Featured articles, ሐተታ

ሲቪክ ማኅበራት ይደገፉ፤ ይጠናከሩ!

የሕዝባችን የእርስ በርስ መስተጋብር ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲቀጥልና የአገራችን ህልውና እንዲጠበቅ፣ ብሎም የዴሞክራሲ ሽግግር ማድረግ እንድትችል ከተፈለገ ከፖለቲካ ድርጅቶች ይልቅ አገር በቀል የሆኑት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ ሚና መጫዎት ይገባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ የአገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ከዴሞክራሲና ከዴሞክራሲያዊ አሠራር አንጻር ሲመዘኑ ከፍተኛ ችግር ያለባቸው በመሆናቸው በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መጠናከር ላይ ትልቅ ትኩረት ሊደረግ ይገባል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የተቋቋመ የፖለቲካ ስብስብ ዴሞክራሲያዊ ስብዕና ባላቸው፣ ሐሳብ በሚያመነጩ፣ የሐሳብ ልዩነትን በሚቀበሉና ከልዩነት ጋር ለመኖር በሚችሉ፣ እንዲሁም ሐሳባቸውን ሳይፈሩ ለመግለጽም ሆነ የማይቀበሉትን ሐሳብ ለመቃወም ድፍረቱ ባላቸውና አገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል በቆረጡ ዜጎች የተቋቋመ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በላይ ግልጽና ሕዝብ በቀላሉ ሊረዳው የሚችለው ዓላማ፣ ይህን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ የሚችሉ ዴሞክራቶች የተሰበሰቡበት ዴሞክራሲያዊና ውስጠ ፓርቲ ህልውናው ጠንካራ የሆነ ድርጅት፣ ተግባሩ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚያስችል ግለሰባዊና ድርጅታዊ ቁርጠኝነት ወይም ዲሲፕሊን እንዲሁም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን የፖለቲካ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ገንዘብም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ 

የቀድሞዎችም ሆኑ የአሁኖቹ የአገራችን ፖለቲካ ፓርቲዎች ከላይ ከተጠቀሱት መመዘኛዎች አንጻር ሲመዘኑ ትልቅ ጉድለት ያለባቸው ናቸው፡፡ በየካቲቱ አብዮት ወቅት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ድርጅቶች የዘመኑን ሌኒኒስትና ስታሊኒስት አስተሳሰብ መሠረት አድርገው በምስጢር የተደራጁና በሕቡዕ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

በአብዮቱ ዘመን የነበሩት ብዙዎቹ ድርጅቶች ስለ ዴሞክራሲ ቢሰብኩም ራሳቸው ድርጅቶቹ ዴሞክራሲያዊ እንዳልነበሩ ይታወቃል፡፡ በምስጢር የተደራጁ፣ የተለየ ሐሳብን ብቻ ሳይሆን የተለየ ሐሳብ ያራመደውን አካል ለማጥፋት የሚሠሩ፣ በሴራ ፖለቲካ የተካኑ፣ ብዙሃኑ አባላት በማያውቋቸውና በድርጅታዊ አሠራር በተመረጡ ጥቂት አፈ ጮሌ ግለሰቦች የሚመሩ እንጂ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር በአካባቢያቸው ያልዞረ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ በወቅቱ በድርጅቶቹ ኢዴሞክራሲያዊ ባሕርይ ምክንያት የሐሳብና የአመለካከት ልዩነትን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ባለመቻሉ፣ በርካታ ብሩህ አእምሮ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተቀጥፈዋል፡፡

በአገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተፈቅዷል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የተቋቋሙት አብዛኛዎቹ ድርጅቶችም ቢሆኑ ከፍተኛ የሆነ የዓላማና የርዕዮተ ዓለም ውዥንብር ያለባቸው፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እንደሚታገሉ እየገለጹ ነገር ግን በድርጅታቸው ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሠራር የሚባል የማያውቁ፣ ማኅበራዊ መሠረታቸው የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንደሆነ እንኳን ይደግፈናል ለሚሉት ሕዝብ ለራሳቸውም ያልገባቸው፣ ከፍተኛ የሆነ የዲሲፕሊን ችግር የሚታይባቸው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ በጣም የገዘፈ የገንዘብ አቅም ችግር ያለባቸው ብቻ ሳይሆን ከውጭም ከውስጥም በልመና የተገኘችውን ገንዘብ በወጉ ማስተዳደር የማይችሉና ከልመና በተገኘ ገንዘብ የሚጣሉ ናቸው፡፡ 

የአህጉራችን ፖለቲካ ትልቁ ችግር፣ ፖለቲካ የግለሰቦች የችግር ማስወገጃ መሆኑ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ (ብዙውን ጊዜ) ሰዎች ፖለቲካ ውስጥ የሚገቡት መጀመሪያ የራሳቸውን ኑሮ አሸንፈውና ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ሐሳብ ይዘው ሳይሆን፣ የፖለቲካ ሥልጣንን የሀብት ምንጭ ለማድረግና ራሳቸውንና ወገኖቻቸውን በአገርና በሕዝብ ሀብት ለማበልጸግ ነው፡፡ ይህ በአገራችን በተቃዋሚውም ሆነ በገዥው ፓርቲ አካባቢ በግልጽ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ ፖለቲካ ከግለሰቦች ችግር ማስወገጃ መሣሪያነት እስካልወጣ ድረስ ደግሞ የትም ፈቀቅ አንልም፡፡

ፖለቲካ አገርና ሕዝብን ለማገልገል የሚገቡበት እንጂ የሚገለገሉበት መሆን የለበትም፡፡ በሌላ በኩል፣ በሥልጣን ላይ ያሉት አካላት የትናንቱ የግራ ፖለቲካ ሰለባ ሲሆኑ፣ ከእነሱ ውጪ ያለውም በከፍተኛ ችግር የተተበተበና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንጻር ተስፋ ሊጣልበት የሚችል አልሆነም፡፡

የኢትዮጵያ ህልውና እንዲጠበቅ፣ የዜጎች ሰላማዊ ግንኙነት ያለ እንከን እንዲቀጥልና የዴሞክራሲ ሽግግር እንዲመጣ ትልቁን ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት፣ አገር በቀል የሆኑት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ልዩ ልዩ የሙያና የጥቅም ማኅበራት ናቸው፡፡

በዘመነ አብዮት ስለ ብዙሃን ድርጅቶች አስፈላጊነት ያልተባለ ነገር አልነበረም፡፡ በወቅቱ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ስለ ብዙሃን ድርጅቶችና ማኅበራት አስፈላጊነት ይከራከሩ እንጂ፣ ድርጅቶቹ ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ሳይሆን በእነሱ ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ ነበር ምኞታቸው፡፡ የሙያ ማኅበራቱንና ሌሎች ብዙሃን ድርጅቶችን ሰርጎ ገብቶ ለመቆጣጠር የነበረው ሽኩቻና ትግል ከፍተኛ ነበር፡፡ ኢዴሞክራሲያዊ ከሆነው የሰርጎ መግባትና የመቆጣጠር አስተሳሰብ አሁንም ተፈውሰናል ማለት ያስቸግራል፡፡

አሁንም ቢሆን በሁሉም ጎራ ያለው አብዛኛው ፖለቲከኛ ከዚያው ከግራው አስተሳሰብ ያልተላቀቀ ወይም በዚያ ባህል ያደገና ሳያውቀው በዚያ ቫይረስ የተለከፈ በመሆኑ ሁሉንም ነገር በመቆጣጠር የሚያምን ነው፡፡ ማንኛውም ስብስብ በዐይነ ቁራኛ ነው የሚታየው፡፡ ከተቻለ ሰርጎ መግባትና መቆጣጠር ካልሆነ ደግሞ ማጠልሸት፣ ማዳከም፣ ማፍረስ ወይም በሌላ ተለጣፊ ማኅበር መተካት የተለመደ አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ አደገኛ አስተሳሰብና አካሄድ እስካልተላቀቅን ድረስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት አንችልም፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ከተቻለ ለመቆጣጠር ካልሆነም ለማዳከም የሚደረገው ጥረት ተቋማቱ ገለልተኛ አገራዊ ተቋማት እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ዘመን ተሻጋሪ ከመሆን ይልቅ ሁልጊዜም መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር ከፈጣሪያቸው ጋር አብረው የሚጠፉ ተቋማት ይሆናሉ፡፡ ከዚህ የጥፋት አዙሪት መውጣት ይኖርብናል፡፡ ሁላችንም በገለልተኝነት የሚያስተናግዱ ጠንካራ አገራዊ ተቋማትና ሥርዓታት ያስፈልጉናል፡፡ ኢትዮጵያዊን ከአጥፊው የአምባገነን አዙሪት ለመላቀቅ ጠንካራ ሲቪክ ማኅበራት ያስፈልጉናል፡፡ ጠንካራና ገለልተኛ ሲቪክ ማኅበራት እንዲኖሩን እንሥራ፡፡

(Visited 19 times, 1 visits today)
June 24, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo