ቴክኖሎጂ, ጥበባት

ቋንቋ፣ ቴክኖሎጂ እና አስተሳሰብ_(በሔኖክ ይዘንጋው)

መግቢያ

ከሰው ልጅ የትመጣነት ወይንም ቅድመ ዝርያ (origin) ጋር ተያይዞ በዓለማችን ላይ በስፋት የሚታወቁ ሁለት ገዥ የሆኑ ፍልስፍናዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የሰው ልጅ የተፈጠረ ወይንም አስገኝ ያለው ነው ብለው የሚከራከሩ (creationist view) ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ በሂደት በዝግመተ ለውጥ ከአንድ ፍጥረት ወደ ሌላ ፍጥረት ተሸጋገረ የሚለው (scientific view) ምልከታ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጠርዝ ላይ የቆሙ ፍልስፍናዎች በአንድ የጋራ ጉዳይ ላይ ስምምነት ያላቸው ይመስላል፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ኑሮውን ለማሻሻል እና ለማቅለል በማያቋርጥ ጥረት ውስጥ መሆኑ ላይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ኑሮውን ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት በእርስ በእርስ ተራክቦው ላይ የተመሠረተ መሆንን ለመረዳት ብዙ አዳጋች አይመስልም፡፡ ይህም ተራክቦ ሥርዓት ባለው የመግባቢያ መንገድ ቋንቋን መሠረት አድርጎ የሚፈፀም ነው፡፡ ከቀደመው ዘመን ጀምሮ ሥልጣኔ ወይንም በኑሮ መሻሻልን ፅንሰ ሐሳባዊ መሠረት ለመስጠት ወይንም ፍልስፍናውን ለመግለጽ ቋንቋ ከዘመነ አፋዊነት (orality) እስከ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን በተለያዩ የለውጥ ሂደቶች ውስጥ አልፏል፡፡ ቀደም ሲል ለ3500 ዘመን ያክል በዓለማችን ላይ የቆየው የቋንቋ ስልት የንግግር ቃላትን መሰረት ያደረገ ነበር፡፡ ቀጥሎ የጽሕፈት ቴክኖሎጂ ሲዳብር ቀጣዩ የቋንቋ ስልት የጽሕፈት ቃላትን መሠረት አድርጓል፡፡ ይህ የአሁን ዘመን ደግሞ በዲጂታል ቃላት ስልት የሚመራ የቋንቋ መንገድ ጀምሯል ይህንን መነሻ በማድረግ ይህ ጽሑፍም ቋንቋ ከየዘመኑ ቴክኖሎጂዎችና አስተሳሰብ ጋር ያለውን ቁርኝት ለማየት ሞክሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ እና በፍጥነት በመጥፋት ላይ የሚገኙ ቋንቋዎች ለመታደግ ቴክኖሎጂ ምን ድርሻ ይኖረዋል የሚለውን ሐሳብም ያነሳሳል፡፡

1. ቋንቋ፣ የሰው ልጅ እና ቴክኖሎጂ

ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤ እና የእርስ በርስ ተራክቦ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ለመመርመር የተነሱ ምሁራንን ቀልብ ከሚስቡት ዐብይ ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው ባለፉት ሁለት ሺሕ ዓመታት ውስጥ የተከናወነው “ድምፅ አልባ አብዮት” ነው፡፡ ይኸውም የንግግር ቃላት (Spoken words) በጽሕፈት ቃላት (written words) እና በመጨረሻም በቴክኖሎጂያዊ ቃለት (technologized word) የመካተታቸው ጉዳይ ነው፡፡ አሁን እኛ የምንገኝበት ዘመን የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከሆኑት እንደ ኢንተርኔት፣ ኮምፒዩተር ወርድ ፕሮሰሲንግ፣ ሶሻል ኔትወርኪንግ እና የአጭር የጽሕፈት መልዕክት (text message) ጋር በፅኑ የተቆራኘበት ዘመን ላይ ነው፡፡ በዚሁ ሰበብ የንግግር ቃላት በጽሕፈት እና በቴክኖሎጂያዊ ቃላት እየተተኩ ፈፅሞ እየጠፉ ይገኛሉ፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች እርስ በርስ የሚያደርጉት የፊት ተራክቦን (face to face communication) እየገታው ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሰውን ልጅ በውስጡ ከሚገኘው እምቅ አቅም (ችሎታ) ጋር እየነጣጠለው ያለ ይመስላል፡፡

ይህንን ችግር ለመቋቋም በአንድ አንድ ተመራማሪዎች ዘንድ የሚሰጠው መፍትሔ በአካል ተቀራርቦ እየተደማመጡ ደጋግሞ መነጋገር የሚል ሆኗል፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን የታሪክ አስረጂዎቹን ስንፈልግም ይህንኑ የሚያስረዱ ጉዳዮችን እናገኛለን፡፡ ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ሰው የራሱን የረሳና እርስ በርሱም የተረሳሳ ይመስላል፡፡ ቴክኖሎጂ ፈጣን እና ውስብስብ ከሆነው ንግድ ጋር ተደማምሮ ተፈጥሯዊው የሆነውን የሰው ልጅ አቅም በዝግታ እየሸረሸረው ይገኛል፡፡ ዛሬ ላይ በምዕራቡ ዓለም የሚስተዋለው ድብርት፣ ግለኝነት፣ የአልኮል ሱሰኝነት፣ የአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚነት፣ የተጋነነ የክብደት መጨመር እና ረጅም ሰዓት በሥራ በማሳለፍ የሚመጣ የጭንቀት በሽታ፣ አሁን አሁን ደግሞ በእንግሊዘኛ አጠራሩ internet enhanced compulsive syndrome የተሰኘው በሽታ በዚሁ ምክንያት እንደሚከሰት እየተነገረ ይገኛል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን አብዮት በምዕራቡ ዓ.ም. እንደታየው ሁሉ የሰው ልጅ በአካል ተገናኝቶ ከቤተሰቡ፣ ከጓደኞቹ፣ ከጎረቤቶቹ እና ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር የሚያደርገውን ተግባቦት ይቀንሰዋል ወይንም ጨርሶ ያጠፋዋል የሚል ስጋት በተመራማሪዎች ዘንድ እያደገ ይመስላል፡፡ በኢኮኖሚ አድገዋል በሚባሉ አገሮች ዘንድ ደግሞ በሚበልጠው ሰዓት በከባድ ሥራ በመጠመድ፣ በመብል፣ በመጠጥ፣ በማሽከርከር፣ ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ረዘም ላለ ሰዓት ኮምፒዩተር ላይ ኦንላይን በመሆን በመቆየት፣ ኢሜል እና አጭር የጽሑፍ መልዕክት በመላክ ይጠፋል፡፡ የምዕራቡ ዓለም ማለቂያ የሌለው ለሚመስለው ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የንግድ እንቅስቃሴ እጁን የሰጠ ይመስላል፡፡ ውክቢያ እና መጣደፍ በበዛበት በዚህ የምዕራባዊያን አገሮች አኗኗር ላይ ለወዳጅና ለጎረቤት የሚተርፉ ጥቂት ቃላት መለዋወጥ ከባድ ይመስላል፡፡ ይህንን የመሰለው ቴክኖሎጂ ላይ አብዝቶ ጥገኛ መሆን ኅብር ያለው አኗኗር ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፣ በጤና ረገድም እንዲሁ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው እየተነገረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በሰው ልጅ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና በማኅበራዊ ግንኙነት በተለይም እርስ በርስ በአካል ተገናኝቶ የሚደረጉ ውይይቶች እና ማኅበራዊ ግንኙነቶች መካከል ፍፁም ሚዛናዊ መሆን ተገቢ ይመስላል፡፡ ይህ ጽሑፍም የሰው ልጅ በአፍ መፍቻ ቋንቋው በአካል ተገናኝቶ የሚያደርገው ተግባቦት እና ማኅበራዊ ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ ገፍ ምክንያቶች መካከል አንዱን ማሳያ በማድረግ ችግሮቹን ማሳየት እና የችግሮቹን መነሻ እና ይሆናሉ ብሎ የጽሑፉ አቅራቢ የሚያምንበትን የመፍትሔ ሐሳብ ለመጠቆም ይጥራል፡፡

የሰውን ልጅ የቋንቋ ዕድገት ስንመለከተው የንግግር ቃላትን ከማዳበሩ አስቀድሞ በአካላዊ እንቅስቃሴ (hestures)፣ ድምፅ በተለያዩ ዓይነት መንገድ በማውጣት (mixtures of sounds and tones of voice)፣ በተለያዩ የፊት ገፅታዎች (facial expressions)፣ ይግባባ ነበር፡፡ ይህም ዓይነት የመግባቢያ መንገድ በዘመናዊ ሳይንስ ዘርፍ የፕሮቶ ላንጉጅ (proto-language) በመባል ይታወቃል፡፡ የሰው ልጅ ይህንን መሰሉን የመግባቢያ መንገድ ምን አልባት ለ35000 ዓመት ያኽል ሳይጠቀምበት እንዳልቀረ ግምቶች አሉ፡፡ የቋንቋን ዕድገት ከሰው ልጅ ዝግመታዊ ለውጥ ጋር አያይዘው የሚተነትኑ ተመራማሪዎች የሰው ልጅ የንግግር ቃላትን መፈጠር የጀመረው በዘመነ ሆምኢሬክትስ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ዘመን የንግግር አካላት ከሚባሉት መካከል በላንቃ አካባቢ የሚገኘው የቪላር ክሎዠር ማደግ ጋር ተያይዘው ነው ይላሉ፡፡ ይህንን መሠረት አድርገው ተመራማሪዎች ሲያስረዱ፣ ይህንን የመሰለው የንግግር አካል በሰው ልጅ አካል ላይ ዕድገቱን መጨረሱ የንግግር ቃላት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነ ይሉናል፡፡

በእስተን ፎርድ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ ጥናትና በመረጃ ማዕከል ውስጥ አንጋፋ ተመራማሪ የሆኑት ደስታርኬት ዴቨሊን “The Math Gene” በተሰኘው መጽሐፋቸው የንግግር ቃላት የተፈጠሩት ከ75,000 – 200,000 ዓመት ውስጥ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ቀደም ሲል በዚህ ምድር ላይ ይኖር የነበረው የሰው ዘር ለረዥም ዘመን የንግግር ቃላትን ቀዳ የመግባቢያ መንገድ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡ ብዙ ሥልጣኔዎችም በዚህ ዘመን አስዝግቧል፡፡ ለአብነት ያኽልም የዝነኛው ባለቅኔ ሆሜር እና የሶቅራጠስ ቅኔዎች እና ፍልስፋናዎች አለመጻፋቸውን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ ዘመን የሰው ልጅ ጠቃሚ የመሰለውን ሐሳቦች በሙሉ በጭንቅላቱ መዝግቦ ያስቀምጣቸው ነበር፡፡ ለትውስታ እንዲረዳውም በማሰብ ግጥም፣ ዘፈን፣ ዝማሬ እና የዳንስ ጥበብን አዳብሯል፡፡ እነዚህ ሙዚቃዊ ምት ላለው ግጥማዊ አነጋገሩ አጋዥ እንደነበሩ ይነገራሉ፡፡ ታዋቂው ፈረንሳዊ ፈላስፋ ጂን ጃኩስ ሩስ (1712 – 1778) “Essay on the Origin of languages” በተሰኘ ጽሑፉ ስለ ቋንቋ አፈጣጠር ሲናገር የሙዚቃ (musical imitation) ቅጅ ነው  ይለናል፡፡ ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ ለብዙ መቶ ሺሕ ዓመታት የሰው ልጅ የኖረበት ባሕል የጽሕፈት ዕውቀት ያለጎበኘው አፋዊ ነበር ሲሉ ያስረዳ፡፡ አፋዊነት እርግጥም ዛሬም በዓለማችን ላይ በተለያዩ ማኅበረሰቦች (ሕዝቦች) ዘንድ የሚታይ ባሕል ነው፡፡ በተመራማሪዎች ዘንድም ቀልብን እየሳበና እያደገ ያለ የጥናት ዘርፍ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

2. የጽሕፈት ትንሣኤ

ረጅሙ የአፋዊነት ታሪክ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንደ ትልቅ ክስተት በሚታየው እና ትልቅ ቦታ በሚሰጠው የጽሕፈት ቃላት ሲረታ እና የመጀመሪያው ሆሄ በጥንታዊያኑ ግሪኮች ዘንድ ሲፈጠር የቋንቋ ዕድገት ሌላ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተለት፡፡ ቀደም ሲል በነበረው የንግግር ቃላት ዘመን ለመግባቢያነት የሰው ልጅ ሲጠቀምባቸው የነበሩት የአካል ክፍሎቹ፣ ጆሮውን ለማዳመጥ እና አንደበቱን ደግሞ ለንግግር ነበር፡፡ በዘመነ ጽሕፈት ግን ሌሎች የአካል ክፍሎቹን ማለትም ዓይኑን እና የእጅ ጣቶቹን ደግሞ በጽሕፈት ለመግባባት ተጠቀመባቸው፡፡ ይሄም እንደ አንድ ትልቅ የታሪክ እርምጃ ሊወስድ ችሏል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የንግግር ቃላትም ሆነ የጽሕፈት ቃላት መቼ እና የት ተፈጠሩ የሚለውን ትክክለኛ መልስ ማግኘት ሌላኛው የምርምር አቅጣጫ ሆኗል፡፡ ነገር ግን የንግግር ቃላት መቼ እና የት ተፈጠሩ የሚለውን ጥያቄ መመለስ እጅግ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ እና እስከዛሬ በዚህ ረገድ ሁነኛ ምርምር እና ማስረጃ ያቀረበ ሰው ማግኘት አልተቻለም፡፡

እንደ ኤሪክ ኤ ሀቨሎክ (1903 – 1988) እና ዋልተር አንግ (1912 – 2003) ባደረጓቸው ምርምሮች የጽሕፈት ቃላት የንግግር ቃላትን ድል ነስተው አሸናፊነታቸውን ያወጁት፣ በግሪክ ሲሆን ዓመቱም ከ700 – 400 ቅ.ል.ክ ነው፡፡ የጽሕፈት ባህል መዳበር ወይንም የጽሕፈት ቴክኖሎጂ መፈጠር “በአስተሳሰብ፣ በስብዕና እና ማኅበራዊ መዋቅር ላይ ጥልቅ የሆነ ለውጥ አምጥቷል” ሲሉ ይከራከራሉ ኤሪክ ኤ ሀቨሎክ ፡፡ ሌላኛው ስፔናዊው ሐኪም፣ ፈላስፋ፣ ተመራማሪ እና ጸሐፊ የሆነው ፔድሮ ሌይን ኢንተርላጎ (1908 – 2001) “The Therapy of the world in Classical Antiquity” ሲል በጻፈው ጽሐፉ ላይ ‘ሳይንቲፊክ’ የተባው ሕክምና የቀደሙት የግሪክ ሐኪሞች በዘመነ ሄፐኦክራተስ (460-370 ቅ.ል.ክ) ሲጀምሩ የተኩት ነባሩን በቃል ወይንም በንግግር የሚደረገውን ሕክምና ነበር፡፡ ሕክምናውም የንግግር እና የዜማ ቃላት፣ የድምጽ እርግብግቢት፣ ግጥም፣ ሙዚቃ፣ ዝማሬ፣ መነባንብ፣ ምስጢራዊ ቃላትን በመናገር እና በፀሎት ይከናወን ነበር፡፡

በግሪክ እና ሮም ሚትሎጂ ውስጥ ስለዘጠኙ ሞሰሶ ስለተሰኙት አማልክትም ሲናገር ቅኔን፣ ሙዚቃን፣ ስነ ጥበብን በጠቅላላው ይወዱ እና ያበረታቱ እንደነበር ይተረካል፡፡ ሂሶይድ የተሰኘው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ700 (ዓ.ዓ.) የተነሳው ባለቅኔም ስለዘጠኙ የግሪክ አማልክት ሲተርክ፣ የሙዚቃ ስልተምቱን ተከትለው ሲደንሱ በጣፋጭ ድምጻቸው ስለሆነው፣ እየሆነ ስላለው እና መሆን ስላለበት ሲናገሩ ከአንደበታቸውም ጥዑመ ዜማ ሲደመጥ ልዩ ስሜት እንደሚፈጥር ይገልጻል፡፡ እንደ ሂሶይድ ገለጻ ከሆነ የሰውን ልጅ ንዴት ብስጭት እና ችግርን ያስወግዳሉ፡፡ ተወዳጆቹም ምሰሶች ለቅኔዎች፣ ለሙዚቃ፣ ለዳንስ እና ለጥበብ ሁሉ ምንጮች ተደርገው ይወሰዱ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ ታራድኦቸው ግን ከጽሕፈት ቴክኖሎጂ ኖሮ ቢሆንም እንኳን ያን ያኽል የአማልክቱን እና በጊዜው በአማልክተ ተራድኦት ቅኔዎችን እና ፍልስፍናዎችን አዳበርን የሚሉትን ሰዎች ቀልብ መግዛት አልቻሉም ነበር፡፡ ስለሆነም በጥንታዊ የዓለም (የምዕራቡ) የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የቃል ዝማሬ፣ ዳንስ፣ ቅኔ እና የድምፅ እና የንግግር ቃላት ሰፋ ያለውን ቦታ ይይዙ ነበር፡፡ የአማልክቱ ግብአታዊ የፈጠራ ክህሎት እና እንደ ፏፏቴ ከልባቸው የሚፈልቅ የሚባለው የጥበብ ሥራ ተረጋግቶ ተቀምጦ በንባብ እና በጽሕፈት ቋንቋ የሚገለፅ አልነበረም፡፡ እነርሱ በቃል ያስደመጧቸው የነበሩት ጥልቅ ቅኔዎች፣ ዝማሬዎች እና ዳንሶች በሂደት የጽሕፈት ቴክኖሎጂ በዳበረበት ወቅት አፋዊ ጥበቦች ወደ ጽሕፈት መሸጋገራቸው እውነት ይመስላል፡፡

3. የሕትመት ቴክኖሎጂ

ንባብ እና ጽሕፈት ከ700 እስከ 400 ቅ.ል.ክ ባለው ዘመን ውስጥ ከጥንት ግሪክ ተነስቶ መላውን ዓለም አደረሰው፡፡ እስከ 15ኛው መ.ክ.ዘ የንባብ እና የጽሕፈት ዕድገት ዝግ ያለ ነበር፡፡ በቀደመው ዘመን የተለያዩ የብራና ጥቅሎች ነበሩ፡፡ በኋላ በየገዳማቱ በመነኮሳት አማካኝነት የሚጻፉ የእጅ ጽሕፈት ሥራዎች ለመዳበር ችለዋል፡፡ የንግግር ቃላት ለተግባቦት ቀዳሚ ሆነው፣ የጽሕፈት ቃላት ደግሞ በዝግታ ሲከተሉ ነበር፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ. በ1440 ዮሐንስ ጉተንበርግ የማተሚያ ማሽን ሲሠራ መጻሕፍት በብዛት መታተም ጀመሩ፡፡ በመላው አውሮፓ በ15 ዓመቱ ውስጥ ማተሚያ ቤቶች እና የሕትመት ሥራ ትልቅ ንግድ እየሆነ መጣ፡፡ ከዚህ “ድብቅ አብዮት” ጎን ለጎን በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የፕሮቴስታንት ሪፎርሜሽን ንቅናቄ መጀመር ጋር ተያይዞ መጽሐፍ ቅዱስ በየቤቱ መግባቱ እና መጠናቱ ነው፡፡ ሰዎችም መጽሐፍ ቅዱስን እና ሌሎቹ መጻሕፍትን አንብበው ለመረዳት የንባብ እና የጽሕፈት ትምህርት ይከታተሉ ጀመር፡፡ ይህም በመላው አውሮፓ እና በዓለም ሁሉ እየተለመደ መጣ፡፡ በዘመነ ኢንዱስትሪ አብዮትም በንግድ እና በሌላ ሰበብ በርካታ መጻሕፍት መታተም ጀመሩ፡፡

ኢንዱስትሪ፣ ንግድ፣ ቴክኖሎጂ እና ሃይማኖት በጋራ መጻሕፍት በገፍ እንዲታተሙ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይኸውም በሰው ልጅ ንግግር እና የእርስ  በርስ ተራክቦ ላይ ተፅዕኖውን ማሳረፉ በግልፅ መታየት ጀመረ፡፡ በአውሮፓ በቀደመው ዘመን ሰዎች በኢኮኖሚ እና ሃይማኖታዊ ኃይሎች እየተገደዱ ያላቸውን ትርፍ ጊዜ ሁሉ የተጠቃሚነት እና የንባብ ሆነ፡፡ ይህንን መሰሉን ታሪክ መለስ ብለን በምንመለከትበት ጊዜ የሰው ልጅ በሥልጣኔ ሰበብ እርስ በርሱ እየተነጣጠለ ይመስላል፡፡ የኢኮኖሚ ሥርዓቱን ስናስተውል ሰዎች ለረጅም ሰዓት እንዲሠሩ፣ ብዙ እንዲያመርቱ እና ብዙ እንዲጠቀሙ ያበረታታል እንጂ የሰው ልጆች እርስ በርስ በረጋ መንፈስ እንዲወያዩ አይጋብዝም፡፡ ይልቁንም የሰው ልጆች የፊት ለፊት ውይይቶች ተራ የጊዜ ማባከኛ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ በመጻሕፍት ሕትመት ኢንዱስትሪው፣ ብዙሃን መገናኛው እና ቴክኖሎጂ በፊት ለፊት ታረክቦ ህልውና ላይ ግልፅ የሆነ ተፅዕኖ አሳርፈዋል፡፡ በዚህ ሰበብ የፊት ለፊት ውይይት እና ማኅበረሰባዊነት (sociability) እየተዳከመ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የሰው ልጆች ፍላጎት ጉዞው በዚህ ከቀጠለ የግብይትና የማምራት ዕድሉንም የመጠቀም ብቻ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡

4. የቴክኖሎጂ አገልግሎት እና ተግዳሮት

የጽሕፈት ቃላት በሌላ አስደናቂ የቴክኖሎጂ ቃላት ሲተኩ እንዲሁ ድምፅ አልባ በሆነ አብዮት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌስተርን አውስትራሊያ የሶፍትዌር ትግበራ ዳይሬክተር የሆኑት ዴቪድ ግላንስ “How technology is changing language and the way we think about the world” በተሰኘው ጽሑፋቸው “ብዙ ሰው ልብ ያላለው ነገር ቢኖር ቴክኖሎጂ እንዴት አድርጎ ቋንቋችን ላይ ተፅዕኖ እንዳሳረፈ ይህም ተፅዕኖ ወይንም ለውጥ እንዴት የንግግር እና የአስተሳሰብ መንገዳችንን እንደቀየረው ነው” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ በዓለማችን በብዙ ሰዎች የሚዘወተረውን የበይነመረብ መፈለጊያ (internet search engine) ጉግል (Google) በ2002 እ.ኤ.አ የአሜሪካ ዲያሌክት ማኅበረሰብ የዓመቱ ቃል ሲል አውጆለት ነበር፡፡ በኋላ ላይ በ2009 እ.ኤ.አ ጎግል የዐሥር ዓመቱ ቃል (the word of the decade) መርጦታል፡፡ ጉግልም ሆነ ሰው በስፋት የሚጠቀምባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከድርጅት ወይንም ከመገልገያ ስምንት ወደ ትግበራ መንገድ ወይንም ከቃል ክፍሎች ውስጥ ግስ የምንለውን እየተኩ ይገኛሉ፡፡ እዚህ ላይ የእንግሊዘኛ ቃላት የሆኑትን ጎግል (Google) እና ሁቨር (Hoover company) ልብ ይሏል፡፡ ዴቪድ ግለንሰ ከላይ በተጠቀሰው ጽሑፋቸው እንደዚህ ዓይነት የቴክኖሎጂ ቃላትን መጠቀም ዋናውን ሐሳብ ፍፁም ሊያጠፋው ይችላል ይላሉ፡፡ ለዚህም ምሳሌ ሲሰጡ የዝነኛውን ደራሲ የበርናንድ ሾውን ጽሑፍ እስኪ በነዚህ ቃላት ለውጠን እንየው በማለት የሾውን ቃላት በዘመኑ የቴክኖሎጂ ቃላት እንዲህ ተክተዋቸዋል፡፡

“My mother was hacked last night”, “what a great meal – I’ll upload it” “if any one’s out there, can you inbox me?” “How many steps did you get to day?” “Will you torrent me the next series?”

ከላይ በሰፈረው ጥቅስ ውስጥ የሚገኙት ቴክኖሎጂያዊ ቃላት በትክክል ነባሩን ሐሳብ ማስረዳታቸው አጠራጣሪ ነው፡፡ ሌላው የቢቢሲ የቴክኖሎጂ ሪፖርተር የሆነው ዞ ኪሊማን (Zoe Kleinman) በኦገስት 16 ቀን 2010 ዘገባው የአሜሪካ ፖለቲከኛ የሆኑትን የሳራ ፔሊንን ኢሜን ሰብሯል ተብሎ የሚጠረጠረውን ሰው ቋንቋ (የቴክኖሎጂ ቋንቋ) ለማረጋገጥ እና ለመተርጎም ክርስቶፈር ፑል የተሰኘ የኮምፒውተር ምሁር አስፈልጎ ነበር ይለናል፡፡ በችሎቱም ላይ የኢንተርኔት ስላንግ (internet slang) catalogue እንዲተረጎም ተጠይቆ እንደነበር ዘግቧል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ቁጥራቸው ጥቂት በማይባሉ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚዘወተረው የአጭር የጽሑፍ መልዕክት (text message) በሌላ አጠራር የጽሑፉ ንግግር (text speaking) ቋንቋ እና አስተሳሰብ ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳርፉ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡

ፕሮፌሰር ክርስታል የተባሉ የቋንቋ ምሁር ከላይ ከተጠቀሰው የቢቢሲው የቴክኖሎጂ ሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሰዎች አጭር የጽሑፍ መልዕክት አዲስ ቋንቋ ነው፣ ጽሑፉንም በአህጽሮተ ቃላት ለመተካት ያስችለናል ቢሉም የሰው ልጆች ከሚያደርጓቸው ከጠቅላላው አጭር የጽሑፍ መልዕክት ውስጥ 10 በመወቶ ያህሉ ብቻ በአህድሮተ ቃላት እንደሚጻፉ ያስረዳሉ፡፡

ቴክኖሎጂ የሰው ልጆች ቋንቋ ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው “wireless” የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ነው፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ “wireless” የሚለው ቃል በ1950ዎቹ ሬዲዮ ማለት ነበር፤ አሁን ግን በብዙ ሰዎች ዘንድ ይሄ ቃል አይታወቅም፡፡ የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት አንጋፋ ኤዲተር የሆኑት ማክፐርሰት (MC Pherson) ቴክኖሎጂ ያለጥርጥር በቋንቋ ላይ ጉልህ ተፅዕኖውን አሳርፏል ይሉናል፡፡ Internet slang.com የተሰኘው ገጸ-ድርም 5090 ያክል በጥቅም ላይ የሚገኙ የእንግሊዝኛ አህጽሮተ ቃላትን ዘርዝሮ አስቀምጧል፡፡ ይህም ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የተከሰተ አዲስ ክስተት አድርገን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ በ1973 ዓ.ም. የታተመው የኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት “social networking” የሚለውን ሐረግ ሲተረጉመው “የማኅበራዊ ግንኙነቶች ወይንም ትስስሮች ጥቅም ወይንም ምሥረታ ነው” ይላል፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ የሶሻል ኔትዎርኪንግ ትርጉም ኢንተርኔት ላይ መሠረት ያደረጉ ክንውኖችን ብቻ የሚመለከት እየሆነ መጥቷል፡፡ በዕውቁ ማቲማቲካል ሊንጉስት (Mathematical-linguist) አንድራስ ኮርኔ (Andras Kornai) በዓለማችን ላይ ከሚገኙት ቋንቋዎች 5  በመቶ ያክሉ ብቻ ወደ ዲጂታል ዓለም የመሸጋገር ዕድል ሲኖራቸው የተቀሩት 95 በመቶው ያክሉ የዓለም ቋንቋዎች በኢንተርኔት ምክንያት የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲል ያስረዳናል፡፡ እንደ ኮርኔ ትንተና ከሆነ ዓለማችንና ላይ ከሚገኙት 7000 በላይ ቋንቋዎች ውስጥ 2500 ያኽሉ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ ሌላኛው ዕውቅ እና ቀዳሚ የዓለም ቋንቋዎች የአትኖሎግ መዝገብ (data base) የሰመር ኢንስቲቲዩት ኦፍ ሊንግስቲክስ (Summer Institute of linguistics) SIL እንደሆነ ይታወቃል፡፡ SIL (December 2015) ባወጣው ሪፖርት መሠረት በዓለማችን ላይ 7102 ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 916 ወይንም 13 በመቶው እየሞቱ ያሉ ናቸው፡፡ ከ1950 ጀምሮ 367 ቋንቋዎች ከዓለማችን ላይ ጠፍተዋል፡፡ ይህም ማለት አምስት ቋንቋ በየዓመቱ ዓለማችን እያጣች ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቋቋም እና ቋንቋዎችንም ወደ መጪው ትውልድ ለማሸጋገር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሁነኛ መላ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ቋንቋዎች ዲጂታላዊ በሆነ መንገድ እንዲያገለግሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ የሚቀጥለው የጽሑፍ ክፍል ቋንቋን እንዴት በዘመኑ ቴክኖሎጂ እናድን የሚል ይሆናል፡፡

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ዓለማችን ፈጣን እና ውስብስብ መሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ናት፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ የሰው ልጅ ላይ ሁለንተናዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀሬ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ በጥንታዊ የአኗኗር ስልቱ ውስጥ እንኳ ይዞት የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ቴክኖሎጂ ሌላው ላይ የበላይነት እየያዘ ነባሩን እያዳከመ የሚሄድ ይመስላል፡፡ እንደዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ግምት ከሆነ፣ የሰው ልጅ ከቴክኖሎጂ ነፃ (technology free  period) የሆነ ዘመን ያሳለፈ ምንአልባትም በዘመነ አፋዊነት (at the time of oral) ሳይሆን አይቀርም፡፡ አፋዊነትን የተካው የጽሕፈት ባሕል ደረጃው እና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በድንጋይ ላይ፣ በከብት ቆዳ፣ በቅጠላ ቅጠልና በመሳሰሉት ዘመኑ በፈቀደው ቴክኖሎጂዎች ሁሉ ሲግባባ ኖሯል፡፡ ነገር ግን የቴክኖሎጂም ምጥቀት እና ርቀት በበዛ ቁጥር የሰው ልጅ ነባር ቋንቋዎች እና ባሕሎች እየጠፉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም መፍትሔው ከቴክኖሎጂ የራቀ ቴክኖሎጂ ጠል የሆነ መፍትሔ ሳይሆን ቴክኖሎጂን ያስቀደመ ነው፡፡ ለአብነት ያኽል እየጠፋ ለሚገኙ ቋንቋች መፍትሔ ተደርገው የሚወሰዱ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንመልከት፡፡

የማኅበረሰብ ራዲዮኖች

ምንም እንኳን የብዙዎችን ቀለብ የሚስብ ባይመስልም፣ ከዘመኑም ከፍተኛ ቴክኖሎጂዎች አንጻር ጥቅሙ ዝቅ ተደርጎ ቢገመትም፣ ራዲዮኖች አሁንም በቀላሉ ተደራሽ በመሆን እና በቀላል ዋጋ ነባሩ ማኅበረሰብ ቋንቋውን እንዲናገር እና እንዲያደምጥ የሚያገለግሉ መድረኮች ናቸው፡፡ በጓቲማላ፣ ኤልሳልቫዶር እና በቤልዝ እነዚህ የማኅበረሰብ ራዲዮኖች ለቋንቋ ዳግሞ ማንሰራራት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (UNESCO) ከሆነ፣ በታዳጊ አገሮች 75 በመቶ ያኽሉ አባወራ/እማወራ ቤት ራዲዮ ይገኛል በዓለማችን ላይም 44,000 ገደማ የራዲዮ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ በዚህ በተራቀቀ ዘመን አሁንም የራዲዮ አገልግሎት ከፍተኛ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ይህንም በመገንዘብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. ጥር 14 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የዓለም የራዲዮ ቀንን አውጇል፡፡

የፊልም ጥበብ

የፊልም ጥበብ በዓለማችን ላይ በእጅጉ እየገነኑ ካሉ የጥበብ ሥራዎች መካከል ይመደባል፡፡ ታዲያ ይህን የመሰለው የጥበብ ዘርፍ በምን መልኩ ቋንቋ ከጥፋት ይታደገዋል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ የአውሮፓውያንን የአነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች ፊልም ፌስቲቫል (European minority film festival) ማጤን ይቻላል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ላይ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ፊልም በመሥራት ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን ማዳበር ከጥፋት ማዳን የሚቻል ይመስላል፡፡

ካርታ (mapping)

ከዘመናችን የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል የተፈጥሮ ሀብቶችን፣ የአገሮችን እና የሕዝቦቻቸውን መገኛ እንዲሁም፣ የጦርነት ቀጠናዎችን በዝርዝር የሚገልጹልን እና የምንመለከትበት ስልት ካርታ (mapping) ነው፡፡ ይህንን የካርታ ስልት በመጥፋት ላይ ለሚገኙ እና የመጥፋት አደጋ የተረጋገጠባቸው ቋንቋዎችን ለመለየት ይህንኑ የሚያግዝ ካርታ ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህ ረገድም ቴክኖሎጂ እያገዘ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

የመረጃ ቋት እና ስነዳ (data base and documentation)

በዚህ ረገድ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ሥራ ከሚሠራባቸው ፕሮጀክት መካከል “endangered languages projects” የተሰኘው ጥምረት (Alliance for linguistics diversity) ከጉግል ጋር በጋራ የሚያከናውኑት ፕሮጀክት ነው፡፡ እየጠፉ ያሉ ቋንቋዎች በመቅዳት፣ በማሰራጨትና ምርጥ ተሞክሮዎችን የሚጋሩበት መድረክ ተፈጥሯል፡፡ የኦንላይን ቤተመጻሕፍት ተፈጥረዋል፡፡ ያለምንም ወጪ የእነዚህን ቋንቋዎች መዝገበ ቃላት፣ ጽሑፎች እና ለአስቸጋሪ ጽሑፎች ደግሞ መፍቻ አዘጋጅተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር እነዚሁ ሰነዶች ከፍ ባለ ቴክኖሎጂ በተንቀሳቃሽ ስልኮች መሰራጨት ጀምረዋል፡፡ በመሆኑም ቴክኖሎጂ የመረጃ ቋት እና ሰነድ ዝግጅትም ላይ ቋንቋን እየታደገ ይገኛል፡፡

የሒሳባዊ ሞዴል (statistical modeling)

ይህ ተግባር በሒሳብ ምሁራን አማካኝነት በበርክሌ እና በብሪቲሽ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኮሎምቢያ አማካኝነት የቀረበ ሲሆነ የጥንት ቋንቋዎች አሁን ላይ በሚገኝ የመረጃ ቋት ላይ መሠረት አድርጎ ለመረዳት እና መልሶ ከሞት ለማስነሳት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ አሁን ያሉት ቋንቋዎች በምን ያህል ጊዜ ወይንም መቼ ይለወጣሉ የቋንቋዎች የርስ በርስ ዝምድናስ በሚል ጽንሰ ሐሳባዊ መሠረት ላይ ያረፉ ነው፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ገፀበረከት ነው፡፡

ሀሰሳ ዳና (trakcing)

በዘመናዊ ሳይንስ ዘርፍ የእንስሳትን እንቅስቃሴና የአኗኗር አጠቃላይ ሁኔታ ለማጥናት (smast collars) የተሰኘ ብዙውን ጊዜ አንገት ላይ የሚታሰር መረጃ ሰብሳቢ መሣሪያ አለ ከዚሁ ጋር ተነጻጻሪ የሆነ (indigenous tweet) የተሰኘ እና የስነ ልሳን ተመራማሪዎች ምቹ የሆነ ፕሮግራም ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት 250 ቋንቋዎች ትዊተር ላይ ተመዝግበዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 139 ቁጥራቸው ጥቂት በሆኑ ሕዝቦች የሚነገሩ ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ የሰዎችን እውነተኛ ንግግር ሳይተረጉም በኦንላይን ያስቀምጠዋል፡፡ ይሄ ሌላኛው የቴክኖሎጂ ግኝት ነው፡፡

በአጠቃላይ ቴክኖሎጂ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ሕዝቦች እና ቋንቋቸውን ከመታደግ ባሻገር ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመውሰድ የቀረው ዓለም እንዲያጠናው እና ፍላጎት ያደረበትም ታምር እንዲናገረው እያገዙ ይገኛሉ፡፡

ማጠቃለያ

ይህ ጽሑፍ ሦስት ዐቢይ ጉዳዮችን አንስቶ ለማብራራት ሞክሯል፡፡ እነዚህም ቋንቋ፣ ቴክኖሎጂ እና አስተሳሰብ ናቸው፡፡ ቋንቋ ከአፋዊነት አንስቶ እስከ ዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን ድረስ የሄደበትን ረዥም ጉዞ እና አንደኛው ቴክኖሎጂ በሌላኛው ላይ ያሳረፈውን ተጽዕኖ ለመቃኘት ሞክሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሰው ልጆች ተፈጥሯዊ አስተሳሰብ ላይ በቴክኖሎጂው አብዮት ረገድ ያለውን አዝማሚያ ዳሷል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ቴክኖሎጂ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ቋንቋዎች ለመታደግ እያንሰራፋ ያለውን አዎንታዊ ተፅዕኖም ተችቷል፡፡ ምንም እንኳ ከሥልጣኔ እና ከአገራችን የዕድገት ደረጃ አንፃር በቴክኖሎጂ ሰበብ እየተፈጠረ ያለውን ተጽዕኖ ለመገምገም ጊዜው ገና ቢመስልም ጉዳን በቅጡ አጥንቶ እና አዘጋጅቶ መጠበቁ ተገቢ ይመስላል፡፡ ጥልቅ ጥናት የሚጠይቀውን እና ርዕሰ ጉዳዮች እርስ በርስ ያላቸውን ትስስር ለመነሻ እንዲሆን በዚህ ጽሑፍ መነሻነት ተሞከረ እንጂ እንደሚፈለገው ተብራርቷል ለማለት አይችልም፡፡ ስለሆነም ይህንን መነሻ ጽሑፍ ተከትሎ የሚነሱ ጥናቶች ርእሰ ጉዳዩን በተገቢው ጥልቀት ያብራሩታል ተብሎ ይገመታል፡፡ የምዕራቡ ዓለም ቁሳዊ ፋላጎቱን ለማሟላት ሲል የፈጠራች ቁሶች የስጋት ምንጮች እየሆኑበት ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ድብርት፣ ግለኝነት፣ የአልኮል ሱሰኝነት፣ የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነት፣ የተጋነነ የክብደት መጨመርና ረዥም ሰዓት በሥራ ማሳለፍ በሚመጣ የጭንቀት በሽታ፣ በእንግሊዝኛ አጠራሩ “internet enhanced compulsive syndrome” የተሰኘው በሽታ በሙሉ ቴክኖሎጂ አመጣሽ ልንላቸው ባይቻልም እንኳን ቴክኖሎጂ ለአንዳንዶቹ ዋንኛ ምንጭ ሲሆን ለቀሪዎቹ ደግሞ ለመባባሳቸው ጉልህ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ይህ ችግር በቀሪው የዓለም ክፍል፣ በተለይም በታዳጊ አገሮች እንዳይስፋፋ ምን መደረግ ይገባል የሚል ጥያቄ እዚህ ላይ ማንሳቱ ተገቢ እንደሆነ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያምናል፡፡ በርግጥ በታዳጊ አገሮች ላይ በቴክኖሎጂ ሰበብ የተፈጠረውን ችግር በጥልቅ መመርመር ቀዳሚ ተግባር ቢሆንም፣ ለጊዜው ግን እንደዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት ከሆነ በአውሮፓ በዐሥራ ሰባተኛው መቶ ክ/ዘመን ላይ ዝነኛ ከነበሩት መካነ-ሰብ (መካነ-ሕያዋን) ሳሎን ጋር ተነጻጻሪ የሆኑ ክበቦችን ማጠናከር ወይንም መመሥረት በእጅጉ ተገቢ ነው፡፡  

(Visited 257 times, 1 visits today)
December 10, 2018

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo