World News, መጻሕፍት

ነገን መፍራት:- የአማራ ክልል ሕዝብ ሥር የሰደደ ችግር _ይሁኔ አየለ (ዶ/ር)

የዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) አዲስ መጽሐፍ “ሰበዝ” ከያዘቻቸው መጣጥፎች ውስጥ አንዱ “ነገን መፍራት” የሚል አርስት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ጽሑፍ፣ ደራሲው አንድ የሥራ ገጠመኙን ይተርክልናል፡፡

ገጠመኙ፣ ራሱ በሚመራው ድርጅት (አመልድ) በተዘረጋ ፕሮጀክት የታቀፈን “ደሃ” አርሶ አደር ቤት ተገኝቶ የተመለከተው ነው፡፡ አርሶ አደሩ በፕሮጀክቱ በሚሰጥ ስልጠና ታግዞ የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን በማካሄድ በዓመት ወደ 87 ሺሕ በር አግኝቷል፡፡ አርሶ አደሩ  ቤቱ ለተገኙት ደራሲ ባለሥልጣን ውጤታማነቱን ይተርክላቸዋል፡፡ የአርሶ አደሩ የኑሮ ደረጃ አለመቀየሩን ያስተዋሉት ደራሲ “በገንዘቡ ምን አደረግህብት?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ አርሶ አደሩም ከሚኖርበት የገጠር ቀበሌ 20 ኪሎ ሜትር እርቃ በምትገኝ አስፋልት ዳር በተከተመች የገጠር ከተማ ውስጥ ትንሽ መሬት ገዝቶ የቆርቆሮ ቤት እንደሠራ ይናገራል፡፡ “ለምን?” ተብሎ ሲጠየቅ፡- “የልጆቼ የወደፊት ቅርስ እንዲሆናቸው” የሚል መልስ ይሰጣል፡፡

ደራሲው፣ አጠቃላይ የቤተሰቡ ገጽታና ቁመና እንዲሁም የአካባቢው  ሁኔታ ምንም መሻሻል የሚባል ነገር እንደማይታይበት ታዝበዋል፡፡ በዚህም፣ ገጠመኛቸው ትልቅ ችግር መሆኑን ተገንዝበው ሊታሰብበት እንደሚገባ መጽሐፋቸው አመላክተዋል።

በእኔ እይታም የማይነገረው የክልሉ ሕዝብ ትልቅ ችግር ይኸው ለነገ በመዘጋጀት ዛሬ ላይ ጉዳት ማስተናገድ ነው፡፡ ችግሩን “ነገን እየፈሩ መኖር” ልንለው እንችላለን፡፡

ዛሬን የማይኖርበት፣ በተቻለ መጠን ነገን ለመኖር ዝግጅት እየተደረገ ዛሬን በእርዛትና ረኀብ የሚኖርበት ባህል፡፡ እኔን የሚመቸኝና ገላጭ የሆነው የድህነት ትርጉም “ነገን እየፈሩ መኖር” የሚለው ነው፡፡ የዛሬ ሁኔታህ ነገን የበለጠ እንድትፈራው ያደርግሃል፡፡ የእናቶች ትልቁ ጭንቀት “ነገ ለቤተሰቤ ምን የሚቀመስ ነገር አቀርባለሁ?” የሚል ነው፡፡

በአመጋገብ ሥርዓት ላይ በክልሉ ጥናት ያደረገ ሰው እንደነገረኝ “ሚሊየነር” ተብለው የተሸለሙ አርሶ አደሮች ልጅች ተደይነው (ስታንትድ ሆነው) ተገኝተዋል፡፡ እንደዚህ ያለው ክስተት የምግብ እንቆቅልሽ (Food paradox) ምግብ እያለ በግንዛቤ እጥረት መራብና መደየን ነው፡፡

ከድህነት ለመውጣት ለውጥ ይፈለጋል፡፡ ለውጡን የሚያመጣው ደግሞ ሰው ነው፡፡ ሰው የለውጥ ኀይል ነው፡፡ ጤነኛ ሰው፣ በአካሉ የበቃ፣  በአእምሮው የነቃ ሰው ለውጥ ያመጣል፡፡ ለውጥ ሲታሰብ በመጀመሪያ መገንባት ያለበት የለውጥ ኀይሉ ሰው ነው፡፡ ሰው ሲለወጥ ሌላውን ነገር መለወጥ ቀላል ይሆናል፡፡

ልጆች ጠግበው ሳይበሉ እንዴት ሊማሩና መውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ? ችግሩን ሳይንሱ ግልጽ ካደረገው ቆየ፡፡ ሌላው ቀርቶ ሚሲዮናውያን ወደ አፍሪካ ሲመጡ እርዳታን የሚያስቀድሙት “ባዶ ሆድ የሆነን ሕፃን ስለ ኢየሱስ መወተወት ከንቱ ድካም እንደሆነ ተረድተው ነው” ብሎ አንድ እንግሊዛዊ ፀሐፊ ማስቀመጡን አንብቤያለሁ፡፡

የአማራ ክልል አርሶ አደር ዋና ችግር ይህ ነው፡፡ የልጆቹን አቅም ሳይገነባ በተቃራኒው አቅም እያሳጣ ስለ ነጋቸው ይጨነቃል፡፡ የልጆች አቅም የምለው የመማርና በሽታን የመቋቋም አቅምን ነው።

የአርሶ አደሩ ጥረት የሚደነቅ ቢሆንም ትልቅ ስህተት መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ከዚህ ታሪክ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አንዲት በቁጠባና በምግብ ዋስትና መካካል ያለውን ዝምድና ያጠናች ሰው፡- “በአማራ ክልል ሰው እንዲቆጥብ እየተወተወተ ያለው ከፍጆታው እየቀነሰ እንጂ ከሚተርፈው አይደለም” ብላኛለች፡፡

ባለማወቅና ድህነቱ ባሳረፈው ጫና ላይ “ቆጥቡ” የሚል ውትወታ ትውልዱን እንዳያመክነው ስጋት አለኝ፡፡ በእውነት የተቆጠበው ገንዘብ የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት የሚመጣውን በሽታና ጉስቁልና ሊፈውሰው ይችላል? ለእኔ አይመስለኝም፡፡

ወገኔ ሆይ፣ ለልጅህ ጥሪት ሳይሆን ጥረትን አውርስ!

(Visited 44 times, 1 visits today)
June 24, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo