Economy, ኢኮኖሚ

ለማን እናምርት? ለገበያ – በጌታቸው አስፋው

ገበያ

ምናልባት ብዙ ሰዎች ስለ ግብይይት የሚረዱት እንደ መርካቶ ባለ የገበያ ቦታ የሚከናወን ድርጊትን ብቻ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በቤታችን ውስጥ እንኳ ውሃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ የሠራተኛ አገልግሎት እንገዛለን፡፡ የሕክምና ምርመራ ስናደርግ፣ ልብሳችንን ስናሳጥብ፣ ጫማ ስናስጠርግ፣ የሕክምና፣  የልብስ እጥበት፣ የጫማ ማሳመር አገልግሎቶችን ከገበያ ገዝተናል፡፡ ድርጅት ወይም መንግሥት ሠራተኛ ሲቀጥሩ የሠራተኛውን አገልግሎት ገዝተዋል ሠራተኛውም አገልግሎቱን ሽጧል ዋጋውም ደሞዙ ነው፡፡ ብር ከባንክ ስንበደር የብሩን አገልግሎት ከባንኩ ገዝተናል፡፡ ባንኩም የብሩን አገልግሎት ለእኛ ሸጧል፡፡ ገንዘብ ቆጥበን ባንክ ስናስቀምጥ ባንኩ የብሩን አገልግሎት ገዝቷል፡፡ እኛም የብሩን አገልግሎት ሽጠናል፡፡ ለባንኩ የምንከፍለው ወይም ባንኩ የሚከፍለን የግብይይት ዋጋ ወለዱ ነው፡፡ ግለሰብ ወይም ድርጅት የከተማ ቦታ ከመንግሥት ሲከራይ የቦታውን አገልግሎት ገዝቷል፡፡ የከፈለው ዋጋ የቦታው ኪራይ ነው፡፡  

በብዙ አገሮች ብዙ ዓይነት ገበያዎች አሉ፡፡ በበለጸጉት አገሮች ጎልተው የሚነገሩት የካፒታል ወይም የገንዘብ ገበያዎችና የሠራተኛ ገበያዎች ናቸው፡፡ በምርት ገበያዎቻቸውም የውሾችና የድመቶች ማስታወቂያዎች የቴሌቪዥንና የሬድዮ ፕሮግራሞችን አጣበዋል፡፡ እኛም አገር ብዙ ዓይነት የምርትና የግብዓተምርት ገበያዎች አሉ፡፡ በቀድሞ ጊዜ ከጓሮው ይቀጠፍ የነበረና በሥልጣኔ ምክንያት በጥርስ ቡሩሽ ተተክቶ የነበረው የጥርስ መፋቂያም ተክለሃይማኖት አካባቢ ማምረቻ ፋብሪካውን እና የጅምላ ማከፋፈያውን ተክሎ ልጆች በድፍን አዲስ አበባ እየተዟዟሩ በችርቻሮ ይሸጣሉ፡፡ መሪዎቻችን በዓለም ዙሪያ ኢንቬስተር ለመሳብ ርካሽ የጉልበት ገበያ አለን ይላሉ፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በዐሥራ ኹለትና ዐሥራ ሦስት ዓመት ሕፃናት የሚሰደዱት፤ በሎሌነትና በግርድና የሥራ ገበያ ውስጥ ለመግባት ነው፡፡ ለእኔ ከምንም በላይ አሳፋሪው የድህነት መገለጫችን መሀል መርካቶ ጉርሻ በዋጋ ተለክቶ እየተከፈለ የሚበላበት የሆቴል ቤት ገበያ ነው፡፡  እናት ወፍ ምግብ በአፏ ይዛ ለሕፃን ልጇ ቁልቁል ታጎርሳለች፡፡ ሕፃኗ ወፍም ወደ ላይ አንጋጣ የእናቷን ጉርሻ በአፏ ለመቀበል ትዘጋጃለች፡፡ ሰው እንደ ወፍ ወደ ላይ አንጋጦ ለጎረሰው ጉርሻ ዋጋ የሚጠየቅበት የገበያ አገር ውስጥ ስለምንኖር ስለ ገበያ ማወቅ ለእኛ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡

ነጻ ገበያ

የሸቀጦች ዋጋ በገበያ ውስጥ በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር የሚወሰንበት ሥርዓት ነጻ ገበያ ሲባል የሸቀጦች ዋጋ በተለያዩ መንገዶች የሚወሰንባቸው የተለያዩ የነጻ ገበያ ዓይነቶች አሉ፡፡ የገበያዎች ዓይነት በሻጮች ብዛት፣ በሸማቾች ብዛት፣ በሸቀጦች ተመሳሳይነትና ልዩነት፣ በገበያተኞች ስለሸቀጡ በቂ መረጃና ዕውቀት መኖርና አለመኖር ሁኔታዎች ላይ ተመርኩዞ የጠራ ገበያ (Perfect Market) እና ያልጠሩ ገበያዎች (Imperfect Markets) በመባል በኹለት ዋና ዋና ምድቦች ይከፈላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ዋጋዎች ለምን እንደሚወደዱና ለምን የተለያዩ ሸቀጦች የተለያዩ የዋጋ ጭማሪዎች እንዳሏቸው ለማወቅ እነኚህን የገበያ ዓይነቶች ለይቶ ማወቅ ይገባል፡፡

የጠራ ነጻ ገበያ

የጠራ የሚለው ቃል ከገበያ ጋር ባይያያዝም ትርጉሙ ‹እንከን የለሽ፣ ያልጎደፈ ወይም አንድ ገጸ ባሕሪይ ያለው› ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ንጹሕ ውሃ የጠራ ውሃ፣ ያልጎሸ ጠላ የጠራ ጠላ፣ ጥሩ ዕቃ ጥራት ያለው ዕቃ፣ ፀሐያማ ቀን የጠራ ቀን ይባላሉ፡፡ የሸቀጥ ፍላጎትና የሸቀጥ አቅርቦት የገበያ ጥናትም ቢያንስ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ቢሆን ኖሮ በሚል ታሳቢ በጠራ ገበያ ውስጥ የሚታየውን ግብይይት በማመልከት ይጠናል፡፡ ቢሆን ኖሮ የሚባለውም ሙሉ በሙሉ የጠራ ገበያ በየትኛውም አገር ስለማያጋጥም ነው፡፡ የጠራ ገበያ የሚፈጠረው ለገበያ የቀረበው ሸቀጥ በዓይነትና በጥራት ደረጃ ተመሳሳይ ሆኖ ፍላጎትና አቅርቦት የሸቀጡን ዋጋ በጋራ ለመወሰን የሚያስችላቸውን ተመጣጣኝ አቅም እንዲያገኙ በገበያው ውስጥ ሸቀጡን የሚያቀርቡ ሻጮች ብዛት እና ሸቀጡን የሚፈልጉ ሸማቾች ብዛት በርካታ ሲሆኑ ነው፡፡ በጠራ ገበያ ሥርዓት የአንድ ነጋዴ ሸቀጥ ለገበያው ከቀረበው ብዙ ተመሳሳይ ሸቀጥ ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ስለሚሆን፣ ነጋዴው ዋጋ በማስወደድ በገበያው ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ምክንያቱም አምራቾችም ሻጮችም ብዙ በማምረትና ብዙ በመሸጥ ብዙ ለማትረፍ ውድድር ውስጥ ስለሚገቡ ነው፡፡ በሸማቾች በኩልም ለገበያ የቀረበው ሸቀጥ ሁሉም ነጋዴዎች ዘንድ በጥራትና በዓይነት ተመሳሳይ ስለሆነና ዋጋው ሁሉም ጋ እኩል መሆኑን ስለሚያውቁ ነጋዴ ሳይመርጡ መግዛት ይችላሉ፡፡

ያልጠሩ ነጻ ገበያዎች

በፋሲካ ዋዜማ አመሻሸተው ገበያ ወጥተው ያውቃሉ? ከሆነ ከኹለት አማራጮች አንዱ ያጋጥሞታል፡፡ ብዙ ዶሮና በግ ሻጮች ሸማች አጥተው ዋጋ ሰብረው ሲሸጡ ወይ ደግሞ ጥቂት ዶሮና በግ ሻጮች በብዙ ሸማቾች ተከበው ዋጋ ሲያስወድዱ፡፡ እነዚህ ናቸው ያልጠሩ ገበያዎች የሸቀጦች ዋጋ በቀንስ ጨምር ንትርክና ጭቅጭቅ የሚወሰንባቸው የገበያ ቦታዎች የገበያ ወቅቶችና የገበያ ሥርዓቶች፡፡ የተለያዩ ሰዎች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ለሆኑ ሸቀጦች የተለያዩ ዋጋዎች የሚከፍሉባቸው የገበያ ቦታዎች የገበያ ወቅቶችና የገበያ ሥርዓቶች፡፡ ያልጠሩ ገበያዎች እንደ የሸቀጡ ዓይነትና የሸቀጡ አምራች ድርጅቶች ብዛት የተለያዩና በርካታ ዓይነቶች ሊሆኑ ቢችሉም በኢኮኖሚ ጥናት ውስጥ በሦስት ንዑሳን ምድቦች ተከፍለው ይገለጻሉ፡፡

አንድ ድርጅት ብቻውን አንድ ዓይነት ሸቀጥ ለገበያ የሚያቀርብ ከሆነ የአሐዳዊ (የሞኖፖል) ገበያ ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ የዚህን ዓይነት ገበያ ያላቸው ድርጅቶች በአገር ዐቀፍ ደረጃ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የመብራት ኀይል፣ ቴሌኮምኒኬሽን ናቸው፡፡ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች ግን በአንድ የገጠር ከተማ አንድ መድኃኒት ቤት ወይም አንድ መጠጥ ቤት ወይም አንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ብቻ ቢኖሩ ለአካባቢው ገበያ የአሐዳዊ (የሞኖፖል)ገበያዎች ናቸው፡፡

ኹለተኛው ያልጠራ ገበያ ዓይነት የአናሳ ገበያ (ኦሊጎፖሊ) በመባል የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ ገበያ ጥቂት ምርት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች እርስ በርሳቸው ስለሚተዋወቁ አንዱ ሌላውን ሊጫረት የሚችልበት ወይም የዋጋ ስምምነት የሚያደርጉበት ወይም ከመካከላቸው አንዱ ግዙፍ ሆኖ የዋጋ አወሳሰኑን ሲመራ ሌሎች ፋናውን የሚከተሉበት የገበያ ዓይነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በአገር አቀፍና በተለያዩ አካባቢዎችም ለአካባቢው ኅብረተሰብ ተመሳሳይ ሸቀጦች የሚያቀርቡ በዚህ የገበያ ዓይነት የሚመደቡ ጥቂት ተመሳሳይ ምርቶች አምራችና የውጭ አገር ሸቀጥ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ 

ሦስተኛው ያልጠራ ገበያ ዓይነት የአሐዳዊነት (ሞኖፖላዊ) ውድድር (Monopolistic Competition) ገበያ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ነጋዴ እጅ ያሉት ሸቀጦች በዓይነትና በጥራት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሆነው የነጋዴዎቹና የሸማቾቹ ቁጥር ብዙ ቢሆንም በሸማቹ ዓይን ድርጅቶቹ ለሸማቹ የመኖሪያ አካባቢ ቅርብ በመሆናቸው ወይም ሸማቾች ደንበኛ በመያዛቸው ወይም ሸማቾቹ በሸቀጡ ጥራት ጣዕም ቀለም ቅርጽ እሽግ ዓይነት ምርጫ የግል ግምት በመውሰዳቸው ምክንያት ነጋዴውን የሚመርጡበት ነጋዴውም ራሱን ከሌሎች የተለየ ለማድረግ የሚጥርበት የገበያ ዓይነት ነው፡፡

የጽንሰ ሐሳብና የተግባር ልዩነት

የጠራ ገበያ የግብይይት ሥርዓትን በሙሉ የሚያሟላ ገበያ በየትኛውም አገር አልነበረም፤ የለም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብቻ የሚታሰብ ነው፡፡ የግበይይት ሥርዓትን ለመተንተን የሚረዳ የእንከን የለሽ ግብይይት ትርጓሜ ሆኖ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ገበያዎችን ወደ ጠራ ገበያ ሥርዓት የተቃረቡ ወይም ከጠራ ገበያ ሥርዓት የራቁ በማለት መፈረጅም ይቻላል፡፡ በበለጸጉት አገሮች የጠራ ገበያ የግብይይት ሥርዓት ሁኔታዎች ከሞላ ጎደል የተሟሉ ስለሆነና የዕቃዎች ዋጋም የሚወሰነው በሻጮች የእርስ በርስ ውድድር እንጂ ከሸማች ጋር በቀንስ ጨምር ንትርክ ስላልሆነ ገበያዎች ወደ ጠራ ገበያ የግብይይት ሥርዓት የተቃረቡ ናቸው፡፡

በአገራችን ብዙ ሻጮችና ብዙ ሸማቾች ያሉባቸው የእርሻ ምርት ውጤቶች በዓይነታቸውና በጥራት ደረጃቸው በሻጮች ዘንድ በመጠኑ ተቀራራቢ ከመሆናቸውም በላይ ሸማቾችም ሆኑ ሻጮች ስለዕቃዎቹ ዓይነትና ዋጋ ስለገበያው ሁኔታ በቂ ዕውቀት ስለሚኖራቸው ዋጋዎችም በአንድ አካባቢ ተመሳሳይ ስለሆኑ የእነዚህ ሸቀጦች ገበያዎች ወደ ጠራ ገበያ የግብይይት ሥርዓት የተቃረቡ ናቸው፡፡ በጅምላ ንግድም ሻጮችና ሸማቾች ብዙ መጠን ስለሚሸጡና ስለሚገዙ ስለገበያው ሁኔታ ስለሸቀጡ ዓይነትና ስለሸቀጡ ዋጋ አስቀድመው አጥንተውና አውቀው ስለሚገበያዩ ገበያዎቹ ወደ ጠራ ገበያ የግብይይት ሥርዓት የሚያደሉ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል መጠናቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ በጥቂት ነጋዴዎች እጅ የሚገኙ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ምርቶች ከሸቀጦቹ በመጠን ማነስም ባሻገር በዓይነትና በጥራት ተመሳሳይ ባለመሆናቸው እና ሸማቾች ስለዕቃዎቹና ስለገበያው በቂ ዕውቀት ስለሌላቸው ግብይይቱም በቀንስ ጨምር ንትርክ ስለሚፈጸም ገበያዎች ከጠራ ገበያ የግብይይት ሥርዓት የራቁ ናቸው፡፡ መርካቶ ያሉ የልብስና የሌሎች ሸቀጦች ዋጋቸው ጎን ለጎን ባሉ ሱቆች እንኳ በጣም የተለያዩ ስለሆኑ የጨምር ቀንስ ንትርኩም የጦፈ ስለሆነ እነዚህ ያልጠራ ገበያ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በታዳጊ አገሮች እና በኢትዮጵያ ያሉ ገበያዎች አብዛኞቹ ያልጠሩ ገበያዎች ናቸው

የልጠት ጽንሰ ሐሳብ

ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ የአንዳንዶቹ ሸቀጦች ዋጋዎች ሦስት እጥፍ ሲያድጉ የሌሎች ሸቀጦች ዋጋዎች አምስት እጥፍና የተቀሩትም ዐሥር እጥፍ አድገዋል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለምን የሁሉም ሸቀጦች ዋጋዎች በእኩል መጠን አላደጉም፡፡ መልሱ ለዋጋ ለውጥ የፍላጎትና የአቅርቦት አጸፋዊ ለውጦች ጥንካሬና መላላት በኢኮኖሚክስ ሙያዊ ቋንቋ የልጠት (Elasticity) ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡

በዐሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃና በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በእንግሊዝ የኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚስት አልፍሬድ ማርሻልና ሌሎች ኢኮኖሚስቶች የፍላጎትና የአቅርቦት ለውጦች ጥንካሬና መላላትን በልጠት ጽንሰ ሐሳብ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የዋጋ ዕድገትና ዋጋ መዋዠቅ ኑሯችንን አመሰቃቅለውብናል፡፡ ገበያዎቻችን ውስጥ የአንዱ ሸቀጥ ዋጋ በፍጥነት ያድጋል የሌላው ሸቀጥ ዋጋ አዝጋሚ ነው፤ የሌላው በተለይ የሥራ ዋጋ የሆነው ደሞዝ ባለበት ለብዙ ጊዜ ይቆያል፡፡ ሸማቾችና አምራቾች በግብይይት አልተጣጣሙም ስለዚህም የልጠት ጽንሰ ሐሳብን ተረድተን ለምን የሸቀጦች ዋጋ ዕድገት እንደሚለያይ ማወቅ እንደ ሸማችም እንደ አምራችም ይጠቅመናል፡፡

በዋጋ ለውጥ የፍላጎት ልጠት ማለት ለዋጋ ለውጥ መጨመርና መቀነስ አፀፋዊ የሸቀጥ ፍላጎት ለውጥ ደረጃ ነው፡፡ ለኑሮ እጅግ አስፈላጊ በሆኑ እንደ ሽንኩርት፣ ጨው፣ ዘይትና ሌሎች የምግብ ምርቶች፣ የኤሌክትሪክ መብራት፣ የንጽሕና መጠቀሚያዎች የመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ በዋጋ ጭማሪ ፍላጎት የሚቀንሰውና በዋጋ ቅነሳ ፍላጎት የሚጨምረው በመቶኛ ሲሰላ ከዋጋው ለውጥ መቶኛ በታች ነው፡፡ በአንጻሩ መሠረታዊ ባልሆኑ የቅንጦት ሸቀጦች በዋጋ ጭማሪ ፍላጎት የሚቀንሰውና በዋጋ ቅነሳ ፍላጎት የሚጨምረው በመቶኛ ሲሰላ ከዋጋው ለውጥ መቶኛ በላይ ነው፡፡ ከዋጋ ለውጥ መቶኛ በላይ የፍላጎት ለውጥ መቶኛ ከተፈጠረ ፍላጎት ተለጣጭ (Elastic) ነው ከዋጋ ለውጥ መቶኛ በታች የፍላጎት ለውጥ መቶኛ ከተፈጠረ ፍላጎት ኢተለጣጭ (Inelastic) ነው፡፡ ከዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት መቶኛ የአቅርቦት ከፍና ዝቅ ማለት መቶኛ የሚበልጥባቸውና የሚያንስባቸው ለማምረት አጭርና ረጅም ጊዜ የሚጠይቁ የምርት ዓይነቶችም አሉ፡፡ ከዋጋ ለውጥ መቶኛ በላይ የአቅርቦት ለውጥ መቶኛ ከተፈጠረ አቅርቦት ተለጣጭ ነው ከዋጋ ለውጥ መቶኛ በታች የአቅርቦት ለውጥ መቶኛ ከተፈጠረ አቀርቦት ኢተለጣጭ ነው፡፡   

እያንዳንዱ በተናጠልና ብዙዎች በጋራ በዋጋ ለውጥ የፍላጎት ልጠት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ምክንያቶች አሉ፡፡ አሮጌ ሸቀጦች ከገበያ ይወጣሉ አዳዲስ ሸቀጦች ወደ ገበያ ይገባሉ፡፡ ቀድሞ ሸቀጦቹን ይፈልጉ የነበሩ ሰዎች ወደ ሌሎች ሸቀጦች ሲቀይሩ አዳዲስ ሸቀጦቹን ፈላጊዎች ይፈጠራሉ፡፡ የአንዱ ፍላጎት ሲቀንስ የሌላው ፍላጎት ይጨምራል የማያቋርጥ ሰንሰለታዊ የለውጥ ሂደት ነው፡፡ የገቢ ተጽዕኖ፣ የጣዕም ተጽዕኖ፣ የሕዝብ ብዛት ተጽዕኖ፣ የሸቀጡ በሸማቹ እጅ መኖር አለመኖር ተጽዕኖ፣ ሸቀጡን የሚተካ ሌላ ሸቀጥ መኖር አለመኖር ተጽዕኖ፣ የሸቀጦች አብሮ መወሰድ ተጽዕኖ፣ በዋጋ ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ የፍላጎት ልጠቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡  

የሰዎች ገቢ ሲጨምርና ሲቀንስ በዋጋ ለውጥ የሸቀጥ ፍላጎት ልጠት በተለያየ መልኩች ይከሰታል፡፡ ገቢ ሲጨምር ቀድሞ ተፈላጊ የነበሩ እንደ ጎመን ሽሮ ዘይት ርካሽ ልብሶች ላስቲክና ሸራ ጫማዎች የዘንጋዳና የበቆሎ እህሎች የፍጆታ ሸቀጦች ፍላጎት ቀንሶ በምትኩ እንደ ቅቤ ሥጋ ውድ ልብሶች ቆዳ ጫማዎች ሸቀጦች ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ከሸማቹ ገቢ መጠን አንጻር የሸቀጡ ዋጋ ዝቅተኛ ከሆነ ለምሳሌ እንደ ጨው፣ ክብሪት፣ እርሳስ፣ ወረቀት፣ ምላጭ ወዘተ… የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋቸው በእጥፍ ቢጨምርም እንኳ መካከለኛ ገቢ ላለው ሰው የሸቀጦቹ ፍላጎት ብዙ አይቀንስም፡፡ 

በኢትዮጵያ የወደፊት የዋጋ ለወጥ አዝማሚያ

በዝቅተኛና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኝ ኢትዮጵያዊ በገቢ ተጽዕኖ ከምግብ ከልብስና ከመጠለያ በስተቀር የሌሎች ሸቀጦች በዋጋ ለውጥ የፍላጎት ልጠት ከፍተኛ ነው፡፡ ከፍተኛ ገቢ ለሚያገኙና ሀብት ላከማቹ ጥቂት ሰዎች ግን በገቢ ተጽዕኖ ውድ የሆኑ የውጭ አገር ምርቶችና ጌጣጌጦችም ሳይቀሩ በዋጋ ለውጥ የፍላጎት ልጠት ዝቅተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ የባዕድ አገር ሸቀጦች ጣዕም ምርኮኛ ሆኗል በየጊዜው የጣዕም ለውጡ እየባሰበትም ነው፡፡ ስለዚህም በጣዕም ተጽዕኖ በዋጋ ለውጥ የውጭ ሸቀጦች ፍላጎት ልጠት ዝቅተኛ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን የብዙ ሸቀጦች ፍላጎቶች ከዓለም ዐቀፍ የኑሮ ደረጃ ጋር ሲነጻጸር አልተሟሉም፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው እጅግ መሠረታዊ የሆኑ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ማሟላት ቀርቶ ምግቡን መላበሻውንና መጠለያውንም ማግኘት አልቻለም፡፡ የሕዝቡ ቁጥር በየዓመቱ በሦስት በመቶ በማደግ የልጆችና ወጣቶች ቁጥር ዕድገት ፈጣን ቢሆንም አገሪቱ ባላት አቅም ፍላጎቱን ለማርካት የሚችል ማምረቻ ድርጅቶችን ስላላሟላች ሕዝቡ በሸቀጥ ፍላጎት እንደተራበ ነው፡፡

አቅርቦት ግን ከማምረት ሂደት ጋር የተያያዘ ስለሆነ እንደ ፍላጎት ለዋጋ ለውጥ ፈጣን ምላሸ አይሰጥም፡፡ ዋጋ ሲጨምር አቅርቦትን ለመጨመር አምራች ድርጅቶች የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ወይም ሌሎች አዳዲስ ድርጅቶች ለመከፈት ጊዜ ስለሚወስድባቸው በዋጋ ለውጥ የአቅርቦት ልጠት ዝቅተኛ ስለሆነ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፍላጎትና አቅርቦት አይጣጣሙም፡፡

ሸማቾች ምን እንዲመርትላቸው እንደሚፈልጉ ትዕዛዝ ሰጪዎችና አምራቾችም ትዕዛዝ ተቀባዮች ቢሆኑም ሸማቾች የማዘዝ አቅም የሚያገኙት በገቢያቸውና በሀብታቸው መጠን ነው፡፡ ሸማቾች እንደ አምራችነታቸው ከደሞዝና ከትርፍ የሚያገኙት ገቢና ሀብትም የመገበያያ ጥሬ ገንዘብ አካል የሆኑትን ብርና ሳንቲም ምንዛሪዎች አትሞ በሚያሰራጨው መንግሥት ተጽዕኖ ሥር ነው፡፡ በዚህም ላይ በነጻ ገበያው ውስጥ ጣልቃ እየገባ የአንዳንድ ግብዓቶችን እና ምርቶችን ዋጋዎች ይወስናል፡፡ ስለዚህም ነጻ ገበያ ነጻ ሆኖ አያውቅም፤ የአገሮች የገበያ ጉዞ መንገድ ወደ ነጻ ገበያ መቃረብ ወይም ከነጻ ገበያ መራቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ ወደ ነጻ ገበያ እየቀረበች ነበር፡፡ በደርግ ጊዜ ከነጻ ገበያ ራቀች፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ አንዱን ለማክበር ሌላውን ለማደህየት በመወሰኑ ገበያዎች ተመሰቃቀሉ፡፡

(Visited 67 times, 1 visits today)
June 10, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

About Us

The Black Lion is a magazine and online media outlet focusing on the issues of Ethiopia and Ethiopian politics. To serve you best, we produce our journalism across a range of platforms, with a particular focus on politics, economy, culture, entertainment and new forms of storytelling. We’ve grown from a single Facebook page into a suite of digital products like website and into a newsletter.

Email: theblacklionafrica@gmail.com

Logo