ሕግን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ-ተሾመ ተስፋዬ (የሕግ ባለሙያ)
History, Politics, ሕግ, ፖለቲካ

ሕግን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ-ተሾመ ተስፋዬ (የሕግ ባለሙያ)

የአንድ አገር የሕግ ሥርዓት በከፊልም ቢሆን የግለሰቦች ወይም የሕዝቦች የጋራ የፖለቲካ ውሳኔ ውጤት ነው፡፡ ሆኖም ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ተቋም ለሕግ ተገዢ የሆነበትንና ፍትሕ የሰፈነበትን አገር ለመገንባት እና ዜጎችን ከፖለቲካ ሥርዓትና ባለሥልጣናት ጭቆና ለመከላከል የሕግ ሥርዓቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከፖለቲካ ሥርዓቱ ነጻ መሆን ይኖርበታል። የሕግ ሥርዓት የፖለቲካ ሥርዓቱ በተቀያየረ ቁጥር የሚቀያየር ሳይሆን ዘላቂነት ባለው መልኩ መደራጀት ያለበት ከመሆኑም በላይ የሥልጣን ሽግግር በሕግ መሠረት መከናወን ስላለበት በፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ ገደብ የሚያደርግበት ሁኔታም ይኖራል። ይህም ከሕግ የበላይነት መርሆ ጋር የተቆራኘ ሲሆን በተለይም በምዕራቡ ዓለም ያልተገደበ ንጉሣዊ ሥርዓት መቅረትና ዘመናዊ ሥልጣኔን ተከትሎ ተቀባይነትን ካገኘ ቆይቷል።

ለረጅም ጊዜ ለሕግ የበላይነት ይሰጥ የነበረው ትርጓሜ የጠበበ ሲሆን በጥቅሉ ሲታይ ሕግ አስቀድሞ የተደነገገ ሥርዓትን ተከትሎ መውጣት ያለበት መሆኑ፣ በሕግ ፊት ዕኩል ሆኖ መታየትን፣ ሕጉም ሆነ አፈጻጸሙ ለሕዝብ ግልጽ፣ ተገማችና ወጥ መሆንን በመስፈርትነት ያስቀምጣል። ነገር ግን የተጠቀሱትን መመዘኛዎች ባሟላበት ሁኔታ እንኳን አንድ የሕግ ሥርዓት ባደጉት አገሮች ጭምር በዜጎች ላይ በርካታ በደሎችንና የመብት ጥሰቶችን ሊፈፅም እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። ለምሳሌ ብዙዎቻችን የምናውቃቸው በአሜሪካ እስከ 1960ዎቹ አጋማሽ ድረስ ጥቁሮች በዘር ላይ የተመሠረተ መገለል የደረሰባቸው እና ሴቶች የመምረጥ መመረጥ መብት የተነፈጉት፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ሥርዓትም አፍሪካዊያኑን የጨቆነው ከሞላ ጎደል መመዘኛዎቹን ያሟላ የሕግ ሥርዓትን በመጠቀም ነበር። የጀርመን የናዚ ሥርዓት በተመሳሳይ መልኩ ሕግን ተጠቅሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዶችን ፈጅቷል፣ በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ አሰቃይቷል። እነዚህና ሌሎች በርካታ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ በተለይም ከ1960ዎቹ በኋላ አገሮችና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የሕግ የበላይነት መሥፈርቶችን እንደገና ለመፈተሽ ተገድደዋል።

በዚህም መሠረት በአንድ አገር የሕግ የበላይነትን በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ ከተፈለገ ከላይ የተገለጹትን መመዘኛዎች ከማሟላት ባለፈ የሕግ ሥርዓቱ በይዘትም የተወሰኑ መሠረታዊ መብቶችን በሚያስከብር መልኩ ሊቀረጽና ሊተገበር እንደሚገባ ከሞላ ጎደል መግባባት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነው።

በእርግጥ ሕግ በዋናነት ከአንድ አገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ የሁሉም አገር ሕግ ተመሳሳይ እንዲሆን አይጠበቅም። ሆኖም የሚወጡ ሕጎችና አተገባበራቸው ቢያንስ የግለሰቦችና የሕዝቦችን መሠረታዊ መብቶች ያከበሩና የፖለቲካ ተሳትፎዋቸውን የሚያጎለብቱ ሊሆኑ እንደሚገባ መግባባት ላይ የተደረሰ ይመስላል። በተግባርም ሲታይ የዳበረ የፍትሕ ሥርዓት ባላቸው አገሮች የሕግ የበላይነት መርሆ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን የፍትሕ ተቋሞቻቸው አወቃቀርም ሆነ አሠራር በዚሁ የተቃኘና ከፖለቲካ ሥርዓት ነጻነት ያለው ነው። ይህን መነሻ በማድረግ የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት የሕግ ሥርዓቱ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥን እየተከተለ እየፈረሰ፣ የገዢዎችን የፖለቲካ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ሲደራጅ የነበረ በመሆኑ ቋሚና ወጥ የሆነ ሥርዓት ያልገነባን መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል።

“በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን እንገነባለን!”

***

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አገሪቱን የማዋቀሪያ ዋና ዓላማ አድርጎ ከወሰዳቸው ጉዳዮች አንዱ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሆነ በመግቢያው ላይ ያመለክታል። በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ በርካታ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኙ የግለሰቦችና ሕዝቦች መሠረታዊ መብትና ነጻነቶችን በዝርዝር አስፍሯል። በአንቀጽ 9 እና 13 ላይ ደግሞ ማንኛውም የመንግሥት አካልና ባለሥልጣን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ግዴታ ያለበት መሆኑን በግልጽ ደንግጓል። ከዚህም በመነሳት የሕግ የበላይነትና የሰብአዊ መብት ጉዳይ ቢያንስ በሕገ መንግሥት ደረጃ ጉልህ ስፍራ የተሰጠው መሆኑን ብዙ ባለሙያዎችም ይስማማሉ። ሆኖም በተለይም ከምርጫ 1997 በኋላ በሕገ መንግሥቱ ከተገቡት ተስፋዎች ባፈነገጠ መልኩ ገዢው ፓርቲ የሕግ ሥርዓቱን ሥልጣኑን ለማደላደልና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለማፈን በስፋት እየተገለገለበት እንደሚገኝ በርካታ የዘርፉ ምሁራንና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የተለያዩ ማሳያዎችን በማንሳት ይሞግታሉ። የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ትኩረትም ይህንኑ ከነመነሻ ምክንያቱ ማሳየት ስለሆነ ወደዚያው እንለፍ።

አብዮታዊ ዲሞክራሲና የሕግ የበላይነት ምንና ምን ናቸው?

***

በአገራችን ያለው የፍትሕ ሥርዓት ተቋማዊ ነጻነት የሌለውና በአገዛዝ ሥርዓቱ ጡንቻ ሥር የወደቀ መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል። በዚህ የተነሳ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር ይልቅ የሥርዓቱ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግልባቸው አጋጣሚዎች በርካታ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ። ገዢው ፓርቲ ከላይ የሕግ የበላይነትና ሌሎች ተያያዥ መርሆዎችን በሕገ መንግሥቱ አስፍሮ እያለ፣ ከዚህ በተጻረረ መልኩ ሕግን ለሥልጣኑ ማደላደያና የተቃውሞ ድምፅ ማፈኛነት በስፋት ወደ መጠቀም ያዘነበለበትን ሁኔታ በተመለከተ ባለሙያዎች በርካታ መነሻ ምክንያቶችን ያቀርባሉ። በዋና መነሻ ምክንያትነት የሚጠቀሰውም ድርጅቱ የሚያራምደው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም በሕገ መንግሥቱ ላይ ከሰፈረው የሕግ የበላይነት መርሖ ጋር የማይሔድ መሆኑ ነው። ለምሳሌ አቶ አደም አበበ የተባሉ ጸሐፊ “Rule by Law in Ethiopia: rendering constitutional limits on government power non sensical” በተባለ ጽሑፋቸው ላይ ይህንኑ ጠቅሰው ይከራከራሉ።

ምንም እንኳን የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ትክክለኛ ትርጉም ለማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም ርዕዮተ ዓለሙ መንግሥትንና ፓርቲን አንድ አድርጎ የመመልከት፣ ሁሉን ነገር የመቆጣጠር ፍላጎትና የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱ ወገኖችን በጠላትነት የመፈረጅ ዝንባሌ እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ። ይህም ገዢው ፓርቲ አራምደዋለሁ በሚለው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮግራምና በሕገ መንግሥቱ ላይ በሰፈሩ የሕግ የበላይነትን የሚደነግጉ ድንጋጌዎች መካከል ከመነሻው አለመጣጣም መኖሩን ያረጋግጣል። በፓርቲው ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው የአመራር አባላትን ጨምሮ በርካቶች እንደሚስማሙት ድርጅቱ ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት ዓለም ዐቀፍ ሁኔታው ሊብራሊዝም አሸንፎ የወጣበት በመሆኑና የምዕራባውያን አገሮችና ዓለም ዐቀፍ ተቋማትን ድጋፍ ለማግኘት በማሰብ የሕግ የበላይነት መርሆንና የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በሕገ መንግሥቱ አካተተ እንጂ ከድርጅቱ የፖለቲካ ፕሮግራምና ባህል ጋር እምብዛም የማይሄዱ ናቸው።

ሕገ መንግሥቱን በማውጣት ሒደትም ቢሆን ከሕግ የበላይነትን መርሆ ጋር ተጣጥመው የማይሄዱና የድርጅቱን የፖለቲካ ዓላማ ታሳቢ በማድረግ በሕገ መንግሥቱ የተካተቱ ድንጋጌዎችም እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ። ለምሳሌ የሕገ መንግሥትን ትርጉም ጉዳይ ለገለልተኛ ፍርድ ቤት ከመስጠት ይልቅ ባልተለመደ ሁኔታ የፖለቲካ ተቋም ለሆነው ለፌደሬሽን ምክር ቤት መስጠቱን በማሳያነት በመጥቀስ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው ጸሐፊ ይከራከራሉ።

ድርጅቱ እከተለዋለሁ የሚለው የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብም ቢሆን ልማትን ከሕግ የበላይነትና ከፍትሕ የሚያስቀድም ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አስቀድመው የነበሩት የዐፄውና የደርግ ሥርዓትም በንጉሡ ሁሉን አድራጊና ፈጣሪነት፣ በደርግና በጓድ መንግሥቱ ጠቅላይነትና አምባገነንነት ላይ የተመሠረቱና ለሕግ የበላይነት የማይገዙ መሆናቸውን፣ በተጨማሪም በማኅበረሰቡ ዘንድም “ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ” እና መሰል አባባሎች መገለጫ የሆኑበት ለአምባገነንነት የተመቸ ባህል መኖሩ ገዢው ፓርቲ የሕግ ሥርዓቱን ለፖለቲካ ዓላማው ለማዋል እንዲችል ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ የነበረው አስተዋጽዖ የማይናቅ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። በነዚህና ሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች የተነሳ በሒደት በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ድርጅቱ እውነተኛ መልኩ እየተገለጠ ሲሄድ በሕገ መንግሥቱ ለተደነገገው የሕግ የበላይነት መርሖ ከመገዛት ይልቅ የሕግ ሥርዓቱን ለፖለቲካ ዓላማው በስፋት ወደ መጠቀሙ አዘንብሏል። አሁን ሁኔታው ቀጥሏል።

ጭንብሉ ሲገለጥ

***

በመሠረቱ የአንድ አገር የፍትሕ ሥርዓት የፖለቲካ ተጽዕኖን የመጋፈጥና የሕግ የበላይነትን የማስከበር አቅሙ በዋነኛነት የሚፈተነው በፖለቲካም ሆነ በሌላ ምክንያት ችግር ሲከሰት መሆኑን የዓለም ተሞክሮ በግልጽ ያሳየናል። የሕግ የበላይነት ተከብሯል ለማለት የሚቻለው በእንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች የፍትሕ አካላት ተቋማዊ ነጻነታቸውን ጠብቀውና በተለይም ከባለሥልጣናቱ የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ ተቋቁመው ሥራቸውን በሕግ መሠረት ማከናወን ሲችሉ ነው።

ወደ አገራችን ሁኔታ የመጣን እንደሆነ ገዢው ፓርቲ በእስካሁኑ የተራዘመ የሥልጣን ጉዞው የሕግ የበላይነትን አክብሬ አስከብራለሁ በማለት በተለይ በሥልጣን ጅማሮው ወቅት ያሰማው የነበረው ዲስኩር ከውስጠ ፓርቲ የፖለቲካ ባሕርይውና ፕሮግራሙ ጋር የማይሄድ በመሆኑ የተነሳ በተለይም የሥልጣኑ መደላድል ችግር በገጠመው ወይም ችግር የገጠመው በመሰለው ጊዜ ሁሉ እውነተኛ ባሕርይው አደባባይ ወጥቶ፣ በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የፓርቲው አሠራር ተጠርንፈው ረቂቅ ሕግ በቀረበላቸው ቁጥር ያለ ምንም ተቃውሞ እጅ አውጥተው በሚያጸድቁ የፓርላማ አባላቶቹን በመጠቀም የፈለገውን ሕግ በማውጣትና የፓርቲውን ተጽዕኖ ለመቋቋም አቅም የሌላቸውን የፍትሕ አካለት በመጠቀም የሕግ ሥርዓቱን ለጠበበ የፖለቲካ ዓላማው ሲያውለው በበርካታ አጋጣሚዎች ለመታዘብ ችለናል።

ሥርዓቱ ሕግን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ በግልጽ ከተጠቀመባቸው አጋጣሚዎች አንዱ በ1993 በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት የፈታበት የሕግ ሒደት ነው። በወቅቱ በስዬና በመለስ ቡድኖች መካከል ውስጥ ውስጡን ሲካሄድ የነበረው መተጋገል በመለስ ቡድን አሸናፊነት የተደመደመ ሲሆን አሸናፊው ቡድን የፀረ ሙስና ሕግ በማውጣት ከአንድ ቀን በኋላ እነ ስዬን በቁጥጥር ሥር ያውላል። በኋላም ፍርድ ቤት ተከሳሹ በዋስትና እንዲለቀቁ ሲያዝ ሁለት የሥራ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሙስና የተከሰሰ ማንኛውም ሰው ዋስትና የሚከለክል በብዙዎች ዘንድ “የስዬ ሕግ” በመባል የሚታወቀውን አዋጅ በማውጣት ሕጉ ወደኋላ ተመልሶ እንዲሠራ በማድረግ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ዋጋ እንዲያጣ አድርጓል።

የሚያስገርመው ሕጉ ይህን የታቀደለትን ዓላማ ካሳካ በኋላ ዋስትና በሚፈቅድ ሌላ አዋጅ ተተክቷል። ወደ ፖለቲካ መተጋገሉ ዝርዝር ሁኔታ መግባት ሳያስፈልግ ሕጎቹ የወጡበትና ተግባራዊ የተደረጉበትን ሒደት መነሻ በማድረግ ብቻ የሕግ የበላይነት መርሆን በሚጥስ መልኩ ተከሳሾችን ለማሰርና የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ዋጋ ማሳጣትን ዓላማ ያደረጉ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።

የምርጫ 97ን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ መሆንን ተከትሎ ሥርዓቱ የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካትና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለመገደብ የሕግ ሥርዓቱን በመሣሪያነት በስፋት እንደተጠቀመበት ብዙዎች ይስማማሉ። ለዚህም እንደ ማሳያነት የሚጠቀሰው በምርጫው ጊዜያዊ ውጤት ተቃዋሚዎች ከአንድ መቀመጫ በስተቀር በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ማሸነፋቸው፣ እንዲሁም በፌዴራል ምክር ቤት በርካታ መቀመጫዎችን ማግኘታቸው ገዢውን ፓርቲ ስላስደነገጠው ለመሰናበት ጥቂት ጊዜ የቀረውን ምክር ቤት በመጠቀም በጥድፊያ ባወጣቸው አዋጆች የከተማውን የፖሊስ ተቋምና ሌሎች የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ተቋማትን በፌደራል መንግሥቱ ሥር በማዋቀር በወቅቱ የአዲስ አበባን አስተዳደር ሊረከብ የነበረው ቅንጅት ለማዳከም አቅዶ እንደ ነበር ብዙዎች ይስማማሉ – ጸሎቱ ሰምሮ ሥልጣን ሳይረከቡ ቀሩ እንጂ።

በሌላ በኩልም በፌደራል ምክር ቤት ተቃዋሚዎች በርካታ መቀመጫዎችን በማግኘታቸው ቀደም ሲል በምክር ቤቱ ውይይት አጀንዳ ለማስያዝ የሚስፈልገው ድምፅ 20 ብቻ ቢሆንም አብላጫ ድምፅ አስፈላጊ እንዲሆን በማድረግ ሕጉን አሻሽሏል። ይህም ተቃዋሚዎቹ የራሳቸውን አጀንዳ ለማስያዝ እንዳይችሉ ለማድረግ ታልሞ የወጣ መሆኑን ብዙዎችን የሚያስማማ ጉዳይ ነው። በኋላም ሥርዓቱ የፖለቲካ ግቡን ዋነኛ ዓላማ ያደረጉ በርካታ ሕጎችን ያወጣ ሲሆን በተለይም የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅና የሲቪክ ማኅበራትን ለመቆጣጠር በሚል ያወጣቸው አዋጆችም የተቃውሞ ድምፅን ለማፈንና የሥልጣኑን ዕድሜ ለማርዘም የተጠቀመባቸው መሆኑን በእርግጥም ሕጎቹ በተቃውሞ ጎራ ያሉትን ግለሰቦችና የነጻ ሚዲያ ጋዜጠኞችን ለማሰር ማዋሉን በማየት ለማረጋገጥ ይቻላል።

ሕግን በዘመቻ

***

የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ ከተፈለገ ሕግም ሆነ የሕግ አተገባበር ለሕዝብ ግልጽና ተገማች መሆን አለበት። ሕግን በማስፈፀምና በመተርጎም የተሰማሩ የፍትሕና ሌሎች ተቋማትም አሠራራቸው ወጥና ግልጽ ሊሆን ይገባል። ይህ በተሟላበት ሁኔታ ሕዝቡ ስለመብትና ግዴታው እርግጠኝነት ስለሚኖረው ሕይወቱን በዕቅድ ለመምራት ይችላል። በኛ አገር የመንግሥት ተቋማት ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ አይደሉም። በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ በፓርቲና በመንግሥት መካከል የነበረው ቀጭን መስመር የበለጠ እየጠበበና የመንግሥት ተቋማቱ በፓርቲው ጥላ ሥር እየወደቁ መምጣታቸው የአደባባይ እውነታ ነው። በዚህ የተነሳ ሕጎች ወጥተው በኅብረተሰቡ ሳይለመዱ፣ ጉዳትና ጥቅማቸው በአግባቡ ሳይመዘን፣ ሕዝቡን በበቂ ሁኔታ ባሳተፈ መልኩ በቂ ጥናት ሳይደረግባቸው ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳትን በመከተል የሚቀያየሩበት አጋጣሚ ብዙ ነው።

ሕግን የሚያስፈፅሙ ተቋማትም ከፖለቲካ አመራሮች በሚሰጣቸው ቀጭን ትዕዛዝ የሚዘወሩ በመሆኑ ሕግንና የአሠራር ሥርዓትን ተከትለው ተግባራቸውን ወጥነት ባለው መልኩ ከማከናወን ይልቅ ከፖለቲካ አመራሮች በሚሰጣቸው ቀጭን ትዕዛዝና ጫና የተነሳ ተግባራቸው የተዘበራረቀና በዘመቻ የተሞላ ነው። በቅርቡ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳበውን በአዲስ አበባ ሕገ ወጥ ናቸው ያላቸውን ቤቶች ለማፍረስ መንግሥት የጀመረው ዘመቻ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆነን ይችላል። ዝርዝር ሁኔታዎችን ወደጎን ትተን ጉዳዩን በጥቅሉ ስንመለከተው ቤቶቹ ከተሠሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፣ መንግሥትም እንደየወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ በተለይም በምርጫ ወቅት ‹ሕጋዊ ትሆናላችሁ› እያለ፣ ሲያሻው ደግሞ ‹ሕገወጥ ናችሁ› እያለ ለማፍረስ በመንቀሳቀስ ግልጽና ወጥ ያልሆነ የሕግ ማስፈፀም ሒደት ውስጥ ማለፉ የአደባባይ እውነታ ነው። ይህ የመንግሥት አካሄድ በርካቶች ስለመብትና ግዴታቸው እርግጠኛ እንዳይሆኑ ያደረገ ሲሆን ቤቶቹን በማፍረስ ሒደትም የሕግ አስፈጻሚዎችን ጨምሮ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማስከተሉ በቁጭት የምናስታውሰው እውነታ ነው።

(Visited 139 times, 1 visits today)
January 30, 2019

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo