Articles, News, Opinion, ሐተታ

“ሸኔ በመንግሥት ሰዎች ፕሮፓጋንዳ የተፈጠረ ነው”-አቶ ቀጀላ መርዳሳ (የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ)

አቶ ቀጀላ መርዳሳ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ናቸው፡፡ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራልና የክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የሥልጣን ዘመን እንዲራዘም በቅርቡ ባሳለፈው ውሳኔ እና ተያያዥ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከሲራራ ዝግጅት ክፍል ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሲራራ፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራልና የክልል የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥልጣን ዘመን እንዲራዘም መወሰኑን በመቃወም ድርጅታችሁ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የተቃውሟችሁ መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? ውሳኔው ከፀደቀ በኋላ መቃወማችሁ የሚኖረው ፋይዳስ?

አቶ ቀጀላ፡- የተቃውሟችን መሠረታዊ ምክንያት፣ ሕገ መንግሥቱ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መደረግ አለበት የሚል መሆኑ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንዲያ ስላለ ብቻም ሳይሆን በአንድ በአገር ዴሞክራሲያዊ ውክልና ካለ ምርጫ ማድረግ እንደ ትልቅ መርህ የሚቆጠር በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የተመረጡ ባለሥልጣናትም ይሁኑ፣ ምክር ቤቶች በሥልጣን ላይ መቆየት የሚችሉት በሕግ እስከተቀመጠላቸው ወይም እስከተፈቀደላቸው ጊዜ ድረስ ብቻ ነው፡፡

ሥልጣን የሚሰጠውም ከሥልጣን የሚያወርደውም ሕዝብ ነው፡፡ ለዚያ ደግሞ ምርጫ ማድረጉ ወሳኝ እና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ በእኛም አገር በሕገ መንግሥቱም በምርጫ ሕጉም ይህ ጉዳይ በግልጽ የተቀመጠ ነው፡፡ ሕጉ ወዲያ ወዲህ የሚል የሚዋዥቅ ነገር የለውም፡፡ በጣም ግልጽ ነው፡፡ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ መካሄድ ይገባዋል፤ በሕዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ሥልጣን መያዝ አይችልም ነው የሚለው ሕገ መንግሥቱ፡፡

በእርግጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ምርጫን ማራዘም የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ አሉም፡፡ ነገር ግን ሥልጣን ላይ የተቀመጠውን መንግሥት የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የሚያስችል የተቀመጠ ሕግ የለም፡፡ እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት፣ እኛ በምርጫው መራዘም ላይ ጥያቄ የለንም፡፡ ነገር ግን አገሪቱ በቀጣይ የምትመራበትን ሁኔታ እንዴት መልክ እናስይዘው በሚለው ወሳኝና አንገብጋቢ አጀንዳ ላይ መነጋገር ያስፈልጋል ብለን ተደጋጋሚ ጥሪ ስናቀርብ ነው የቆየነው፡፡ በበኩላችን የራሳችንን ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) አዘጋጅተን አቅርበናል፡፡ በገዥው ፓርቲ በኩል የተሰጠ በጎ መልስ ግን የለም፡፡ አሁን በግልጽ እንደሚታየው፣ እየሆነ ያለው ያቀረብነውን ምክረ ሐሳብ ወደ ጎን ትተው፣ ጉዳዩ በቂ ትኩረት ሳይሰጠው እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለውይይት ሳንጋበዝ፣ ሥልጣን ላይ ባለው ቡድን ውሳኔ ሰጪነት ብቻ ሥልጣን ለማራዘም ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ይህ አካሄድ በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱም በአንድ ፓርቲ ተወካዮች የተሞሉ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ለራሳቸው የራሳቸውን ውሳኔ ያሳለፉበትን ሁኔታ ነው አሁን እያየን ያለነው፡፡ በእኛ በኩል ይህነገር  በፍፁም አግባብነት የለውም፤ ጎጅ ነው እያልን ነው ያለነው፡፡

ለሕገ መንግሥት ትርጉም የተጠቀሱት አንቀጾችም ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንቀጽ 84(1) የሕገ መንግሥት አተረጓጎም ሂደቱን ነው የሚገልጸው፤ የሚተረጎም ነገር የለውም፡፡ አንቀጽ 78 ቢሆን የሚተረጎም ነገር የለውም፡፡ መተርጎም ከፈለጉ አንቀጽ 54 እና 58 ነበር መታየት የነበረባቸው፡፡ የሆነው ግን እሱ አይደለም፡፡

በአጠቃላይ ሥልጣን ለማራዘም የተሄደበት መንገድ አገሪቱንና ሕዝቦቿን በምንም ዓይነት የማይጠቅም ብቻ ሳይሆን የተለመደው የአንድ ቡድን ፍፁም አግላይ የሆነ አካሄድ ነው፡፡ ሥልጣን ለማራዘም በዚህ ደረጃ የሄዱት ሰዎች ሥልጣኑ በእጃቸው በመሆኑ ምክንያት የፖለቲካ ውሳኔ ነው የወሰኑት፡፡ በእኛ በኩል ሥልጣን ለማራዘም የተሄደበትን መንገድም ውሳኔውንም በመቃወም መግለጫ አውጥተናል፡፡ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይም ያለንን ሐሳብ ገልጸናል፡፡ በሥልጣን ላይ ያሉት አካላት ወደቀልባቸው ይመለሳሉ፤ በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ድርድሮች ይደረጋሉ ብለን እናምናለን፡፡

ሲራራ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ እኮ በርካታ የሕገ መንግሥት ምሁራንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተከታታይ የሆኑ ውይይቶች አድርገዋል፡፡ ሕዝቡ በቀጥታ በቴሌቪዥን የተከታተላቸው ምክረ ሐሳቦችም ቀርበዋል፡፡ ሒደቱን የምትቃወሙበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ቀጀላ፡- ውይይቶቹ በምንም ዓይነት ሁኔታ አሳታፊ አልነበሩም፡፡ ምክንያቱም በርካታ ምሁራን፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበራት የተሳተፉበት አልነበረም፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር አባላት ተሰባስበው ምክረ ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን በመድረኩ ላይ እንዲቀርብ አልተደረገም፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ናቸው እንዲሳተፉበት የተደረገው፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር ሕገ መንግሥቱን የሚቃወሙ፣ ሕገ መንግሥቱ መቀደድ አለበት፣ ሕገ መንግሥቱ አፍራሽ ነው፣ እኛን አይወክለንም፣ እኛን አላካተተንም የሚል ሐሳብ ከዚህ ቀደም ሲያራምዱ የነበሩ ሰዎች ናቸው ስለ ሕገ መንግሥት ትርጓሜ ሐሳብ ሲሰጡ የተመለከትናቸው፡፡ ይህም የነበረውን ውይይት ተዓማኒነት እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡

አንቀጽ 84ትም ቢሆን የሚለው በሕጉ አወዛጋቢ ነገሮች ሲኖሩ ጉዳዩን የሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚቴው ያያል ነው የሚለው፡፡ አሁን ላይ ምኑ አወዛግቦ ወደ ሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንደሄድን እንኳን ግልጽ ነገር የለም፡፡ ፍርድ ቤት ተመርቶ አሻሚ የሆነ አንቀጽ ወይም አዲስ ሕግ ወጥቶ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተቃረነ ነገር የለም፡፡ በነዚህ ሁኔታዎች ነው ትርጉም የሚፈለገው፡፡ ፍሬ ነገሩ ምርጫ ማራዘም አለማራዘም፤ የመንግሥትን ሥልጣን የማራዘም ያለማራዘም ጉዳይ ነው፡፡ አሁን የታዩት አንጾችም ቢሆኑ ስለ መንግሥት ሥልጣን መራዘም አንድም የሚሉት ነገር የለም፡፡

ሕገ መንግሥቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ክፍተት እንዳለው ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊም ሲናገሩ ነበር፡፡ እስከሚገባን ድረስ ክፍተት ካለው የሚተረጎም ነገር የለውም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ መፍትሔው መሆን የነበረበት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቁጭ ብሎ እንዴት እናድርግ ብሎ መመካከሩ ነበር፡፡ በዚያ መንገድ መተማመን ቢኖር አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የተስማሙበት ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ የሚኬድበትን መንገድ መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ከዚያ ይልቅ የአንድ ደርጅት ፍላጎት ነው ተፈጻሚ እንዲሆን የተደረገው፡፡

ሲራራ፡- አሁን የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች የሥልጣን ዘመን ተራዝሟል፡፡ የድርጅታችሁ ቀጣይ እርምጃ ምንድን ነው?

አቶ ቀጀላ፡- እኛ የምንለው አሁንም ጊዜው አላለፈም ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችመወያየት አለበን የሚል ሐሳብ ነው ያለን፡፡ የእኛ አገር ዴሞክራሲ የመድበለ ፓርቲ ርዕዮትን የሚቀበል ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን አንድ ፓርቲ ብቻውን የወሰነውን ውሳኔ ተቀበሉ ከተባለ ፓርቲውም ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ የበርካታ ፓርቲዎች ድምጽ እያታነቀ ከሄደ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ እየፈረሰ፣ ሕገ መንግሥቱም እንዲሁ እየተናደ እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ይህ ነገር የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ነው፡፡ ለማንም አይጠቅምም፤ የዴሞክራሲ ሽግግር የሚደረግበትን ዕድልም የሚዘጋ ነው፡፡

ከመስከረም 30 በኋላ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የሆነ ተጠያቂነት እና ኀላፊነት ነው የሚኖረን፡፡ በነጻና ፍትሐዊ ምርጫ በሕዝብ ተመርጦ ያሸነፈ ድርጅት አይኖርም፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ቅርቃር ውስጥ ለመውጣት ነው ከመስከረም በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ እንምከር-እንዝከር የምንለው፡፡

በእኛ በኩል፣ እንደ ፓርቲ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰነው ውሳኔ ግጭት ሊመጣ ይችላል የሚል ስጋት አለን፡፡ እንደሚታወቀው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች አሉ፡፡ ከመስከረም በኋላ እነዚህ ግጭቶች እንዳይባባሱ የሚል ትልቅ ስጋት ነው ያለን፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ከመስከረም 30 2013 ዓ.ም. በኋላ በሚኖረው ሁኔታ ላይ መወያየት ይገባናል፡፡ ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ከሁሉም የፖለቲካ ኀይሎች ጋር ለመደራደርና ለመወያየት በሩን ክፍት ማድረግ ይገባዋል፡፡ የድርድርና ውይይት በር ሲዘጋ የግጭትና አመጽ በር እንደሚከፈት በታሪካችን በሚገባ አይተነዋል፡፡

ሲራራ፡- በኦሮሚያ ክልል ላይ የምትንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኅብረት ለመመሥረት ጥረት ስታደርጉ ብትቆዩም አልተሳካላችሁም፡፡ እንዲያውም ኅብረቱ ከመመሥረቱ ፈርሷል ተብሏል፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ ቀጀላ፡-  ኅብረት ልንመሠርት ጥረት ስናደርግ የነበረው በክልል ደረጃ ነበር፡፡ እሱ በሐሳብ ላይ እንዳለ ሌላ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የፈጠርናቸው ሌሎች ጥምረቶች አሉ፡፡ “ትብብር ለኅብረ ብሔር እና ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም” የሚል እኛም ያለንበት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ሌሎችም ፓርቲዎች ያሉበት ጥምረት እየመሠረትን ነው፡፡ አሁን ላይ ኹለት ቦታ በአገር ዐቀፍ ደረጃ እና በክልል ደረጃ ጥምረት መመሥረት ይቻላል ወይ የሚለውን ለመወሰን ሕጎቹን እያየን ነው፡፡ በውስጣችን ግን ስምምነቶቹ እንዳሉ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል፣ በኦሮሚያ ክልል የምንቀሳቀስ ፓርቲዎች ኅብረት ለመመሥረት ተስማማን እንጂ ኅብረቱን በሕጋዊ መንገድ አልመሠረትንም ነበር፡፡ ስለዚህ ሳይመሠረት የሚፈርስ ነገር የለም፡፡ ለመመሥረት ቢያንስ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ሰርተፍኬትም አላገኘንም፡፡ አሁን በፌዴራል ደረጃ ያለው ጥምረት እያለቀ ስለሆነ በቀጣይ ሙሉ ትኩረታችን እዚያ ላይ ነው የሚሆነው፡፡

ሲራራ፡- በቅርቡ ብ/ጀኔራል ከማል ገልቹ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ በወለጋ የሚንቀሳቀሰውን “ሸኔ” የተሰኘ ታጣቂ ቡድን የሚያደራጀውና የሚመራው ኦነግ ነው የሚል አስተያየት ሰንዝረው ነበር፡፡ ከሸኔ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምንድን ነው?

አቶ ቀጀላ፡- የብ/ጀኔራል ከማል እንዲህ ማለት እኔንም በጣም ነው ያስገረመኝ፡፡ ምክንያቱም  በኦሮሚያ ክልል ሥልጣን ተሰጥቷቸው ከሥልጣን ሲነሱ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ስለ ባንኮች መዘረፍና ስለ አካባበቢው ፀጥታ መደፍረስ ተጠይቀው ቡድኑን የሚመራው ኦዲፒ ነው ብለው ነበር፡፡ የኦዲፒ ካድሬዎች ናቸው ባንክ የሚያዘርፉት፡፡ ድራማውን እናውቃለን ብለው ነበር፡፡ዛሬደግሞግለሰቡ በሌላ ገጽነው የሚናገሩት፡፡ ይኼ ምን ያህል ተዓማኒነት እንዳለው ማንም ሰው ሊረዳው የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡ ጀኔራሉ የሚናገሩት መሠረተ የሌለው እና እሳቸውንም ትዝብት ውስጥ የሚጥል ነገር ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ፣ ሸኔ የሚለውን ስያሜ የመንግሥት ካድሬዎች ናቸው ያወጡት፡፡ ሸኔ በመንግሥት ሰዎች ፕሮፓጋንዳ የተፈጠረ ነው፡፡ ይህን የሚሉትን ኀይል ለምን ዓላማ እንደፈጠሩትና እንዳደራጁትም ራሳቸው ናቸው የሚያውቁት፡፡ እኔ በግሌ ሸኔ የሚባለውን ድርጅት አላውቀውም፡፡

የታጠቁትን ኀይሎች ከሆነ እየተባለ ያለው እነሱ ራሳቸውን የሚጠሩበት የራሳቸው ስያሜ አላቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ ከእኛ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም፡፡ የእኛ የነበሩት ኀይሎች ወደ አገር ቤት ገብተው ሰላማዊ ትግል እያደረግን ነው ያለነው፡፡ ከየትኛውም የታጠቀ አካል ጋር ግንኙነት የለንም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እኛን ከታጠቁ ድርጅቶች ጋር የማያያዝ አካሄድ የድርጅታችንን ስም ለማጥፋትና ለማጠልሸት ሆን ተብሎ የሚደረግ ሴራ እንደሆነ ነው የምንረዳው፡፡ የምናደራጀውም ሆነ የምንመራው የታጠቀ ኀይል የለም፡፡ በሰላማዊና ሕጋዊ ሁኔታ ለመታገል ነው አገር ቤት የገባነው፡፡

ሲራራ፡- ከሕወሓት ጋር ያላችሁ ግንኙነትስ ምን ይመስላል? ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በኅብረትም ይሁን በግንባር ደረጃ ለመሥራት እንደምትሞክሩት ሁሉ ከሕወሓት ጋር አብሮ የመሥራት ዕቅድ የላችሁም?

አቶ ቀጀላ፡- ይኼየሚሆን አይመስለኝም፡፡ ሕወሓት የሚሄድበት መንገድ እና እኛ የምንሄድበት መንገድ ከፍተኛ ልዩነት ያለው ነው፡፡ እኛ መንግሥትን የምንቃወምበት መርህ እና እነሱ የሚቃወሙበት መርህም እንዲሁ በብዙ መልኩ የተራራቀ ነው፡፡ ለምሳሌ  እነሱ አሁን ምርጫ መደረግ አለበት ብለው ያስባሉ፤ በክልል ደረጃ ምርጫ ለማድረግ መወሰናቸውንም ተናግረዋል፡፡ እኛ ግን አሁን ከገባንበት የኮሮና ወረርሽኝ ችግር እስክንወጣ ድረስ በሥልጣን ያለው የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ እስከ አንድ ዓመት እንዲሠራ አቋም ወስደናል፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው ኢሕአዴግ ውስጥ ብዙ ችግር ነበር፡፡ ያ ችግር ነው ዛሬም ቢሆን አገሪቱን እያተራመሳት ያለው፡፡ “የለውጥ አመራር” የተባለው አካል ወደ ሥልጣን ሲመጣ በግንባሩ አባል ድርጅቶች መሀከል ልዩነቶች ተፈጥረዋል፡፡ የሕወሓት እና የብልጽግና ፓርቲ ልዩነት የምርጫ ብቻ ሳይሆን የውስጥ የፖለቲካ አለመስማማትም ያለበት ነው፡፡ በመሠረቱ የሥልጣን ክፍፍል ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የቀድሞ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እንደሚሉት መሠረታዊ ልዩነት አላቸው ማለት ያስቸግራል፡፡

ጥያቄውን ለመመለስ ያህል ግን፣ በእኛና በሕወሓት መሃል ያለው ልዩነት በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ከሕወሓት ጋር ኅብረትም ይሁን ጥምረት ለመፍጠርም ምንም ዓይነት ዕቅድ የለንም፡፡

(Visited 48 times, 1 visits today)
June 15, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo