈሉትን ርዕዮታዊ ልዩነቶች በማቻቻል የራሱን አንድነት ለማስፈን፣ በአገራዊ ጉዳዮችም የጋራ መግባባት መፍጠር አልቻለም:: ከናካቴው በጠላትነት እየተቧደነ ከሐሳብ ወደ ትጥቅ ሽኩቻ በመካረር ለውድቀት ተመቻቸ:: ከዚሁ አብዮታዊ ትውልድ የተገነጠለው ዘውጋዊ ጎራም የኢትዮጵያን ብሔራዊ አንድነት በግልፅ ለመፈተን ታጥቆ ተሰለፈ:: በአገሪቱ ውስጥ ከኀይል በመለስ የጋራ የፖለቲካ አውድ ጠፋ::

በ1966 ዓ.ም. አብዮቱን ከዳር ያደረሰው ወታደራዊ ደርግ በአገራዊ አንድነት ረገድ የማያወላውል አቋም ነበረው:: እንዲያውም የአገዛዙ ርዕዮት እምብርትና የቅቡልነቱ መሠረት ብሔራዊ ሉዓላዊነትና አንድነት ነበር:: እነዚህን ከባዕዳን ወራሪዎችም ሆነ ከዘውጋዊ አማጺያን ተከላክሎ ለማስጠበቅም ለ17 ዓመታት ኀልዮታዊና ወታደራዊ ዘመቻ አድርጓል:: ንዑስ ብሔራዊ የማንነትና የመብት ጥያቄዎችን ከሰላም ይልቅ በጉልበት ለማፈን ሞክሯል:: ይሁን እንጂ የደርግ ሶሻሊስታዊ ኢትዮጵያዊነት እጅግ መሠረተ ጠባብ በመሆኑ ዓለም ዐቀፍ የሶሻሊስቱ ጎራ ከደረሰበት ውድቀት ጋር አብሮ ሊንኮታኮት ችሏል::

የደርግ መውደቅ እንደ አንድነቱ ጎራ ሽንፈት ተቆጥሯል:: ስለዚህም በወታደራዊ ድል ሥልጣን የያዘው የኢሕአዴግ የአገር ግንባታ በአሸናፊው ዘውጋዊ መርህ ላይ የተመሠረተ ነበር:: አገራዊ አንድነትን አክስሞ በዘውጋዊ አንድነት ላይ ፌዴራላዊ ሥርዓትም አዋቅሯል:: ይሁን እንጂ በአገራዊና ሕዝባዊ ሉዓላዊነት የተተካው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ከአንድነት ይልቅ መነጣጠልን ያበረታታ ይመስላል:: እያደር ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ክፍፍሎች የገነኑበት፤ በብሔራዊና ንዑስ ብሔራዊ ማንነቶች መካከል ባላንጣነት የተካረረበት ሥርዓትን ወልዷል::

በደምሳሳው የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሂደት ፖለቲካዊው መንግሥት ባህላዊውን ብሔር አለቅጥ የተጫነበት ወይም ወደዳር የገፋበት ነበር:: ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የተነሳ፣ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ከጥንካሬው ይልቅ ልፍስፍስነቱና ተከፋፋይነቱ ሊያመዝን ችሏል:: ከናካቴው ከኢትዮጵያዊነት መንፈሱ እየራቀ ወደ ዘውጋዊና አውራጃዊ ጥጋጥግ በመንሸራተቱ ርዕዮታዊ ውዥንብር፣ ሰፊና መዋቅራዊ የማኅበረሰቦችና ቡድኖች ፍትጊያና ግጭት፣ አልፎም ብሔራዊ የመበታተን ስጋት አስከትሏል::

3.3.ዘላቂነት

ዘላቂነት የአገር ግንባታውን ታሪካዊና ኅሊናዊ ቀጣይነት የሚያሳይ ግንዛቤ ነው:: በተከታታይ ትውልዶች መካከል ስለአንድ ማኅበረሰብ የጋራ ባህል፣ ታሪክና ትውስታ እንዲሁም ስለ መጻኢ እጣ ፈንታው የሚኖረውን ቀጣይነት ይመለከታል:: ከጊዜ አንጻር ዘላቂነት በታሪክ ያልተቋረጠና የተመዘገበ ቀጣይነት ነው:: ይህ ማለት ግን በለውጥ ውስጥ ያለ ቀጣይነት ነው:: አንድ ብሔር የቀጣይነት ስሜቱን ሳያጣ ከፊሉን ወይም ጠቅላላውን ውጫዊ ባሕሪያቱን ሊለውጥና ሊተው ይችላል::

የኢትዮጵያ አገር ግንባታ መድረሻ ግብ ብሔራዊ ቀጣይነትን ማረጋገጥ ነው:: በዚህ ረገድ የታሪካዊት ኢትዮጵያ ዘላቂነት አንዱ መሠረት ግልፅ ብሔራዊ ርዕዮትና ርዕይ ነው:: ሰሎሞናዊው ትውፊት ከይሁዲነት አልፎ ወደ ክርስትና የተሻገረ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሥነ ልቡናዊ ዘላቂነት መሥርቷል:: ብሔረ ኢትዮጵያን በሃይማኖታዊ ኀልዮትና በሥርወ መንግሥታዊ መርህ በማረቅ የመንግሥቱን መረጋጋት፣ ፅናትና ቀጣይነት ለማረጋገጥ አስችሏል:: እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊነት የማዕዘን ድንጋይና የአገር ግንባታው ዘላቂ መሠረት ሆኖ አገልግሏል::

ሌላው የኢትዮጵያ አገር ግንባታ ዘላቂነት መሠረት ሕዝባዊ ባህል ነው:: ኢትዮጵያውያን ከቀደምት አባቶቻቸው ባህሎችና እሴቶች ቅርስ ጋር ያላቸውን የቀጣይነት ስሜት ይመለከታል:: እነዚህ ባህላዊ መሠረቶች እንደ ሃይማኖት ያሉ ሁሉን ዐቀፋዊ (universal) ባሕሪ ያላቸው ፅኑ እሴቶች ይሁኑ እንጂ፣ እያንዳንዱ ትውልድ ለኢትዮጵያዊነት ባህላዊ ንጣፍ የየተመክሮውን ድርሻ ማዋጣቱ አይቀርም:: በዚህ ዓይነት የለውጥና ቀጣይነት መወራረስ ሕዝባዊው ባህል ከታሪክ እየተስማማ የኢትዮጵያን ማንነት በጊዜና በቦታ የሚያሸጋግር ዋነኛው ድልድይ ነው::

የኢትዮጵያዊነት እሳቤ ለረዥም ዘመናት ተጠብቆ ሊኖር የቻለው በሰፊው ብሔራዊ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ነው:: ለዚህም አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያዊነት አዳዲስ ርዕዮታዊና ወታደራዊ ኀይሎችን ለማስተናገድና በየጊዜው የሚፈጠሩ ለውጦችን ለማጣጣም ያለው አንጻራዊ አቻቻይነትና ክፍትነት ነው:: አጠቃላይ የሥርዓቱ ማኅበራዊ ክፍትነትና የዕድገት መሰላሎችን ዘርግቶ ከአስኳል ማኅበረሰቡ ውጭ ያሉ ዘውጎችንና ባህሎችን ማካተቱ የአገር ግንባታው በራስ የመተማመን ምልክት ነው:: በየዘመኑ ኢትዮጵያ ስትዳከም መልሳ የምታንሰራራው በባህላዊና መንፈሳዊ ጥንካሬዋና አቻቻይነቷ ነው::

በዚህ ረገድ ታሪካዊው የአድዋ ድልም ሆነ የአምስቱ ዓመታት የአርበኝነት ተጋድሎ መንግሥትና ብሔር በአገሪቱ ህልውና ላይ ያላቸውን ታሪካዊ ሚና በግልፅ ያሳዩ ናቸው:: የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ሩሲያና ጃፓን በተሳካ ሁኔታ የአውሮፓን ቅኝ ወረራ የመከላከል ብቃቱንና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጥልቅ ታሪካዊና ማኅበራዊ መሰረት እንዳለው ያረጋገጡ ናቸው:: በተለይ የአምስቱ ዓመታት የጀግንነት ተጋድሎ የኢትዮጵያውያን ጠንካራ የብሔራዊ ማንሰራራት አቅም ምስክር ነው::

የአዲሲቱ ኢትዮጵያ እሳቤ ብሔራዊ መሠረቱን ከእምነት ወደ ፖለቲካዊ ርዕዮት በመቀየሩ፤ ለኢትዮጵያዊነት ሰፊ ትርጉም የሰጠና ብዝሃዊነትን የሚያስተናግድ እርምጃ መሆኑ አይካድም:: ነገር ግን እያደር አቅጣጫውን የሚያስቱ ድክመቶችንም የፀነሰ ነበር:: በተለይ የግንባታው ርዕዮተ ዓለም ጉራማይሌና ከአገዛዞች ዕድሜ የማይሻገር በመሆኑ የተነሳ የሚያስከትላቸው ለውጦች ቀጣይነት አልነበራቸውም::

ከባህላዊ ግንባታ አኳያ ነባሩን ባህላዊ ቅርስ መልኩን አሻሽሎ ለመጠቀም የተደረገው ጥረት አመርቂ አልነበረም:: ከባህል፣ ትምህርትና ማስታወቂያ ሚኒስትሮች አንስቶ የብሔር ግንባታውን የሚመሩ መንግሥታዊና ሕዝባዊ አካላት ዘመናዊና አካታች ባህል ለመገንባት ያደረጉት ጥረት በርዕዮታዊና መዋቅራዊ ውዥቀት የተጎዳ ነበር:: የባህል ቀጣይነቱ ዐቢይ መዘውር የነበረው ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት አገራዊ መሠረቱን ትቶ ሙሉ በሙሉ በባዕድ አስተምህሮ መተካቱ ትውልዳዊ የባዕድ አምልኮና የባህል ውልቃት ያስከተለ ይመስላል::

የግራ ዘመሙ አብዮተኛ ትውልድ የአገር ግንባታ እሳቤ በነባሩና አዲሱ፣ በጥንታዊውና በዘመናዊው፣ በሩቁና በቅርቡ መካከል ተቃርኗዊነትን አስፍኗል:: ቀጣይነትን ሳይሆን አዲስ ጀማሪነትን ታሪክ ሠሪነትን የሚያራምድ በመሆኑ ረዥም የታሪክ እይታና ኀላፊነት መንፈስ ተዳክሟል:: በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ ግፋ ቢል ከአፄ ቴዎድሮስ የሚሻገር አልነበረም:: ከነባሩ ኢትዮጵያዊነት ጋር የሚጣጣምበት ብልሃት ባለማግኘቱ፣ እትብቱን ቆርጦ የመጣል ሂደት ውስጥ ገብቷል::

በተለይም የደርግና ኢሕአዴግ አገዛዞች የተከተሏቸው ስልቶች የባህል ፖለቲካ ተጽዕኖ ያረፈባቸው፣ በብሔራዊና በዘውጋዊ ማንነት ላይ አፅንኦት የሚያደርጉ፣ አንዱ ለሌላው ተቃርኗዊና አፍራሽ ነበሩ:: ወታደራዊው አገዛዝ የብሔረ ኢትዮጵያ ቅርስ በጅምላ ሰፊውን ሕዝብ የማይወክል የፊውዳል ቅርስ ነው በማለት አውግዞ ከአዲስ ለመነሳት ሞከረ:: በተራው ኢሕአዴግ ደግሞ ከእኔ በፊት የነበሩት ሥርዓቶች በሞላ አንድ ዓይነትና በጅምላ ብሔረሰቦችን የማይወክሉ ናቸው በማለት ሌላ አዲስ ግንባታ ጀመረ:: በአጭሩ ዘመናዊው የአገር ግንባታ መሠረተ ሰፊ፣ አስተማማኝና ዘላቂ ብሔራዊ ባህልና ማንነት ለመገንባት አልታደለም::

4.ምን ይደረግ ?

የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ከሥርወ መንግሥታዊ ወደ አብዮታዊ ከዚያም ወደ ዘውጋዊነት ባደረገው ታሪካዊ ጉዞ ምክንያት የጥንታዊነትና ዘመናዊነት፣ ዜግነታዊነትና ዘውጋዊነት፣ ባህላዊነትና ፖለቲካዊነት፣ ወዘተ… መንትያነቶች በአገሪቱ ብሔራዊ ማንነት ግንዛቤ፣ የብሔርተኝነት ፖለቲካና ጥናት ውስጥ በሰፊው ይንጸባረቃሉ::

ስለዚህም ተቀዳሚው እርምጃ እነዚህን ጉራማይሌዎች የሚያስተናግድ ለአገር ግንባታው መሠረት የሚሆን ግልፅና አካታች ርዕዮተ ዓለም መንደፍ ይሆናል:: ሕዝብን ከሕዝብ፣ ሕዝብን ከመንግሥት፣ እንዲሁም የመንግሥትን አካላት በአዎንታዊነት የሚያቀራርብ መሆን አለበት:: የአገሪቱን የታሪክና ባህል ቀጣይነት የሚያረጋግጥና መጻኢ እጣፈንታዋንም በግልፅ የሚያስቀምጥ መሆን አለበት::

ከዚህም አልፎ አገራዊነት/ብሔራዊነትና ዘውጌነት የሚደጋገፉበትን መንገዶች መተለም ያስፈልጋል:: ምንም እንኳን ለብሔራዊው መንግሥት የሚኖር ውዴታና ታማኝነት መገለጫ እንደየማኅበረሰባዊና ወቅታዊ ጭብጦች ቢወሰንም፣ አገራዊነት ከዘውጌነት ንቃተ ኅሊና ጋር አብሮ ተባብሮ ሊኖር ይችላል:: ኢትዮጵያና ብሔረሰቦቿ በተቃርኖ የቆሙ ሳይሆኑ፣ ተደጋጋፊዎችና አንዱ ያለሌላው የተሟላ ትርጉም የማይሰጡ ናቸው::

ከታሪካችን እንደምንገነዘበው የአገሪቱ ህልውና ምርጫ በአሐዳዊነትና በመበታተን መካከል አይደለም:: ሁለቱም ተሞክረው ያላዋጡ መንገዶች ናቸው:: ስለዚህም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የአገር ግንባታ ሥርዓት ብዝሃነትና አሐዳዊነትን በዴሞክራሲ አማካይነት የሚያቻችል ነው:: ፌዴራሊዝም ለብዝሃነት ባለው ትኩረትና ዴሞክራሲ ለእኩልነት ባለው ትኩረት መካከል አለመጣጣም የለም:: ብዝሃዊ መንግሥታት በመገንባት ረገድ ቀንደኛው ተግዳሮት ሕዝቡ መንታ ዘውጋዊና ብሔራዊ ማንነት እንዲላበስ ማስቻል ነው:: ለዚህም ማንነት ንብርብራዊ ተፈጥሮ እንዳለውና በደመነፍሳዊ ጥጎች ብቻ እንደማይገደብ መገንዘብ ያስፈልጋል::

ያለንበት ፌዴራላዊ ሥርዓት በዋነኝነት በቋንቋ መሥፈርት የተሠራ መሆኑ መሠረታዊ ግድፈቱ ነው:: በተጨማሪ አብዛኞቹ የፌዴራል ሥርዓታችን ግዛታዊ አሐዶች ታሪካዊ መሰረት የላቸውም:: ይህም የክልሎችን ተቀባይነት አሳንሶታል:: ስለዚህም ተመራጩ የአገር ግንባታው ርዕዮት የባህል ነፃነትን ወይም ራስ ገዝነትን ኢግዛታዊ (በኮንሶሽየሽናል ዴሞክራሲ ተመራጩ) የሚያደርግ ሊሆን ይገባል::

የፌዴራል ሥርዓቱን ከዘውጋዊነት ወደ አስተዳደራዊነት አሐዶች መቀየር ብቻ አይበቃም:: አሁን እንደሚታየው ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከአገር ዐቀፋዊ ትብብር ይልቅ የክልሎች ፉክክር ማዕቀፍ እንዳይሆን፣ በክልሎችም ሆኑ ክፍለ ሀገራት መካከል ጠንካራ ድንበር ተሻጋሪ ትብብሮችና ትስስሮችን መፍጠር ያስፈልጋል::

የአገር ግንባታ ዕቅዶች የዜጎችን ባህላዊ አድማስ በድምር በሚያሰፉ እርስ በርሳቸው በሚሰናሰሉና በሚመጋገቡ ለውጦች መተለም አለበት:: ከርዕዮታዊና ባህላዊ ጉዳዮች በተጨማሪ መሠረቱ ሰፊ የሆነ ማኅበረ – ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎችንም ማካተት አለበት::

አገር ግንባታ ነባሩን የሚያጠናክር፣ የሚያሻሽልና አዲስ የሚፈጥር ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስልቶችን ያቀናጀ መሆን አለበት:: ማንኛውም አዎንታዊ የግንባታ ጥረት ታሪካዊና ባህላዊ ቀጣይነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል:: በአዲሱ የብሔርተኝነት እሳቤ ውስጥ ነባሩን ማንነት ችላ ማለት ፅኑ ግድፈት ነው:: በተጨማሪም የአገር ግንባታውን በአገር በቀልና በማኅበረሰቦች የጋራ እሴቶች ላይ መመሥረትም የማይታለፍ ቁም ነገር ነው::

የአገር ግንባታ በሁለት መልኩ በላዕላዊና ታኅታዊ መዋቅሮችና ሂደቶች የተቀናጀ መሆን አለበት:: መንግሥት በግንባታው ሂደት ማዕከላዊ ቦታ ቢኖረውም፣ በተጓዳኝ ከታች በሰፊው ሕዝብ ፈቃዳዊ ጥረት የሚደገፍ መሆን አለበት:: በኢትዮጵያ እንደታየው መንግሥታዊ ብሔርተኝነት ራሱ በታሪክና በፖለቲካዊ ኀይል አሰላለፍ ተጽዕኖዎችና በፖለቲካዊ ብልጠት የተነሳ አገራዊነቱ ወይም ዘውጋዊነቱ ሊጎላ ይችላል:: ለዚህ ሚዛን የሚያስይዝ ዘላቂ ሕዝባዊ ብሔርተኝነት ማስፋፋት ያስፈልጋል:: የአገር ግንባታው በልሂቃዊ መደቦች ተንጠልጥሎ እንዳይቀር በስፋትና በጥልቀት ከሕዝባዊነት ጋር ማጣጣም ተገቢ ነው::

በአጠቃላይ በአገር ግንባታው ሂደት ማን ምን እንዴት ይሥራ የሚለው ፍኖተ ካርታን በጥንቃቄ ማዘጋጀት ታላቅ ትኩረት የሚጠይቅ ሥራ ነው:: የፖለቲካ ተዋናዮች፣ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት የሕዝባቸውን ብሔራዊ ማንነት በመቅረፅ ጥረት ላይ ሊሠሩ የሚፈቀድላቸው፣ የሚበረታቱት፣ የሚፈለግባቸው ወይም የሚከለከሉት ተለይቶ ሊታወቅ ይገባል:: የአገር ግንባታው ባህላዊ ዘርፍ ሕዝባዊ ትዕምርቶችን በየትኞቹ የጋራ እሴቶች ላይ ይገንባ፤ ከታሪካችን የጋራ ብሔራዊ ትውስታን በመገንባቱ ጥረት የቱ ይፈቀድ፣ ይበረታታ ወይም ይከልከል የሚሉትን በቅጡ የሚለይ ሊሆን ይገባል::

ሲራራ ጥር 30/2012 1ኛ ዓመት ቁጥር 001

(Visited 113 times, 1 visits today)
June 9, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo