Featured articles, ሐተታ

አሁንም የሥርዓት ግንባታ ውድቀት እንዳይገጥመን!

ኢትዮጵያዊያን ለፖለቲካ ሽግግር እንግዳ ነን፡፡ በታሪካችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የፖለቲካ ውድድርና ፉክክር (political contestation) የተጀመረው በጣም በቅርቡ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ሁሉም ተፎካካሪዎች በእኩል መሠረት ላይ በማይሆኑበት ኢፍትሐዊ የጨዋታ ሜዳ ላይ የሚካሄድ ፉክክር ነው፡፡

ይህ ጊዜ አገራችን ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ምሁራን የሚፈተኑበት ጊዜም አሁን ነው፡፡ ምን ያህል ዝግጁ ነን? የፖለቲካ ልሂቃኑ ይህ ለውጥ አገርና ወገንን በሚጠቅም መልኩ እንዲቀጥል ምን ያህል ዝግጁነት አላቸው? የታሪክ ጥያቄ አለ፤ የፍትሕ ጥያቄ አለ፤ የዴሞክራሲ ጥያቄ አለ፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ አለ፡፡ ሌሎችም ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የተለያዩ፣ እንዳንዴም የሚጋጩ የፖለቲካ ፍላጎቶች ያሏቸው በርካታ የፖለቲካ ኀይሎችም አሉ፡፡ አፍጥጠው የመጡት የሚጋጩ ፍላጎቶች ሊስተናገዱ የሚችሉባቸው ተቋማት ግን የሉንም፡፡ ሥርዓታት (institutions) አልገነባንም፡፡ ትልቁ ፈተናም ይህ ነው፡፡

ጠንካራና ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ የሚደረግ የፖለቲካ ውድድር ፍሬው ያማረ አይሆንም፡፡ አገርና ሕዝብ ከፖለቲካ ኀይሎች ውድድር ሊጠቀሙ የሚችሉት ውድድሩን ሊያስተናግድ የሚችል መጫዎቻ ሜዳና ጨዋታውን በእኩል መንገድ የሚያስተናገድ ሥርዓት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ካልሆነ ለውጡ በተደራጁ ኀይሎች እጅ ገብቶ ሊኮላሽና መልሰን ወደ አፈና ሥርዓት ልንገባ የምንችልበት ሰፊ ዕድል አለ፡፡ ልክ የግብጽ አብዮተኞች በ2002 ዓ.ም. ማግስት እንደገጠማቸውና የማታ ማታ አገሪቱም ተመልሳ በአምባገነነናዊ ሥርዓት መዳፍ ሥር እንደገባችው፡፡ የዚህ ዓይነቱ መዘዘኛ ቅልበሳ እንዳይመጣና ሁላችንም ተስፋ ያደረግንበት ለውጥ ወደ ዴሞክራሲ የሚያሸጋግረን እንዲሆን ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል፡፡

በሚበዙት የአገራችን የፖለቲካ ኀይሎች አካባቢ ያለው ሁኔታ ግን ይህን አያመለክትም፡፡ አንዳንዶች የአፈና አገዛዙ ይንኮታኮት እንጂ ሌላው ይደረስበታል የሚሉ ይመስላል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በየትኛውም መንገድ ከብሔራዊ ኬኩ እንዴት እንደሚቋደሱ ነው እያሰሉ ያሉት፡፡ ስለ ሥርዓታት ግንባታና አገራዊ ተቋማትን ስለማጠናከር አጀንዳ ቀርጸው የሚንቀሳቀሱት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡

ለዚህ ነው የለውጡ እርምጃ ሁሉ በዶ/ር ዐቢይ እና “የለውጥ ኀይል” በሚባሉት ወገኖች አማካይነት ብቻ ሲከወን የሚታየው፡፡ የለውጡ መሪ ተዋናዮች እነሱ ናቸው፡፡ “የለውጥ ኀይል” የተባለው ቡድንም እየሞተም እየተገለለም እየተንጠባጠበ ከሐዲዱ እየወረደ ይገኛል፡፡ ይህ በራሱ አደጋ ያረገዘ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካ ልኂቃን ይቅርና በራሱ በገዥው ፓርቲም ውስጥ ልዩነቶች መኖራቸውን ጠቋሚ ነውና፡፡

የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሽግግር በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊከናወን አይችልም፡፡ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሽግግር እውን ሊሆን የሚችለው ገለልተኛ የሆኑ አገራዊ ሥርዓታትና ተቋማትን እየገነባ የሚሄድ ሲሆን ነው፡፡

አሁን ከሆይ ሆይታና ከበለው ጣለው ያለፈ፣ ከስሜታዊነት የተሻገረ የፖለቲካ ብስለት ልናሳይ የሚገባን ጊዜ ላይ ነን፡፡ በአገራችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ በፖለቲካም ይሁን በሲቪክ ማኅበረሰብ አባልነት እየተደራጀንና ንቁ ተሳትፎ እያደረግን ጠንካራ ሥርዓታትና ተቋማት እንዲፈጠሩ የምንታገልበት ጊዜ ነው፡፡ በብዙ ኢትዮጵያዊያን የተገኘው ለውጥና ለውጡ የሰጠንን ዕድል ማባከን አይገባንም፡፡ ለውጡ ከግለሰብና ቡድኖች ተዋናይነት ወጥቶ ሥርዓት እንዲይዝ፤ ሥርዓቱን የሚሸከሙ ጠንካራ ተቋማትም እንዲመሠረቱ በንቃት መሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ያለፈው ዓይነት አንድ ወይም ጥቂት ቡድኖች ሙሉ በሙሉ አሸናፊ የተቀሩት ቡድኖችና ሕዝቡ ተሸናፊ የሚሆኑበት የዜሮ ድምር ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቀብሮ፣ ሁሉም የፖለቲካ ፍላጎቶች የሚስተናገዱበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት አርቆ አሳቢነትና ብስለት ያስፈልጋል፡፡ ትኩረታችን ሥርዓታት ግንባታ ላይ፤ ትግላችንም ጠንካራ ተቋማትን በመፍጠር ላይ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡

ጠንካራና ገለልተኛ ተቋማት ካልተገነቡ ሕይወታችን በግለሰቦች ችሮታና ይሁንታ ላይ የተንጠለጠለ ነው የሚሆነው፡፡ ዜጎች በእኩልነትና በፍትሐዊነት እንዲኖሩ ጠንካራና ገለልተኛ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጾታቸው፣ በዘውጋዊና ሃይማኖታዊ ማንነታቸው ወይም በፖለቲካ አመለካከታቸው ተለይተው እንዳይበደሉ ጋሻ የሚሆናቸው ጠንካራ ሥርዓት ነው፤ ጠንካራና ገለልተኛ የፍትሕ ተቋማት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያዊያን፤ እያንዳንዳችን እንደ ዜጋ በዚህች አገር ፍትሕና እኩልነት የነገሠበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡ በዜጎች ላይ ያልተገባ በደል ሲደርስ አንዳችን ለሌላችን መቆም ይገባናል፡፡ ሰዎች በጾታቸው ምክንያት ሲጠቁ፣ ሴቶችና ሕፃናት ሲደፈሩና በደል ሲደርስባቸው፣ ኢትዮጵያዊያን በዘውጋዊም ይሁን በሌላ ማንነታቸው ምክንያት ሲጠቁ እንደዜጋ ይመለከተኛ ያገባኛል ብለን መነሳትና ከጎናቸው መቆም ይገባናል፡፡ በቅርቡ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለው ጥቁር አሜሪካዊ በነጭ አሜሪካዊ ፖሊስ አረመኔያዊ በሆነ መልኩ ታፍኖ መገደሉን በመቃወም በርካታ አሜሪካዊያን አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ብዙ ውድመትም ደርሷል፡፡ አሜሪካዊያን ነጭ ጥቁር ወይም ሌላ ሳይሉ በአንድ ላይ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያን ኢሰብአዊ ድርጊት እያወገዙ ነው፡፡ ከዚህ የምንማረው በጣም ብዙ ነገር አለ፡፡

ዜግነት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ትልቅ መብት የሚያጎናጽፈውን ያህል ከፍተኛ ኀላፊነትም አለበት፡፡ ዜግነታቸውን ከምር የተቀበሉ ሰዎች ለሌሎች የአገራቸው ዜጎች ጥብቅና ይቆማሉ፤ ለእኩልነትና ፍትሐዊነት መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡

ኢትዮጵያዊያን አሁን ያገኘነው የሽግግር ዕድል እንዳያመልጠን ብዙ ጥረት፣ ብዙ ውይይትና ምክክር ማድረግ ይገባናል፡፡ ይህ የሽግግር ዕድል ጠንካራና ዘመናዊ ሥርዓትን በማዋለድ እንዲጠናቀቅ ሁላችንም የዜግነት ኀላፊነታችንን መወጣት አለብን፡፡

(Visited 11 times, 1 visits today)
June 10, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo