ምን ዓይነት ሽግግር? የለውጡ ተግዳሮቶችና አጣዳፊ የፖሊሲ እርምጃዎች -(በሙሉጌታ ጉደታ (ጋዜጠኛና ደራሲ)
Articles, Featured articles, ሐተታ, ፖለቲካ

ምን ዓይነት ሽግግር? የለውጡ ተግዳሮቶችና አጣዳፊ የፖሊሲ እርምጃዎች -(በሙሉጌታ ጉደታ (ጋዜጠኛና ደራሲ)

በፖለቲካ ሽግግር ላይ ለሚገኝ ለማንኛውም አገር የሚሠራ ‘የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሞዴል’ ወይም ‘ንድፈ ሐሳብ’ የሚባል ነገር የለም፡፡ የሽግግር ዘመን ታክቲክም ሆነ ስትራቴጂ፣ እንዲሁም የሚወሰዱት የፖሊሲ እርምጃዎችም ሆኑ ፕሮግራሞች በእያንዳንዱ አገር ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የሚመሠረቱ እንጂ ለሁሉም አገር የሚሠሩ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ሽግግር ወቅት መቃኘት የሚኖርበት በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ፣ ተግዳሮቶቹና እድሎቹን በመገምገምና በእነሱም ላይ በመመሥረት የሕዝብ ተጠቃሚነት የሚያስገኙ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመተንተን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የከሸፈ ዴሞክራሲና የከሸፉ ሽግግሮች

እስከ ዛሬ ድረስ በአገሪቱ ከሦስት ያላነሱ ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር አመቺ የሆኑ ወቅቶች ተከስተው ሁሉም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳኩ ማለፋቸውን ልሂቃን ደጋግመወው ይናገራሉ፡፡ እስካሁን በአገሪቱ ከተካሄዱትና ከከሸፉት ሽሽግሮች መካከል በኢሕአዴግ መሪነት የተካሄደውን ሽግግር መቃኘትና ለምን እንደ ከሸፈ ማየት የአሁኑን ሽግግር ዕድሎችና ፈተናዎች ለመረዳት፣ እንዲሁም ሽግግሩን ለማሳካትና ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ  መወሰድ የሚገባቸውን የፖሊሲ እርምጃዎች ለመቃኘት ሊረዳ ይችላል፡፡

የሽግግር መንግሥት በሚለው ርእስ “ኢንካርታ ኢንሳይክሎፒዲያ” የተባለው የማጣቀሻ መጽሐፍ በ1983 የተካሄደውን የኢትዮጵያን ሽግግር እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፡-  

  “የ36 ዓመቱ የኢሕአዴግ መሪ በሆነው በመለስ ዜናዊ አማካይነት ጊዜያዊ መንግሥት ተቋቁሞ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ የተባለው ስብስብ አብዮቱን በመራው በሕወሓት የበላይነት የሚመራ ነበር፡፡ መለስ ከትግራይ የመጣ የቀድሞ ማርክሲስት ሲሆን የትግራይ ማርክሲስት ሌኒኒሰት ሊግን የመሠረተውም እሱ ነበር፡፡ ይህም ማሌሊት የሚባለው መንግሥቱ ኀይለ ማርያም ከሚመራው የማርክሲዝም ዓይነት የተለየ ነበር፡፡ ሆኖም ግን መለስ የሚለው ዴሞክራሲ ሰላማዊ በሆነ ሽግግር አማካይነት ጊዜያዊ መንግስት ይቋቋማል ብሎ ነበር” (ማይክሮሶፍት ኢንካርታ፣ 2002)

ታሪክ እንደ መዘገበው ሁሉ መለስ ዜናዊ ሐቀኛ ዴሞክራሲም ሁሉን ወካይ ወይም አካታች የሽግግር መንግሥትም አልመሠረተም ነበር፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ባሕሩ ዘውዴ የሶሺያሊስት ተምኔትን ፍለጋ (The Quest for Socilaist Utopia) በሚለው መጽሐፋቸው በሕወሓት ፊታውራሪነት የተመሠረተው በዘር ላይ የቆመው ፌዴራሊዝም፣ “…ከውጪ ሲመለከቱት የዴሞክራሲያዊ ስተዳደር ገፅታ ያለው ቢመስልም በ1997 በተካሄደውና በአገሪቱ የመጀመሪያው በሆነው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ፊት መቆም አቅቶት ተሰባብሮ ወድቋል…” (ገፅ 264) ተመሳሳይ አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡

የሽግግር ዘመን ስኬትም ሆነ ክሽፈት የሚለካው ወደ ሐቀኛ ዴሞክራያዊ ሥርዓት በማምራቱ ወይም ባለማምራቱ ሲሆን፣ ከዚህ አንጻር ሲታይ በኢሕአዴግ የተማራውም ሆነ ከዚያ በፊት የተከሰቱት የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ዕድሎች ባክነው መቅረታቸው በአብዛኞቹ ምሁራን ትንተና የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡   

አሁን ብዙዎች እንደሚስማሙበት የሽግግር መንግሥት አቋቋምኩ ያለው አንድ ፓርቲ ለ27 ዓመታት አገሪቷን ፀጥ ለጥ አድርጎ ቀጥቅጦ ሲገዛ ቆይቷል፡፡ ከ1997 ምርጫና ከከሸፈው የዴሞክራሲያዊ ሽግግር እድል በኋላ የነበሩት ዐሥራ አራት ዓመታት በፖለቲካ ረገድ ፍፁም የባከኑ መሆናቸው አሁን ይበልጥ ግልፅ ሆኗል፡፡ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሕዝቡና አገሪቱ ከገሃነም ደጃፍ ላይ ቆመው ቆይተዋል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሽግግሩን ለመምራት እንደ መለኮታዊ ኀይል ድንገት መከሰታች ለጊዜውም ቢሆን አገሪቷ ከቆመችበት የገሃነም አፋፍ እንድትመለስ ረድቷታል፡፡ ወደ ገሃነም አፋፍ ላለመመለስና ሽግግሩን ለማሳለጥ፣ እንዲሁም ሕዝቡ ከለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚከተሉትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎችን መውሰድ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡  

ብሔረተኛነትን በአግባቡ መያዝ

ብሔርንና ብሔረተኛነትን በተመለከተ ላለፉት 27 ዓመታት ከፍተኛ የጽንሰ-ሐሳብና የተግባር ውዥንብር ሰፍኖ መቆየቱ ይነገራል፡፡ በንድፈ-ሐሳብ ደራጃ እንኳን በ“ብሔር፣ በብሔረሰብ”፣  “ዘር” እና “ጎሳ” መካከል ያለው ልዩነት እስከዛሬ ድረስ አልጠራም፡፡ ግልጽ ባልሆኑ አስተሳሰቦች የተነሳ ግን አያሌ ሕዝብ አሁንም እየሞተ ወይም እየተጋደለ ነው፡፡

በኢሕአዴግ የሚያቀነቅነው ብሔረተኛነት ከሩሲያው አምባገነን ጆሴፍ ስታሊን “የብሔር ጥያቄ” (The National Question) ከሚለው መጽሐፍ በቀጥታ የወረደ ነውም ይባላል፡፡ ይህ ንድፈ-ሐሳብ ብሔረተኛነትን ከጠባቡ የማርክሲስት ሌኒኒስት አቋም አንጻርና ከሩሲያ ተሞክሮ በቀጥታ ስለተቀዳ ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ሳይሆን የችግር ምንጭ ሆኖ እስከ ዛሬ ዘልቋል የሚል የሰላ ሂስ ሲሰነዘርበት ቆይቷል፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙት በተለይ የሂሱ ዒላማ የሆነው በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 የሰፈረውና፣ “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር-ብሔረሰብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማንኛውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው” የሚለው ክፍል ነው፡፡  

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት የብሔር ጥያቄው የማይቀርብና ኢሕአዴግ በመቃብሩ ላይ ካልሆነ በስተቀር ከማይለውጣቸው ያለቀላቸው ፖሊሲዎች አንዱ ሆኖ ስለተቆለፈ ውይይት ለማካሄድም ሆነ አማራጮችን ለመፈለግ ዕድል አልነበረም፡፡ የብሔረተኛነት አተገባበር የሚወሰነው በመሠረቱ በገዢ መደቦችና በስልጣን ኤሊቶች አመለካከት መሆኑን አቴና ኤስ ሌዊስና አንቶኒ ዲ. ስሚዝ “የብሔረተኛነት ኢንሳይክሎፒዲያ” በተባለው መጽሐፋቸው አብራርተውታል፡፡ ተመራማሪዎቹ እምደሚሉት፡-

“…ብሔረተኛነት፣ እንደ ማንኛቸውም የእምነት ሥርዓቶች ሁሉ፣ በተቀዳሚነት ጥቅም ላይ የሚውለውም ሆነ የሚበላሸው በገዢ መደቦች፣ ወይም በስልጣን ላይ ባሉ ልሂቃን፣ በተቀናቃኝ የገዢ መደቦች ወይም ልሂቃን ለመሆን በሚመኙ ወገኖች ነው…” (ገፅ 147)

ብዙዎች እንደሚስማሙበት ብሔረተኛነት የኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ ወይም ዛሬ የተፈጠረ ክስተት አይደለም፡፡ በዚህኛው ወይም በዚያኛው የፖለቲካ ንቅናቄ የፈጠረም አይደለም፡፡ ብሔረተኛነት ከፖለቲካ ንቅናቄዎች መፈጠር አስቀድሞ ለብዙ መቶ ወይም ሺሕ ዓመታት የኖረ ነው፡፡ በይቅር ቢባልም ሊቀር የሚችል የፖለቲካ ክስተትም አይደለም፡፡ እነዚሁ ወገኖች ጀምረው እንደሚሉት ብሔረተኛነት ችግር መን የጀመረው የፖለቲካ ንቅናቄዎች ከተፈጠሩ በኋላ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸው ተመራማሪ እንደሚሉት ብሔረተኛነት የሚበላሸው “ያላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል” እንዲሉ በገዢ መደቦችና በልሂቃን ስህተት ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ የሽግግር ሂደቱን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ በአገሪቷ ፖለቲካ አድማስ ላይ ሙሉ ለሙሉ የተንሰራፋው የብሔረተኛነት ፖለቲካ ነው፡፡ ብሔረተኛነት በራሱ መጥፎ ነገር አይደለም፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ተመራማሪ እንዳሉት፣ ብሄረተኛነትን ክፉም ደግም የሚድያደርገው የሚስተናገድበት ወይም የሚተገበርበት መንገድ መሆኑ ነው፡፡  

ታፍኖ የኖረው የኦሮሞ ብሔረተኛነት አሁን በተፈጠረው አመች ሁኔታ ውስጥ በፍጥነት በማደግ ላይ መሆኑና የአገሪቱን ፖለቲካ በበላይነት መቆጣጠሩን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ እንደሚባለው ከሆነ የአቶ ለማ መገርሳና የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የኦሮሞ ብሔረተኛነት ከሌሎቹ የኦሮሞ ብሔረተኛነት አዝማሚያዎች የሚለይበት ዋናው ነጥብ ለጊዜውም ሆነ በዘለቄታ ከኢትዮጵያዊነት ወይም ከኅብረ-ብሔራዊነት ጋር መስማማቱ ወይም የኢትዮጵያዊነትን ጠንካራ አቀንቃኝ ሆኖ መውጣቱ ነው፡፡

በብዙዎች ዘንድ መልካም ዕድል የሚባለው ይህ ቡድን በዚህ የሽግግር ወቅት አገራዊ የመግባባት ወይም የመቻቻል ፖሊሲ ግንባታ (consensus building) መሠረት መሆኑ ነው፡፡ አደጋ ሊፈጥር ይችላል የሚባለው ደግሞ፣ ይህ ለዘብተኛ ብሔረተኛነት በጽንፈኛ ብሔረተኛነት ጫና ስር መሆኑና ሁለቱን ወገኖች በሚዛናዊነት ለመያዝ ከፍተኛ የፖለቲካ በልሃትና ጥንቃቄ ስለሚጠይቅ ነው፡፡ በተለያዩ የኦሮሞ ብሔረተኛነት አዝማሚያዎች መካከል (ፌዴራሊዝምን ከሚያቀነቅኑት አንስቶ የኦሮሚያ ነጻነትን በስውርም ሆነ በግልጽ እስከሚያራምዱት ድረስ) የሚነሱ የታክቲክም ሆነ የስትራቴጂ ቅራኔዎች ላላስፈላጊ ፉክክሮችና ለግጭቶች መንስኤ እሆኑ ስለመሆናቸው ተጨናጭ ምልክቶች እየታዩ ናቸው የሚል ፍርሃትና ጥርጣሬ ከብዙ ወገኖች ይሰነዘራል፡፡ ለዚህም ነው የሽግግሩ ወቅት ለግጭቶች የተጋለጠ ሊሆን ይችላል የሚባለው፡፡

በዚህ ረገድ ዶ/ር ዐቢይን የገጠማቸው ግዳሮት እጅግ ከባድ ነው፡፡ በመሠረቱ ተግዳሮቱ የሚመነጨው ከራሳቸው የኦሮሞ ‹ኮንስቲትወንሲ› ነው፡፡ በአንድ ወገን ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን በሌላ ወገን ደግሞ ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔረተኛነት ከቁጥጥር ውጪ እንዳሆን እያባበሉ ሽግግሩን ለማሳለጥ መሞከር ዐቢይን የገጠማቸው ከባዱ ፈተና ነው፡፡ ይህንን ፈተና እንዴት በተመለከተ በቅርቡ በተከናወነው 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ላይ እንደ ተነገረው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን የሚጭሩና ሕዝቡን ለሞትና ለስደት የሚዳርጉ ቡድኖች (በውሰጠ ታዋቂነት አክራሪ የኦሮሞ አንጃዎች) ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ነገር ግን ይህ ካልሆነ ግን መንግስታቸው የሕግ በላይነት ለማስከበር ማንኛውንም እርምጃ እንደሚወስድ ዶ/ር አብይ አስጠንቅቀዋል፡፡ ይህ በበኩሉ በፍቅር፣ በሰላምና በመደመር “ፍልስፍናቸው” እና በነዚህ አፈንጋጭ ቡድኖች ላይ ሊወሰድ በሚችለው የኀይል እርምጃ መካከል ሌላ የምርጫ እንቆቅልሽ መደቀኑ አይቀርም፡፡ የኦሮሞን ፖለቲካ ከሚዘውሩት ኦሮሞዎች መካከል፣ (ለምሳሌም ጃዋር መሐመድ በቅርቡ በአዲስ ስታንዳርድ ድረ-ገጽ ላይ በጻፉት አስተያየት) እንደሚሉት ከሆነ ዶ/ር ዐቢይ ኀይል ለመጠቀም ማመንታታቸው ደካማ አድርጎ ሊያሳያቸው ይችላል፡፡ ኀይል መጠቀማቸው ደግሞ የሰላማዊ ሽግግሩን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል፡፡   

 ግዙፍ የሆነው የአገር ውስጥ ስደት ማስቆም

የዘርና ብሔረሰብ ፖለቲካ በኢሕአዴግ አማካይነት የአገሪቱ ይፋ የፖለቲካ አቅጣጫ ሆኖ ከተጫነ ጊዜ ጀምሮ በልሂቃን ቀጥተኛ ተሳትፎና አስፈጻሚነት ለግጭት በመዳረግ ለብዙ ሺሕ ለሚቆጠሩ ንጹሐን ሕዝቦች መጨፍጨፍ ምክንያት ሆኗል ይባላል፡፡ በመቶ ሺሕዎች ወይም በሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎች በአገር ውስጥ ለመሰደዳቸው ዐቢይ ምክንያት ሆኗል፡፡ በቅርቡ በወጣው መረጃ መሠረት ኢትየጵያ በአገራቸው ውስጥ በሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር ግንባር ቀደሙን ቦታ ይዛለች፡፡ ኢሕአዴግ ሲያራምደው የቆየው ብሔረተኛነት በተለያዩ ምክንያቶች ብሔራቸውን ወይም ዘራቸውን በግልፅ መናገር የማይችሉትን ወይም የማያውቁትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ያገለለ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ብሔረተኛነት የሚገራበትንና የግጭትና የደም መፋሰስ መነሻ የማይሆንበትን እንዲሁም ከዲሞክራሲ ጋር የሚቀናጅበትን መንገድ ለመፈለግ በዚህ ኮንፈርንስ በአጀንዳነት ለውይይት ቢቀርብ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ በዘርና በብሔር ላይ የተመሠረቱ ፓርቲዎች እንዳይመሠረቱ በሕግ ለመከልከል፣ የተመሠረቱትም አቅጣጫቸውን እንዲለውጡ ለማድረግ ወቅቱ አይፈቅድ ይሆናል፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚያስጠነቅቁት ከሆነ ብሔረተኛነት የግጭትና የህዝብ እልቂት ምንጭ መሆኑን ከቀጠለ አንድ ደረጃ ላይ ማስቆም አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ አገር ዘረኛነትንና ጽንፈኛ ብሔረተኛነትን ለማስቆም የሩዋንዳው ዓይነት ጭፍጨፋ እስኪፈፀም መጠበቅ አያስፈልግም የሚሉ ድምፆች ተደጋግመው ይሰማሉ፡፡    

የኢህአዴግን የወደፊት ህልውና መወሰን

በቅርቡ ከሚሰነዘሩ አስተያየቶች መካከል የኢሕአዴግን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ሐሳቦች ይገኙበታል፡፡ ይህ የአራት የብሔር ቡድኖች ስብስብ ተለውጦ፣ በምትኩ እያንዳንዱ ድርጅት ለብቻው ሆኖ ስሙንና ዓላማውን ከብሔርተኛነት ወደ ኅብረ-ብሔራዊነትና ወይም ደግሞ እንደ ኦዴፓ ኹለቱንም አጣምሮ የሚይዝበት መንገድ መፈለግ ይገባዋል የሚሉም ወገኖች አሉ፡፡  

ለዚህ አባባላቸው የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ ኢሕአዴግ አሁን ባለበት የፖለቲካ ቁመናው የሚቀጥል ከሆነ ሥልጣኑን ላለመልቀቅ ከመጀመሪያው ጀምሮ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ ቀመር ላይ የተመሠረተ ውክልና ስላለው ዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ጠንክሮ ሥር እስካልሰደደ ድረስ እንደ ተለመደው በማጭበርበርና በሴራ አሸናፊ ሊሆንና ሥርዓቱን በተለመደው መንገድ በውድም በግድም ሊያስቀጥል ይችላል የሚለው ትንተና ነው፡፡

ለዚህም አባባል የተወሰኑ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ መጀመሪያ ነገር ኢሕአዴግ ያረጀ ያፈጀ ርዕዮተ-ዓለሙን ማለትም፣ “አብዮታዊ ዴሞክራሲን” በይፋ አራግፎ አልጣለም፡፡ ለአንድ ሰው ወይም ለአንድ ቡድን አምባገነንነት ምክንያት የሆነው ”ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” የሚባለው ረቂቅ የመቆጣጣሪያ ድርጅታዊ ስልቱን አልተወም፡፡  እነዚህ ሁኔታዎች በግልጽና በይፋ እስካልተለወጡ ድረስ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ስም መቀየርና ዓርማ መቀየር ወይም “ወጣቱን ወደ አመራር ማምጣት” የሚባለው ዘይቤ በመሠረቱ ኢሕአዴግን እየጠጋገኑ ለማስቀጥል ከመሞከር አያልፍም በማለት እነዚሁ ወገኖች ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡

በቅርቡ በተካሄደው 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ወቅት የኢሕአዴግ የወደፊት ህልውና ዕድል ተድበስብሶ የታለፈ ሲሆን ወደፊት ‘ርዕዮተ-ዓለሙን ለማደስ’ ጥቆማ ተደርጎ ታልፏል፡፡ ይህ አካሄድ “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” የሚለውን የአማርኛ አባባል የሚያስታውስ ሲሆን ጉዳዩ ተሸፋፍኖ መታለፉ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው መሠረታዊ ቅራኔ አለመፈታቱን ያመለክታል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ይደመጣሉ፡፡ ሌሎች ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ የኢሕአዴግ ውጫዊ አንድነት እስከ ምርጫ 2012 ብቻ የሚቆይ ሲሆን ከዚያም ወዲህ ቢሆን በስትራቴጂ ጥያቄዎች ላይ ቅራኔ ሊፈጠርና የድርጅቱን ህልውና በማንኛውም ጊዜ አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል፡፡   

 ቁልፍ ሆነውን የሽግግር ወቅት የኢኮኖሚ ጥያቄ መመለስ

በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ዙሪያ የሚጽፉ ልሂቃን እንደሚሉት ሕዝቡ በመስዋዕትነት ለውጥ እያመጣ ልሂቃን ወይም ኢሊቶች ፍሬውን ሲነጥቁት ቆይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሽግግር ላይ በሰፊው የሚተነትኑ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ የአሁኑ ለውጥ መነሻና መድረሻ እንዲሁም የሽግግሩ ወቅት እምብርት ጉዳይ የመሬት ጥያቄ ነው፡፡   

በእነዚህ ወገኖች አስተያየት ሕዝቡ እስከ ዛሬ የተሰቃየውና የሞተው ለመሬቱና ለነጻነቱ ስለሆነ የትግሉ ፍሬ የሆነውን መሬት ማንም የማይነጥቀው፣ ሊሸጠውና ሊለውጠው የሚችለው የግል ሀብቱ መሆን ይገባዋል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በፊት በመንግስት ቢሮክራሲና በሕወሓት እኩይ ፖሊሲ የሚያርሱትን መሬታቸውን የተቀሙና የተነጠቁ ወይም በውዳቂ ዋጋ እንዲሸጡ የተደረጉ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የሚኖሩ ገበሬዎች ካሳ እንዲከፈላቸው፣ መሬታቸው እንዲመለስላቸውና የባለቤትነት ማስተማመኛ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ፖለሲ መቅረፅና በአስቸኳይ መተግበር ያስፈልጋል፡፡

እንደ ተንታኞቹ አባባል ይህ ከየካቲት 1966 ጀምሮ ሲንከባለል የመጣው የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ አሁን የመጨረሻ መቋጫ ካላገኘ መቼም አያገኝም፡፡ ስለሆንም በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት፣ “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና ሕዝብ ብቻ ነው” በሚል ሽፋን የገዢ መደቦች የሥልጣን ማስፈፀሚያና ማስጠበቂያ የሆነውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ በመለወጥ “መሬት የአራሹ ገበሬ ሕዝብ ንብረት ነው” በሚለው ለመተካት የሚያመች አዲስ ፖሊሰ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡  በመሬት ጉዳይ ላይ የሰላ ሂስ የሚሰነዝሩ ወገኖች እንደሚሉት፣ የአገሪቱን 80 ከመቶ የሚያህል ሕዝብ የሚመለከተው ይህ የፖሊሲ ለውጥ እስካልተተገበረ ጊዜ ድረስ አሁን የሚካሄደው ለውጥ ትርጉም የለሽና እንደ ተለመደው የልሂቃን ጫጫታና የሥልጣን ሽኩቻ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡

ይህንን ነጥብ በተመለከተ በቅርቡ የአዳማ ኢንዱስትሪ ዞን በሚመረቅበት ወቅት ዶ/ር አሕመድ ጊዜያዊ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገባ ጠቆም አድርገው አልፈዋል፡፡ ኢንዱስትሪ ዞኑ ሲመሠረት መሬታቸውን ለለቀቁት ገበሬዎችና ለልጆቻቸው የሥራ ዕድል ቅድሚያ እንዲሰጥ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ ይህ ነጥብ መታየት ያለበት በአለፍ ገደም ሳይሆን በፖሊሲ መልክ ተቀናጅቶ መሬታቸውን በተለያየ መልክ የተነጠቁ ገበሬዎች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ የሚያደርግ ሕግ መደንገግ አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው የገበሬዎች የመሬት ጥያቄ በመላው አገሪቱ ወጥነት ባለው መንግሥት ሊመለስና የለውጡ ዋና ደጋፊ የሆነው ክፍል ለውጡን እየደገፈ እንዲቆይ የሚያደርገው፡፡

በሽግግር ወቅት ከኢኮኖሚ ይልቅ ለፖለቲካው የበለጠ ትኩረት ስለሚሰጥ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ችላ ሊባሉ ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ ምሁራን ግምት አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ከሽግግር መንግሥት ጠቃሚ የኢኮኖሚ ለውጥ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ቁልፍ የሚባሉትን የአገሪቱን የኢኮኖሚ አውታሮች ወደ ግል ይዞታ ለማዞር የተወሰዱት የፖሊሲ ውሳኔዎች፣ በፋይናንስ ሴክተሩ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ለማጠናከር፣ የአገሪቱን የወደብ አማራጮች ያሰፋውን የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት የመሳሰሉት ወሳኝ የፖሊሲ እርምጃዎች ሲሆኑ፣ በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ መሰረታዊ የማክሮኢኮኖሚክ ለውጦችን በእርሻውና በኢንዱስትሪው ሴክተሮች እንደሚጠበቅ እነዚሁ ምሁራን ያሰምሩበታል፡፡

ለወጣቱ ተጨባጭ ጥቅም ማስገኘት

ዲሞክራሲያዊ ለውጡ የተጀመረውም ሆነ እዚህ ደረጃ የደረሰው በመላው የአገሪቱ ሕዝብ ትግል መሆኑን ሁሉም ወገኖች ይስማሙበታል፡፡ እንደ ብዙ ሰዎች እምነት ከሆነ በኢትዮጵያ የሽግግር መሠረታዊ ችግር ሆኖ የቆየው ሕዝቡ መስዋዕትነት ከፍሎ ለውጥ ማምጣቱና ነገር ግን የተለያዩ የኢሊት ወይም የልሂቃን ቡድኖች በግልጽም ሆነ በስውር የለውጡን ፍሬ መቀማታቸው ነው፡፡ ይህ ሲሆን የሽግግር ሂደቱም በዚያው ተኮላሽቶ ወደ ሌላ አቅጣጫ ይሄዳል፡፡ በተለይም ወጣቱ የለውጥ ማምጫ መሣሪያ ከሆነ በኋላ ወደጎን የመገፋት ወይም የመረሳት እጣ ፈንታ እንደሚገጥመው ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡  

በኢትዮጵያ የቀድሞውንም ሆነ የአሁኑን የሽግግር ሂደት በቀግንባር ቀደምነት ያፈነዱት ወጣቶች ቢሆኑም የሽግግሩ ባለቤቶች ግን እነሱ አይደሉም፡፡ ባህሩ ዘውዴ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው እንሚሉት፣ “ብዙውን ጊዜ ተማሪዎች የአብዮት አነሳሾች ቢሆኑም የድኅረ-አብዮቱን ሂደት የራሳቸው ማድረግ ይሳናቸዋል፤” (ገፅ 265)፡፡ ለዚህም አባባላቸው እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት ከአራት አመት በፊት በግብፅ ታህሪር አደባባይ የተካሄደውንና የሕዝቡን የለውጥ ንቅናቄ የፈጠረውን የተማሪዎችና የወጣቶች እንቅስቃሴ ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት “ይህ እንቅስቀሴ በሂደት ወደጎን ተገፍቶ ወታደሩና የእስላም ወንድማማቾች የተባለው ድርጅት ለሥልጣን የሚፋጩበት ሁኔታ ተፈጠረ” በኢትዮጵያም የሽግግሩን ሂደት ከሚያደናቅፉት ሁኔታዎች መካከል አንደኛው የወጣቱ ወደጎን መገፋት ወይም የለውጡ ባለቤት አለመሆኑ ነው የሚሉ ስጋቶች ከወዲሁ እየተሰሙ ነው፡፡

ብዙዎች እንደሚስማሙበት ወጣቱን የለውጡ ፍሬ ተቋዳሽ የማድረጉ ከባድ ተግዳሮት ቢሆንም፣ ለነገ የሚተው ጉዳይ ግን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወጣቱ በተዘነጋና ወደጎን በተገፋ ቁጥር የሌላ ተቃውሞና አለመረጋጋት እንዲሁም የግጭት ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡ የተቆጣና ተስፋ የቆረጠ ወጣት ደግሞ የሚያቆመው ኀይል እንደሌላ እያሳየ ነው በማለት እነዚሁ ወገኖች ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ በተለይም በቄሮዎች መካከል መናበብና አንደነት ማስፈን ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ቄሮ ተከፋፈለ ማለት ደግሞ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪ ዶ/ር መረራ ጉዲና በቅርቡ እንዳሉት ወጣቱ ለተለያዩ የኦሮሞ አንጃዎችና ኤሊቶች የአጀንዳ ማስፈፀሚያ መሣሪያ ለመሆንና በደርግ ዘመን ለተከሰተው ዓይነት የእርስ በርስ ጦርነት መጫሪያ ክብሪት ሊሆን ይችላል፡፡ 

የአገሪቱ ሕዝብ 70 ከመቶ ይሆናል የሚባለው የወጣቱ ክፍል፣ በተለይም የተማረው ወጣት ክፍል፣ ለለውጡ አስተዋጽዖ እንዳደረገ ሁሉ ከለውጡ ተጨባጭ ጥቅም እስካላገኘ ድረስ ለውጡን የደገፈውን ያህል ሊጠላው ይችላል፡፡ ወጣቱን በመሸንገልም ሆነ ያለውሆነ ተስፋ በመስጠት መያዝ አይችልም፡፡ የወጣቱ ሆድ ባዶ ሆኖና እጆቹ ሥራ ፈትተው ለውጡን ማስቀጠል አይችልም፡፡ አገሩን ለመለወጥ ከሁሉም ነገር በፊት ወጣቱ መስራት፣ መብላትና በሕይወት መቆየት ይኖርበታል፡፡ የወጣቱ ክፍል የተረጋጋ የመደብ መሰረት ስለሌለውና በአብዛኛው በአመለካከቱም ሆነ በተግባሩ የሚዋልል የኅብረተሰብ ክፍል ስለሆነ ለመልካምም ለመጥፎም ድርጊቶች ግንባር ቀደም ሲሆን ይስተዋላል፡፡

በተለይም የከተሞች መስፋፋትና የሥራ አጥ ወጣቱ ቁጥር በሚያስደነግጥ ሁኔታ እያደገ መምጣቱ ለማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፍንዳታዎች አቀጣጣይ ንጥረ ነገር ይሆናል፡፡  አቺም ዌንማን የተባሉ በግጭቶች ዙሪያ ምርምር የሚያካሂዱ ምሁር “የኦስሎ ፎረም” በተባለው መፅሄት ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንደሚሉት፣

“በሚቀጥሉት ዐሥርት ዓመታት ግጭት በከፍተኛ ደረጃ የሚካሄደው በከተሞች ይሆናል፡፡ የዚህም ምክንያቶች የከተሞች በፍጥነት መስፋፋት፣ ማኅበራዊ እኩልነት መታጣት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጫና ውስጥ የሚወድቁ የአስተዳደር ሥርዓቶች ይሆናሉ…” 

እነዚህ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦች በኢትዮጵያም እየተከሰቱ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡  

ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ምክንያቶች ወጣቱን ማዕከል ያደረጉና ሽግግሩን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ለውጦች በአስቸኳይ ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ከዚህ አኳያ የልማት ፖለሲዎችን እንደገና ለመከለስ የእራሱ የወጣቱ ተወካዮች በተገኙበትና በሙስማሙበት ሁኔታ የወጣቶች የስራ ፈጠራ ፕሮጀክቶች ሊዘረጉና በገጠርም ሆነ በከተማ ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል፡፡ አስፈላጊም ከሆነ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዘነውን ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠፍ ከዚያ የሚገኘውን ከፍተኛ ፋይናንስ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ማዋል ይቻላል፡፡ ችግሩ እጅግ ግዙፍ ስለሆነ ይህ ተግባር በሚኒስቴር ደረጃ መመራት የሚገባው ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡       

ማጠቃለያ

የሽግግር ወቅት ብዙ ችግሮች በአጭር ጊዜ እንዲፈቱ የሚጠበቅበት አጣዳፊ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ጊዜ ወሳኝ ነው፡፡ በተለይም በቀጥታ በሕዝብ ላልተመረጠ መንግሥት አስጨናቂ ይሆናል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት መርሐ-ግብር አውጥቶ የገባውን ቃል ኪዳን በቅደም ተከተል በፍነት ካልተገበረ በስተቀር ጊዜ ሊያጥረው ይችላል፡፡  

አንድ መንግሥት በሕዝብ ድጋፍና ተወዳጅነት ብቻ ረጅም መንገድ ሊጓዝ አይችልም፡፡ ድጋፍ የፖለቲካ ካፒታል ነው፡፡ ከፒታሉ ደግሞ እንደ ተበላ እቁብ ተመንዝሮ ሊያልቅ ይችላል፡፡ የህዝብ ድጋፍና ስሜት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ጊዜ ወሳኝ እርምጃዎችን መውሰድና ውሳኔዎችን ማስተላለፍ እንዲሁም ፖሊሲዎችን ማፅደቅ የግድ ይላል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የሚታማበት  አንድ ነጥብ ቢኖር ተጨባጭ እርምጃ ለመውሰድ የሚፈጅበት ጊዜ ነው፡፡ ነገሮች በፍጥነት በሚለዋወጡበት በአሁኑ ወቅቱ አስፈላጊ እርምጃዎችን በጊዜ አለመውሰድ ተመልሰው የማይገኙ መልካም አጋጣሚዎችን በከንቱ የማባከን ያህል ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡ 

(Visited 88 times, 1 visits today)
December 13, 2018

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo