Featured articles, Politics, ሐተታ, ፖለቲካ

ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሥርዓት ይበጃታል?-በቴዎድሮስ ኅይለማርያም (ዶ/ር)

ይህ ጥያቄ ገና ከ1928 ዓ.ም የጣልያን ወረራ ቀድሞ ባለው ዘመን ባቆጠቆጠው የለውጥ ሐዋሪያ ልሂቃን በተለያየ መልኩ የተነካካ ቢሆንም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ በማንሳት የተሟላ መልስ ለማቅረብ የሞከሩት እውቁ ሊቅ ሀዲስ ዓለማየሁ ነበሩ፡፡ ከዚያ ወዲህ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ሀዲስ ካቀረቡት አማራጭ ሌላ ሁለት ፍፁም የተራራቁ የአገር አስተዳደር ርዕዮት ዓለሞች የተከተሉ ሁለት አገዛዞች  በተግባር ተሞክረዋል፡፡ የወታደራዊው ደርግ አብዮታዊ መንግሥት ለ17 ዓመታት፤ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘውጋዊ መንግሥት ለ27 ዓመታት በተቃራኒ አቅጣጫ አገሪቱን ሲያንገላቱ ከርመዋል፡፡ ሆኖም ዛሬም እንዳዲስ ለአገራችን ምን ዓይነት ብሔራዊ ሥርዓት እንደሚበጃት መነጋገሪያ ሰዓት ላይ ነን፡፡ “ዞሮ ዞሮ ዜሮ” እንደሚባለው ዓይነት፡፡

ጥያቄውን ያስታወሰኝ ላለፉት 27 ዓመታት “ሞቶ ተቀበረ” እየተባለ ሲሟረትበት የከረመው ኢትዮጵያዊነት ካልተጠበቀ አቅጣጫ ባልተጠበቀ ሰዓት በለውጥ ፍልስፍናነት አንገቱን ቀና ማድረጉ ነው፡፡ ይህ በአስደናቂነቱ ልክ በአግባቡ ያልተወያየንበትን ክስተት አብዛኞቻችን የተቀበልነው በሁለት ተቃራኒ ስሜቶች ነው፡፡ አንደኛው  “ጠርጥር ከገንፎ አይጠፋም ስንጥር!” ነው፡፡ ለውጡንም ሆነ የለውጡን ኀይል የኢትዮጵያዊነት ትርክት እስካሁንም በጥርጣሬ የሚመለከቱ አሉ፡፡  ጥርጣሬ መዳረሻው ወደ ሴራ ንድፈ-ሐሳብ ነውና ባለፉት ስምንት ወራት ገደማ የተግተለተለውን ሁሉ ነገር እንደ ታላቅ የወያኔ ድራማ አለበለዚያም እንደ ኦሕዴድና ኦነግ የጣምራ ተውኔት የሚቆጥሩ አሉ፡፡ መጠራጠር በልኩ ሲሆን ጤናማነት ነው፡፡ እንደዚህ ለከት ያጣ ጥርጣሬ ግን በሽታ ነው፡፡  ናፖሊዮንና ሂትለር አልሞቱም ብለው የሚያምኑና ምድር ጠፍጣፋ ናት ብለው ማኅበር ያቋቋሙም ሁሉ መኖራቸውንም መዘንጋት የለብንም፡፡

ሁለተኛው የለውጡን ኢትዮጵያዊነት የተቀበልንበት መንፈስ ደግሞ በሙሉ ልብ ማመን ነው፡፡ በዚህም ወገን ከተንጸባረቁት የተለያዩ ዝንባሌዎች ዋነኛው ክስተቱን ከተአምራት መቁጠር ነው፡፡  ኢትዮጵያ የፈጣሪ ተራዳኢነት የማይለያት ቅድስት አገር ናት፡፡  ስለዚህ ለውጡ አይቀሬ ነው፡፡ ቲም ለማም ሆነ ዐቢይን በግል የኢትዮጵያ አምላክ የላካቸው ተአምራት አስፈፃሚዎች ናቸው፡፡ ይኼ ነገር ብሔራዊ እምነት እንጂ ሃይማኖት አይደለም፡፡ በተለምዶ በአንድ ሃይማኖት አለመገደቡ ብቻ ሳይሆን እምብዛም በሃይማኖት ጥብቅነት የማይታወቁ “ሳይንቲስቶችን” ጭምር የማረከ እምነት ነው፡፡ “ይኼ ልጅ አግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የላከላት ነው!” እውነትም ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን አገር ናት!

እነዚህ ሁለት ዝንባሌዎች አግባብ ናቸው ወይም አይደሉም ማለት ጉንጭ አልፋ ነው፡፡ ጥርጣሬው በብሔራዊ ፖለቲካችንና ፖለቲከኞቻችን ሥነ-ምግባር ላይ ካሳደርነው ተጨባጭ ትዝብት የሚነሳ ነው፡፡ እምነቱም ጭፍን ሳይሆን በአገሪቱ ብሔራዊ ትውፊተ ታሪክ የተደገፈና ኢትዮጵያዊነት ለብዙ ሺሕ ዘመናት በታሪክ ውጣ ውረድ ካለፈበት የጽናት ተመክሮ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም አመለካከቶች የሚያማክለውን የኢትዮጵያዊነት ማንሰራራት ምሥጢር የሚገልፁት በምክንያትና ውጤት ላይ ተመስርተው አይደለም ለማለት ነው፡፡

ባለፈው ግማሽ ምዕት የአገር ግንባታ መንግሥታዊና ብሔራዊ አማራጮች ላይ ለመደማመጥ ትዕግሥት አጥተናል፡፡ ምን ዓይነት ፖለቲካዊ ሥርዓትና መንግሥታዊ አወቃቀር ይበጀናል? የብሔራዊ አቋማችን ቅርፅና ይዘት ምን ይምሰል? የሚለው በጡንቻና በሁካታ የሚወሰን ነበር፡፡ በተለይ ስለኢትዮጵያዊነት በወጉ ተነጋግረን አናውቅም፡፡ በየራሳችን የኢትዮጵያዊነት ትርጉም ተቧድነን ተፋለምን እንጂ፡፡ በዘመነ ደርግ ኢትዮጵያዊነት ለጥቃት ባይጋለጥም እምብዛም ከመፎክር ያለፈ ትኩረት አላገኘም፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ ደግሞ ከናካቴው በይፋ የተወገዘ ርዕሰ ጉዳይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት በደረሰበት ዙሪያገብ ጥቃት ከፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ከምሁራዊውም ዓለም ወደ ጥጋጥግ ተገፍቶ ቆይቷል፡፡

ስለዚህም እንደ ሕዝብ በአንገብጋቢ የብሔራዊ ማንነትና የአገር ግንባታ ርዕሶች ላይ ለማሰላሰልና ለመምከር የምንችልበት እድል ተዘግቷል፡፡ በአንድ ጥግ “ኢትዮጵያዊነት ወይም ሞት!”  በሌላው ደግሞ  “የፌዴራል ሥርዓቱ የሚፈርሰው በመቃብራችን ላይ ነው፤” የሚል ፈሊጥ አለ፡፡  ይህ ቀና ያልሆነ መንፈስ ደግሞ ሙግታችን፣ ጥላቻችንና ውዴታችን ከፊደሉ ያለፈ እንዳይሆን እግር ተወርች አስሮታል፡፡ ይህን የጭፍንነት ገረገራ ሰብረን በጭብጡ ላይ መነጋገር ከጀመርን ስለአገር ግንባታ አማራጮች ለመተማመን ረዥም መንገድ እንጓዛለን፡፡

በዚህ መንፈስ ለውይይት መቀስቀሻ እንዲሆን ያሳለፍናቸውን ሁለት የአገር ግንባታ ሙከራዎች አጠር አጠር አድርጌ አቀርብና አሁንስ ምን ይበጀናል ለሚለው በአማራጭ ሐሳብ እደመድማለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ስለ አገር ግንባታ ምንነት ጥቂት ልበል፡፡ አገር ግንባታ በአጭሩ መንታ ዘርፎች ያሉት ብሔራዊ መንግሥት ግንባታ ነው፡፡ አንደኛው መንግሥት ግንባታ ሲሆን፣ ይህም ለአገር አስተዳደር የሚያገለግሉ ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊና ሥርዓታዊ መዋቅሮች ላይ ያተኩራል፡፡ በተለይም ወታደራዊና ኤኮኖሚያዊ ሀብቶችን የማማከል፤ የመሬት ስሪትና የግብር ሥርዓት የመዘርጋትና የመቆጣጠር፤ የፍትሕና ሕግ ሥርዓት የማቆምና የማስከበር ተግባራትን ያጠቃልላል፡፡ ሁለተኛው ብሔር ግንባታ ደግሞ አገራዊ ማንነትና ሥነ-ልቡናዊ አንድነት ላይ የሚያተኩር ሂደት ነው፡፡ ይህም የጋራ ርዕዮተ ዓለም መንደፍ፣ የጋራ ሥርዓተ ትምህርት፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችንና ትዕምርቶችን  ማደራጀት፣ ማበልፀግና መጠበቅን ያካትታል፡፡

በዚህ መሠረት ቀጥሎ የቀረቡትን እስከ ዘመነ ደርግ የዘለቀው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትና በዘመነ ኢሕአዴግ ሥራ ላይ የዋለው አዲስ የዘውጌ ብሔርተኝነት የአገር ግንባታ ሂደቶች የምንገመግማቸው ልዩና ግልፅ የብሔራዊ ማንነት ንቃተ ኅሊና ፈጥረዋል ወይ? ጠንካራ የብሔራዊ አንድነት መሠረት ተጥሏል ወይ? የአገሪቱን ህልውና ቀጣይነትስ አረጋግጠዋል ወይ? እያልን ነው፡፡

  1. ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት

ኢትዮጵያዊነት በአጭሩ ኢትዮጵያ የምትባል አገር፣ ሕዝብና መንግሥት አሃዳዊ ዜግነታዊ ብሔርተኝነት ነው፡፡ ብሔራዊ ታሪካችን እንደሚመሰክረው ኢትዮጵያዊነት በተደጋጋሚ ፈተና ላይ ሲወድቅና ሲነሳ እዚህ ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ቀንደኛ ባለጋራዎች ደግሞ ባሕር ተሻግረው ድንበር ሰብረው የሚመጡ ብቻ አልነበሩም፡፡ ሌላው ቢቀር ከአገሪቱ መሪዎች ውስጥ ለኢትዮጵያዊነት ባላቸው የመረረ ጥላቻ ግንባር ቀደምቱን ሦስት እንጥቀስ ቢባል በተዋረድ መለስ ዜናዊን፣ ሚካኤል ስሁልንና ሱስንዮስን ማንሳት ይቻላል፡፡ ምናልባት ልዩነቱ የሚካኤል ስሁልና የሱስንዮስ ጥላቻ በኢትዮጵያዊነት እሳቤ ላይ የተወሰነ ሲሆን፣ የመለስ ጠላትነት ግን አገሪቱ ከምትመራበት ሥርዓት አልፎ ከህልውናዋ ጋር ጭምር መሆኑ ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚመኙ ኀይሎች በሙሉ ዋነኛው የጥቃት ዒላማቸው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ አገር በቀል ጽንፈኛ ዘውገኞችን እንደ ጣልያን ካሉ ባዕዳን ወራሪዎች የሚያመሳስላቸው ከኢትዮጵያ ጋር የቋጠሩት ዘላለማዊ ደመኝነት  ነው፡፡ አገሪቱን በእጃቸው ማስገባት አይበቃቸውም፡፡ መንግሥቱን በማፍረስ ወይም በመውረስ አይመለሱም፡፡ አጋጣሚ እየጠበቁ ኢትዮጵያዊነትንም ከምድረ ገፅ ጠራርገው ለማጥፋት መገለጫ ርዕዮቱን፣ ባህሉን፣ ተቋማቱን፣ ትዕምርቶቹን፣ እምነቶቹን፣ እሴቶቹን ለማውደም ይዘምታሉ፡፡

በተቃራኒው ኢትዮጵያ ደረታቸውን ለጦር ግንባራቸውን ለጥይት ያለማቅማማት የሚሰጡላት በሀገር ፍቅር የነደዱ ልጆችን አላጣችም፡፡ የኢትዮጵያን መንግሥት ተቆጣጥሮ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብክ መሪ የኢትዮጵያ ጠላት ሊሆን አይችልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ሲናገሩ ከአንጀት እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በሕይወታቸው የቋጠሩ መሆናቸውን መጠራጠር አይቻልም፡፡ ነገር ግን ፍልሚያው የግል ሳይሆን የለውጡ ኀይሎች ርዕዮት በሆነው በኢትዮጵያዊነትና በአልሞት  ባይ ተጋዳዩ በፀረ-ኢትዮጵያዊነት መካከል ነው፡፡ የአዲሱ ሥርዓት ጠላቶች የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ደመኞች ናቸው፡፡ ዋነኛው ፍልሚያ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የሚደረግ ነው፡፡

የለውጡ ኀይሎች ለ27 ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበትን ቀመር ገልብጠው “ኢትዮጵያዊነት ውስጤ ነው” ማለታቸው የአገሪቱን ፖለቲካ መልክዐምድር ክፉኛ ገለባብጦታል፡፡ ዘውጌ ሥርዓቱ ባመቻቸላቸው መሠረት እንደ አሸን የፈሉት ጥቃቅን ‹ጨርቦሌ› ፓርቲዎች ክፉኛ ሚዛናቸውን አስቷቸዋል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ተስፋ አንቆርጥም ብለው በረሃ ድረስ የወረዱት ጥቂት የፖለቲካ ቡድኖች ደግሞ አጀንዳቸውን ተነጥቀዋል፡፡ ራሱ ኢሕአዴግ ዘረመሉ ዘውጋዊ ስለሆነ ከአዲሱ ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ጋር እንዴት እንደሚላመድ የቸገረው ይመስላል፡፡ ዞሮ ዞሮ በሚቀጥሉት ዓመታት የፖለቲካ ሥልጣን ፉክክሩ ምሕዋር ኢትዮጵያዊነት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

በአጠቃላይ የአገራችን ብሔራዊ ታሪክ ሂደት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኀይል ኢትዮጵያዊነት በውስጣዊም ውጫዊም ኀይሎች እየተፈተነ የሚያልፍበት ዲያሌክቲክ ነው፡፡ ለብዙ ሺሕ ዓመታት የአገሪቱን ሉዓላዊነትና ህልውና አስጠብቆ በመኖር ፍቱንነቱን ያረጋገጠ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡  በዚህ ታሪካዊ ማዕቀፍ ካየነው ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያዊነት መንምኖ ለህልውናው በሚፋለምበት ወቅት እንደገና የማንሰራራቱ  ምሥጢር ያለው በተፈጥሯዊ ባሕርያቱ ላይ ነው፡፡

አንደኛ ኢትዮጵያዊነት በዜግነት ላይ የተመሠረተ አዎንታዊ የአገር ግንባታ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡  በትናንትና በዛሬ ላይ ብቻ ሳይተከል ነገንም በቀና መንፈስ የሚያልም ራዕይ ነው፡፡ በጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ እሴቶች፣ ተቋማትና ሥርዓታት ላይ የቆመ ነው፡፡

ሁለተኛ ኢትዮጵያዊነት የሃርነት ርዕዮት ነው፡፡ በመላው ዓለም ራሳቸውን ከጥንታዊም ሆነ ዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ ተከላክለው፣ ብሔራዊ ነፃነታቸውን አስከብረው እስከዛሬ የኖሩ ሕዝቦች  ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው፡፡ የአይበገሬነታቸው ምሥጢርም የነጻ ሕዝብነታቸው ምልክት የሆነው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የፈጣሪዋ ተራዳኢነት የማይለያት፣ ብትወድቅ ወድቃ የማትቀር፣  በትሸነፍ በድል መውጣቷ አይቀሬነቱን የሚሰብከው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት የሆነ የሃርነት ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡

ሰው በላውን የወያኔን ሥርዓት የገረሰሱት የለውጥ ኀይሎች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር የተሰባሰቡት ኢትዮጵያዊነት የማታ ማታ አሸናፊ ርዕዮት በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በተጨባጭም ራሳቸውን  ከሕወሓት ጋሻ ጃግሬነት፣ ሕዝባቸውንና አገራቸውን ከጭቆና ቀንበር ነፃ ለማውጣት የሚያስችል የሃርነት መሳሪያ ስለሆነ ነው፡፡ ‹ቲም ለማ› ከወደቀበት ያነሳው የኢትዮጵያዊነት ዓርማ ካራማራ ላይ ኢትዮጵያውያን በጋራ የወደቁለት ነው፡፡

ሦስተኛ ኢትዮጵያዊነት የመቻቻልና አብሮ የመኖር አስተምህሮ ነው፡፡ በታሪክ ሂደት ማኅበራዊ ልዩነቶችን በጋራ ፈትል እያሰናሰለ፣ ድንበሮች እየተሻገረ የሚዘልቅ፤ ፅናትን ከልዝብነት፣ ታጋሽነትን ከቆራጥነት፣ መስጠትን ከመቀበል ያጣመረ ርዕዮት ነው፡፡  ክፍትና አካታች በመሆኑ መስፈርቶቹ ሚኒመም/ገራገር ናቸው፡፡ በዚህም ባሕሪው  በየጊዜው ማኅበራዊ ድንበሩን እያሰፋ ያመነበትን ኀይል ያለልዩነት ያቅፋል ይቀበላል፡፡ በአንድ ቡድን ወይም ማኅበረሰብ ያልተገደበ የበርካታ ማኅበረሰቦች የጋራ  ርዕዮት ለመሆን ችሏል፡፡ በቅርብ ዓመታት በአገሪቱ ህልውና ላይ አንዣብቦ የነበረውን ማዕበል ገስፆ ፀጥ የማድረግ ኀይሉ ምክንያት መሠረተ ሰፊነቱ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት በተግባርና በሂደት ለመሻሻልና ለመለወጥ ቀና ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከጊዜው ጋር ለመራመድ፣ አዳዲስ እሳቤዎችንና ኀይሎችን ለማስተናገድ አይቸገርም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከአገዛዝ አገዛዝ እንኳን ልዩነቶችን ሊያስተናግድ የሚችልበት ክፍትነት አለው፡፡ ለዚህ ሁነኛ ምሳሌ የሚሆነው የወታደራዊው ደርግ ሶሻሊስት ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት ያደረገው ጥረት ነው፡፡

ከደርግ ብሔርተኝነት ሕጋዊ መሠረቶች የመጀመሪያው አገር በቀል ብሔርተኛ አቋሙ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የተባለው  ነው፡፡ ሁለተኛው በታኅሣሥ 11 ቀን 1967 ዓ.ም ባወጣው “ኅብረተሰባዊነት” የተባለውና ኢትዮጵያዊነትን ከሶሻሊዝም መርሆች ለማዳቀል የሞከረበት የፖለቲካና ኤኮኖሚ መርሐ ግብሩ ነው፡፡ ኅብረተሰባዊነት ከኢትዮጵያ አፈር፣ ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖቶች የመነጨ ፍልስፍና ነው፡፡ ከታላላቅ ሃይማኖቶቻችን የሰብአዊ እኩልነት አስተምህሮ፣ ከአብሮና ተካፍሎ መኖር ባህላችን፣ እንዲሁም በብሔራዊ መስዋዕትነት ካሸበረቀው ታሪካችን የሚመነጭ የፖለቲካ ፍልስፍና ነው፡፡ የኅብረተሰባዊነት አምስት ቁልፍ መርሆች ብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ አንድነት፣ ብሔራዊ በራስ መተማመን፣ የሥራ ክቡርነት እና የሕዝብ ጥቅም ቀዳሚነት ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ከባህል አኳያ ዘውዳዊውና ወታደራዊው አገዛዞች የተከተሉት ብሔራዊ ፖሊሲ ባህላዊ ይዘት የሌለው ፖለቲካዊ አንድነት ፋይዳ ቢስ ነው የሚል ነበር፡፡ የሁለቱ የባህል ግንባታ አቅጣጫና ይዘት እንደ ርዕዮተ ዓለማቸው የተራራቀ ቢሆንም ቅሉ ፣ የባህል ውሕደት ስልታቸው ግን ኢትዮጵያን በአንድ ቡድን ባህል ሥር የሚጨፈልቅ (assimilationist) አልነበረም፡፡ የባህላዊ ማኅበረሰቦች መሠረታዊ ልዩነቶች እንደተጠበቁ በቁልፍ ብሔራዊ ምልክቶች የተዋሃደና ከዘውጎች የላቀ አገራዊ ባህል የመገንባት (integrationist) እንጂ፡፡

  • ዘውጋዊ  ብሔርተኝነት

ዘውጋዊ ብሔርተኝነት በትውልዳዊ ማኅበረሰቦች ሉዓላዊነት ላይ የተመሠረተ ድምር ማንነታዊ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ዘውገኝነት በአውራጃዊነት የተበታተነ ስለነበር በማዕከላዊ መንግሥቱ ላይ የሚያሳድረው ጫና በዘላቂነት የህልውና አደጋ አልሆነም፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ እንደ ጉዲት፣ ግራኝ የመሳሰሉ ጠንካራ የጦር አበጋዞች የየአውራጃቸውን ህዝብ ቀስቅሰው ሲነሱ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተላቸው አልቀረም፡፡ ዘውጋዊነት ዘለግ ያለ ጉልበት ያገኘው ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚታወቀው የአገራችን ታሪክ (ከ1760 ዓ.ም እስከ 1848 ዓ.ም) ባለው የአንድ ምዕት ገደማ ወቅት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ዛሬ እንደሚታየው ያለ መላውን ዘውግ ያቀፈ ሳይሆን በአንድ ዘውግ የበላይነት የሚመራ አውራጃዊ ክስተት ነበር፡፡

ስለዚህም ዘውጋዊነት ለመጀመሪያ ጊዜ በመደበኛ የአገር ግንባታ ርዕዮትነት እውን የሆነው በዘመነ ኢሕአዴግ ነው፡፡ በዚህ እሳቤ መሰረት ኢትዮጵያ አሃዳዊ ብሔር ሳትሆን ብዝሃዊ ወይም የብሔሮች ብሔር ናት፡፡ ብሔራዊ መሰረቷም ሕዝባዊ ሉዓላዊነት ሳይሆን ዘውጋዊ ሉዓላዊነት ነው፡፡ ስለሆነም ዜግነታዊ ብሔርተኝነት በዘውጋዊ ብሔርተኝነት ተተክቷል፡፡ ኢሕአዴግ ለ“ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ፖለቲካዊ ነፃነት በማጎናፀፍ  የመንግሥቱ አስተዳደራዊ መዋቅር መሠረት አድርጓቸዋል፡፡ 

የዚህ ዘመናዊ ዘውጋዊነት ለዘብተኛ መነሻዎች በራስ ማንነት የመኩራት፣ ቋንቋንና ባህልን የመጠበቅና የማበልፀግና በደምሳሳው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ዘውጋዊነት በተፈጥሮው በነዚህ አዎንታዊ ባሕርያት ላይ አይቆምም፡፡ ከራስ በላይ የሚል የግለኝነት ስሜትና ተቀናቃኝነት የገነነበት የመለያየት፣ የመቃቃር፣ የማፍረስ ርዕዮት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ጽንፈኛ ዘውጋዊነት ጎሰኝነት ይባላል፡፡

ዘውጋዊነት ማኅበራዊ ድንበሮቹ የተዘጋና በሐሳይ ሥነ-ሕይወታዊ ወይም ተፈጥሯዊ ጠባይ ባላቸው እንደ ደምና ዘር ያሉ የማያፈናፍኑ መስፈርቶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ወደ ደመነፍሳዊነት የሚያወርድ እሳቤ ነው፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ እንደታየው ዘውጋዊነት ጽንፈኛ ሲሆን ከናካቴው የሰው ልጅን ተፈጥሯዊ አንድነትና ሰብአዊ እኩልነት ይክዳል፡፡ ከጠባብ ቅጥሩ የዘለለ ምንም ዓይነት የዴሞክራሲና የፍትሕ መንፈስ የለውም፡፡

በአገሪቱ የተዘረጋው ዘውጋዊ ፌዴራል ሥርዓት በዚህ እሳቤ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ፣ ብዙውን ጊዜ ደጋፊዎቹ እንደሚሉት ችግሩ አተገባበሩ ነው የሚለው የጠነዛ ሙግት ነው፡፡ አንድን ፖለቲካዊ ሥርዓት የምንመዝነው ቢያንስ ለአብዛኛው ዜጋ በሚያስገኘው ዘላቂ ጥቅሙ ከሆነ፣ ፌዴራል ሥርዓቱ ከጥንስሱ ጀምሮ ያስከተለውን ሰቆቃና በአገር ህልውና ላይ የደቀነውን አደጋ አስተባብሎ ማለፍ አይቻልም፡፡ ካለፉት 27 ዓመታት ተመክሯችን  ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ በእጅጉ ያመዘነ መሆኑን ዓይን ያለው ሁሉ የሚያየው ነው፡፡

የኢሕአዴግ ዘውጌ ብሔርተኝነት መሠረቶች አንደኛው በ1975 ዓ.ም. ማሌሊት ሲመሠረት አንስቶ የሕወሓት መሪ የፖለቲካ አስተምህሮ የነበረው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ነው፡፡ ሁለተኛው የሽግግር ቻርተሩ (ከሐምሌ 15 ቀን 1983 እስከ ነሐሴ 15 ቀን፣ 1987 ዓ.ም) እና ሦስተኛው በታኅሣሥ 2 ቀን 1984 ዓ.ም. የታወጀው “የብሔራዊ ክልላዊ ራስ-ገዝ አዋጅ ቁ.7/1984” ነው፡፡ ይህ አዋጅ “ብሔር ወይም ብሔረሰብ ማለት በአንድ ኩታ ገጠም መልክዐ ምድር የሚኖር፣ አንድ የሚያግባባ ቋንቋና የአንድነት ሥነ-ልቦና ያለው ሕዝብ ነው” ይላል፡፡ አራተኛው በነሐሴ 1987 ዓ.ም. የታወጀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አወዛጋቢ አንቀፅ 39 ንዑስ አንቀፅ 5 የጨመረው ማሻሻያ የጋራ ባህልን ብቻ ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ የፌዴራል ሥርዓቱ አንዳችም ሞራላዊም ሕዝባዊም ቅቡልነት የለውም፡፡ ሕወሓት ኢትዮጵያን በአፈሙዝ ፣ ያለሕዝብ ይሁንታ፣ ያለበቂ ጥናትና ያለብልሃት ወደ ጽንፈኛ ጎሰኝነት ያዘለለበትና  በድቡሽት ላይ የቆመ መዋቅር ነው፡፡ ምንም እንኳን ቻርተሩም ሆነ ሕገ መንግሥቱ  የአገራዊውን መንግሥት አወቃቀር በግልጽ ባይወስኑም በተግባር የተሰራው መዋቅር ዘውጌ ፌዴራላዊ ነበር፡፡

ለመሆኑ የዚህ ሥርዓት የማያጨቃጭቅና አስተማማኝ መሠረት ምንድነው? በሕግ የተመሠረተባቸው ግዛታዊ አንድነት፣ የቋንቋ አንድነት፣ የጋራ ሥነ-ልቦና፣ የባህል አንድነት የሚባሉት መስፈርቶች በተግባር ካለው ክልላዊ መዋቅር ጋር በፍፁም አይሰምሩም፡፡ ማለትም መስፈርቶቹ ቀድሞውንም በተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ አልተመሠረቱም፡፡ ኢሕአዴግ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አስተዳደራዊ እርከኖችን ለመወሰን የተጠቀመው ዋነኛ መስፈርት ቋንቋ ነበር፡፡ 

ወያኔ የዘረጋው የጎሳ ሥርዓት በዘመናት መስተጋብርና መቻቻል የተፈጠረውን ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ማኅበራዊ ሚዛን በቀላል ፖለቲካዊ ቀመር ሰትሮ ለማጠናቀቅ የማይቻል መሆኑን አልተገነዘበም፡፡ ሆኖም በሕገ መንግሥቱ ላይ ምናባዊ መስፈርቶቹ የተቀመጡትበት ሁነኛ ምክንያት አላቸው፡፡ ይህም እያንዳንዱ የክልል ባለቤት የሆነ ማኅበረሰብ ሌሎች በመጤነትና በባዕድነት የተፈረጁትን ነዋሪ ማኅበረሰቦች እያባረረም፣ እየጨፈለቀም ይሁን እየገደለ ግዛቱን በማፅዳት ብቸኛ ማንነት እንዲገነባ በግብነት ነው፡፡ ስለዚህም የጎሳ ፌዴራሊዝሙ ታሪክን ለማሻሻልና ወደፊት ለማራመድ ሳይሆን የአገሪቱን ተፈጥሯዊ ሂደት የኋሊት ለመቀልበስ የተወጠነ ምህንድስና ነው፡፡ ከብዝሃነት ጎሳነትን፣ ከመቻቻል መቃቃርን፣ ከመቀራረብ መራራቅን፣ ከመተማመን መጠራጠርን፣ ወዘተ. ለማስፈን የታለመ ስልት ነው፡፡

የወያኔ የጎሳ ፌዴራሊዝም ለፍትሕና ርትዕ አልቆመም፡፡ በገራፊና ተገራፊ መርህ የሚመራ የበቀል ሥርዓት ነው፡፡ ጭቆናን፣ ግፍና መድልኦን ከብሔራዊ ደረጃ አውርዶ በክልልና በብሔረሰብ ደረጃ  በሕግና በፖሊሲ የተከለና የሚደግፍ አገዛዝ  ነው፡፡ ስለዚህም ባዕድ ቋንቋና ባህል ተጫነብኝ ይል የነበረው ጫኝ ሆነ፡፡ ተገፋሁ ተበደልኩ የሚለው ገፊና በዳይ ሆነ፡፡ ተነቀልሁ፣ ተነጠቅሁ የሚለው ነቃይና ነጣቂ ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ ዜጎቿ በሚሊዮኖች የሚሰቃዩባት ወህኒ ቤት ሆነች፡፡

በኢሕአዴግ ጎሰኛ ሥርዓት የሕዝቦች እኩልነት የለም፡፡ በሕግ የተደነገገ የበላይነትና የበታችነት፣ የባለቤትነትና ባዳነት አለ፡፡ አንደኛ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ እርከኖች ያሉት፣ ንዑሳን ማኅበረሰቦችና ቡድኖች ብዙሃንን የሚያሽቆጠቁጡበት አገዛዝ ነው፡፡ በግልጽ መድልዖ ላይ የተመሠረተና ዓይን ያወጣ የአንድ ብሔረሰባዊ ቡድን አገዛዝ ነው፡፡ አንዱን ሕዝብ በጠላትነት በመፈረጅ፣ ሌላውን ደግሞ የእጅ አዙር ባሪያ በማድረግ እያሸማቀቀ የሚኖር ነው፡፡  በዚህ የከፋፋይነት ማዕቀፍ መሠረታዊ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንዳሻው የሚጥስ አረመኔ ሥርዓት ነው፡፡ የአገሪቱን አንጡራ ሀብት ያለቅንጣት ይሉኝታ በአንድ ብሔረሰብ ስም የሚዘርፍ ቀማኛ ስርዓት ነው፡፡ እውነተኛውና የለየለት የብሔር ጭቆና የሰፈነው በዘመነ ኢሕአዴግ ነው፡፡

ዘውጋዊነትና ማንነታዊ ቡድነኝነት በመንገሡ ምክንያት፣ ዜግነት ሕገ መንግሥታዊም ተግባራዊም ህልውና አጥቷል፡፡ ግለሰብ ዜጋ ፍጹም ተውጧል፣ ተደምስሷል፡፡ በምትኩ ጎሰኝነት በእለት ተዕለት መስተጋብር ድረስ በመዝለቁ ተራ የግል ፀብ እንኳን ቀርቷል፡፡ በብሔረሰብ ስም ዘረፋ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ግብረ ሰዶማዊነት አፀያፊነቱ ቀርቶ የሚፈቀድና የሚያስመሰግን ሰናይ ምግባር ሆኗል፡፡ አረመኔያዊነቱም  ወንጀሉም ብሔረሰባዊ ሽፋንና ከለላ ተሰጥቶት ሰላማዊ ሰልፍ እስከማስወጣት እንደደረሰም ታዝበናል፡፡

በአጠቃላይ አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢፌዲሪ መንግሥታዊ መዋቅር ለአገር ግንባታ የተሠራ አይደለም፡፡ በአንድ አገርና ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ እንደሚኖር ሕዝብ ቅንጣት ብሔራዊ መንፈስ የለውም፡፡ የባህል ፖሊሲ ዘውጋዊ ማንነቶችንና ባህሎችን በየራሳቸው ክበብ የሚገድብና የሚያጋንን ፤ አገራዊ ባህሎችንና ትስስሮችን የሚያዳክም ነው፡፡ ቢያንስ የብዝሃነት መርህ ኅብረ-ባህላዊነት (multiculturalism) የሚፈልገውን በተለያዩ ማንነታዊ ማኅበረሰቦች መካከል ቀጭን ድልድይ እንኳን አልዘረጋም፡፡ የጋራ መስተጋብርን የመፍጠር፣ ብዝሃነትን በአንድነት ውስጥ የማስተናገድ ሚዛናዊ ቀመር የለውም፡፡  ኢትዮጵያውያንን ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ በሚል ማደናገሪያ የተከፋፈሉና በራቸውን ዘግተው የሚቀመጡ ባላንጦች አድርጓል፡፡ የጋራ እሴቶችና ግቦች እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ ስለሆነም በመቀራረብና መተዋወቅ ፈንታ መራራቅንና ባይተዋርነትን የሚያባብስ፣ ሰፊ የተራክቦ መንገዶችንና ዕድሎችን ከመዘርጋት ይልቅ  በጠባብ ፖለቲካዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ አፍራሽ (disintegrationist) ነው፡፡

ከፋፍለህ ግዛ የሥርዓቱ ምሰሶ በመሆኑ ሁሉም በየጎሳው ከታጠረስ በኋላ ምን ይከሰታል የሚል አርቆ አሳቢነት ከጥያቄ ውጭ ነበር፡፡ ሕወሓት ከበቀል ሥነ-ልቦና ፀድቶ በሆደ ሰፊነትና አርቆ አሳቢነት ስለአገር ግንባታ ቢሠራ ኖሮ እንዲህ ያለ ሥርዓት በኢትዮጵያ አይፈጠርም ነበር፡፡ ከአጭርና ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ የላቀ ራዕይ ቢኖረው እንዲህ ያለ ከቅኝ አገዛዝ የከፋ ሰው በላ ሥርዓት አይዘረጋም ነበር፡፡  ዛሬ በአገራችን የምናየው ዝብርቅርቅ መሠረታዊ ምክንያት የጎሳ ፌዴራል ሥርዓቱ ከአነሳሱ በቅጡ ያልመለሳቸው ጥያቄዎች ድምር ውጤት ነው፡፡ 

  • የመፍትሔ ሐሳቦች

ዛሬስ ለአገራችን ምን ዓይነት የአገር ግንባታ ያስፈልጋታል የሚል አማራጭ ከማቅረባችን በፊት ሁለት ነገሮች እናንሳ፡፡ አንደኛ ከላይ ባየናቸው የዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ሙከራዎች የነበረው ቁልፍ ጥያቄ ብዝሃነትን ከአንድነት እንዴት እናስተናግድ ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በጎሳ ማንነትና በፖለቲካ ሥልጣን መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት የለም፡፡ በተግባራዊነትም ሚዛን የቋንቋና የባህል ጥያቄዎች በአሃዳዊም በፌዴራላዊም ሥርዓተ መንግሥታት ውስጥ ሊስተናገዱ ይችላሉ፡፡

ሁለተኛ ማናቸውም አዎንታዊ የአገር ግንባታ፤ የመንግሥቱን አወቃቀርም ሆነ የብሔራዊ መንፈሱን ይዘት የሚወስነው የየአገሩ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወሳኙ መነሻ የሕዝብ ይሁንታ ነው፡፡ በግንባታው ሂደት መንግሥት ማዕከላዊ ቦታ ቢኖረውም፣ በተጓዳኝ ከታች በሰፊው ሕዝብ ፈቃዳዊ ጥረት የሚደገፍ መሆን አለበት፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ፤ በቅድሚያ ለአገር ግንባታው መሠረት የሚሆን ግልፅና አካታች ርዕዮተ ዓለም መንደፍ፡፡ ዘላቂ አገር ግንባታ ከእኔ ይልቅ የኛ መንፈስን በሚፈጥሩ አገር በቀል የጋራ እሴቶችና ግቦች ላይ መመሥረት አለበት፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ሕዝብን ከመንግሥት፣ እንዲሁም የመንግሥትን አካላት በአዎንታዊነት የሚያቀራርብ መሆን አለበት፡፡ የአገሪቱን ቀጣይነትና የሕዝቡን ጥቅም የሚያረጋግጥና የወደፊት እጣ ፈንታቸውንም በግልፅ የሚያስቀምጥ መሆን አለበት፡፡

ቀጥሎ መንግሥቱ በአወቃቀሩም በግቡም እውነተኛ አገራዊነት ይኑረው፡፡ በበኩሌ በፌዴራላዊነቱ ቢቀጥልም ከሌጣ ዘውጋዊነት/ቋንቋ ይልቅ ታሪክንም፣ ባህልንም፣ አስተዳደራዊ ምቹነትንም ወደሚያካተቱ አሃዶች ይቀየር፡፡ ብዝሃነትና አንድነትን በዴሞክራሲ አማካይነት የሚያቻችል  ሊሆን ይገባል፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከአገር ዐቀፋዊ ትብብር ይልቅ የፉክክር ማዕቀፍ እንዳይሆን፣ በክልሎችም ሆኑ ክፍለ አገራት መካከል ጠንካራ ድንበር ተሻጋሪ ትስስሮችን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ሦስተኛ በሕዝቦችም መካከል እውነተኛ ኅብረ ባህላዊነት የሚያሰፍን መሆን አለበት፡፡  ከዘውጎች የዘለለ ብሔራዊ ባህል መፍጠርና ማዳበር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ አገራዊነትና ዘውጌነት ሽቅብም አግድምም የሚደጋገፉበትን መንገዶች መተለም ያስፈልጋል፡፡ የዜጎችን ባህላዊ አድማስ በድምር በሚያሰፉ፣ ማኅበራዊ ወረትን በሚያዳብሩና እርስ በርሳቸው በሚመጋገቡ ለውጦች መተለም አለበት፡፡ ማንኛውም አዎንታዊ የግንባታ ጥረት ታሪካዊና ባህላዊ ቀጣይነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል፡፡

አራተኛ መሠረቱ ሰፊ የሆነ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎችንም ማካተት አለበት፡፡ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት፣ በዘርፈ ብዙ ምጣኔ ሀብታዊም ሆነ ማኅበረሰባዊ ልማት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና መልከዐ ምድራዊ ድንበሮችን የሚያቆራርጡ ሰፊ ትስስሮችንና መደጋገፎችን ማበልፀግ ያስፈልጋል፡፡ 

በመጨረሻ በአፈፃፀሙ ረገድ አገር ግንባታ ከዜሮ የሚጀምር ሳይሆን ነባሩን የሚያጠናክር፣ የሚያሻሽልና አዲስ የሚፈጥር ስልቶችን ያቀናጀ መሆን አለበት፡፡ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግና በቡድናዊና ግላዊ፣ በዘውጋዊና ብሔራዊ፣ በብዙሃኑና ንዑሳን፣ ወዘተ. መካከል ሚዛኑ የተስተካከለ መሆን አለበት፡፡

በአገር ግንባታው ሂደት ማን ምን እንዴት ይሥራ? የሚለውን በጥንቃቄ ማዘጋጀት ታላቅ ትኩረት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ የፖለቲካ ተዋናዮች፣ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት የሕዝባቸውን ብሔራዊ ማንነት በመቅረፅ ጥረት ላይ ሊሠሩ የሚፈቀድላቸው፣ የሚበረታቱት፣ የሚፈለግባቸው ወይም የሚከለከሉት ተለይቶ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የአገር ግንባታው ባህላዊ ዘርፍ ሕዝባዊ ትዕምርቶችን በየትኞቹ የጋራ እሴቶች ላይ ይገንባ፤ ከታሪካችን የጋራ ትውስታን በመገንባቱ ጥረት የቱ ይፈቀድ፣ ይበረታታ ወይም ይከልከል የሚሉትን  በቅጡ የሚለይ ሊሆን ይገባል፡፡ የአገር ግንባታው በልሂቃዊ መደቦች፣ በውሱን ቡድኖችና ማዕከሎች ተንጠልጥሎ እንዳይቀር በስፋትና በጥልቀት ከሕዝባዊነት ጋር ማጣጣም ተገቢ ነው፡፡

(Visited 166 times, 1 visits today)
February 7, 2019

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo